ማብቂያ የታጣለት የኮንጎ ውዝግብ | አፍሪቃ | DW | 01.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ማብቂያ የታጣለት የኮንጎ ውዝግብ

በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ የሚካሄዱት ግጭቶች የፖለቲካው ውዝግብ እንዲባባስ አድርጓል፣ ብዙዎቹን የሀገሪቱ ዜጎችም ለስደት እና ለመፈናቀል ዳርጓል። የአውሮጳ ህብረት ሰሞኑን  በኮንጎ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ የጣለው ማዕቀብ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ውዝግቡን እንዲያበቁ ግፊት ሊያሳርፍባቸው ይችል ይሆናል በሚል አንዳንዶች ተስፋ አድርገዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:40

ኮንጎ

በዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ውስጥ የፖለቲካው ቀውስ  አሁንም ገና አልረገበም። ኮንጎን ከአንጎላ ጋር በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ በሚገኘው የካዛይ ግዛት ውጊያ እየተካሄደ ነው፣ በምሥራቅ ኮንጎ ባለው የሰሜን ኪቩ ግዛት የሚንቀሳቀሱት ዓማፅያን ቡድኖችም በመንግሥቱ ጦር እና በሲቭሉ ህዝብ አንፃር ጥቃት መሰንዘራቸውን አላቋረጡም፣  በፕሬዚደንት ዦሴፍ ካቢላ መንግሥት አንፃር በመዲናይቱ ኪንሻሳ በተደጋጋሚ በተካሄዱ ተቃውሞዎች ቢያንስ የ50 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። 

የርስበርሱ ግጭት ለብዙ ሕዝብ መፈናቀል እና መሰደድ ምክንያት ሆነዋል። በገዛ ሀገራቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ ተመልካች ማዕከል  በተመድ መዘርዝሮች ላይ በመመርኮዝ ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ በጎርጎርዮሳዊው 2016 ዓም ብቻ ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በተመ የህፃናት መርጃ ድርጅት፣ «ዩኒሴፍ» ዘገባ መሰረት፣በማዕከላይ ኮንጎ በቀጠለው የኃይል ርምጃ ም ወደ 400,000 የሚጠጉ ህፃናት አሳሳቢ የዕድሜ ልክ የጤና ችግር ያሰጋቸዋል። ውጊያው በሚካሄድበት የካዛይ ግዛት የሚገኙ የጤና ማዕከላት በዝርፊያ ሰበብ ከተዘጉ በኋላ ወደ 9,000 የሚጠጉ ህፃናት ድንበር ተሻግረው ወደ አንጎላ መሰደዳቸውን የ«ዩኒሴፍ» ባልደረባ አቡበከር ሱልጣን ገልጸዋል።

« ህፃናቱ ረጅም መንገድ ተጉዘው ዶንዶ መጠለያ ጣቢያ የደረሱ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ በውጊያው ቆስለዋል፣ ጥይቶቹ ገና በሰውነታቸው ውስጥ አሉ፣ አንዳንድ የሰውነት አካላቸውም ተቃጥሎዋል። ብዙዎቹም ወላጆቻቸውን አንድም በመኖሪያ ቀያቸው ሳሉ በተፈጠረ ግጭት ወይም ወደ መጠለያ ጣቢያው ለመድረስ ባደረጉት ጉዞ  ወቅት  በመንገድ ላይ አጥተዋል። »
የኮንጎ መንግሥት ውዝግቦቹን ለማስቆም በቂ ርምጃ እየወሰደ አይደለም በሚል ተቺዎች  ነቀፌታ አሰምተዋል። የኮንጎ ፕሬዚደንት ዦሴፍ ካቢላ የአመራር ዘመን ባለፈው ታህሳስ 2016 ቢያበቃም ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸውም  በመላይቱ ሀገር የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ እና በሰበቡ የተፈጠረውን ግጭት ለማብቃት ከተቀናቃኝ ቡድኖች ጋር በተካሄደ ድርድር ፕሬዚደንት ካቢላ በሀገሪቱ እጎአ በ2017 ዓም መጨረሻ አዲስ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ በስልጣን እንዲቆዩ ያኔ ስምምነት ተደርሷል። ይሁንና ፣ በስምምነቱ የተጠቀሰው የሽግግር ሂደት እንደታሰበው በመከናወን ላይ አይገኝም፣ የምርጫው እቅድም ግልጽ አይደለም። የካቢላን በስልጣን መቆየት በመቃወም  የተነሳውን ሁከት ተከትሎ የአውሮጳ ህብረት ባለፈው ታህሳስ በሰባት ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉ የሚታወስ ሲሆን፣ ሰሞኑን ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ በዘጠኝ ባለስልጣናት ላይ የማዕቀብ ውሳኔ አሳልፏል።  የዝውውር ገደብ ጭምር የሚያሳርፈው አዲሱ ማዕቀብ ተየሀገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ ላምቤርት ሜንዴን እና የሀገር ውስጥ ሚንስትር ራማዛኒ ሻዳሪንም ይነካል።

 
መንግሥታዊ ባልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች(መያዶች) ግፊት የተጣለው ማዕቀብ በሀገሪቱ ባለስልጣናት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ እንደማይቀር የአውሮጳ መረብ ለማዕከላይ አፍሪቃ የተሰኘው መያድ ዳይሬክተር ዶናቴላ ሮስታኞ ገልጸዋል።
« የአውሮጳ ህብረት የጣለው ማዕቀብ የኮንጎ ባለስልጣናት ለውዝግቡ ትኩረት እንዲሰጡ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ፣  ስልጣናቸውን በማጠናከሩ ተግባር ላይ ብቻ ያተኮሩት እነዚህ ባለስልጣናት ሕዝቡ ለውጥ እንደሚፈልግ ረስተውታል። እና ማዕቀቡ ስማቸው የተጠቀሱትን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሀገሪቱን ባለስልጣናት ነገሮችን በጥሞና  እንዲያጤኑ እና ለማዕቀቡ ምላሽ እንዲሰጡ ያደርጋል  ብለን እናስባለን። »
ማዕቀቡን በተመለከተ እስካሁን ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ሬፓብሊክ መንግሥት በኩል በይፋ አስተያየት አልተሰጠም። ይሁን እንጂ፣ የህብረቱ ውሳኔ ሳያሳስበው አልቀረም።  የአውሮጳ ህብረት ኮንጎን በሊቢያ ወይም በኢራቅ የሚታየው ዓይነት ቀውስ ውስጥ ለመጣል እየሞከረ መሆኑን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የመንግሥት ባለስልጣን ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ገልጸዋል። ይሁን እንጂ፣ የአውሮጳ መረብ ለማዕከላይ አፍሪቃ የተሰኘው ድርጅት ዳይሬክተር ሮስታኞ ህብረቱ፣ ምንም እንኳን ማዕቀብ ቢጥልም፣ ኮንጎ ታካሂደዋለች ለሚባለው ምርጫ የፊናንስ ድጋፍ ለማድረግ የገባውን ቃል ለመጠበቅ እቅድ እንዳለው ገልጸዋል፣ ። ለዚህም ኮንጎ ባለፈው ታህሳስ በተፈረመው ስምምነት መሰረት የምርጫውን ጊዜ እና ሕጎች፣ እንዲሁም፣  በጀቱን እንድታሳውቅ ህብረቱ ቅድመ ግዴታ አስቀምጧል።

አርያም ተክሌ 

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic