1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማብቂያ ያጣዉ የዘር ጥቃት

ሰኞ፣ መጋቢት 27 2013

ከአስከሬን፣ ቁስለኛ ተፈናቃዩ ቁጥር ስሌት፣ ከገለጩ ቃል ምስል፣ ፎቶ ባሻገር ሟች እንደሚሞት ካወቀበት ሕይወቱ እስከምታልፍ የሚፈራረቅበትን ሲቃ-ጭንቀት፣ ወላጅ፣ዉላጅ ዘመድ ወዳጆቹ የደረሰባቸዉን ስቃይ-ሰቆቃ የሚያዉቅ-ቢያዉቅም በትክክል የሚገልጥ ማግኘት ከባድ ነዉ።

https://p.dw.com/p/3rbTi
Äthiopien Horo Guduro Wollega | Hilfe für bedürftige Familien
ምስል DW/N. Dessalegn

የዘር-ዛር ምሱ ምድነዉ?

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ባለፈዉ ቅዳሜ (መጋቢት 25፣ 2013) ያወጣዉ «አስቸኳይ» መግለጫ «በሐገራችን ኢትዮጵያ ክብሩን የሰዉ ሕይወት ማጥፋት፣ የአካል ጉዳት ማድረስ» እያለ ይቀጥልና ግድያ፣ ጥፋት፣ማፈናቀሉን በየዕለቱ የምንሰማቸዉ ጉዳዮች ከሆኑ ከርመዋል ይላል።የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ገለልተኛ ጋዜጠኞች፣አጥኚዎች እንዳምና ሐቻምናዉ ሁሉ ዘንድሮም መተከል፣ ወለጋ፣ ማይካድራ፣ አክሱም፣ አማሮ፣ ሚኒት፣ መዥንገር፣ ከሚሴ፣ አጣዬ አዲስ አበባ እያሉ አካባቢ ይዘረዝራሉ፤ አስከሬን፣ ቁስለኛ፣ ተፈናቃይ ያሰላሉ።የዘር-ዛር ቆሌ የሚነዳዉ ጥቃት-ጥፋት ሰሞኑን ወለጋ ላይ በርትቷል።የዘር-ዛር ምሱ ምድነዉ? ስንት አስከሬን፣ ስንት በርሜል ደም፣ስንት ሊትር እንባ ቢፈስለት ይበቃዉ ይሆን? ላፍታ እንጠይቅ።
                                      
ከአስከሬን፣ ቁስለኛ ተፈናቃዩ ቁጥር ስሌት፣ ከገለጩ ቃል ምስል፣ ፎቶ ባሻገር ሟች እንደሚሞት ካወቀበት ሕይወቱ እስከምታልፍ የሚፈራረቅበትን ሲቃ-ጭንቀት፣ ወላጅ፣ዉላጅ ዘመድ ወዳጆቹ የደረሰባቸዉን ስቃይ-ሰቆቃ የሚያዉቅ-ቢያዉቅም በትክክል የሚገልጥ ማግኘት ከባድ ነዉ።
እሱ ያምፕ ከተባለች የመተከል ቀበሌ ከተፈናቀለ ስድስት ወር ሊሆነዉ ነዉ።ቤት ንብረቱን በለቀቀበት ዕለት «የፈጣሪ ጥላ» እና «ተዓምር» ያለዉን  ለመዘርዘር ሞከረ።
ያየና የሚያየዉን ግን ያላለዉን ብዙ ስቃይ ለማለት፣ «ቃላት ይችላሉ ግን ደካማ ናቸዉ» እንዲሉ የስነ ልሳን ሰዎች ሆኖበት «ቃላት ያጥረኛል» ማለት ነዉ-የቻለዉ።
እሱና ብዙ፣ በጣም ብዙ ሺ ብጤዎቹ፣ የእነሱን «እድል» (ዕድል ከተባለ) ሳያገኙ የተገደሉ የብዙ መቶ ልጅ፣ አባት-እናት፣ ወንድም-አሕት፣ የዘመድ-ጎረቤቶቻቸዉን ሐዘን እንኳን በቅጡ ለማዉጣት አልቻሉም።የመጠለያ ጣቢዉ ኑሮም እሱ እንደሚለዉ «ኑሮ ካሉት» ዓይነት ነዉ።ወደ ቀያቸዉ የመመለሱ ነገር አሁን አይታሰብም።«ሽፍቶች» የሚላቸዉ ታጣቂዎች፣ ተፈናቃዮቹ እሰፈሩበት ከተማ ድረስ እየተከተሉ እየገደሏቸዉ ነዉ።
የመተከል-ቤኒ ሻንጉል ጉሙዙ ክልል ጭፍጨፋ የናረዉ የአዲስ አበባ-አስመራ የጦር አዛዥ፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ የብራስልስ-ዋሽግተን ዲፕሎማት-ፖለቲከኞች ስለትግራይ ዉጊያ በሚያወሱ በሚወዛገቡበት መሐል ነዉ።
ባለፈዉ ታሕሳስ ከፍተኛ የጦር ጄኔራሎቻቸዉንና ሚንስትሮቻቸዉን አስከትለዉ ወደ አካባቢዉ የተጓዙት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ጭፍጨፋዉን ለማስቆም ሁነኛ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዉ ነበር።
በጉብኝት-ዉይይቱ ማግስት ባካባቢዉ ተጨማሪ ጦር መስፈሩ፣ የመንግሥት ባለስልጣናትን ጨምሮ በጭፍጨፋዉ የሚጠረጠሩ መያዛቸዉ ተስፋ አጭሮ ነበር።እሱ ግን የሚባልና የሚሆነዉ «ለየቅል ነዉ» ባይ ነዉ።
የትግራዩ ጦርነት፣ የማይካድራዉ ጅምላ ግድያ፣ የመተከሉ ጭፍጨፋ፣የአክሱም የሰብአዊ መብት ጥሰት እና አሰጥ አገባዉ የሸፈነዉ የጉራ ፈርዳ፣የአማሮ፣ የምስራቅ ጉጂ የዘር ጥቃት የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ቀጥሏል።የአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን ላይ የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ብዙዎችን የገደለዉ የአማራ-ኦሮሞዎች ግጭትም ከሁለት ሳምንት በፊት ዳግም አገርሽቶ በአንዳዶች ግምት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል።ብዙ አፈናቅሏልም።
የሰሜን፣ የደቡብ፣ የደቡብ ምዕራብ እና የመሐል ኢትዮጵያ አካባቢዎች ጦርነት፣ ጭፍጨፋ፣ ግድያ፣ ግጭት፣ የመብት ረገጣ፣ ጥቃትና ሽሽት ሲያርገበግባቸዉ ምዕራብ ኢትዮጵያ  ወለጋም የጨካኞች ግፍ ያናጥርባት ነበር።
ጥር።የእሳቸዉን መንደር የወረሩ የኦነግ ሸኔ ታጣቂ የተባሉ ኃይላት  የሚገድሉትን ገድለዉ፣ የእሳቸዉን ወንድም ጨምሮ በ10 የሚቆጠሩትን አገቱ።«አፈኗቸዉ ነዉ» የሚሉት እሳቸዉ።ወንድም ታገተ። ወንድም ተሰደደ።
 ዘር የማፅዳት የመሰለዉ የወለጋዉ ግድያ፣እርሸና፣ አፈና አሁንም ብሶ ቀጥሏል።ባለፈዉ ሳምንት ማክሰኞ ማታ የባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ የቦኒ ቀበሌ የመሰብሰቢያ አዳራሽን ታጣቂዎቹ፣ ወደ ሰዉ መረሸኚያ ቄራነት ቀየሯል።
 አጣዬ፣ ጊዳ ኪራሙ፣ ጎርቴ፣ ሰዴቃ፣ ቦኒ፣ ወይም ሌሎች የኦሮሞ ቀበሌ-ወረዳዎች  በደም አበላ ሲታጠቡ የኦሮሚያ ገዢዎች ከ1984ቱ የባርሴሎና የዓለም ኦሌይምፒክ ጀምሮ ዓለም ደጋግሞ የሸለመ፣ያደነቀ፣ ኢትዮጵያዉያን ጅግንነቷን የመሰከሩ፣ ያከበሩ፣ የሾሟትን አትሌት ዳግም በሾሙ በሸለሙበት ድግስ-ፌስታ  አዲስ አበባ ዉስጥ ይበሻበሹ ነበር።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የቀድሞ ይባሉ ያሁን፣ የፌደራል ይሁኑ የክልል የሕዝባቸዉን ሠላም ደሕንነት ለማስጠበቅ ይሁን ሥለ ሥራ አሰራራቸዉ ከገለልተኛ መገናኛ ዘዴዎች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ጊዜ የላቸዉም።ስራ ይበዛባቸዋል።
ብዙ ጊዜ ረዳቶቻቸዉ ወይም ራሳቸዉ እንደሚሉት ስብሰባ ላይ ናቸዉ።በስራ የተወጠሩት ሹማምንታት በሚቆጣጠሩ፣ በሕዝብ ገንዘብ በገዙትና በሚያዙት መገናኛ ዘዴ ለሰዓታት ሲያወሩ፣ጉብኝት፣ ምረቃ፣ ዕዉቅና በሚሉት ድግስ ሲታደሙና ሲደሰኩሩ ማየት እንግዳ አይደለም።
ስለ ሰሞኑ ግድያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ከወረዳ እስከ ክልል ለሚገኙ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ደዉለናል።እንደተለመደዉ እስካሁን አንዳቸዉም  የሉም።ለምን? ወይስ የተፈናቃዮች ጥርጣሬ እዉነት  ይሆን? የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ማዕከል ኃላፊ አቶ ያሬድ ኃይለ ማርያምም ማዕከላቸዉ ያነጋገራቸዉ ተፈናቃዮች ጥርጣሬዉን እንደሚጋሩ ማስታወቃቸዉን ገልጠዋል።ከግድያዉ የሸሹ እንደሚሉት ጥቃቱ ትናንትም ቀጥሏል።
አብዲሳ አጋ (ኃላ ኮሎኔል) ሮም ድረስ የተዋጉት ኢትዮጵያን ጨምሮ ድፍን ዓለምን ከፋሽስታዊ አገዛዝ ለማላቀቅ እንጂ ኢትዮጵያዊቱን የትዉልድ ከተማቸዉን ነጆን ከሌሎች ኢትዮጵያዉያን ለማፅዳት አልነበረም።ቄስ ጉዲና ቱምሳ እንደ ወንጌላዊዉ እምነት ፍቅር፣ወድማማችነት፣መደጋገፍ መረዳዳትን ለመላዉ ኢትዮጵያዊ የመካነየሱስ ቤተ ክርስቲያን አማኝ ሰበኩ እንጂ የተወለዱበትን ወለጋን ከትግሬ፣ከሸዋ፣ ከወሎ፣ ጎንደር ወይም ከሐረርጌ አልነጠሉም ነበር።
ሐይሌ ፊዳ እንደ ማርኪስስት ፖለቲከኛ፣ ይልማ ዴሬሳ እንደ ጋዜጠኛ እንደ ገጣሚም ከኢትዮጵያ አልፈዉ ለዓለም ግፉዓን ታገሉ፣ ተሟገቱ፣ ፃፉ፣ አስተማሩ እንጂ አርጆ፣ ጩታ፣ ወለጋ ይሁን ድፍን ኢትዮጵያ የዘር ዛር የሚያክለፈልፈዉ ትዉልድ ያፈራል ብለዉ ማሰባቸዉ ያጠራጥራል።ነጋሶ ጊዳዳ፣ ቡልቻ ደመቅሳ እና ብዙ ብጤዎቻቸዉ የበቀሉበት ያ ምድር በደም፣ ኢትዮጵያዊ በሚያፈሰዉ በመሳኪን ኢትዮጵያዉያን ደም የሚጨቀይበት ምክንያት ለምን ይሆን? ፖለቲካ፣ ሥልጣን፣ ምጣኔ ሐብት ወይስ እብደት?
                                   
የአብዲሳ ጀግንነት፣የጉዲና ርሕራሔ፣ የኃይሌ ሕብረተ-ሰብአዊነት፣ የይልማ ፍልስፍና፣ የነጋሶ ፅናት፣የቡልቻ ድፍረት፣ሰመረም ሳተ ሁሉም የሆነዉ ኢትዮጵያና በኢትዮጵያዉያን መሐል፣ ሁሉም የታወቁ-የተከበሩት በኢትዮጵያ እንጂ በየጎጣቸዉ አይደለም።የነሱን ጅምር መከተል፣ የተዛባዉን ማቃናት የሚገባዉ ትዉልድ ብጤዉን ለመግደል ሲያድም ኃይ የማለት ኃላፊነት ደግሞ የመንግስት መሆኑን ለማረጋገጥ ተንታኝ መፈለግ ጅልነት ሊሆን ይችላል።

Äthiopien Horo Guduro Wollega | Hilfe für bedürftige Familien
ምስል DW/N. Dessalegn
Äthiopien Horo Guduro Wollega | Hilfe für bedürftige Familien
ምስል DW/N. Dessalegn
Äthiopien Vertriebene Menschen in Mendi
ምስል DW/N. Dessalegn

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ