ማረሚያ ቤት እስክንድር ነጋን ለምስክርነት አላቀርብም አለ | አፍሪቃ | DW | 19.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ማረሚያ ቤት እስክንድር ነጋን ለምስክርነት አላቀርብም አለ

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት እየታየ ላለው የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና አምደኛ አምሳሉ ገብረኪዳን ክስ፣ በመከላከያ ምስክርነት ተቆጥረው የነበሩ እና በእስር ላይ ያሉ ሶስት ጋዜጠኞች ችሎት ሳይቀርቡ ቀሩ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:41
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:41 ደቂቃ

ማረሚያ ቤት እስክንድር ነጋን ለምስክርነት አላቀርብም አለ

በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስር ያለው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት እስክንድር ነጋን “አላቀርብም” ሲል የዝዋይ ማረሚያ ቤት በበኩሉ ተመስገን ደሳለኝ እና ውብሸት ታዬን ለማቅረብ የመጓጓዣ ችግርን በምክንያትነት አንስቷል፡፡ ችሎቱ ግን ምስከሮቹ “በተለዋጭ ቀጠሮ ይቅረቡ” ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ሁለቱ ተከሳሾች አሁን በህትመት ላይ በማይገኘው “እንቁ” መጽሔት ላይ ታትሞ በነበረ ጽሁፍ ምክንያት “ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር” ፈጽመዋል በሚል ነበር የተከሰሱት፡፡ ሁለት ዓመት ሊደፍን ወር የቀረው ይህ የክስ ሂደት ለዛሬ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው በጋዜጠኛ ኤልያስ እና አምደኛ አምሳሉ በኩል የሚቀርቡ የመከላከያ ምስክሮችን ለማድመጥ ነበር፡፡

ተከሳሾቹ በምስክርነት ካስመዘገቧቸው ግለሰቦች ውስጥ ሶስት የተከሳሾቹ የቀድሞ ባልደረቦች በችሎት ተገኝተው ነበር፡፡ በእስር ላይ የሚገኙት እና በዛሬው የምስክርነት ሂደት እንዲቀርቡ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተሰጥቶላቸው የነበሩት ጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ እና ውብሸት ታዬ በማረሚያ ቤቶቹ ምክንያት ወደ ችሎት ሳይመጡ ቀርተዋል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ አምሳሉ ገብረኪዳንም ክሱን ለመከታተል በስፍራው አልነበረም፡፡

ጋዜጠኞቹ ታስረው የሚገኙባቸው የየማረሚያ ቤቶቹ አስተዳደሮች ምስክሮቹን ለምን እንዳለመጧቸው በደብዳቤ ለፍርድ ቤት አስረድተዋል፡፡ የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን በበኩላቸው አቶ አምሳሉ ፍርድ ቤት መቅረብ ያልቻለው ጤናው በመታወኩ ምክንያት ካለበት ክፍለ ሃገር መምጣት ባለመቻሉ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡

የምስክሮቹን እና የሁለተኛ ተከሳሽን በችሎት አለመገኘት የተመለከተው ፍርድ ቤት የምስክር መስማት ሂደቱን ለሌላ ጊዜ እንዳሸጋገረው ለምስክርነት በቦታው ተገኝቶ የነበረው ጸሀፊ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ይናገራል፡፡

“በሁለት ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል፡፡ አንደኛ ሁለት ምስክሮች ከማረሚያ ቤት የሚመጡት አልተገኙም ነበር፡፡ በሁለተኝነት ደግሞ እንዱ ተከላካይ አምሳሉ ገብረኪዳን አልተገኘም ነበር፡፡ ስለዚህ በሁለቱ ምክንያት ቀጠሮው ተሻግሯል” የሚለው በፍቃዱ ከማረሚያ ቤት ይመጣሉ ተብለው ችሎት እንዳይገኙ ስለተደረጉት ጋዜጠኞች የተባለውን ያጋራል፡፡

“የተመስገን ደሳለኝ ወቅቱ ለጥበቃ በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ እና ለአጀባ ችግር ስለሚሆንባቸው እንዳላመጡት ገልጸዋል፡፡ ጠበቃውም በዚህ ላይ ምንም ቅሬታ አላሰሙም፡፡ የእስክንድር ነጋ ግን ‘አንደኛ ነገር የተከሰሰበት ከባድ ወንጀል ነው፣ ሽብር ነው፣ ረጅም ዓመት ነው የተፈረደበት ለጥበቃ ይከብደናል፤ ሁለተኛ ነገር ደግሞ ማረሚያ ቤቱ ውስጥም አመጽ የሚያነሳሱ ነገሮችን እያደረገ ስለሆነ አናመጣውም’ የሚል ምክንያት ነው ያቀረቡት፡፡ ጠበቃው ይህን ተቃውመዋል” ብሏል በፍቃዱ በችሎት ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጽ፡፡   

ጠበቃ አምሃ ለፍርድ ቤቱ ባሰሙት መቃወሚያ “እስክንድር ነጋ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ አመጽ የማነሳሳት እና የማደራጀት ተግባር ስራ ይሰራል የተባለው በማስረጃ ተደግፎ የቀረበ አይደለም” ማለታቸውን አቶ በፍቃዱ ይናገራል፡፡ “እኛ አቶ እስክንድርን ለምስክርነት ነው የጠራናቸው፡፡ የተጠቀሰው ጉዳይ ከእኛ ጋር በምን እንደሚገናኝ አይገባንም” ሲሉ ጠበቃው መከራከራቸውንም ጨምሮ ገልጿል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ በጉዳዩ ላይ “ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ ይስጥ” ማለቱን ከችሎቱ ታዳሚዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡

የሁሉንም ወገኖች አስተያየት ያደመጠው ፍርድ ቤቱ በምስክርነት የተቆጠሩት እስረኛ ጋዜጠኞች ችሎት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ለታህሳስ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ሰጥቷል፡፡ ዛሬ በችሎት ተገኝተው የነበሩት ቀሪ ምስክሮችም በቀጣይ ቀጠሮ ተሟልተው እንዲገኙ ማዘዙን አቶ በፍቃዱ ያስረዳል፡፡   

“ፍርድ ቤቱ እንዲመጡ ብይን አሳልፏል፡፡ ረጅም ቀጠሮ ነው የተሰጣቸው፡፡ ይቅረቡ ነው የተባለው፡፡ በዚህ ቀን እንዲቀርቡ ሲል ሰምቻለሁ” ይላል በፍቃዱ፡፡ በችሎት ተገኝተው ስለነበሩ ሌሎች ምስክሮች ደግሞ “እኔን ጨምሮ ፍቃዱ ማህተመወርቅ እና በሪሁን አዳነ ቀርበን ነበር” ሲል ይገልጻል፡፡ ነገር ግን “ሁሉም ተሟልተው ይቅረቡ” በመባሉ ምስክርነታቸው ሊደመጥ አለመቻሉን ያብራራል፡፡

ለክሱ መነሻ የሆነው ጽሁፍ “የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ ሀውልቶች የማን እና ለማን ናቸው?” በሚል በ“እንቁ” መጽሔት በመጋቢት 2006 ዓ.ም በአምሳሉ ገብረኪዳን አማካኝነት የታተመ አስተያየት ነበር፡፡ በወቅቱ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ የነበሩት አቶ ኤልያስ ለጽሑፍ መታተም ተጠያቂ ናቸው በሚል ከጸሀፊው ጋር አብሮ ተከስሷል፡፡ መጽሄቱን ያነበቡ የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ብጥብጥ አስነስተው 40 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት እንዲያወድሙ ጽሁፉ ምክንያት እንደሆነ በክሱ ላይ ተጠቅሷል፡፡   

ተስፋለም ወልደየስ

ሒሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች