1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የፕሬቶሪያ ስምምነት ጥቅምና ጉድለቱ

ሰኞ፣ ጥቅምት 25 2017

ያቺ ጥንታዊት፣ደሐ፣ጦረኞች የሚፈራረቁባት ሐገር ዳግም በጦርነት ትንፍር ያዘች።ትግራይ ጋየች፣ ከፊል አማራ ነደደ፣ ከፊል አፋርም ተለበለበ።የኤርትራ፣የኢትዮጵያ መደበኛ ወታደሮችና የአማራ ሚሊሻዎች ከሕወሓት ወይም የትግራይ ኃይሎች ከሚባለዉ ጦር ጋር ሁለት ዓመት በገጠሙት ጦርነትና መዘዙ አንዳዶች እንደሚሉት በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አልቋል

https://p.dw.com/p/4mb19
የኢትዮጵያ መንግሥትና የህወሓት ዋና ተደራዳሪዎች አቶ ሪድዋን ሁሴንና አቶ ጌታቸዉ ረዳ ፕሪቶሪያ ዉስጥ የስምምነት ሲፈራረሙ
ከግራ ወደ ቀኝ አቶ ሪድዋን ሁሴን የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስት ዋና ተደራዳሪና አቶ ጌታቸዉ ረዳ የሕወሓት ዋና ተደራዳሪ ግጭት የማስቆም ስምምነትን ሲፈራረሙ።ፕሪቶሪያ-ደቡብ አፍሪቃምስል PHILL MAGAKOE/AFP/Getty Images

ማሕደረ ዜና፣ የፕሬቶሪያ ስምምነት ጥቅምና ጉድለቱ

 

ሕዳር መጀመሪያ ነዉ።2022 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ፕሪቶሪያ።ደቡብ አፍሪቃ።«ዛሬ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪቃ ቀንድ፣ በእርግጥም ለመላዉ አፍሪቃ የአዲስ ንጋት ብረቀት ነዉ።»

የቀድሞዉ የናጄሪያ ፕሬዝደንትና የአፍሪቃ ሕብረት የአፍሪቃ ቀንድ ዋና አደራዳሪ ኦሌሴጎን አባሳንጆ።የኢትዮጵያ መንግሥትና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መሪዎች ግጭት ለማቆም ተስማሙ።ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ሁለት ዓመቱ።እስከ ስምምነቱ ድረስ ሁለት ዓመት የተንፈቀፈቀዉ የጠመንጃ ላንቃ ተዘጋ።መቀሌ የሰላም አየር ተነፈሰች።አዲስ አበባ ዘመረች-«ሠላም ለሁሉም» እያለች።የስምምነቱ ሁለተኛ ዓመት መነሻ፣የጦርነቱ ጥፋት ማጣቃሻ፣የስምነቱ ገቢራዊነት መድረሻችን ነዉ። 

ለሠላምና ለዴሞክራሲ የሚጠሩ መሪዎች

ነሐሴ 1994 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዎረን ክርስቶፎር ዋሽግተንን የሚጎበኙትን የኢትዮጵያን ጊዚያዊ ፕሬዝደንት መለስ ዜናዊን ለማነጋገር ቢሯቸዉ ሲቀበሉ «---ከጎኔ የቆሙት የዛሬ እንግዳዬ---ጥንታዊቱን ሐገር ኢትዮጵያን ከጦርነት ወደ ሰላም፣ከአምባ ገነዋዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር የሚጥሩ ከአፍሪቃ ወጣት ዴሞክራቶች አንዱ---» እያሉ ጋዜጠኞች ፊት አድናቆት ዉዳሴዉን አንቆረቆሩት።ታዘብን።

እኛ አዛዉንት ዲፕሎማት «ለሠላም፣ ዴሞክራሲ የሚጥሩ» ያሏቸዉ ኢትዮጵያ መሪ፣ «ጥንታዊት» ያሏትን ሐገር ከ4 ዓመት በኋላ ዳግም ከጦርነት ሲሞጅሯት ያሉት ከነበረ፣ የሚሰሙበት ሥልጣን ላይ አልነበሩም ወይም ያሉት የለም።

የአዳዲሶቹ መሪዎች ፍቅርና ጠብ

የመለስ ዜናዊዉ ሕወሓት/ ኢሕዴግ፣ የኢሕአዲጓ ኢትዮጵያ ግን ያኔ እንደተነገረላት «ለሠላም ስትል» የሰሜን ግዛትዋን ኤርትራን ከነወደቦቿ ካስገነጠለችም በኋላ ከአዲሲቱ ጎረቤቷ ጋር ካዲስ ጦርነት ተመስጋለች።ግንቦት 1998።

የኢትዮጵያ መንግሥትና የሕወሓት ዋና ተደራዳሪዎች ሁለቱን ወገኖች ከአደራዳሩት የአፍሪቃ ሕብረት፣ የኬንያና የደቡብ አፍሪቃ ፖለቲከኞች ጋር
የኢትዮጵያ መንግሥትና የሕወሓት ዋና ተደራዳሪዎች ሁለቱን ወገኖች ከአደራዳሩት የአፍሪቃ ሕብረት፣ የኬንያና የደቡብ አፍሪቃ ፖለቲከኞች ጋርምስል PHILL MAGAKOE/AFP

ሁለት ዓመት ያስቆጠረዉ ጦርነት ከመቶ ሺሕ በላይ ወጣት ካረገፈ በኋላ የአዲስ አበባና አሥመራ  መሪዎችን ገሳጭ፣ ገላጋይ፣ ዋና አስማሚም አሜሪካኖች ነበሩ።ከሐራሬ እስከ ዋጋዱጉ፣ ከአልጀርስ እስከ ዘ ሔግ የአፍሪቃ፣የአዉሮጳ፣ የአሜሪካ፣ የአረብ ዳኛ-ዲፕሎማቶችን ያባተለዉ፣የዓለም ሠላም አስከባሪ ሠራዊትን ያስዘመተዉ ስምምነት ግን ቀጥታ ዉጊያዉን ከማስቆም ባለፍ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል አግባቢ ሰላም አላሳፈነም።

በጦርነቱ ላለቀዉ፣ ለቆሰለ፣ ለተፈናቃለዉ ሕዝብ ጉዳትም ሆነ ለወደመዉ ሐብት ንብረት በሕግ የተጠየቀ ወገንም የለም። በ1998 ባድመ በምትባል ትንሽ ቀበሌ ሰበብ መቶ ሺዎችን እስኪያስፈጁ ድረስ «ነፋስ የማይያስገቡ ጥብቅ ወዳጆች» የነበሩት ወይም የመሰሉት የአዲስ አበባና የአስመራ መሪዎችም አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለመጉዳት፣ ማሳጣት ማጥፋት ሲጣጣሩ 20 ዓመት አስቆጥረዋል።

                አዲስ አበባና አሥመራ «አዲስ ፍቅር»

በ2018 ሚያዚያ አዲስ አበባ ላይ የተደረገዉ የመንግሥት ለዉጥ ልክ እንደ 1966ቱ፣ እንደ 1983ቱ ሁሉ ለኢትዮጵያ አዲስ የሠላም፣ የዴሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት መከበር ተስፋ ፈንጥቆ፣ አሮጌዎቹን የአስመራ መሪዎች ከአዳዲሶቹ የአዲስ መሪዎች ጋር አወዳጅቶ ነበር።

የኢትዮጵያዉን ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድን ለዓለም ታላቅ የሰላም ሽልማት ኖቤል ያበቃዉ የሁለቱ ሐገራት መሪዎች ፍቅር አዲስ አበባዎችን «ኢሱ፣ ኢሱ» ን« እያስደነቀ ሲያስጨፍር ምናልባት አስመሮችን «አንቺ ልጅ ኮሪባቸዉ በአማርኛ አናግሪያቸዉ ሳያሰኝ አልቀረም።አሰኘም አላሰኘ የኤርትራው መሪ ካዲስ አበባ ለኢትዮጵያዉያን ባማርኛ የማይዘነጋ መልዕክት አስተላለፉ።

                                   

መልዕክቱ፣ የምኒሊክ ቤተ መንግሥትን በመቀማታቸዉ አኩርፈዉ መቀሌ ዉስጥ ለሰፈሩት ለቀድሞዉቹ የኢትዮጵያ ገዢዎች ወይም ለሕወሓት መሪዎች መሆኑን ለማወቅ ጥልቅ የፖለቲካ ዕዉቀት አልጠየቀም ነበር።ጠይቆም ከነበር ሕዳር መጀመሪያ 2020 መቀሌ የሰፈረዉ የኢትዮጵያ የሰሜን ዕዝ ጦር ሲመታ ሐቁ ፈጋ።

ያቺ ጥንታዊት፣ደሐ፣ጦረኞች የሚፈራረቁባት ሐገር ዳግም በጦርነት ትንፍር ያዘች።ትግራይ ጋየች፣ ከፊል አማራ ነደደ፣ ከፊል አፋርም ተለበለበ።የኤርትራ፣የኢትዮጵያ መደበኛ ወታደሮችና የአማራ ሚሊሻዎች ከሕወሓት ወይም የትግራይ ኃይሎች ከሚባለዉ ጦር ጋር ሁለት ዓመት በገጠሙት ጦርነትና መዘዙ አንዳዶች እንደሚሉት በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አልቋል።ብዙ ሚሊዮን ተፈናቅሏል ወይም ተሰድዷል።በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ንብረት ወድሟል።ሰዎች በጅምላ ተገድለዋል።ታስረዋል።፣  ሴቶች በፈረቃ ተደፍረዋል።

የማስፈፀሚያዉ ዉል በተፈረመበት ወቅት የአፍሪቃ ሕብረት ዋና አደራዳሪ ኦሌሴጎን ኦባሳንጆ (ከጀርባ በስተግራ) እና የቀድሞዉ የኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ (ከጀርባ በስተቀኝ) ተገኝተዋል
የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሐኑ ጁላ (ከግራ) እና የትግራይ ኃይሎች ጦር አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ናይሮቢ ዉስጥ የሰላም ስምምነቱን ማሥፈፀሚያ ዉል ከተፈራረሙ በኋላምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

አንዳዶች የዘር ማጥፋት፣ ሌሎች የጦር ወንጀል ተፈፅሞበታል ያሉት ጦርነት የመቀሌ፣ የአዲስ አበባና የአስመራ ገዢዎችን ሥልጣን ከማስጠበቅ ባለፍ ለትግራይ ክልል ይሁን ለሌላዉ ኢትዮጵያ የተከረዉ ነገር።የቀድሞዉ የኢሕአፓ ታጋይ፣ የኢሕዴን መሥራችና የፖለቲካ ተንታኝ ያሬድ ጥበቡ እንደሚሉት ከአዉዳሚዉ ጦርነት ያተረፈ ቢኖር አንድ ሰዉና ሥርዓታቸዉ ብቻ ናቸዉ።

«ከዚሕ ጦርነት ያተረፈ ካለ ኢሳያስ ባካባቢዉ ላይ ትልቅ ኃይል ሆኖ ሊመጣ መቻሉ።ከሶማሊያ እስከ ጅቡቲ እስከ ግብፅ ድረስ የሚጎማለል የፖለቲካ ተዋኝ የሆነበትና----»

ከሁለት ዓመቱ እልቂት፣ ፍጅት፣ ጥፋት፣ ከጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ በኋላ የኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስትና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የዛሬ ሁለት ዓመት ፕሪቶሪያ ላይ ያደረጉት ስምምነት ዉጊያዉን አስቁሞታል።የአፍሪቃ ሕብረት ዋና አደራዳሪ የቀድሞዉ የናጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሌሶጎን አባሳጆ ያኔ እንዳሉት ሁለቱ ወገኖች የተፈራረሙት ስምምነት በርካታ ጉዳዮችን የያዘ ነዉ።

«በኢትዮጵያዉ ግጭት የሚሳተፉት ሁለቱ ወገኖች፣ ግጭትን ለማስቆም፣ በዕቅድ፣ በሥርዓት፣ በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ትጥቅ ለመፍታት፣ ሕግና ሥርዓትን ዳግም ለማስፈን፣አገልግሎቶችን ዳግም ለመጀመር፣ ያልተገደበ ሰብአዊ ርዳት እንዲደርስ ለማድረግ፣ሰላማዊ ሰዎችን በተለይም ሴቶች፣ ሕፃናትና ሌሎች ለአደጋ ተጋላጭ ሰዎችን ከጥቃት ለመጠበቅና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ በይፋ ተስማምተዋል።»

ስምምነቱ ገቢራዊ አልሆነም

ብዙዎች እንደሚሉት ስምምነቱ አስከፊዉ እልቂት እንዳይቀጥል ማድረጉ በጣም ጠቃሚ ነዉ።በስምምነቱ የተካተቱት ዋና ዋና ጉዳዮች ግንአሁንም ገቢር አልሆኑም።ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ እንደሚሉት የኤርትራ ጦር ከትግራይ ግዛት ሙሉ በሙሉ ለቅቆ አልወጣም።ትግራይና የአማራ ክልልን የሚያወዛገቡ ግዛቶችን በጦርነቱ ወቅት የተቆጣጠሩት የአማራ ኃይላት አሁንም አካባቢዎቹን እየተቆጣጠሩ ነዉ።በመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምሕር ገብረስላሴ ካሕሳይ እንደሚሉት የኤርትራና የአማራ ኃይላት ከሚቆጣጠሩት አካባቢ የተፈናቀሉ በርካታ ነዋሪዎች ወደየቀያቸዉ አልተመለሱም።

«በዚሕ ምክንያት ከምዕራብ ትግራይ፣ ጎሎመከዳና ከኢሮብ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወ።ደየቀያቸዉ አልተመለሱም።ከደቡብ ትግራይ የተፈናቃሉ የተወሰኑ ነዋሪዎች ወደየቀያቸዉ ቢመለሱም አሁንም ጥበቃ አይደረግላቸዉም።ሰላማዊ ሰዎች አሁንም ለአደጋ እንደተጋለጡ ነዉ።«

አቶ ያሬድ ጥበቡም በዚሕ ይስማማሉ።ግን የዉጊያዉ መቆም ራሱ እንደ ጥሩ ዉጤት መታየት አለበት  ባይ ናቸዉ።

የሁለት ዓመቱን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያስቆመዉ የፕሪቶሪያ ስምምነት እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ አልሆነም
የትግራይ የሲቪል ማሕበረሰብ አባላት መቀሌ ዉስጥ ባደረጉት የአደባባይ ሰልፍ፣ የፕሪቶሪያዉ የሰላም ሥምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።ምስል Million Hailesilassie/DW

«የትግራይም ሆነ፣ የሰሜኑ የአማራ ክፍልና የአፋር ክልል ከጦርነት ነፃ መሆናቸዉ አፕርሼት መደረግ አለበት።ነገር ግን ጦርነቱ የፈጠራቸዉ የተፈናቀሉ ሰዎች አሉ።በድንኳን የሚኖሩ አሉ።---የፕሪቶሪያ ሥምምነት በተፃፈበት መንገድ ተግባራዊ ሊደረግ አለመቻሉ ችግር አለዉ።»

የፖለቲካ ተንታኖች እንደሚሉት ስምምነቱ ገቢር ላለመሆኑ የአዲስ አበባና የመቀሌ ፖለቲከኞችም፣ ሁለቱን ወገኖች የሸመጉሉት በተለይ ጠንካራ አቅም ያላቸዉ የዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ መንግሥታትም ተጠያቂዎች ናቸዉ።

ሥምምነቱ ሙሉ በሙሉ ገቢር ሳይሆን የሕወሐት ፖለቲከኞች እርስበርስ ይናጫሉ።የኢትዮጵያ መንግሥም በጦርነቱ ወቅት በአብዛኛዉ አጋሩ ከነበሩት የአማራ ኃይላትና ከተባባሪዎቻቸዉ ጋር ዉጊያ ገጥሟል።ከሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት በፊት ምዕራብ ኦሮሚያ ዉስጥ ሸምቀዉ የነበሩት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ኃይላትም አዲስ አበባ ጥግ ድረስ ጥቃት እያደረሱ ነዉ።እና ኢትዮጵያ ዛሬም ከዉጊያ፣ግጭትና ጥቃት አልተላቀቀችም።

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ