ማርያ ቴሪዛ ማን ናቸዉ? | ባህል | DW | 23.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ማርያ ቴሪዛ ማን ናቸዉ?

«ስለማርያ ቴሬዛ ከማለታችን በፊት ኢትዮጵያ በዓለም ገንዘብን ካሳተሙ የመጀመርያዎቹ ሃገሮች አንዷ ናት። በአክሱም መንግስት የወርቅ፤ የብር፤ የነሃስ ሳንቲም ይታም ነበር። ከአክሱም መዉደቅ በኋላ ወደ ሜዲተራንያንና ወደ አረብ ሃገር የሚደረገዉ የንግድ ልዉዉጥ ሲዳከም የገንዘብ ስራም ቆመ፤ በጨዉ ንግድ ተጀመረ »

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:10

በአጼ እያሱ ሁለተኛ የማርያ ቴሬዛ ብር ወደ ኢትዮጵያ ገባ

ከጎርጎረሳዊ 1717 እስከ 1780 ዓ.ም የኖሩትና በይፋ የንግስና አክሊልን ያልደፉት የኦስትርያን ንግሥት ማርያ ቴሪዛ ዘንድሮ 300 ኛ ዓመት የትዉልድ ዓመታቸዉ በአዉሮጳ በተለይ ደግሞ በትዉልድ ሃገራቸዉ በኦስትርያ በተለያዩ አዉደ ርዕዮች በመከበርና በመታሰብ ላይ ይገኛል። ሃንጋሪን እንዲሁም የቦሂሚያ ግዛት በመባል ይታወቅ የነበረዉን የአሁኑን ቼክ ሪፓብሊክን እንዲሁም ትዉልድ ሃገራቸዉን ኦስትርያን የመሩት ማርያ ቴሪዛ ስልታዊ አስተዳዳሪ፤ ሩህሩህ፤ አሳቢ፤ ሙሉ ፍቅር ሰጭ እናት ብሎም ተሃድሶ አምጭ በመሆናቸዉ ይታወቃሉ።  ማርያ ቴሪዛ በግዛት ዘመናቸዉ ያሳተሙት የመገበያያ ዘመን ከግዛታቸዉ አልፎ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሰሜን አፍሪቃ እንዲሁም በመካከለኛዉ ምስራቅ ታዋቂ የመገበያያ ገንዘብ ሆኖ ቆይቶአል። ማርያ ቴሪዛ ማን ናቸዉ? በዚህ ዝግጅታችን የማርያ ቴሪዛን የህይወት ታሪክ እያየን በኢትዮጵያ የማርያ ቴሪዛ ብር ግብይት ታሪክን እናያለን።

በጎርጎረሳዊዉ 1740 ዓ.ም በ 23 ዓመታቸዉ የኦስትርያ ንግስት ሆነዉ ማስተዳደርን የጀመሩት ማርያ ቴሪዛ በይፋ የንግሥና ተክሊልን አልደፉም። በዝያ ዘመን ማርያ ቴሬዛ በኦስትርያና አካባቢዋ ላይ የነበሩ ብሩህ አላማ የነበራቸዉ የመጀመርያዋና አንድየዋ ንግሥት መሆናቸዉ ተዘግቦላቸዋል።   

ማርያ ቴሪዛ በተለይ በወጣትነት ዘመናቸዉ ከግንባራቸዉ ገባ ያሉ ፊታቸዉ ክብና ሙሉ ገፅታ ያላቸዉ ነጣ ያለ ወርቅማ ባለጠጉር ቆንጆ ሴት ሲሉ የዘመናቸዉ ሰዎች ይገልጹዋቸዋል። ማርያ ቴሬዛ በዘመናቸዉ በሰዓልያን ጥበብ በስዕል መልክ የቀረቡ ሴት መሆናቸዉም የታሪክ መዝገባቸዉ ያሳያል። የአስራ ስድስት ልጆች እናትዋ ማርያ ቴሬዛ ወሊድ በሰዉነታቸዉ እየታ ላይም ከበድ እንዲሉ አድርጓቸዋል። የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለሚካኤል ስለ ንግሥት ማርያ የታሪክ መጻሕፍትን አገላብጦአል።

« የኦስትርያ ንጉሠ ነገስት ነዉ የሚባለዉ። ስለማርያ ተሬዛ ብዙ ነገር ይነገራል። የሕዝቡ የአገር እናት፤ ሩሕሩህና ያላቸዉን ቆርሰዉ የሚያካፍሉ፤ ቸር ንግሥት እንደሆኑ ይናገራል። አንድ ጊዜ የማስታዉሰዉና ያነበብኩት ነዉ፤ እኝህ ንግሥት በቤተ መንግሥታቸዉ በመናፈሻ ቅጽር ጊዚ ዉስጥ ሲዘዋወሩ አንዲት የኔ ቢጤ ልጅዋን ታቅፋ ደክሟት ዛፍር ስር ስታቃስት ያገኝዋታል። ንግስቲቱ ልጁን ተቀብለዉ ደረታቸዉ ላይ ለጥፈዉ ጡት እያጠቡ፤ የኔ ቢጤ እናቱን አነጋግረዋል፤ ነዉ የሚባለዉ። እንዲህ አይነቱ የንግስቲቱ የማርትሬዛ ስራና ገድል በ 19ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን በሰፊዉ የሚወራ ነበር። » 

በአዉሮጳ ሰፊ ግዛትን ይገዙ የነበሩት የኦስትርያዋ ንግሥት ማርያ ትሬዛ  ስማቸዉን በበጎ ለማንሳት የተነገረ ይመስለኛል፤ ማርያ ቴሬዛ የዛሬ ሦስት መቶ ዘመን የሴት ንግሥና በሌለበት ወደ ስልጣን ላይ የወጡት እንደአጋጣሚ ነዉ፤ ሲል የገለፀልን ይልማ ኃይለሚካኤል በመቀጠል፤

«ማርያ ቴሬዛ ወደ ስልጣን የወጡት እንደ አጋጣሚ ነዉ አንድኛዉ ምክንያት፤ ወንድማቸዉ በደረሰበት ድንገተኛ ህመም መሞቱ ነዉ። ስለዚህ አባታቸዉ ካርል ስድስተኛ አንድ ልዩ የሆነ ግን ለአጭር ጊዜ የሚሆን ዉሳኔ አድርጎ ነዉ የሄደዉ። ዉሳኔዉ የመጀመርያዋ ልጄ ማርያ ትሬዛ እኔ ከሞትኩ በኋላ አልጋዬን እንድትወርስ ብሎ የሰጠዉ ትዕዛዝ በመሆኑ ነዉ። እኝህ ሴትዮ ስልጣን ላይ እንደወጡ እንደሚታወቀዉ ታሪኩ የዛሬ 300 ዓመት ነዉ። በዝያን ጊዜ አዉሮጳን የሚመሩ የጀርመን ንጉሶች የሩስያ ንጉሶች የእንጊሊዝ ንጉሶች ፤ ሌላም አካባቢ ያሉት ንጉሶች ወንዶች ናቸዉ። ወንዶች ደግሞ አገርን ማስፋፋት አገርን መጠበቅ ጦርነት ነዉ የሚሹት፤ በዚህ መሃል አንዲት ሴት ወደ ስልጣን ላይ ስትመጣ፤ ይህ በሴት የተያዘዉን አካባቢ በቁጥጥራችን እናገባለን፤ ፈረንሳዮችም የጀርመኑ ንጉስ ፊሬድሪክም ተነስቶአል፤ ሌሎች የባየርንም ንጉስ ተነስቶአል። እኝህ ሴት ግን፤ አሁን በቅርቡ የወጡት ሁለት ሦስት መጽሐፎች እንደሚያሳዩት፤ ሴት ብሆንም ስልጣን ሃገር እንዲሁም ያለኝን መንግሥት ለማንም አሳልፊ አልሰጥም በሚል ጦር ሜዳ ሳይሄዱ የጦር ጀነራል ሆነዉ ሳይመሩ በልዩ ብልሃት ኦስትርያን የሃንጋሪን መንግስት የያዙና ያቀፉ እስከተቻላቸዉ ዘመን ድረስ የሄዱ ናቸዉ።»    

በዓለም ላይ ካሉ ሃገሮች ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘብን የሰራች ሃገር ነች፤ የአክሱም መንግሥት ሳንቲሞችን ያመርት ነበር፤ የአክሱም ዘመነ መንግሥት በስድስተኛ መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ሲዳከም በአሞሌ ጨዉ እቃን በቃ መለወጥ የመገበያያ መንገድ ተፈጠረ። ከዝያም የማርያ ትሬዛ የመገበያያ ገንዘብ መጣ፤ ያሉን የታሪክ ተመራማሪና በኢትዮጵያ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ ናቸዉ። 

«ስለማርያ ቴሬዛ ከመነጋገራችን በፊት ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከሰለጠኑ ሃገሮች ኢትዮጵያ የመጀመርያዉ የመገበያያ ገንዘብ ከታተሙባቸዉ ሃገሮች መካከል ትገኛለች። በአክሱም ዘመነ መንግስት የወርቅ ሳንቲም፤ የብር የነሃስ ሳንቲም የተመረቱባት ሃገር ናት። በኋላ ላይ ከአክሱም መዉደቅ በኋላ ወደ ሜዲተራንያንና ወደ አረብ ሃገር የሚደረገዉ የንግድ ልዉዉጥ ሲዳከም የገንዘብ ስራም ቆመ። ኢትዮጵያዉያን በገበያ ላይ መጠቀም የጀመሩት እቃን በእቃ መለወጥ በአሞሌ ጨዉ በመሳሰሉት ነዉ። የአክሱም ዘመነ መንግሥት የመገበያያ ገንዘብን ያመርት ነበር። በዓለም ላይ ሳንቲሞችን ማተም የስልጣኔ ምልክት ነዉ። ይሄ እንግዲህ ዛሬ እነ አሜሪካ እነ አዉሮጳ ሳይፈጠቱ «አይ ኤም ፊ» ፤ የ«ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም» ሳይፈጠር ኢትዮጵያ ዉስጥ የሳንቲም ምርት ነበር። ኢትዮጵያ ከሰለጠኑት ሃገሮች ዉስጥ አንድዋ ነበረች። የራስዋ ገንዘብ ነበራት። የአክሱም ዘመነ መንግስት በስድስተኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ሲዳከም፤ የእቃ በእቃ ልዉዉጥ ተፈጠረ። በኃላ ላይ የአሞሌ ጨዉ የመገበያያ ገንዘብ ሆነ። »

የአሞሌ ጨዉ እንደ መገበያያ ገንዘብ ለረጅም ዓመታት ሲሰራበት ቆይቶ፤ በአፄ እያሱ ሁለተኛ ዘመነ መንግሥት የማርያ ቴሬዛ ብር ወደ ኢትዮጵያ ገባ ሲሉ አቶ ኃይለ መለኮት አክለዋል።

« ይህ አሞሌ ጨዉ ለብዙ ጊዜ ሲሰራበት ቆይቶ በአጼ እያሱ ሁለተኛ በማርያ ቴሬዛ ታለር የምንለዉ ወደ ጎንደር መጣ። በዝያ ዘመን የነበረዉ ይህ ሳንቲም ከ 1781 ዓ,ም በፊት ታትሞ የነበረዉ ነዉ። ይህን ታሪክ ሪቻርድ ፓንክረስት በመጽሐፋቸዉ ጠቅሰዉታል። 

የዶይቼ ቬለዉ ጋዜጠኛ ይልማ ኃይለሚካኤል እንደሚለዉ ማርያ ትሬዛ በአላት የፖለቲካ አያያዝና ጥበብ ወንዶች፤ በተለያዩ ሃገራት፤ መሳፍንትና ንጉሶች በነበሩበት ዓለም ብቸኛ ሴት መሬ ሆና ማሳለፍዋ ታሪኳን የደመቀ አድርጎታል፤  

«በጣም ልዩ የሚያደርጋት ነገር ሴት ሆና የንጉሰ ነገስቱን ዙፋን ላይ ተቀምጣ የአባትዋን ዘዉድ ደፍታ አገሪቱን ችግር ላይ ሳትጥል በሴትነትዋም ማንም ሳይነካት በአላት የፖለቲካ ጥበብና የስልጣንም አጨባበጥ ኦስትርያ ሃንጋሪን በማሳደግዋ በመያዝዋ ነዉ። በሌላ በኩል ያደረገችዉ መንግስትን ጠብቃ የመንግሥትን አካሄድ ለማድረግ እስዋ አካባቢ የነበሩትን ሹማምንቶች በተለይም ደግሞ ባልሆነ ሥነምግባር ዉስጥ የነበሩ፤ በሙስናም ይሁን የራስን መንፈስ በማስደሰት በመብላት በመጠጣት ስርዓት ቢስ የነበሩትን ሰዎች አባራ፤ ሌሎች ወጣቶችን ተክታ ትምህርት እንዲስፋፋ አድርጋለች፤ የመንግሥት አሰራርና የመንግስት ሁኔታን መልክ እንዲይዝ አድርጋለች፤ ይህን ነገር ሁሉ ኦስትርያ ዉስጥ አስተዋዉቃ አልፋለች።»  

ንግስቲቱ ቀደም ሲል መሳፍንቱና መኳንቱ ከአደን ሲመለስ ያርፍበትን ግዙፍ ቤት ወደ ቤተ መንግሥት ቀይራ አድርጋዉ የነበረዉን ግዙፍ ሕንፃ «ዩኔስኮ» በክብርና ቅርስና ዉርስ መዝገብ ተመዝግቦ ጥበቃ እየተደረለገለት እየተጎበኘ ይገኛል። አጼ ምኒሊክ ከአሞሌ ጨዉና ከማርያ ቴሬዛ መገበያያ ብር በኋላ የራሳቸዉን ብር አሳትመዋል፤ እንዲህም ተገጥሞላቸዋል፤

ልመደዉ መሸከም ፤ አሞሌ ማንከብከብ ሲወዘዉዘኝ ፤

እምዬ ምኒልክ ብር አሰራልኝ፤

አጋሰስ መጋዣ አህያ እንዳንጭን

ፈረንጁ በጥበቡም እንዳይኮራብን፤

እምዬ ምኒሊክ ሰራልን ብሩን።

ከገበያ ዉጡ ጥይትና ጨዉ

የፈረንጆቹን ብር ሰራ አባ ዳኘዉ።

ዝቀህ ስጠኝና አሽከርህ ልክበር፤

ዳኘዉ ካስነጠርከዉ ካሰራኸዉ ብር።  ተብሎ ተገጥሞአል። ኦስትርያ የንግስት ማርያ ቴሬዛን የ300 መቶኛ የልደት ዓመትን በማስመልከት ከጎርጎረሳዊዉ መጋቢት 15 እስከ ኅዳር 29 2017 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቅ ልዩ ልዩ አዉደ-ርዕዮችን፤ ትያትሮችን በማሳየት ንግስቲቱን በመዘከር ላይ ትገኛለች። ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

 

Audios and videos on the topic