ማርቲን ሹልዝ እና የኃላፊነት ዘመናቸው | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 17.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ማርቲን ሹልዝ እና የኃላፊነት ዘመናቸው

ሹልትስ በፕሬዝዳንትነታቸው ዘመን ከሚታወሱባቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል በተለይ ፓርላማው ተሰሚነትን እንዲኖረው ያደረጉት ጥረት እና ያስገኙት ውጤት እንዲሁም የፈጠሩት ጤናማ የሥራ ግንኙነት ጎልቶ ይታያል

 

«ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ ። በሚቀጥለው ዓመት ለሦስተኛ ዘመን የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነት አልወዳደርም ። ከዚያ ይልቅ በጀርመን ምክር ቤት የኖርዝ ራይን ቬስት ፋልያን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ወክዬ ለፓርቲየ ለሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ SPD እወዳደራለሁ ።» 
ዛሬ በአዲስ ፕሬዝዳንት የሚተኩት ጀርመናዊው ፖለቲከኛ ማርቲን ሹልዝ በአውሮጳ ኅብረት ፕሬዝዳንትነት እንደማይቀጥሉ ባለፈው ኅዳር የሰጡት መግለጫ ነበር ። የ61 ዓመቱ ሹልዝ በፖለቲካው ዓለም ከአደጉበት ትንሽ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክር ቤት አባልነት ተነስተው በሂደት ለተለያዩ ኃላፊነቶች በመመረጥ የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤትን እስከ መምራት የበቁ በሳል ሶሻል ዴሞክራት ፖለቲከኛ ናቸው። በ1994 የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ አባል የሆኑት ሹልዝ የምክር ቤቱን የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን ያገኙት በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓም ነበር  ። ለዚህ ኃላፊነት ከመብቃታቸው በፊት ደግሞ በፓርላማው የሶሻሊስቶች እና የዴሞክራቶች ጥምረት መሪም ነበሩ ።  ላለፉት አምስት ዓመታት የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የሰሩት ማርቲን ሹልዝ ፣ሁለት ጊዜ ነው ለዚህ ኅላፊነት የተመረጡት ። የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ እንደሚለው ሹልዝ ሁለት ጊዜ የተመረጡት በምክር ቤቱ የሶሻሊስቶች እና ዴሞክራቶች ጥምረት ስምምነት መሠረት ነው ። 
ሹልትስ ወደ ፖለቲካውን ዓለም የገቡት ከዛሬ 42 ዓመት በፊት በጎርጎሮሳዊው 1974 ዓም ነው። በ19 ዓመታቸው ነበር የጀርመኑ ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ

SPD የወጣት ክንፍ አባል የሆኑት። የሹልትስ የትውልድ ስፍራ ከምዕራብ ጀርመንዋ ከአኽን ከተማ በስተሰሜን የምትገኘው ኤሽቫይለር ክፍለ ከተማ ውስጥ ያለችው ሄህልራዝ የተባለችው ቦታ ናት። ያደጉት ደግሞ ኋላ በከንቲባነት ያገለገሉባት ቩርሰልን በተባለችው ከተማ ነው ። ሆኖም ለወጣቱ ሹልዝ ህይወት በቩርስል እጅግ አስቸጋሪ ነበር ። የፖሊስ መኮንን ልጅ የነበሩት ሹልትስ በወጣትነታቸው የአልኮሆል ሱሰኛ ነበሩ። በዚህ ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናም አልወሰዱም። ሥራም አልነበራቸውም። ያም ሆኖ በፓርቲያቸው በSPD ንቁ ተሳትፎ ስለ ነበራቸው ባደጉበት በዚህችው ከተማ የዕድላቸው በር ተከፈተ ። የSPD አባል ከሆኑ ከ10 ዓመት በኋላ የቩርስለን ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክር ቤት አባል ሆነው ተመረጡ ። በማዘጋጃ ቤቱ ምክር ቤት አባልነት ለሁለት የሥራ ዘመን ያገለገሉት ሹልትስ ለ11 ዓመታት ከተማዋን በከንቲባነት አስተዳድረዋል። ሹልትዝ በ32 አመታቸው ነበር ከንቲባ ሆነው የተሾሙት ። ከተማዋ በምትገኝበት በኖርዝ ራይን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር በዚህ እድሜ ከንቲባ ለመሆን የበቁ የመጀመሪያው ፖለቲከኛም ሆነዋል። ሹልዝ አሁንም ከአኽን በስተሰሜን በምትገኘው በዚህች ከተማ ነው የሚኖሩት። ማርቲን ሹልዝ በአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ውስጥ በልዩ ልዩ ኃላፊነቶች በሰሩባቸው ዓመታት የኅብረቱ ፓርላማ ተቀባይነት እንዲሰፋ እና አቅሙም

እንዲጠናከር የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ይወደሳሉ። ከፓርላማው እንደሚሰናበቱ ባሳወቁበት ንግግራቸው ይህን ያነሱት ሹልትስ በአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ሲያካሂዱ የቆዩትን ትግላቸውን በጀርመንም እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል።   
«በአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ በሶሻሊስቶቹ ቡድን ፕሬዝዳንትነት አለያም በምክትልነት በሠራሁባቸው ጊዜያት የአውሮጳ ፖለቲካ ተዓማኒና ግልጽ እንዲሆን ፣ በህዝብ በቀጥታ የሚመረጠው የአውሮጳ ፓርላማ ተጽእኖም እንዲጠናከር ከፍተኛ ጥረት አድርጌያለሁ። ከአሁን በኋላ ደግሞ ለዚህ የአውሮፓ ፕሮጀክት በብሔራዊ ደረጃ እታገላለሁ። የሰዎች የእለት ተእለት ህይወት እንዲሻሻል እሞክራለሁ።»  
የብራሰልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ ሹልትስ በፕሬዝዳንትነታቸው ዘመን ከሚታወሱባቸው  ዋና ዋና ተግባራት መካከል በተለይ ፓርላማው ተሰሚነትን እንዲኖረው ያደረጉት ጥረት እና ያስገኙት ውጤት እንዲሁም የፈጠሩት ጤናማ የሥራ ግንኙነት ጎልቶ ይታያል ይላል። 
ከፓርቲዎች ይልቅ የጋራውን አውሮጳን አጀንዳ ያስቀድሙ የነበሩት ሹልትስ ከሄዱ በኋላ የፓርላማው አሠራር እንደ በፊቱ እንደማይቀጥል ነው የሚገመተው። ይህም ገበያው እንደሚለው አውሮጳዊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት አለ።

 ሹልትስ በኅብረቱ ፓርላማ የፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመናቸው ታዋቂነትን ካተረፉባቸው ንግግሮቻቸው መካከል በየካቲት 2014  በእስራኤል ፓርላማ ማለትም ክኔሴት ያሰሙት ንግግር ይገኝበታል። በወቅቱ የእስራኤልን የሰፈራ መርሃ ግብር በይፋ በመተቸታቸው በርካታ የእስራኤል ፓርላማ አባላት አዳራሹን ለቀው እስከ መውጣት ደርሰው ነበር። በሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይም በሰነዘሩት ግልጽ ትችት ስማቸው ይነሳል። ሹልትስ ከአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ፕሬዝዳንትነት ሲሰናበቱ በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ለመራሄ መንግሥትነት የፓርቲያቸው እጩ ሆነው ይቀርባሉ ተብሎ ተገምቶ ነበር። ቀጣዩ የጀርመን ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁትን የአሁኑን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየርንም ተክተው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎም ነበር። ፓርቲያቸው SPD ሊቀመንበሩን ዚግማር ገብርየልን ለመራሄ መንግሥትን ካጨ በኋላ የመጀመሪያው ግምት አልያዘም። ሁለተኛውም አልተረጋገጠም። እስካሁን የታወቀው ሹልትስ በጀርመን ምክር ቤት ምርጫ ፓርቲያቸውን ወክለው ለፌደራል ክፍለ ሀገራቸው መሪነት እወዳደራለሁ ማለታቸው ብቻ ነው።  

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ
 

Audios and videos on the topic