ማብቂያ ያጣዉ የየመን ጦርነት | ዓለም | DW | 23.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ማብቂያ ያጣዉ የየመን ጦርነት

የመን ዉስጥ ግጭት ከተቀጣጠለ ከጎርጎሮሳዊው 2014 ወዲህ የተለያዩ ግንባሮች ተጠናክረዋል። በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሁቲ አማፅያን በአንዱ የተቃዉሞ ጫፍ  ፤በደቡብ በኩል ደግሞ በስደት የሚገኘዉ የፕሬዝዳንት አብዱራቢ መንስር ሃዲ መንግስት ይገኛል።በሀገሪቱ ደቡባዊና ሰሜናዊ ክፍሎችም የቆየ ግጭት  በማገርሸት ይዟል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:36

ግጭት የወለደዉ የየመን ቀዉስ

 

 ይህ ግጭት የሀገሪቱን ህዝብና መሰረተ ልማቶቿን  በእጅጉ ጎድቷል።
አቶ አብዱል ያስተዳድሩት የነበረዉ ኤደን ከተማ  የሚገኘዉ ቅንጡዉ የሸራተን ሆቴል የመን አሁን ላላችበት ችግር ማሳያ ይመስላል። አቶ አብዱል እንደሚሉት ላለፉት ሶስት አመታት ሆቴሉ እንግዳ ተቀብሎ አያዉቅም ።
የሆቴሉ መወጣጫወች በሸክላ ተሞልተዋል። ጠርዞቹ ጠቋቁረዋል። ጣራዉያዉ  ላይ የደበዘዙ የመብራት አምፑሎች ተንጠልጥለዋል። ሁሉም ነገር  አቧራ የለበሰ የከፈን ጨርቅ መስሏል።ከዝርፊያ የተረፉ የቤት እቃወችም መደርደሪያ ላይ እንደነገሩ  ተቀምጠዋል።አቶ አብዱ የጦር መሳሪያቸዉን  ወደታች ገፋ አድርገዉ  በእጃቸዉ ሲጋራቸዉን  እንደያዙ እንዲህ አሉ።
1,«ከሌሎች አራት ሰዎች ጋር በመሆን እዚህ እጠብቃለሁ።እነዚህ እቃዎች ከአሁን በኋላ አይዘረፉም።ከአንድ አመት በፊት ይህንን  አቋም በመዉሰዳችን  እዚህ ማንም ለስርቆት አይመጣም።»
አብዱል ወደ ሆቴሉ አምስተኛዉ ፎቅ ሲዘልቁ ፤ከዉጭ በኩል ባለዉ የሆቴሉ ግድግዳ  ላይ ትልቅ ክፍተት አለ።የሮኬት ጉዳት ነዉ።በዉጭ በኩል በሚታየዉ አሸዋማ የባህር ዳርቻ  ቀኝና ግራ  እሳተ ገሞራ የአለት ቋጥኞችን ትቷል።አብዱ  ከሁለት ዓመት በፊት እዚህ ቦታ ተኩስና ግድያ ነበር ይላሉ።እናም ለመገመት ይከብዳል። ጥቃቱ በጥቂት ቀናት ዉስጥም ሊመለስ ይችላል የሚል ስጋትም አላቸዉ።


የሆቴሉ ዉድመት በኤደን ከተማ ለደረሰው ጥፋት ማሳያ ነዉ። በወደብ ከተሞች ብዙ ነገሮች እንዳልነበሩ ሆነዋል።። በተለይ ትልልቅ ህንፃዎች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል። በግጭቱ ድሃህነት የተባባሰባት የመን በሚሊዮን የሚቆጠር መዋዕለ ንዋይ ማጣቷ ነዉ የሚነገረዉ።
በፍጥነት እየጨመረ የመጣዉ የዋጋ ንረትም ሁሉም ያማርራል። ከ3 ዓመት በፊት ከመዲናዋ ሰንዓ የተሰደደዉ የሀገሪቱ መንግስት ኤደን ዉስጥ ምንም ሊፈይድ ባለመቻሉ ፤ ዉንጀላዉ ፣ዉጥረቱና  ሮሮዉ አሁንም ቀጥሏል።
እሳተ ገሞራ በፈጠራቸዉ ተራሮች በተከበበችዉ የኤደን ከተማ ፤በገበያ ቦታዎቿ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬወች በወጉ ተደርድረዉ ይታያሉ።  ነጋዴዎቹ  ግን  ገዥ የለም ሲሉ ያማርራሉ።
2,«ሰወች ከዚህ በኋላ ምንም ገንዘብ የላቸዉም።መንግስት ዘግይቶም ቢሆን  ደሞዝ እየከፈለ ነዉ።ነገር ግን የዋጋ ንረት አለ።በዚህ ሶስት ዓመት ዉስጥ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል።የአንድ ሳጥን ጋቫ ዋጋዉ 6 ሺህ ሪያል ነበር።አሁን 10 ሺህ ሆኗል።እናም የዋጋ ግሽበት አለ። 


በየነዳጅ ማደያዎቹ የሚታየዉ ረጃጅም ሰልፍም ሌላዉ የምሬት ምንጭ ነዉ።በደቡብ የመኗ ፤የወደብ ከተማ  ኤደን  የሚካሄደው ጦርነት ያስከተለው የኢኮኖሚ ችግር ብቻ አይደለም ።በደቡብና በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል መካከል ለዓመታት የተረሳ ግጭትም ተቀስቅሷል።በጎርጎሮሳዉያኑ 1990 በተዋሀደችዉ የመን አዲስ የመገንጠል ሀሳብ የያዙ ኃይሎች «የደቡብ ሽግግር ምክር ቤት» በሚል ስያሜ  ብቅ ብለዉባታል። ይህ ዉዝግብ በብዙዎች ዘንድ ወደ ደም መፋሰስ  ሊወስድ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል ።
በደቡብ የመን ፤የጥምር ጦር አካላትም ይሁን ሳኡዲ አረቢያ ፤የተባበሩት አረብ ኢሜሬትም ይሁን በስደት የሚገኜዉ አብዱራቢ  መንስር ሃዲ መንግስት እንዲሁም   የሀገሬዉ ሰዎች  አንዱ አንዱን በጥርጣሬ የሚመለከቱና የጋራ ፍላጎታቸዉ ጥቂት ቢሆንም በሰሜን በኩል ያሉት የሁቲ አማፅያን የጋራ ጠላት መሆናቸዉ ለጊዜዉ ብቸኛዉ የሚያስተሳስራቸዉ ጉዳይ  ሆኖ ይገኛል።ይሁን እንጅ ራሱን «የደቡብ የሽግግር ምክር ቤት»ብሎ የሚጠራዉ ቡድን አባል አቶ  መንሱር ሳላህ ብዙ ሰዎች መገንጠልን ይደግፋሉ ይላሉ።
«በደቡብ ለሚኖሩ ሰዎች ስለነፃነት እናወራለን ነገር ግን ሁሉም የሚነግሩህ የ1990 አ/ም ዉህደት ዉጤታማ አለመሆኑን ነዉ። የደቡብ የሽግግር ምክር ቤት አባላት የሚፈልጉት መገንጠል ነዉ።እኛ የጥምረቱ አካል ሆነን ነዉ ሁቲን የምንዋጋዉ።ነገር ግን  ነፃነት የሚገኜዉ የጋራ ጠላታችን ከተሸነፈ በኋላ ነዉ።»
በአካባቢዉ ከሚታየዉ ግጭት ባሻገር የተሟላ የጤና አገልግሎት ማግኘት  ለኤደን ከተማ ነዋሪዎች ሌላዉ ፈተና ነዉ። በከተማዋ  የሚገኘዉ የልጆች ሆስፒታል  የታመሙ ልጆቻቸዉን ይዘዉ በተቀመጡ እናቶች ዘወትር የተጨናነቀ ነዉ።የኮሌራ በሽታ ለጌዜዉ ጋብ ያለ ይመስላል።  የኩፍኝ በሽታ ታካሚ ህጻናት ግን በርካታ መሆናቸዉን  ነዉ የሆስፒታሉ ሃላፊ ዶክተር ናሃላ አሪስ የሚናገሩት።


ዶክተር አሊስ ይፀልያሉ፤ ሶስተኛዉ ዙር የኮሌራ ወረርሽኝ እንዳይከሰት።በደቡብ የመን ሁሉም ነገር አስተማማኝ አይደለም።የሰሜንና የደቡብ ግጭት፣በሁቲ አማፅያንና  በጥምር ጦሩ አባላት መካከል ያለዉ ፍጥጫ፣ የወረርሽኝ በሽታና የኑሮ ዉድነት ለሀገሬዉ ሰዎች የለት ተለት ስጋቶች ናቸዉ።
በአካባቢዉ ከሳምንታት በፊት የደቡብ የመን ነፃ አዉጭዎች ከመንግሥት ወታደሮች ጋር ባደረጉት ግጭት ብዙዎች ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል። አሁን ለጊዚዉ ሰላም ያለ ይመስላል።የተዳፈነዉ የችግር እሳተ ገሞራ ግን በማንኛዉም ስዓት ሊፈነዳ የሚችል ነዉ የሚመስለዉ።

ፀሀይ ጫኔ /ራሚ ኦሊበር

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic