ማን ያሰልስ ይሆን?-ሕዝባዊ አመፅ | ዓለም | DW | 21.02.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ማን ያሰልስ ይሆን?-ሕዝባዊ አመፅ

ቤን አሊን፥ ከቱኒዝ፥ ሙባረክን ከካይሮ አሽቀንጥሮ የጣለዉ አዲሱ ሕዝባዊ አመፅ የአረቡን አለም እየናጠ በአዲስ ጎዳና እየዘወረዉም ነዉ። የፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽና የጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌሯ ዲሞክራሲያዊት ኢራቅም ከአዲሱ ሕዝባዊ ነዉጥ አላመለጠችም

default

ቤንጋዚ-ተቃዋሚዉ

21 02 11
እንደ መሪ እንደተከበሩ፣ እንደተፈሩ ምናልባትም እንደ ተፈቀሩ መጦርን እንቢኝ ብለዉ መገዛትን እንቢኝ ባለ ሕዝባቸዉ ተጠልተዉ፣ ተወግዘዉ፣ ከስልጣን የተወገዱት ዘይን አል አቢዲን ቢን ዓሊ ያጣጥራሉ።መሐመድ ሆስኒ ሙባረክ እንደ ጄኔራል፣ እንደ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ እንደ ፕሬዝዳንት ከርባ አመት በላይ ከመንደላቀቅ መቀማጠል ሌላ ሌላ የማዉቀዉ አካል አእምሯቸዉን በቀሪ እድሜያቸዉ ከፍርድ ቤት ሙግት፣ ከወሕኒ ቤት አበሳ የሚያድኑ፣ያጋበሱትን ሐብት የሚበሉበትን ሥልት ያዉጠነጥናሉ።ቤን ዓሊን አስቀድሞ፣ ሙባረክን አስከትሎ ከስልጣን ያስወገደዉ ሕዝባዊ አብዮት የአልጀርስ፣ የአማንና የቴሕራን ገዢዎችን አደናግጦ፣ የራባት ገዢዎችን ደባብሶ ሰነዓ፣ ትሪፖሊ ማናማዎች ላይ ብሶ-ገዢዎቹን እያዳፋ።ማን ያሰለስ ይሆን?ሕዝባዊዉ አመፅ የባሰባቸዉን ሐገራት ቅንጭብ እዉነት እያነሳን ላፍታ እንጠይቅ።
========================================================================

«የሶሻሊስታዊት ሕዝባዊት ሊቢያ አረብ ጁሙሕሪያ የመስከረም አንዱ ታላቅ አብዮት አቅጣጫ አመላካች» ወይም ወንድማዊ መሪ እና የአብዮቱ አቅጣጫ መሪ» ሙአመር አል-ቃዛፊ ኒዮርክ ሲገቡ ከእስከዚያ ጊዜዉ ሁሉ ገለል፥ ቀለል፥ ዘና እንዳሉ ነበር።በዚያ ረጅም ማዕረግ ያቺን ሰፊ፥ ሐብታም ሥልታዊት ሐገር ለረጅም ጊዜ ለመግዛት የበቁበትን መፈንቅለ መንግሥት አርባኛ አመት ድል ባለ ድግስ ካከበሩ ሁለተኛ ሳምንታቸዉ ነበር።
በትልቅ-አስፈሪ ሥም ማዕረግ-ሥልጣናቸዉ ላይ ደግሞ የአፍሪቃ ንጉሰ ነገስት የሚል ዘዉዳዊ ማዕረግ ለመደረብ አንድ ሁለት እያሉ ነዉ።ተደስተዋል ወይም የተደሰቱ መስለዋል።መስከረም ሁለት ሺሕ ዘጠኝ።ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።

በርግጥም ከምዕራባዉያን ጋር መናከስ፥ መናጨቱን አቁመዋል።እንደ ሙባረክ፥ እንደ ቤን ዓሊ እንደ ቡተፈሊቃ ወይም እንደ ቢን ስዑዶች- ወይም እንደ ኸሊፋዎች «ጥብቅ ወዳጅ» ባይባሉም «ጠላት» የሚለዉ ቅፅል ተፍቆላቸዋል።እና ደስታ ብቻ ሳይሆን በራስ የመተማመን ስሜት-መፈንሳቸዉም ጠንክሯል።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን መተዳደሪያ ደንብ ቦጫጭቀዉ ከጣሉ-ስዊዘርላንድ እንድትቦጫጨቅ በጠየቁ ማግስት ያሉ-ያደረጉትን ከነ ምክንያቱ ለጋዜጠኞች ይዘረዝሩ ገቡ።

በቃለ መጠይቁ መሐል ታይም የተሰኘዉ ዩናይትድ ስቴትሱ ሳምንታዊ መፅሔት ዘጋቢ ሥለ መንግሥታቸዉ የሰባዊ መብት ይዞታ ጠየቃቸዉ።«ሰዉ ጀነት ብታስገባዉም መዉቀሱ አይቀርም» መለሱ የታላቁ አብዮት ወንድማዊ መሪ «እዉነቱን ልንገርሕ ሊቢያ አሁን ጀነት ናት።»

በስደት ፈረንሳይ የሚኖሩት ሊቢያዊ የመብት ተሟጋች ስሊማን ቦዉሹይጉሪይ እንደሚሉት ግን የሙዓመር ቃዛፊዋ

Flash-Galerie Libyen 40 Jahre mit Muammar al Gaddafi 1987

«ወንድማዊዉ አብዮታዊዉ» መሪ

«ጀነት» ለብዙዊ ሊቢያዊ «ገሐነብ» አከል ናት።

«የሊቢያ ሕዝብ ከቱኒዚያ ወይም ከግብፅ ሕዝብ የበለጠ ይሰቃያል።ሊቢያ ዉስጥ አንዴም አንዲትም የነፃነት ብልጭታ የለም።ከዚሕም በተጨማሪ ላለፉት አርባ-ሁለት አመታት አንድም ምርጫ ተደርጎ አያዉቅም።ሕዝቡ በፍርሐት ነዉ-የሚኖረዉ።ነፃነት የሚባል ነገር የለም።ሰዉ አፉን ካልዘጋ ዘብጥያ ይወረወራል።ሁኔታዉን ለማሳወቅ ምንም አይነት አማራጭ የለም።»

የያኔዉ የሃያ-ስምንት አመት ሻለቃ ሙአመር አል-ቃዛፊ የመሯቸዉ የጦር መኮንኖች መስከረም አንድ 1969 የንጉስ ሰይድ መሐመድ ኢድሪስ ቢን ሰይድ መሐመድን ዘዉዳዊ ሥርዓት ደም ባልፈሰሰበት መፈንቅለ መንግሥት ለማስወገድ የደፈሩት ከግብፁ መሪ ከኮሎኔል ገማል አድናስር ድፍረት፥ ድርጊት ተምረዉ፥ በናስር ርዕዮት-አላማ ምግባር ተማርከዉ ነበር።

ጋዛፊ ከግብፅ ገዢዎች በርግጥ ብዙ ተምረዋል።ከግብፆች የመማሩ ተራ አሁን የሊቢያ ሕዝብ ነዉ። ከግብፅ ገዢዎች ሳይሆን ከግብፅ ሕዝብ የተማረዉ ሊቢያዊ አማራጭ ያለዉ መሰለ።እንደ ግብፅ-ቱኒዚያዎች «ጀነት» እያሉ ኑሮ ሕይት ሐገሩን «ገሐነብ» ባደረጉበት ገዢዎቹ ላይ አመፀ።ቤንጋዚ ባለፈዉ ሳምንት።እንደ ቤን ዓሊ፥ እንደ ሙባረክ ሁሉ የወንድም ቃዛፊ የመጀመሪያ አፀፋም ጥይት ነበር።ግድያ።

የተገደለ-የቆሰለዉን ሰዉ ቁጥር በትክክል የሚያዉቀዉ የለም።አንዳድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት እስከ ትናንት እሁድ ድረስ ብቻ በትንሽ ግምት ሰወስት መቶ ሰዉ ተገድሏል።የቤንጋዚዋ ነዋሪ እንደሚሉት ግን ሟች-ቁስለኛዉን ቤቱ ይቁጥረዉ።

«በትክክል ጭፍጨፋ ነዉ።በርግጥ ጭፍጨፋ ነዉ።እዚሕ የሚፈፀመዉ ድምፅ አልባ-ጭፍጨፋ ነዉ።የሞቱትን መቁጠር አትችልም።የተገደሉት ሰዎች በየስፍራዉ፥ በየቤቱ፥ በየሆስፒታሉ አሉ።ግልፅ ጭፍጨፋ ነዉ።በርግጥ ጥፋት ነዉ።»
ቃዛፊ በናስር ምግባር፥ መርሕ፥ አለማ ተማርከዉ እንደ ናስር ንጉሳዊ አገዛዝ ጠልተዉ ንጉስ ኢድሪስን አስወግደዉ የትሪፖሊ ቤተ-መንግሥትን በ1969 ሲቆጣጠሩ የዘጠኝ አመት ታናሻቸዉ ሐማድ ቢን ኢሳ አል-ኸሊፋ እንደ አሚር ልጅ ናስር የሚጠሉትን አልጋ ወራሽነትን እንደናፈቁ እንደ ናስር ወታደራዊ ሳይንስን ሊማሩ አንድ ሁለት ይሉ ገቡ።

ቃዛፊ አንዴ ከግብፅ ጋር ልዋሐድ እያሉ ናስርን ሲጨቀጭቁ፥ ሌላ ጊዜ አረብ ባንድ መሪ (በናስር) ይገዛ ሲሉ ደግሞ ሌላ ጊዜ እስራኤል-ምዕራቦችን እንዉጋ እያሉ ሲጋበዙ ልዑል ሐማድ ከብሪታንያዉ የሳንድረስትና ከዩናይትድ ስቴትሱ የፎርትሊቨንወርት የጦር ኮሌጆች ወታደራዊ ትምሕርታቸዉ አጠናቀዉ ተመለሱ።

ባሕሬንን ከ1961 ጀምረዉ የገዙትና፥ በተለይ በ1971 ከብሪታንያ ቅኝ አዛዝ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንድትወጣ አበክረዉ የታገሉት የሐማድ ቢን ኢሳ አል-ኸሊፋ አባት አሚር ኢሳ ቢን ሳልማን አል-ከሊፋ በ1999 ሲሞቱ የያኔዉ የዩናትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን ዩናይትድ ስቴትስ «አንድ የሰላም ጥሩ ወዳጅ አጣች» ብለዉ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የነበሩት ኮፊ አናን በበኩላቸዉ «የአካባቢዉ ታላቅ የመረጋጋት ሐይል» ብለዋቸዉ ነበር።ልዑል ሐማድ ባባታቸዉ እግር እንደተተኩ የፖለቲካ እስረኞችን ለቀቁ። ለረጅም ጊዜ የፀናዉን ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማንሳታቸዉና የሴቶችን መብት ለማስከበር ቃል በመግባታቸዉ ከምዕራባዉን መንግሥታትና ከመብት ተሟጓች ተቋማት አድናቆት ሲንቆረቆርላቸዉ ነበር።

Bahrain Proteste

ማናማ-ተቃዋሚዉ

እንዲያዉም መንበሩን ለንደን ያደረገዉ አለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል የአሚር ሐማድን እርምጃ ለሰብአዊ መብት መከበር ከፍተኛ እመርታ በማለት አወድሶት ነበር።ባሕሬንን ለተከታታይ ዘመናት የሚገዛዉ የአናሳዉ የሱኒ የከሊፋ ቤተ-ሰብ ሥርወ መንግሥት በአብዛዉ የሺዓ እምነት ተከታይ ሕዝብ ላይ የሚፈፅመዉ ግፍ በደል ግን ለምዕራቦቹ፥ ለመብት ተቋማቱም ከቁብ የሚገባ አልነበረም።

ከሁሉም በላይ ምዕራባዉያኑ የከሊፋ ቤተሰቦች አገዛዝን ሲያደንቁ-ሲያወድሱ ባሕሬን ሙሉ ነፃነትዋን ካወጀችበት ከ1971 ጀምሮ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን የያዙት ቀድሞዉ አሚር የኢሳ ቢን ሳልማን አል-ከሊፋ አጎት ከሊፋ ቢን ሳልማን አል-ከሊፋ የትንሺቱን ሐብታም ሐገር አስተዳደር ጨምድደዉ መያዛቸዉን ማስተዋል አልፈለጉም ወይም ዘንግተዉት ነበር።

ባሕሬኖች ግን የኖሩና የሚኖሩበት አገዛዝ የሚያደርስባቸዉን በደል ታገሱት እንጂ በርግጥ ሊዘነጉት አልቻሉም፥ አይችሉምም።የባሕሬን ሕዝብ ምሬት ብሶቱን ለመግለጥ ብልሐቱን ከቱኒዚያና ከግብፅ ለመማርም ጊዜ አል-አልፈጀበትም።የአደባባይ አመፅ።ማናማ-ባለፈዉ ሳምንት።
የአሜርነቱን አልጋ በወረሱ በሰወስተኛዉ አመት በሁለት ሺሕ ሁለት የንጉስነት ዙፋን የደፉት የንጉስ ሐማድ ቢን ኢሳ አል-ኸሊፋ አገዛዝ አፀፋ እንደ ቱኒዝ፥ እንደ ካይሮ የቀድሞ ገዚዎች፥ እንደ ትሪፖሊ፥ አንደ አልጀርስ የቀድሞም ያሁንም ገዢዎች ሁሉ ጥይት ነበር።

ትንሺቱ ሐገር ከትንሽ ሠልፈኛዋ መሐል በትንሽ ግምት ሰባት ሰዉ ቀብራለች።የንጉስ ሐማድን አገዛዝ ከሚቃወሙት አንዱ አሊ ሳልማን ጥይት ለሚዘንብበት ሕዝብ ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት የባሕሬን ለዉጥ ፈላጊ ሕዝብ ብቻዉን አይደለም።

«እናንት አብነቶች ናችሁ። ድፍን አለም እናንተን እያተመለከበተ ነዉ።እናንተም ልክ እንደ ቱኒዚያዉ፥ እንደ ታሕሪሩ አደባባይ ሁሉ የፐርሉ አደባባይ አዲስ ትምሕርት ቤቶች ናችሁ።የሰላማዊ ተቃዋሚዎች እና ጥያቄያችሁን በሰላማዊ መንገድ ያቀረባችሁ ትምሕርት ቤቶች ናቸዉ።»

ሕዝባዊ አመፅ በርግጥ ሕይወት እየጠፋ፥ ደም እየፈሰሰበት ነዉ።የሊቢያ አልጋወራሽነታቸዉ በሰፊዉ የሚነገርላቸዉ ሰይፍ አል-ኢስልማ ጋዛፊ እንደዛቱት ደግሞ ተጨማሪ ሕይወት፥ አካል መጥፋቱ በሳቸዉ እምነት «መአት» መዉረዱ አይቀርም።

«እኛ ሁላችንም ታጥቀናል።ጦሩም ሕዝቡም የታጠቀ ነዉ።በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፥ ብዙ ደም ሲፈስ እናይ ይሆናል።ሰዎች ይሰደዳሉ።ነዳጅ ዘይት ማዉጣት፥ መላክ ከማይቻልበት ደረጃ ሊደረስ ይችላል።የዉጪ ኩባንያዎች ሊቢያን ጥለዉ ይወጣሉ።ከዐለት ወደ እለት ነዳጅ ዘይት ጨርሶ ላይኖር ይችላል።»

Unruhen in Bahrain König King Hamad bin Isa Al Khalifa

ባሕሬን-ንጉሱ

ያም ሆኖ ቤን አሊን፥ ከቱኒዝ፥ ሙባረክን ከካይሮ አሽቀንጥሮ የጣለዉ አዲሱ ሕዝባዊ አመፅ የአረቡን አለም እየናጠ በአዲስ ጎዳና እየዘወረዉም ነዉ። የፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽና የጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌሯ ዲሞክራሲያዊት ኢራቅም ከአዲሱ ሕዝባዊ ነዉጥ አላመለጠችም።ማን ያሰልስ ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ