ማሬ ኖስትሩምን የተካው ትሪቶን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 04.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

ማሬ ኖስትሩምን የተካው ትሪቶን

በጣሊያኒኛዉ«ማሬ ኖስትሩም» ወይም ባህራችን በሚል መጠሪያው ለአንድ ዓመት ያህል ሜዲትራኒያን ባህል ላይ ችግር የሚገጥማቸውን በተለይም ስደተኞችን ባህር ሰምጠው እንዳይቀሩ የማዳን ተግባር ሲያከናዉን የነበረው የኢጣልያ ባህር ኃይል ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በትሪቶን ተተክቷል።

ይህም ኢጣልያ ለጠቅላላ የአውሮጳ ችግር ብቻዋን ኃላፊነት መውሰድ ባለመፈለጓ ነው። አዲሱ የአውሮፓውያን የባህር ተልዕኮ ሥራውን ቢጀምርም ያለው ባጀት መለስተኛ፣ መንቀሳቀስ የሚፈቀድለት የባህር ክልልም የተወሰነ ነው።

Malta Springbrunnen in Valetta

የትሪቶን ኃውልት ማልታ ውስጥ

ትሪቶን ለቀደምት ግሪካውያን የባህር አምላክ ነው። ምስሉም፤ ከላይ ያለው የሰውነት ክፍል የሰው ሲሆን፤ እግሮቹ የፈረስ ፤ የተቀረው ሰውነቱ ደግሞ የዶልፊን ነው። ይህ ትሪቶን ባህሩን የመበጥበጥም ይሁን የማረጋጋት ኃይል አለው ብለው የሚያምኑ ግሪካውያን አልጠፉም። አዲሱ የአውሮፓውያን የባህር ኃይል ተልኮ የዚህን የባህር አምላክ መጠሪያ ይዟል።« ትሪቶን የኢጣሊያን የድንበሮች ቁጥጥር ለማሻሻል ሚና ይጫወታል። ራሱን የቻለ ተልኮ ግን ሳይሆን ጣሊያኖች ለሚያከናዉኑት የድንበር ቅኝት ድጋፍ እንዲሰጥ የታለመ ነው ። ይህ ብቻም አይደለም የኢጣሊያን ድንበር ሲቆጣጠር ባህር ላይ አደጋ ለገጠማቸውም ሊደርስ ይችላል። »

ይላሉ ክላውስ ሮስለር፣ ከአውሮጳ ህብረት ድንበር ጠባቂ ጓድ፣ በምሕፃሩ «ፍሮንቴክስ» ። የ«ፍሮንቴክስ» ሀላፊነት የአውሮጳን ድንበር መጠበቅ እና ከሕገ ወጥ ስደተኞች መከላከል ሲሆን በአዲሱ ትሪቶን የሚል መጠሪያ በያዘው የፍሮንቴክስ ተልኮ እስከ 20 የሚደርሱ አባል ሃገራት ተሳትፈዋል። ሁለት ትላልቅ መርከቦች እና በርካታ ትናንሽ መርከቦች ያሉት ይሄው ኃይል ከዚህም ሌላ ሁለት አይሮፕላኖች እና በርካታ ሄሊኮፕተሮችም አሉት። የጀርመን ተሳትፎ የተወሰኑ የድንበር ፖሊሶችን ወደ አካባቢው በመላክ እና አንድ ሄሊኮፕተር ዝግጁ በማድረግ ነው። በጀቱ ውስን ነው።

ኢጣሊያ ከአንድ ዓመት በፊት በላምፔዱዛ አቅራቢያ አንድ የስደተኞች ጀልባ ሰምጦ 366 አፍሪቃውያን፣ ከሞቱ ጀምሮ በባህር ኃይሏ ያቋቋመችው « ማሬ ኖስትሩም» በወር ወጪው 9 ሚሊዮን ዮሮ ነበር። ትሪቶን ደግሞ 3 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ነው ያቀረበው። ተልኮውም ቢሆን የተለየ ነው የሚሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል ድርጅት ባልደረባ ቢኮላስ በርገር፤ ማሬ ኖስትሩም ሰዎችን ከባህር የማዳን ኃላፊነት ሲኖረው ትሪቶን ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ የአውሮጳን ድንበር ይቆጣጠራል ይላሉ።«ያ ማለት ዋናው አላማቸው የሰዎችን ማንነት መለየት ላይ ያተኮረ ሆኖ፤ የጣት አሻራ እየወሰዱ የመመዝገብ ነው። ይህ ነው አላማው።»

Mission Mare Nostrum Italien

የማሬ ኖስትሩም የማዳን ተልኮ

ትሪቶን ከኢጣልያ እና ማልታ 30 ማይል ክልል በመሸፈን ባህሩን ሲቆጣጠር ማሬ ኖስትሩም ከዚህ ክልል አልፎ ባህሩ ላይ በመቶ ማይየሚቆጠር ርቀትን በመሸፈን፤ አልፎ አልፎም በርካታ የስደተኛ ጀልባዎች ወደ ሚነሱበት ሊቢያ የባህር ክልል አቅራቢያ ድረስም ይጓዝ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴዉም ማሬ ኖስትሩም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 150 000 ስደተኞችን ከባህር ማዳኑን ይናገራል። ይህን የተቀሩት የአውሮጳ ሃገራት አላወደሱትም። ይልቁንስ የማዳን ተግባሩ ስደተኞችን እና ደላሎችን የሚያበረታታ ነበር በማለት ይተቻሉ። ኒኮላስ በርገር ከአምንስቲ ኢንተርናሽናል በትሪቶን ጊዜ የተወሰኑ ነገሮች እንደሚለወጡ ነው የሚናገሩት፤«ባህር ላይ ሰዎችን ከአደጋ ለማዳን የመመልከቱ ተግባር ቀነሰ ማለት፤ ሰዎች የባህር ጉዞዋቸውን ይቀንሱና አደጋውም ይቀንሳል ማለት አይደለም። እንደዉም በከፋ መልኩ የሚሞቱት ቁጥር ይጨምራል።»

ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም እንደ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ትሪቶን ያለውን የስደተኛ ጉርፈት አይቀንስም ባይ ናቸው፤ ከዚህም በተጨማሪ ይህ የአውሮጳ የጋራ የስደተኞች ፖሊሲን አይወክልምም እያሉት ነዉ። እንደ ኒኮላስ በርገር መፍትሄው ስደተኞቹ በሕጋዊ መንገድ የሚገቡበት እና በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራትም በእኩል መጠን ተበትነዉ የሚደላደሉበት መንገድ መፈለግ ይኖርበታል። «ከአውሮጳ አባል ሃገራት የበለጠ ትብብር መታየት አለበት። ፖለቲካቸውን በጋራ እንደሚያራምዱ ሁሉ አጥራቸውንም በአንድ ላይ ነዉ የሚገነቡት። ሁሉም 28 ሃገራት ዓለም አቀፋዊ ሕግጋቶችን በጋራ የመቀበል ኃላፊነት አለባቸው። የጋራ ኃላፊነቱ ግን ጎሏል።»

በአሁኑ ሰዓት ከነዚህ 28 የአውሮጳ ህብረት ሃገራት ግማሽ የሚሆነው ተገን ጠያቂዎችን እንኳን እየተቀበለ አይደለም። አበሻ ኤጀንሲ የተባለው እና ለስደተኞች እርዳታ የሚሰጥው ግብረሰናይ ድርጅት ሃላፊ አባ ሙሴ ዘርዓይ የአዲሱን የትሪቶን ተልኮ ከበፊቱ ማሬ ኖስትሩም ጋር አነፃፅረውልናል።

በሳምንቱ መጨረሻ ስራውን ባጠናቀቀው የኢጣሊያ የባህር ኃይል ማሬ ኖስትሩም ፋንታ የተቋቋመውን የአውሮፓ ህብረት ተልኮ፤ ትሪቶንን አስመልክቶ የቀረበው የአውሮፓ እና ጀርመን ሙሉ ዝግጅትን በድምፅ ያገኙታል።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic