አርዕስተ ዜና
*በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ታጣቂዎች የፈፀሙትን ግድያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አወገዙ ። እናት ፓርቲ ግድያው ሆን ተብለው «በጥንቃቄ የሚፈጸም» መሆኑን ገልጧል ።
*የኬንያ ምክር ቤት ብርቱ ሕገመንግሥታዊ ጥሰት ፈጽመዋል ያላቸው የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት ሪጋቲ ጋቻጉዋን ከሥልጣን ለማንሳት ዛሬ ሕጋዊ ሒደት ጀመረ ። ሀገር ውስጥ መገናኛ አውታሮች ምክትል ፕሬዚደንቱ ከኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ጋር መቃቃራቸውን ዘግበዋል ።
*እስራኤል ሊባኖስ ላይ የምድር ጦር ጥቃት በከፈተችበት በአሁኑ ወቅት የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት እጅግ እየተባባሰ ነው ።
ዜናው በዝርዝር
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ታጣቂዎች ክርስቲያኖችን ለይተው በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውን ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አወገዙ ። የመንግሥት ቸልተኝነትም በብርቱ ኮንነዋል ። መስከረም 16 እና 18 ቀን፣ 2017 ዓ. ም ታጣቂዎች 12 ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውን እናት ፓርቲ በማሳወቅ ድርጊቱ «በጥንቃቄ የሚፈጸም» መሆኑን ገልጧል ። የእናት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ።
«በተደጋጋሚ የሚደረግ ነው በኦሮሚያ ክልል በብዙ ቦታዎች ላይ ። አገልጋይ ካህናት እና ምእመናን ወደ ገዳማዊያን ጭምር የዘለቀ ነው ። እና በጥንቃቄ የሚፈጸም ነው ።»
እናት ፓርቲ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሞጆ ወረዳ ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን አገልጋይ የነበሩ አዛውንት ካህን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል ብሏል ። ከሁለት ቀናት በኋላ በተመሳሳይ መስከረም 18 ቀንም በዞኑ ሉሜ ወረዳ ስምንት ክርስቲያኖች በታጠቁ ኃይሎች ሌሊት ከየቤታቸው ከተወሰዱ በኋላ ጭካኔ የተሞላበት የግፍ ግድያ እንደተፈፀመባቸውም ገልጠል ። ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ዲፕሎማቶች በጉዳዩ ላይ ዝምታን መምረጣቸው እንዳሳዘነው የገለጠው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ ከምንም በላይ መንግሥት በጉዳዩ ላይ «እያሳየ ያለው ዝምታ» እጅግ እንዳሳሰበው ዐስውቋ ። በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና ከምስራቅ ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም አልተሳካም ሲል የአዲስ አበባ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ ዘግቧል ።
የኬንያ ምክር ቤት ብርቱ ሕገመንግሥታዊ ጥሰት ፈጽመዋል ያላቸው የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት ሪጋቲ ጋቻጉዋን ከሥልጣን ለማንሳት ዛሬ ሕጋዊ ሒደት ጀመረ ። ይህንንም የምክር ቤቱ ቃል አቀባይ ዛሬ ተናግረዋል ። የሀገር ውስጥ መገናኛ አውታሮች ምክትል ፕሬዚደንቱ ከኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ ጋር መቃቃራቸውን ዘግበዋል ። በፕሬዚደንቱ እና በምክትላቸው መካከል ያለው መቃቃር ተባብሶ አሁን ወደ አደባባይ መውጣት መጀመሩንም ሮይተርስ የዜና ምንጭ ጠቅሷል ።
የጀርመን ፖሊስ አንዲት ቻይናዊትን ለቻይና ትሰልላለች በሚል ጥርጣሬ ዛሬ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጀርመን ዜና አገልግሎት (dpa) ዘገበ ። ያቂ ኤክስ በሚል የምትጠራውን ቻይናዊት ፖሊስ ትናንት ማሰሩን ያሳወቀው ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ በምትገኘው የላይፕትሲሽ ከተማ ነው ። ፖሊስ የተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት እና የሥራ ቦ ላይም ፍተሻ ማድረጉ ተዘግቧል ።
እስራኤል ሊባኖስ ላይ የምድር ጦር ጥቃት በከፈተችበት በአሁኑ ወቅት የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት እጅግ እየተባባሰ ነው ። የዓለም መንግስታት እሥራኤል መላ ሊባኖስን ከመውረር እንድትቆጠብ አስጠንቅቀዋል ። ኢራን የባለስቲክ ሚሳይሎቿን እሥራኤልን ለማጥቃት ማዘጋጀቷን የዩናይትድ ስቴትስ አንድ ባለሥልጣን መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል ። ቀጣናው ላይ የሚከሰቱትን እያንዳንዱ እንቅስቃሴዎችን በጥንቃቄ እየተመለከተች መሆኗን ያሳወቀችው ዩናይትድ ስቴትስ እሥራኤልን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኗን መግለጧንም የዜና ምንጩ አክሏል ። ከኢራን ጋር የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች የሚነገርላት ሩስያ እሥራኤል «በአስቸኳይ ወታደሮቿን ከሊባኖስ ግዛት እንድታስወጣ» አሳስባለች ። ቻይና ውጥረቱ፦ «እጅግ እንዳሳሰባት» ዐሳውቃለች ። ቱርክ የእሥራኤልን የምድር ጥቃት አውግዛለች ። ሁቲዎች እና ሒዝቦላህ በየፊናቸው ሚሳይሎችን ወደ እሥራኤል ማስወንጨፋቸውን ገልጠዋል ። ሒዝቦላህ፦ ቴል አቪቭ አቅራቢያ የሚገኝ የእሥራኤል የአየር ኃይል ጦር ሰፈርን መምታቱን በመግለጥ፤ ወደ እሥራኤል የሚሳይል ውርጅብኝ ማስወንጨፉንም ዐሳውቋል ። ሒዝቦላህ በዩናይትድ ስቴትስ፤ ጀርመን እና በርካታ የሱኒ ዐረብ ሃገራት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ፤ በኢራን የሚደገፍ የሊባኖስ የሺዓ ፖለቲካ ፓርቲ እና ወታደራዊ ክንፍ ነው ።
እሥራኤል ዛሬ የምድር ጦር ጥቃት የከፈተችባት ሊባኖስ ውስጥ ለተፈናቀሉ አንድ ሚሊዮን ሰዎች የሚውል የርዳታ ጥሪ ቀረበ ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)የሰብአዊ ርዳታ ለጋሾች፦ ሊባኖስ ውስጥ በእሥራኤል መጠነ ሰፊ ጥቃት ለተፈናቀሉ ሰዎች ድጋፍ የሚውል የ426 ሚሊዮን ዶላር ርዳታ ጥሪ ነው ያስተላለፈው ። እስራኤል በአንድ አካባቢ «ዒላማ ላይ ያነጣጠረ» ስትል ሊባኖስ ላይ በከፈተችው መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከ1,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተመድ ገልጧል ። በርካቶች የአየር ጥቃቶቹን ሽሽት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ሸሽተዋል ። እሥራኤል ከአየር ጥቃቱ ባሻገር የምድር ጥቃት ዛሬ መክፈቷን ይፋ አድርጋለች ። የተመድ የሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት ቃል አቀባዪት ሊዝ ትሮሴል ከስዊትዘርላንድ ጄኔቫ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፦ ጥቃቱ በምድርም የሚቀጥል ከሆነ የከፋ ሰብአዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጠዋል።
«እየተባባሰ በመጣው የሒዝቡላሕ እና እሥራኤል ውጊያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ቀድሞውንም የተፈጠረው አስከፊ ሁኔታ በእሥራኤል መጠነ ሰፊ የእግረኛ ጦር ጥቃት ደግሞ እጅግ ከፍተኛ መከራን ብቻ ነው የሚያስከትለው ።»
የምድር ጦር ጥቃት መክፈቱን ያሳወቀው የእሥራኤል ጦር፦ ወደ ሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩትም ሆነ ደቡብ ሊባኖስ ውስጥ ወደሚገኙ ከተሞች አናቀናም ሲል በቃል አቀባዩ በኩል ይፋ አድርጓል ። ቤሩት ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአብዛኛው በቤት ውስጥ ሥራ ተቀጥረው እንደሚሠሩ ይታወቃል ። የእሥራኤል ጦር፦ ሊባኖስ ውስጥ «ውስን» ሲል ዛሬ ሌሊት በከፈተው የምድር ጦር ውጊያ ኮማንዶዎች እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ተሳታፊ መሆናቸውን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ የቱርክ ፕሬዚደንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ቱርክ በማንኛው መንገድ ሊባኖስን እንደምትደግፍ ዛሬ ይፋ አድርገዋል ። «በዚህ አሰቸጋሪ ወቅት የሊባኖስ ወንድሞቻችንን በፍጹም ብቻቸውን አንተዋቸውም» ያሉት ፕሬዚደንቱ፦ «ባለን አቅም ሁሉ እንረዳቸዋለን» ሲሉም አክለዋል ። ለዚህም ቱርክ በሊባኖስ ጉዳይ በተጠንቀቅ ላይ ናት ሲሉ ፕሬዚደንቱ የተናገሩት ዛሬ የቱርክ ምክር ቤት ከበጋ ረፍት መልስ ዳግም ሲከፈት ባሰሙት ንግግር ነው ። ፕሬዚደንቱ ተመድም ሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ «ብዙም ጊዜ ሳያባክን» እሥራኤልን ሊያስቆማት ይገባል ብለዋል ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ቱርክ የምዕራቡ ዓለምን በመደገፍ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO)አባል ሃገር ናት ።