1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የዓለም ፖለቲካዊ ጉዞ ግራ ወይስ ቀኝ ዘመም?

ሰኞ፣ ሐምሌ 1 2016

ጆ ባይደን 35 ዓመታት በሴናተርነት፣ 8 ዓመት በምክትል ፕሬዝደንትነት፣ አራት ዓመት በፕሬዝደንትነት እየሰሩ ነዉ።47 ዓመት።ፈጣሪ ረጅም ዕድሜ ከጤና፣ ከሕዝብ ድጋፍና ስልጣን ጋር ሥለሰጣቸዉ አመስግነዉት ይሆን-ይሆናል፣ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት ግን ገና ፈጣሪን እየጠበቁ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4i1mW
ባለፈዉ ሐሙስ በተደረገዉ የብሪታንያ ምርጫ ኪር ስታርመር የሚመሩት ሌበር ፓርቲ በከፍተኛ ድምፅ አሸንፏል
ድልን በከንፈር፣ብሪታንያ ዉስጥ ባለፈዉ ሳምንት ሐሙስ በተደረገዉ ምርጫ ያሸነፈዉ የሌበር ፓርቲ መሪ ኪር ስታርመር ከባለቤታቸዉ ጋር ምስል JUSTIN TALLIS/AFP/Getty Images

ማሕደረ ዜና፣ የዓለም ፖለቲካዊ ጉዞ ግራ ወይስ ቀኝ ዘመም?

 

ከአፍሪቃ፣ የደቡብ አፍሪቃ የ30 ዘመን ገዢ ፓርቲ የለመደዉን የምርጫ ድል አጥቶ ከተቀናቃኞቹ ጋር ለመጣመር ሲገደድ፣ ርዋንዳ ብዙዎች እንደገመቱት የ30 ዓመት ገዢያዋን ዘመነ-ሥልጣን በሕዝብ ድምፅ ለማራዘም እየተዘጋጀች ነዉ።እስያ፣ ከዓለም በቁጥር አንደኛዉ የሕንድ ሕዝብ የ20 የዓመት ገዢዉን ፈቅዶ የሒንዱ አክራሪዎች በቀየሱለት ፅንፈኛ የፖለቲካ ቦይ መፍሰስን መርጧል።የኢራን ሕዝብ ግን ወግ አጥባቂዎችን እንቢኝ ብሎ ከለዘብተኞች ጎን መቆሙን አረጋግጧል።አዉሮጳ በተለይ ብሪታንያና ፈረሳይ ዉስጥ ባጭር ጊዜ ልዩነት ከቀኝ ፅንፈኞች ሥጋት እፎይ ብላ ወደ ግራና መሐል አዘንብላለች።አሜሪካኖችስ? የዓለም ሐብታም፣ ጉልበኛዋ ሐገር ወደ ግራም ወደ ቀኝም ብትል ከአዛዉንቶች በስተቀር ጎልማሳና ወጣት መሪ አላዘጋጀችም። የከፋዉ ደግሞ አንዱ ከክስ ጋጋታ፣ ሌለኛዉ ከእርጅና ጋር ትግል መግጠማቸዉ ነዉ። 

ዓለም የጦርነት፣ የግጭትና ምርጫ ፍርርቅ መድረክ

ዓለም መሪዎችዋ አመኑም ካዱ፣ ተራዉ ሕዝቧ ወደደም ጠላ ጦርነት ላይ ናት።ከጥቁር ባሕር ጥግ ዩክሬን እስከ ታላቁ ሐይቅ ጠረፍ ኮንጎ፣ ከሜድትራኒያን ባሕር ግርጌ ጋዛ፣ እስከ ቀይ ባሕር ጠርዝ ሱዳን፣ከአደን ባሕረ ሰላጤ መድረሻ የመን፣ እስከ ሔርሞን ተራሮች ሶሪያ፣ ከራስ ደጀን ግርጌ-ኢትዮጵያ እስከ ናጎርኖ ካራባሕ ግራ ቀኝ፣ እስከ ሜድትራኒያን ምሥራቅ ጠረፍ ሊባኖስ ሠላም የለም። በየሥፍራዉ መቶ ሺዎችን በሚያረግፈዉ፣ መቶ ሚሊዮኖችን በሚያሰድድ፣ በሚያፈናቅለዉ ጦርነት፣ ግጭትና ዉዝግብ የዓለም ኃያል፣ ሐብታም መንግስታት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ አይሳተፉም ማለትም ቅጥፈት ነዉ።

ሰሞኑን አዉሮጶች የጦርነት፣ ግጭት፣ እልቂቱን ጭፍግ እዉነት በእግር ኳስ ግጥሚያ ድል-ሽንፈት ቱማታ ጀቡነዉ በምርጫ ዉጤት ዉድቀት-ፌስታ እየቀባቡት ነዉ።ከአዉሮጶች ጥቂት ቀደም ብሎ «የዓለም ትልቅ ዴሞክራሲ» የምትባለዉ ሕንድ ባደረገችዉ ምርጫ ከ2014 (እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር) ጀምሮ የመሯትን የሒንዱ ብሔረተኞችን  አክራሪ ፖለቲከኞች ሙጥኝ እንዳለች ለመቀጠል ወስናለች።
የአፍሪቃዋ ሐብታም፣ ጠንካራ ሐገር ደቡብ አፍሪቃ ደግሞ የ30 ዘመን ገዢ ፓርቲዋን የለመደዉን ድል ነፍጋ ከተቃዋሚዎቹ ጋር እንዲጣመር አስገድዳዋለች።ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ በታልቅ ድል፣ ፕሬዝደንት ሲርየል ራማፎዛ በአነስተኛ ዉጤት የተረከቡትን አዳዲስ ዘመነ-ሥልጣን ሲያመቻቹ ሕንድን በቀጥታ፣ ደቡብ አፍሪቃን በቀላጤ ቅኝ የገዛችዉ ብሪታንያ የ14 ዓመታት የፖለቲካ ጉዞዋን ቀይራለች።

የግራ ዘመም ፓርቲዎች ድል 

የተቃዋሚነት ወንበር ሲያሞቅ 14 ዓመታት ያስቆጠረዉ የብሪታንያዉ ግራ ዘመም ፓርቲ ሌበር ወይም ሠራተኛ ፓርቲ ታላቅ የምርጫ ድል ማስመዝገቡ የተረጋገጠዉ፣ አዉሮጳ ወደ ቀኝ መስፈንጠሯ ብዙዎችን ባሰጋበት፣ ፈረንሳይና ሩዋንዳ ለምርጫ ሲዘጋጁ፣ የዩናይትድ ስቴስ መሪ ዕድሜና ጤና አሜሪካኖችን በሚያነጋግረበት፣ ኢራኖች ድምፅ በሰጡበት ዕለት ነዉ።ባለፈዉ አርብ።የአሶስየትድ ፕሬስ ዘጋቢ ዴንካ ኪርካ የሠራተኛዉን ፓርቲ ድል ካበሰሩት አንዷ ናት። 
                      
«የብሪታንያ ግራ ዘመም ፓርቲ ሌበር ታላቅ ድል አስመዝግቧል።ብሪታንያን ለ14 ዓመታት የገዛዉ ወግ አጥባቂ ፓርቲ የሕዝብ አገልግሎቶችን ባለማሟላቱ፣ ግብር በመጨመሩ፣ የኑሮ ዉድነት ቀዉስን በማባባሱና የሐገር ዉስጥ በጀትን በመቀነሱ መራጩ ሕዝብ ድምፅ ነፍጎታል።የሌበር ፓርቲ መሪ ኪር ስታርመር አርብ ቀን ጠቅላይ ምንስትርነቱን ሥልጣን ተረክበራል።»
አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር መጀመሪያ ከወሰዷቸዉ እርምጃዎች አንዱብሪታንያ የገቡ የዉጪ ሥደተኞች ወደ ሩዋንዳ እንዲጋዙ የሚደነግገዉን የወግ አጥባቂዉን ደንብ መሻር ነዉ።ኪር ስታርመር እንዳሉት ስደተኛን ወደ ሩዋንዳ የመላኩ ርምጃ ሞቶ ተቀብሯል።ኢራን ዉስጥ አርብ በተደረገዉ የመለያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ለዘብተኛዉ ፖለቲከኛ መስዑድ ፔዜሽክያን አሸንፈዋል።
የ71 ዓመቱ ሐኪምና የምክር ቤት እንደራሴ ከምዕራባዉያን ጋር ለመደራደር፣ ኢራን ላይ የተጣለዉን ማዕቀብ ለማስነሳት፣ ምጣኔ ሐብቷን ለማሻሻልም ቃል ገብተዋል።ግራ ዘመም፣ ለዘብተኛ ፖለቲከኞች በተለይ ለንደን ላይ የተቀዳጁት ድል የእንግሊዝ ቻናልን ተሻግሮ ፓሪስ ላይም ተደግሟል።ፈረንሳይ ዉስጥ ከሳምንት በፊት ተደርጎ በነበረዉ የምክር ቤት አባላት የመጀመሪያ ዙር ምርጫ RN በሚል የፈረንሳይኛ ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ ቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ በርካታ ድምፅ ማግኝቱ ዓለምን በጥቂቱ፣ አዉሮጶችን በጣም፣ ፈረንሳዮችን በእጅጉ አስግቶ ነበር።በትናንቱ የመለያ ምርጫ ግን የሶሻሊስቶች ቅንጅት የተባለዉ የግራ ዘመም ፓርቲዎች ጥምረት አሸንፏል።

ፔዜሽክያን ለዘብተኛ ፖለቲከኛ ናቸዉ።ከምዕራባዉያን ጋር ለመደራደርና የኢራንን ኤኮኖሚ ለማሻሻል ቃል ገብተዋል
ባለፈዉ አርብ ኢራን ዉስጥ በተደረገዉ የመለያ ዙር ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ያሸነፉት መስዑድ ፔዜሽክያን (እጃቸዉን ያወጡት)ምስል Vahid Salemi/AP/picture alliance

በቅርቡ አርጀንቲና፣ ሕንድና አዉሮጳ ዉስጥ በተደረጉ ምርጫዎች የተገኙ ዉጤቶች ዓለም ወደ ቀኝ ፅንፍ እያመራች ነዉ የሚል ሥጋት አሳድሮ ነበር።የሰሞኑ የምርጫ ዉጤት ግን ዓለም ከሥጋት ተላቅቃ ወደ ግራ ወይም መሐል ግራ እያዘነበለች ነዉ ያሰኝ ይዟል።የዋሽግተ ዲሲ ወኪላችን አበበ ፈለቀም ይስማማል።
«በገለፅካቸዉ ማሳያዎች መሠረት ዓለም ወደ ግራ እየሔደት ነዉ።ይኼ ምናልባት ሐርድላይነር እሚባሉትን ዓመለካከቶች እስካሁን ተሞክረዉ አልሰሩም፣ ወይም ጥሩ አይደሉም የሚል ድምዳሜ ላይ ነዉ የደረሰዉ።እነዚሕ ለዉጦች ምናልባት በዓለም አቀፍ ግንኙነቱ----»

«ከሐሌ ኩሉ ፈጣሪ ይንገረኝ» ጆ ባይደን

 

ዩናይትድ ስቴትስም ለምርጫ እየተዘጋጀች ነዉ።በመጪዉ ሕዳር ሊደረግ በታቀደዉ ምርጫ በተለይ ለፕሬዝደትነት የሚደረገዉ ምርጫ በዚያች «የዴሞክራሲ ቀዲል» በምትባለዉ ሐገር ዘመናይ ታሪክ ልዩ ዓይነት ነዉ።እስካሁን ባለዉ ሒደት ወግ አጥባቂዉ የሪፐብሊካን ፓርቲ ለሶስት ተከታታይ የምርጫ ዘመናት ባንድ ሰዉ ሲወከል ያሁኑ የመጀመሪያዉ ይሆናል።በዶናልድ ትራም።78 አመታቸዉ ነዉ።በስልጣን ላይ ያሉት የዴሞክራቱ ፓርቲ ዕጩ ጆ ባይደን ናቸዉ።81 ዓመታቸዉ።ባይደን ካሸነፉ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዉ አዛዉንት ፕሬዝደንት ይሆናሉ።የሽማግሌዎች ፉክክር። 

ፈራንስይ ዉስጥ ባለፈዉዕሁድ በተደረገዉ የመለያ የምክር ቤት አባላት ምርጫ ያሸነፈዉ የግራ ፓርቲዎች ጥምረት አባላት ከድል በከፊል
ፈራንስይ ዉስጥ ባለፈዉዕሁድ በተደረገዉ የመለያ የምክር ቤት አባላት ምርጫ ያሸነፈዉ የግራ ፓርቲዎች ጥምረት አባላት ከድል በከፊልምስል Lionel Urman/ABACAPRESS/IMAGO

ትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻዉን የሚደርጉት በተደራራቢ ክሶች ፍርድ ቤት ከሚደረግ ሙግት ጋር ነዉ።ባይደን ደግሞ በቅርቡ ከትራምፕ ጋር በቴሌቪዥን ባደረጉት ክርክር የሚያዉቁትን የማይናገሩ፣ የሚናገሩትን የማያዉቁ ሆነዉ መታየታቸዉ የዲሞክራቲኩን ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎችን አስደንጧል።እንደገና አበበ።
«ከክርክሩ ወዲሕ የአሜሪካ ሕዝብም፣ ዴሞክራቶችም ታላቅ ድንጋጤ ላይ ነዉ ያሉት።ድንጋጤዉ ምንድነዉ ነጋሽ ምርጫዉ የፕሬዝደንት ምርጫ ብቻ አይደለም።በዚያዉ ዕለት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ አለ፤የሴናተሮች ምርጫ፣ የአገረ ገዢዎች ምርጫ----» 

በ2020 እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በተደረገዉ የምርጫ ፉክክር የያኔዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባይደንን የሚያንቀላፋዉ (Sleepy) ባይደን ብለዉ መወረፋቸዉ ለትራምፕ ኪሳራ፣ ለባይደን ትርፍ አስገኝቶ ነበር።አሁን ግን ባይደን በክርክር መሐል የመከራከሪያዉን ነጥብ መዘንጋታቸዉ ከሚመሩት ፓርቲ እንደራሴዎች ሳይቀር ተቃዉሞ ገጥሟቸዋል።
የተወሰኑ የምክር ቤት አባላትና የዴሞክራቲኩ ፓርቲ ደጋፊዎች ፕሬዝደንቱ በሌላ ሰዉ እንዲተኩ ግፊት እያደረጉም ነዉ።ሰዉዬዉ ግን «ለፕሬዝ,ደንት ከኔሌላ ብቃት ያለዉ ሰዉ አሜሪካ የላትም» እያሉ ነዉ።

«ፕሬዝደንት ለመሆንም ሆነ ይሕን ፉክክር ለማሸነፍ ከኔ የተሻለ ሰዉ አለ ብዬ አላምንም።» ጆ ባይደን 35 ዓመታት በሴናተርነት፣ 8 ዓመት በምክትል ፕሬዝደንትነት፣ አራት ዓመት በፕሬዝደንትነት እየሰሩ ነዉ።47 ዓመት።ፈጣሪ ረጅም ዕድሜ ከጤና፣ ከሕዝብ ድጋፍና ስልጣን ጋር ሥለሰጣቸዉ አመስግነዉት ይሆን-ይሆናል፣ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት ግን ገና ፈጣሪን እየጠበቁ ነዉ። «ከሐሌ ኩሉ ፈጣሪ፣ «ጆ ከዚሕ ፉክክር ዉጣ» ማለት ከቻለ እወጣለሁ።ከሐሌ ኩሉ ፈጣሪ አልወረደም።»

የዴሞክራቶቹ ፓርቲ አጣብቂኝ፣ የአሜሪካኖች ፈተና

ከ10 ቀናት በፊት በተደረገዉ ክርክር ነጥቦችን ለመዘንጋት ወይም ለመሳታቸዉ ምክንያት ያደረጉት የፈጣሪን ፈቃድ አይደለም።የዕድሜ መግፋት፣የመዘንጋት ሕመም ምልክትንም አይደለም።አንዴ ጉንፋን ሌላ ጊዜ ኮሮና ስለያዘኝ፣ ደግሞ ሌላ ጊዜ ተፎካካሪያቸዉን እየወቀሱ ነዉ።ካመማቸዉ ክርክር ለምን እና እንዴት ገጠሙ? 
አበበ እንደሚለዉ ዴሞክራቶቹ ከክርክሩ በፊት አልመዉ-አስበዉም የነበረዉ ባይንደን ጥንካሬያቸዉን ያስመሰክራሉ ብለዉ ነበር።

«ጥሩ ጥያቄ ነዉ።እንዲያዉም  መጀመሪያ የዴሞክራት ስትራቴጂስቶች፣ የሳቸዉ ደጋፊዎች ሐሳብ ምን ነበረ፣ እኚሕ ሰዉዬ እያረጁ ነዉ።የሚቀጥሉትን 4 ዓመት (ከተመረጡ) አቅም አላቸዉ ወይ የሚለዉ ፍራቻ የነበረ ነዉ።----እና የዴሞክራቶች ሐሳብ ምን ነበር።ጆ ባይደን በዚሕ ክርክር ላይ ይኸንን ጉዳይ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቃ ጠንካራ ሰዉ መሆናቸዉን ያስመሰክራሉ የሚል ነበር።----»

በክርክሩ ወቅት ባደን ያሳዩት ዘገምተኝነት የዩናይትድ ስቴትስን ሕዝብ በተለይም የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎችን አሳስቧል
ከቀኝ ወደ ግራ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንና የሪፐብሊካኑ አጩ ዶናልድ ትራም ሲከራከሩምስል Mike Blake/REUTERS

የወለፊንድ ባረቀ። ባይደን ከዉድድሩ ይዉጡ የሚለዉ ግፊት አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።ይሁንና ምርጫዉ ሊደረግ የቀረዉ ጊዜ አራት ወራት ነዉ።የዴምክራቲኩ ፓርቲ በይፋ ዕጩ የሚፀድቅበት ጉባኤ ደግሞ በሳምንታት ዉስጥ ይደረጋል።
ባይደን በዚሕ አጭር ጊዜ ከዉድድሩ ቢወጡ ወይም እሳቸዉ እንዳሉት ፈጣሪያቸዉ እንዲወጡ ቢነግራቸዉ ሊተኳቸዉ የሚችሉት እንዲት ሴት ናቸዉ።ምክትል ፕሬዝደንት ካሜላ ሐሪስ።ከዉጪ ዘር የሚወለዱት፣ ሴት ወይዘሮ የፓርቲያቸዉን ድጋፍ ያገኙ ይሆን? 
የአንድሪዉ ጃክሰን፣ የጀምስ ቡካነን፣ የዉድሮዉ ዊልሰን፣ የፍራንክሊን ሩዘቬል፣ የጆን ኦፍ ኬኔዲ፣ የቢል ክልተን፣ የባራክ ኦባማ ፓርቲ በርግጥ አጣብቂኝ ዉስጥ ነዉ።አሜሪካም። ቸር ያሰማን።   

ነጋሽ መሐመድ

ፀሐይ ጫኔ