ማሕደረ ዜና፣ የዩክሬን ጦርነት፣ የምዕራብ-ምሥራቆች ፍጥጫ አብነት
ሰኞ፣ ኅዳር 2 2017የበርሊን ግንብ የፈረሰበት 35ኛ ዓመት ባለፈዉ ቅዳሜ ተዘከረ።የቀዝቃዛዉ ጦርነት ምልክት፣ የዓለም ክፍፍል አብነት የነበረዉ ግንብ መፍረስ ያኔ እንደተዘመረለት የካፒታሊስቱ ርዕዮተ ዓለም ድል፣የዓለም በተለይም የአዉሮጳ አንድነት ብሥራት ነበር።ግንቡ በሕዝብ ዓመፅ የተገነደሰበት 35ኛ ዓመት ዘንድሮ ሲዘከር ግን አዉሮጳ ዩክሬን ላይ ትዋጋለች።ዩክሬንን የወረረችዉ ሩሲያ የምዕራቦቹን ኃይል ጫና ለመቋቋም ከኮሚንስት ሰሜን ኮሪያ ጋር የጦር ቃል ኪዳን ተፈራርማለች። የምዕራቡ ዓለም ዋና መሪ ዩናይትድ ስቴትስ አዲስ መሪ መርጣለች።ዓለምም የኃያሊቱን ሐገር አዲስ መርሕ ይጠብቃል።የበርሊን ግንብ መፍረስ ዉጤት የሆነዉ የፖላንድ መንግስት አዉሮጳን ለሁለት የሚገምስ ግንብ ያስገነባል።የአዲሱ የአሜሪካ መሪ ዕቅድ መነሻ፣ ዩክሬንን የሚያነደዉ ጦርነት ማጣቃሻ፣የዓለም ዳግም ክፍፍል መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
የዋሽግተን ፖስት ዘገባ፣ «ግልፅ ልብ ወለድ» ፔስኮቭ
መጋቢት 2003 (ዘመኑ በመሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የአንግሎ-አሜሪካን መሪዎች ኢራቅን እንዲወር ያዘመቱት ጦር በተጠንቀቅ ቆሟል።መሪዎቹ ወረራዉን «ምክንያታዊ» ና «ተገቢ» ለማስመሰል ለየሕዝባቸዉ የሚሉት ነገር ማግኘት ነበረባቸዉ።የያኔዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር የስለላ «መረጃ» ደርሶኛል ብለዉ ካቀረቡት ምክንያት የኢራቅ መሪ ሳዳም ሁሴን በ45 ደቂቃ ዉስጥ ኬሚካዊና ባዮሎጂያ ጦር መሳሪያ ለመተኮስ ተዘጋጅተዋል የሚለዉ አንዱ ነበር።
«ሳዳም ኬሚካዊና ባዮሎጂያዊ ጦር መሳሪያዎች ማምረታቸዉን ቀጥለዋል።የተመረቱትን ኬሚካዊና ባዮሎጂያዊ መሳሪዎች በራሳቸዉ በሺዓ ሕዝብ ላይ ጭምር በ45 ደቂቃ ዉስጥ ለመተኮስ ወታደራዊ ዝግጅት ማድረጋቸዉን---»
እያሉ ቀጠሉ።
የብሪታንያና የአሜሪካ ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎችም የሁለቱ ሐገራት መሪዎች ያሉትን ተከትለዉ የሳዳም ሁሴንን ጭካኔ፣አረመኔነት፣ ያንን መርዝ ለመርጨት ያላቸዉን ብቃት፣ ዝግጅት፣ ኢላማቸዉን ሳይቀር እየዘረዘሩ ያራግቡት ያዙ።ወረራዉ አልቀረም።ሳዳም ሁሴንም ተሰቀሉ፤ ኢራቅም በደም አበላ ታጠበች፤ ወደመችም።የለንደን-ዋሽግተን መሪዎች ዓለምን የዋሹበት፣ ታላላቆቹ ጋዜጠኞች ያራገቡት ጅምላ ጨራሽ መርዝ ግን እስከ ዛሬ አልተገኘም።
በ21ኛዉ ዓመት ሰሞኑን የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጭ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የወደፊት መርሕ እንዴትነት ዓለምን ሲያነጋግር የአሜሪካዉ ዕዉቅ ጋዜጣ ዋሽግተን ፖስት ያሰራጨዉ ዘገባና የሞስኮዎች መልስ በ2003 የነበረዉን በጨረፍታ የሚያስታዉስ፣ የሚያጠያይቅ፣ ላንዳዶች አስተዛዛቢ፣ ግራ አጋቢም ብጤ ሆኗል።
ዋሽግተን ፖስት እንደዘገበዉ የአሜሪካዉ ተመራጭ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።ባለፈዉ ሐሙስ ተደረገ በተባለዉ የስልክ ዉይይት ፑቲን የዩክሬኑን ጦርነት እንዳያባብሱ ትራምፕ አሳስበዋቸዋል።ዩናይትድ ስቴትስ አዉሮጳ ዉስጥ በርካታ ጦር እንዳላትም ትራምፕ ለፑቲን ነግረዋቸዋል።ተዘዋዋሪ ማስጠንቀቂያ መሆኑ ነዉ።ሌሎች መገናኛ ዘዴዎች ዋሽግተን ፖስትን እየጠቀሱ የሁለቱን መሪዎች የስልክ ዉይይት ሲተነትኑ ዛሬ የፕሬዝደንት ፑቲን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ «ዘገባዉ ልቦለድ ነዉ» አሉ።
«ታዊቂያለሽ፣ ይሕ፣ ባሁኑ ወቅት በተከበሩ ሕትመቶች ሳይቀር አንዳዴ የሚወጡ መረጃዎች ምን ያሕል ጥራት እንደሚጎድላቸዉ የሚያሳይ በጣም ጥሩ ምሳሌ ነዉ።ይሕ ፍፁም እዉነት አይደለም።ግልፅ ልብወለድ ነዉ።ይሕ በቀላሉ የሐሰት መረጃ ነዉ።የስልክ ዉይይት አልተደረገም።»
እዉነቱ ዋሽግተን ይሁን ሞስኮ ለጊዜዉ አይታወቅም።የሚታወቀዉ ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኛ በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት የዩክሬኑን ፕሬዝደንት ቮልድሚየር ዘለንስኪን ካነጋገሩ በኋላ ከተመረጡ ሶስተኛ ዐመቱን ያገባደደዉን የዩክሬንን ጦርነት ባስቸኳይ ለማቆም ቃል መግባታቸዉ ነዉ።
«(ከዘለንስኪ ጋር) ጥሩ ግንኙነት አለን።እንደምታዉቁት ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋርም ጥሩ ግንኙነት አለን።እናሸንፋለን።ጦርነቱንም ቶሎ እናስቆማለን።»
የዩክሬኑ ጦርነት ያደረሰዉ ጥፋትና ኪሳራ
አንዳዶች ሩሲያ ክሪሚያ የሚባለዉን የዩክሬን ግዛት ከግዛትዋ በጠቀለለችበት በ2014 ተጀመረ የሚሉት፣ ብዙዎች ሩሲያ «ዩክሬንን ከወታደራዊ ሥጋትና ከናዚዎች ለማፅዳት» ባለችዉ ወታደራዊ ዘመቻ» ዩክሬንን ከወረረችበት ከየካቲት 24፣ 2022 ጀምሮ ዩክሬን ዉስጥ በተደረገዉ ጦርነት 12 ሺሕ ሰላማዊ ሰዉ ተገድሏል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠር የሩሲያና የዩክሬን ወታደሮች ሞተዋል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ተፈናቅሏል ወይም ተሰድዷል።በአብዛኛዉ የዩክሬን የመሠረተ ልማት አዉታሮች ወድመዋል።
ለፕሬዝደንት ቮልዶሚር ዜለንስኪ መንግስት ሙሉ ድጋፍ የሚሰጡት የአዉሮጳ፣ የዩናይትድ ስቴትስና ከጃፓን እስከ አዉስትሬሊያ የሚገኙ ተባባሪዎቻቸዉ ሐገራት መንግስታት ሩሲያን በተከታታይ ማዕቀብ ቀጥተዋል።ለዩክሬን በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከስክሰዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ባለፈዉ ጥቅምት ባወጣዉ ዘገባ እንዳስታወቀዉ አንዲት አሜሪካ ብቻ 67 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጦር መሳሪያና ለዩክሬን አስታጥቃለች።የአዉሮጳ ሐገራት በተናጥልና በአዉሮጳ ሕብረት በኩል ለዩክሬን የሰጡት ጦር መሳሪያ፣ ወታደራዊ ሥልጠናና የሥልለላ ድጋፍ ከ50 ቢሊዮን ዶላር ይበልጣል ይባላል።
«ሶስተኛዉ የዓለም ጦርነት እየተቃረበ ነዉ»-ትራምፕ
ዩናይትድ ስቴትስ፣ አዉሮጳና ተባባሪዎቻቸዉ ከዩክሬን ጎን እንደቆሙ ሁሉ ቤሎ ሩስ ከሩሲያ ጎን ቆማለች።ኢራን ለሩሲያ መጠነኛም ቢሆን ወታደራዊ ድጋፍ ትሰጣለች።በቅርቡ ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጎን ሆኖ ዩክሬንን የሚወጋ ጦር አዝምታለች።በዚሕም ምክንያት ሲጀመር የሩሲያና የዩክሬን፣ በመሐሉ የምዕራባዉያንና የሩሲያ የመሰለዉ ጦርነት፣ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈዉ መስከረም እንዳሉት አሁን ሶስተኛዉ የዓለም ጦርነት መልክና ባሕሪ እየያዘ ነዉ።አስቆመዋለሁ አሉ-ሰዉዬዉ።
«ሶስተኛዉ የዓለም ጦርነትን አስቀራለሁ።ለሶስተኛዉ የዓለም ጦርነት ተቃርበናል።ባይደንና ካማላ በዩክሬኑ ጦርነት ተዘፍቀዋል።መዉጣት አልቻሉም።መዉጣት አልቻሉም።አይቼዋለሁ ሁልጊዜ። እናሸንፋለን። እናሸንፋለን ይላል።ሶስት ዓመት ሆነዉ።ዜለንስኪ ዩናይትድ ስቴትስ በመጣ ቁጥር በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ይዞ ይሄዳል።እንደሚመስለኝ ጥሩ አሻሻጭ ነዉ።»
የቀድሞዉ የዶናልድ ትራምፕ የቅርብ አማካሪ ብርያን ላንዝ በቅርቡ እንዳሉት የዩክሬን ሕዝብ የሩሲያን ወረራ ለማክሸፍ ያደረገዉን ተጋድሎ አሜሪካ እንደሐገር ትደግፋለች።እሳቸዉ በግል ያደንቃሉ።ግን ቀጠሉ የትራምፕ አማካሪ የክርሚያ ጉዳይ የአሜሪካ ጉዳይ አይደለም እያሉ።
«አሁን ዜለንስኪ ይሕን ጦርነት የምናቆመዉ፣ ሰላም የሚሰፍነዉም ክሪሚያን ሥናስመልስ ብቻ ነዉ ይላሉ።ለዜለንስኪ ዜና አለን።ክሪሚያ ሔዳለች።ትኩረትዎ ክርሚያን ማስመለስ ከሆነ፣ የአሜሪካ ወታደሮች ክርሚያን ለማስመለስ እንዲዋጉ ከሆነ ብቻዎን ነዎት።ይሕ የአሜሪካ ትኩረት አይደለም።የአሜሪካ ትኩረት ሰላም ማስፈን እና ግድያዉን ማቆም ነዉ።»
ዋሽግተንና ብራስልስ ላይ እየተከካ ሥለሚሰለቀዉ የዶናልድ ትራምፕ የወደፊት መርሕ ከሞስኮ እስካሁን የተሰጠዉ መልስ «አድረን እንየዉ» ዓይነት ነዉ።ኪቭ ግን ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምትሰጠዉን ድጋፍ የትራምፕ መስተዳድር እንዳያቋርጥ እየጎተጎተች ነዉ።
የአትላንቲክ ማዶ-ለማዶ መንግስታት ወዳጅነት
የዩናይትድ ስቴትሱ ቱጃር አክራሪ ፖለቲከኛ የሐገራቸዉን ወዳጅ ወይም ጠላቶች፣ የረዳቶቻቸዉን ምክር መቀበል-አለመቀበላቸዉ ወይም በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት የገቡትን ቃል ገቢር ማድረግ-አለ ማድረጋቸዉ በግልፅ የሚታወቀዉ ከጥር 20 በኋላ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጆች የአዉሮጶች ግን ለዩክሬን የሚሰጡትን ድጋፍ አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ከትራምፕ ድል በኋላም እያረጋገጡ ነዉ።
ባለፈዉ ሳምንት አርብ ቡዳፔስት-ሐንጋሪ የተሰበሰቡት የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት መሪዎች ግን እስካሁን በያዙት አቋም እንደሚፀኑ አስታዉቀዋል።የሕብረቱ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሻርልስ ሚሼል እንዳሉት አዉሮጶች የአሜሪካንን ድጋፍ አገኙም አጡ በዕቅድና አቋማቸዉ ይቀጥላሉ።
«በደፈናዉ አዉሮጳን የሕዝባችንን፣ የንግድ ድርጅቶቻችንን፣ የቤተሰቦቻችንን ሕጋዊ ጥቅም፣ለማስከበር ለመስከበር ጠንካራ፣ ፅኑ፣ተፅዕኖ እንደሆንን መቀጠል እንፈልጋለን።ዕቅዳችን፣ ሥልታችን እነዚሕ ናቸዉ።ከዩናይትድ ስቴትስ ጋርም ሆነ ያለ ዩናይትድ ስቴትስ እነዚሕ አላማዎቻችንን ከግብ ማድረስ ዋና ትኩረታችን ነዉ።»
የዩናይትድ ስቴትስን ፍላጎትና ጥቅም ብቻ እንደሚያስቀድሙ ደጋግመዉ የተናገሩት በመጀመሪያ ዘመነ ሥልጣናቸዉም በተግባር ያሳዩት ዶናልድ ትራምፕ፣ አዉሮጶች ባለፈዉ ሳምንት ላንፀባረቁት አቋም እስካሁን በግልፅ የሰጡት መልስ የለም።ይሁንና ትናንት ከጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ጋር በስልክ መነጋገራቸዉ ተዘግቧል።ሁለቱ መሪዎች «አዉሮጳ ዉስጥ ሰላም ለማስፈን» በጋራ እንደሚጥሩ አንዳቸዉ ለሌላቸዉ ቃል መግባታቸዉም ተዘግቧል።
የአዉሮጳ ዳግም ክፍፍል
ጅምሩ ላይ የዩክሬንና የሩሲያ የመሰለዉ ጦርነት ትራምፕ እንዳሉት የሶስተኛዉ የዓለም ጦርነት ምልክት ሊሆን ላይሆንምም ይችላል።ጦርነቱ ምዕራባዉያን መንግስታትና ሩሲያን ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን በከፋ ደረጃ ማፋጠጡ ግን ሐቅ ነዉ።
የዛሬ 35 ዓመት የበርሊን ግንብ ሲደረሰመስ ብዙ የተነገረለት የግጭት፣ፍጥጫ፣ ክፍፍል ፍፃሜ ዘመንም በግልፅ ካበቃ 3ኛ ዓመቱን አገባድዷል።
ኑክሌር የታጠቀዉ ኃያል ዓለም ዳግም በጦር ኃይል መፈላለጉም ከዓለም የተሰወረ አይደለም።ከቤሉ ሩስና ከዩክሬን ጋር ድንበር የምትጋራዉ፣ በርካታ የአሜሪካ ጦር የሠፈረባት ፖላንድም ስደተኞች እንዳይገቡ በሚል ሰበብ ከቤሎ ሩስ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር በግንብ እያሳጠረች ነዉ።
የበርሊንን ግንብ ያስገነቡት ኮሚንስቶች ነበሩ።የፖላንድንስ? ብቻ አንድነቷ ደምቆ የተዘመራላት አዉሮጳ በርግጥ ዳግም በግንብ አጥር ለሁለት እየተገመሰች፣ ጦርነትም ግራ ቀኝ እየፈረቀቃት ነዉ።ቸር ያሰማን።
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ