ማንዴላና የማንዴላ የማይመስሉ እዉነቶች | አፍሪቃ | DW | 09.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ማንዴላና የማንዴላ የማይመስሉ እዉነቶች

ባለፈዉ ዓመት ደግሞ ሳይንቲስቶች አንድ ግንደ ቆርቁር መሰል የጥንት ወፍ ዝርያ አገኙ። «ኔልሰንማንዴላ» ብለዉ ሰየሙት።ማንዴላ ጀርመናዊዉ ፖለቲከኛ እንዳሉት ታሪክን የዘወሩ ታላቅ ሰዉ ነበሩ።በዚያ ዘመን ግን ሰዉ መሆናቸዉን እንኳ ያወቁት ካንዲት የጥቁሮች ነፃ ሐገር ሲደርሱ ነበር።1962።

ማንዴላ እና ማንዴላን የማይመስሉ ማንዴላዎች።ሰዉዬዉ ሞቱ።ሐሙስ።ዕሁድ ይቀበራሉ።ሥራ ምግባራቸዉን እየጠቃቀስን፥ የማንዴላ የማይመስሉ ድርጊቶችን ባጭሩ እንቃኛለን።አብራችሁኝ ቆዩ።

ማንዴላ፥ አንዴ እንዲሕ ብለዉ ነበር አሉ።«እንዲያዉ ሁሌም የሚሞክርን ሐጢያተኛ እንደ ቅዱስ ካለሰብክ በስተቀር እኔ ቅዱስ አይደለሑም።» ይበሉ እንጂ በተለይ ከእስር ቤት ከተፈቱ በኋላ አብዛኛዉ ዓለም እንደ ከከሰዉ በላይ ሰዉ ይመለከታቸዉ ነበር።ሚሊዮኖች ሊያዩ፥ የተሳካላቸዉ ሊያነግሩ፥ ሊጨብጡ፥ ሊያቅፏቸዉ በሚመኙበት ወቅት ግን በቴሌቪዥን መስኮትም አልታይም አሉ።ግን በተቃራኒዉ እኔ እደዉልላችኋለሁ።

«የአደባባይ እንቅስቃሴዬ ከዛሬ ጀምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።እንዳትደዉሉሉኝ። እኔ እደዉልላችኋለሁ።»

የመጨረሻቸዉ መጀመሪያ ነበር።ባንድ ወቅት ግን «ትምሕርት» አሉ «ዓለምን የምትለዉጥበት መሳሪያ ነዉ።» የሌላዉን አናዉቅም ወይም አያገባንም።እሳቸዉ ግን ያሉትን ከማለታቸዉ ከብዙ ዘመን በፊት ተማሩ።በሕዋላም ዓለምን በርግጥ ለወጡ።ዓለምን የለወጡበትን ትምሕርት በ1925 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኤ ከማለታቸዉ በፊት ግን ወላጆቻቸዉ እንደ አፍሪቃዊ ባሕል-ወግ ያወጡላቸዉ ሥም ለአዉሮጳዉያን ቅኝ ገዢዎች እንዲመች፥ በአዉሮጳዉያን ቅኝ ገዢዎች ሲለወጥ መቀበል ግድ ነበረ ባቸዉ።መምሕርት ምዲንጋነ፥ ሆሊሻሻ የሚለዉን የዚያን ሕፃን አፍሪቃዊ ሥም «ኔልሰን» በሚለዉ አዉሮጳዊ ሥም የለወጡት እንደ ቅኝ ገዢዎቹ መርሕ፥ ፈሊጥ የቅኝ ገዢዎቹን ባሕል፣ ቋንቋ፣ ሐይማኖት በቅኝ ተገዢ አፍሪቃዉያን ላይ ለመጫን፥ ለአጠራርም እንዲመቻቸዉ አስበዉ እንጂ አፍሪቃዊዉ ሥም በአፍሪቃዊዉ ሕፃን ሥነ-ልቡና ላይ ተፅኖ እንዳያሳድር አስበዉ አይደለም።

ብቻ ያ ሕፃን አፍሪቃዊ ስሙን ጥሎ፣ ነጭ ቅኝ ገዢዎች የለወጡለትን ሥም ተቀብሎ ተማረ፣ ጎበዘ፣ አደገም።ትምሕርቱን አጋምሶ፣ ቀሪ እድሜዉን የኖረበትን ፖለቲካ ማነፍነፍ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ግን አላማ፣ ምግባሩ ሁሉ ወላጆቹ እንደሰጡት ስም ሆነ።ሆሊሻሻ።የዛፍ ቅርንጫፍ ገርሳሽ፣ወይም አብጤ እንደ ማለት ነዉ-በአገሬዉ ቋንቋ።ስሙን ነጭ ቅኝ ገዢዎች በሰጡት ለዉጦ፣ የነጭ ዘረኞችን እኩይ ዛፍ ለመገንደስ ቅርንጫፎቹን ይዘነጥል፥ ጭካኙን ሥርዓታቸዉን ለመጣል ያብጥ ገባ።

ከእንግዲሕ አንቱ ናቸዉ።ዓላማቸዉ በ1960 እንዳሉት በርግጥ ግልፅ ነዉ።«አንድ ሰዉ አንድ ድምፅ።»«አፍሪቃዉያን የሚጠይቁት አንድ ሰዉ አንድ ድምፅ በሚለዉ መርሕ መሠረት መብታቸዉ እንዲከበር ነዉ።የፖለቲካ ነፃነት።»

ይሕ ቀላል፥ ሰብአዊ ዲሞክራሲያዊ፥ ግን የነጭ ዘረኞችን አገዛዝ ከፍፃሜዉ የሚያደርስ ዓላማ ጥያቄቸዉ አስወነጀላቸዉ።።እድሜ ልክ አስበየነባቸዉ።ተጋዙም።ግን አልተበገሩም።

ታገሉ፥ ተወነጀሉ፥ ታሰሩ።ከቻርልስ ሮበርትስ ብላኪ ስዋርት እስከ ፒተር ቪሌም ቦታ፥ ደቡብ አፍሪቃን ለገዙት የነጭ ዘረኛ መሪዎችና ለየመንግሥቶቻቸዉ ማንዴላ እና የማንዴላ የፖለቲካ ፓርቲ የደቡብ አፍሪቃ አፍሪቃዉያን ብሔራዊ ምክር ቤት (ኤ.ኤ.ሲ) ሲያንስ ሰላምን አባጭ፥ ሲበዛ አሸባሪ ነበሩ።በ1989 የደቡብ አፍሪቃን የፕሬዝዳትነት ሥልጣን የያዙት ፍሬድሪክ ቪለን ደ ክላርክ ከእሳቸዉ በፊት እንተፈራረቁት ስድስት ብጤዎቻቸዉ ሁሉ የነጭ ዘረኞቹ መንግሥት መሪ ነበሩ።


ማንዴላ ግን ለዴክላርክ ከእስር መለቀቅ የሚገባቸዉ ነፃ ሰዉ፣ኤ ኤን ሲም መታገድ የሌለበት ሰላማዊ ፓርቲ ሆኑ።ዴክላክ የአባት፣ አያቶቻቸዉን፣ አስተሳሰብ ለዉጠዉ፣ የቀዳሚዎቻቸዉን ዉሳኔ ሽረዉ፥ የማንዴላን ፓርቲ ሕጋዊነት አፀደቁ።ማንዴላን ለቀቁ።

«መንግሥት ሚስተር ማንዴላን ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመፍታት ወስኗል።»
1990።ለቄስ ዴዝሞንድ ቱት፥ ማንዴላ «ፕሬዝዳት» ለመባል በድምፅ እስኪመረጡ መጠበቅ አያስፈልግም። ለቱቱና እንደ ቱቱ ሁሉ የማንዴላን መርሕ ዓላማ ለሚጋሩት ሚሊዮኖች የማንዴላ መፈታት ራሱ ታላቅ ድል ነበርም።

«አዲሱን ፕሬዝዳታችንን ከሳጥን (ከእስር ቤት) በመዉጣታቸዉ እንድትቀበሏቸዉ እጠይቃለሁ።ኔልሰን ማንዴላን።»

ድል አደረጉ። ነፃ ወጡ።ሰዉዬዉ ግን አስፈላጊዉ ነገር ሌላ ነዉ-አሉ።

«አስፈላጊዉ ነገር የአንድ ግለሰብ ወይም የአንድ ድርጅት ድል አይደለም።የደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ ድል እንጂ።»

እና ነፃዉ ማንዴላ፥ ደቡብ አፍሪቃዉያንን ነፃ ለማዉጣት ከዴክላርክ ጋር ተደራዳሪያቸዉ ሆኑ።፣ ከምርጫ በሕዋላ ፕሬዝዳቱ ማንዴላ፥ ከእስር ነፃ የለቀቋቸዉ የፕሬዝዳት ዴክላርክ አለቃ ሆኑ። ኋላ ደግሞ ዴክላክ በቀደም እንዳሉት ከማንዴላ ጋር በመስራታቸዉ «መኩሪያ፥ መከበሪያቸዉ።» ሆኑ።የታላቅዋ ብሪታንያ ትላልቅ ጠቅላይ ሚንስትሮች በጣሙን የወግ አጥባቂዉ ፓርቲ ጠንካራ መሪዎች ስም ሲጠራ ዊንስተን ቸርችር ብሎ ማርጋሬት ታቻርን ማስከተል ግድ ነዉ።ታቸር በደጋፊዎቻቸዉ ዘንድ «ብረቷ እመቤት» በሚል ቅፅል በሚንቆለጳጰሱበት ዘመን ወሕኒ ቤት ይማቅቁ የነበሩትን ማንዴላን «የአሸባሪዎች መሪ» አሏቸዉ።ኤ ኤን ሲ ደግሞ «የለየለየለት አሸባሪ ድርጅት።» 1987 ነበር-ዘመኑ።

ኔልሰን ማንዴላ የዓላማቸዉ ፅናት፣ የብልጠት፣ ብስለታቸዉ ጥልቀት፣ የድል-እድላቸዉ ትልቅነት በአንዳዶች ዘንድ ከሰዉ በላይ ሰዉ አይነት ስሜት ማሳደራቸዉን ሲቃወሙ «በድሎቼ ብዛት አትመዝኑኝ። ብለዉ ነበር። «ወድቄ በተነሳሁበት ብዛት እንጂ።»

የሰማቸዉ እንጂ የተቀበላቸዉ መኖሩ አጠራጣሪ ነዉ።የማንዴላ ገድል-ድል በዓለም በናኘበት ዘመን የነታቸርን ፓርቲ መርተዉ እንደነታቸር የታላቂቱን ሐገር ትልቅ ሥልጣን የያዙት ዴቪድ ካሜሩን በማንዴላ ምግባር፣ ሥም ዝና ተማርከዉ የሥልጣን መርሕ አዉራሾቻቸዉን የነታቸርን እምነት ብሒል ተቃረኑ።ማንዴላን አከበሩ።በቀደም ደግሞ ቃላት ሊገልፀዉ በሚችለዉ አገላለፅ አወደሷቸዉ።

«ዛሬ ከዓለማችን ደማቅ ብርሐኖች አንዱ ጠፋ።ኔልሰን ማንዴላ የዘመናችን ጀግና ብቻ አልነበሩም። የሁሉም ዘመን ጀግና ጭምር እንጂ።የነፃዋ ደቡብ አፍሪቃ የመጀመሪያ ፕሬዝዳት፥ለነፃነት እና ለፍትሕ ከሚገባዉ በላይ የተሰቃዩ፥ በታሰሩበት ዘመን ባሳዩት ፅናትና ድፍረት የሚሊዮኖችን ቀልብ የሳቡ ሰዉ ነበሩ።እሳቸዉን ባገኛችሁ ቁጥር የሚያድርባችሁ ስሜት ለሌሎች ያላቸዉን ልዩ ፍቅር፥ ደግነትና ይቅር ባይነታቸዉን ነዉ።»

«የሁሉም ዘመን ጀግና።» ከሁሉም ዘመን ባንዱ ዘመን ግን ለለንደን-ዋሽግተን መሪዎች አሸባሪ ነበሩ።ማንዴላና ኤ.ኤን.ሲን በአሸባሪነት ለመወንጀል ማርጋሬት ታቸርና ባለሥልጣኖቻቸዉ የመጀመሪያ፥ የመጨረሻዎቹም አልነበሩም።የፕሪቶሪያ የጥቂት ነጭ ዘረኛ ሥርዓት ገዢዎች ቀደሙ።ያን ዘረኛ ሥርዓት የሚደግፉት የዋሽግተን መሪዎች ተከተሉ።ፕሬዝዳንቱ ዝነኛዉ የሪብሊካኖቹ ፓርቲ ፖለቲከኛ ሮናልድ ሬጋን ነበሩ።

የሬጋን መስተዳድር በ1980ዎቹ ማንዴላን እና ኤ.ኤ.ንሲን በአሸባሪነት ሲወነጅል ጆርጅ ሐዋርድ ደብሊዉ ቡሽ ምክትል ፕሬዝዳንት ነበሩ።ቡሽ የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን በያዙበት ዓመት ማንዴላ ከዕስር ሲፈቱ እንደ ምክትል ፕሬዝዳት የደገፉ፣ ያፀደቁ፣ ያስፈፀሙትን ደንብ ሽረዉ ማንዴላን እንደ ጀግና መሪ ዋይትሐዉስ ጋበዟቸዉ።1990።«የፅናት እና፣ የድፍረት አብነት» አሏቸዉም።


በቀደም ማንዴላ ሲሞቱ ደግሞ «ፕሬዝዳንት በነበርኩበት ወቅት ማንዴላ ያለ ጥፋታቸዉ ለሃያ-ስድስት ዓመታት ያሰሯቸዉን ሰዎች ይቅር ሲሉ፥ ያላቸዉን ልዩ ችሎታና መሐሪነት በአድናቆት አይቻለሁ» አሉ።ጆርጅ ሐዋርድ ቡሽ።

ማንዴላ ነብይ አይደሉም። እራሳቸዉ እንዳሉት ቅዱስ አይደሉም-ይሆናልም።ብዙዎች እንደሚመኙ፥ እንደሚያስቡላቸዉ ከሰዉ በላይ ሰዉ አይደሉምም።የጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት የአንጌላ ሜርክል የአፍሪቃ ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ ግንተር ኖከ እንዳሉት የማንዴላ ምግባር፥ ፅናት፥ ብልሐት አንድ ሰዉ ብቻዉን ሊያከናዉነዉ ከሚገባዉ በላይ ነዉ።

«እንደሚመስለኝ ታሪካቸዉን በትክክል የሚያዉቅ፥ ማንዴላ ለደቡብ አፍሪቃ እና ለመላዉ አፍሪቃ ያደረጉትና ሚናቸዉን የሚረዳ አንድ ሰዉ ብቻዉን ያደረገዉ ነዉ ብሎ ለመገመት ይከብዳል። እሳቸዉ እንደ አንድ ሰዉ በታሪክ ላይ ታላቅ አወንታዊ ተፅኖ አሳርፈዋል።አፓርታይድን ማስወገድ፥ ሃያ-ሰባት ዓመት ሲታሰሩ ያሳዩት ፅናት፥ ከዚያ በሕዋላ ደግሞ ሐገሪቱን በሚመሩበት ዘመን ሕዝቡ በእኩልነት፥ በሰላም እንዲኖር ማድረጋቸዉ በአንድ ሰዉ አቅም የማይታሰብ ነዉ።»

ማንዴላ የተሸለሙትን በትክክል የቆጠረዉ የለም።እንደሚገመተዉ ግን ከስፖርተኞች ቲሸርት እስከ ኖቤል ድረስ ሁለት መቶ ሐምሳ ሽልማቶች አግኝተዋል። ከዩኒቨርስቲ እስከ አደባባይ፥ ከመንደር እስከ መንገድ በብዙ ሐገር ብዙ ሺሕ አካባቢ በስማቸዉ ተሰይመዋል።በ1973 የሊድስ-ብሪታንያ ዩኒቨርስቲ ሳይንቲስቶች አንድ የኑክሌር ቅንጣት ያገኛሉ።ስሟን «ማንዴላ-ቅንጣት» አሏት።

ባለፈዉ ዓመት ደግሞ ሳይንቲስቶች አንድ ግንደ ቆርቁር መሰል የጥንት ወፍ ዝርያ አገኙ። «ኔልሰንማንዴላ» ብለዉ ሰየሙት።ማንዴላ እስከ ዛሬና ከዛሬም በሕዋላ ጀርመናዊዉ ፖለቲከኛ እንዳሉት ታሪክን የዘወሩ ታላቅ ሰዉ ነበሩ።ናቸዉም።በዚያ ዘመን ግን ሰዉ መሆናቸዉን እንኳ ያወቁት ጥቁር እንደ እንሳስ ከሚረገጥበት ሐገራቸዉ ወጥተዉ ካንዲት የጥቁሮች ነፃ ሐገር ሲደርሱ ነበር።1962። በ1990 ከሰዉም ሰዉ ሆነዉ ያቺን ሐገር ዳግም ሲጎበኙ ይሕንን መሰከሩ።«ሰዉ እንደነበርኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅሁት እዚሕ ነበር።»

ያቺ ሐገር ማን ትሆን? ይገምቱ።

«ማንዴላን ያሰለጠነዉ ማነዉ? አድሐሪዉ ንጉስ ሐይለ ስላሴ፥ አብዮታዊዉን ማንዴላን አሠልጥነዋል።»

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ናቸዉ።አሁንስ ማንዴላ ሰዉ መሆናቸዉን ያወቁበትን ያወቁባትን ሐገር እርስዎ አወቋት።ካለወቁ እንደገና ይገምቱ።እኔ ለዛሬ ይብቃኝ።ሥለ ማሕደረ ዜና ያላችሁን አስተያየት፥ ማሕደረ ዜና ቢቃኘዉ ጥሩ ነዉ የምትሉትን ሐሳብ እንደ ተለመደዉ በደብዳቤ፥ በፌስ ቡክ፥ በስልክ፥ በኤስ ኤም ኤስ ላኩልን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ


Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች