1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ ጥልፍልፍ ቀዉሶች

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2016

ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የአዲስ አበባና የመቀሌ መሪዎች ኃላፊነት እንደሚሰማዉ ፖለቲከኛ ትግራይ፣ አማራ ይሁን ኦሮሚያ ክልሎች የሚያልቀዉን ሰዉ ሕይወት ማደን አይደለም ዉዝግባቸዉን እንኳን ራሳቸዉ ማስወገድ አቅቷቸዉ እንደሚያዉቁና እንደለመዱት የአሜሪካ-አዉሮጳና አፍሪቃን ሽምግልና እየተማጸኑ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4dOwZ
በመግባቢያ ስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ወደብን ለትኮናተራለች፣ ለሶማሊላንድ የሐገረ-መንግስትነት እዉቅና ትሰጣለች
የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ መሪዎች የመግባቢያ ስምምነቱን ባለፈዉ ታሕሳስ ማብቂያ ከተፈራረሙ በኋላምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮጵያ ጥልፍልፍ ቀዉሶች


የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በቅርቡ ናይሮቢ-ኬንያን ሲጎበኙ እንዳሉት አካባቢዉ (ምናልባት የአፍሪቃ ቀንድ)፣ ኢትዮጵያና ኬንያም ብዙ ችግሮች አሉባቸዉ።አላበሉም።ሱዳን እርስበርስ ይዋጋል።ሶማሊያ ከሽብር-ሥርዓተ አልበኝነት ጋር እየተናነቀች፣ ከኢትዮጵያ ጋራ እየተወዛገበች ነዉ። ኤርትራ እንደ ካሮት እያደገች፣ ካጎራባቾቿ እየተናጨች ነዉ።ኢትዮጵያስ ከሌሎቹ አይብስ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
                   

አሐዝና ምግባር-አማራ ክልል 

የአማራ ክልል የተለያዩ ቢሮ ኃላፊዎች ካለፈዉ ሳምንት ጀምረዉ የሰሩትን ምንም ወይም በጣም ትንሽ፣ ያልሰሩትን ብዙ እጅግ በጣም ብዙ እየዘረዘሩ ነዉ።«ኃላፊዎቹ በፀጥታ ችግር» እያሉ በሚያድበሰብሱት ዉጊያና ግጭት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ የጤና ተቋማት አገልግሎት ማቋረጣቸዉ፣ ትምሕርት ቤቶች መዘጋታቸዉን፣ ፕሮጀክቶች መታጠፋቸዉን ወይም አለመሰራታቸዉን እየዘረዘሩ ነዉ።ባለሥልጣናቱ የየቢሯቸዉን ስታትስቲክስ ከመደርደር ባለፍ እንደዘበት «የፀጥታ ችግር» ያሉት ጥፋትና ዉድመት የተጫረበትን ሰበብ-ምክንያት፣ ከነሐሴ ጀምሮ በተቀጣጠለዉ ዉጊያ የሞተ፣ የቆሰለዉን ሰዉ ስንትነትም ሆነ መፍትሔዉን ወይም ብዙ ባለመስራታቸዉ ሊወስዱ ያቀዱትን ርምጃ አልጠቆሙም።የአለቆቻቸዉም አለቃ እንዲሁ።
       
«በአካባቢያችን ብዙ ችግሮች አሉብን።በሁለታችንም ሐገራት በኢትዮጵያም በኬንያም ዉስጥ ብዙ ችግሮች አሉብን።ተጨማሪ ችግር ማከል አንፈልግም።»
በመሰረቱ ያልሰራ ሹም፣ ችግሮችን ያላቃለለ መሪ ቦታዉን ለሌሎች መልቀቅ ግድ ነበረበት።ኢትዮጵያ ዉስጥ ግን ይሕ አይሞከረም።ታስቦም አያዉቅ።«ሹማምንታቱ ችግር» የሚሉት የሕዝብ መከራ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተከመረ ነዉ።ኦሮሚያ ከጉጂ እስከ ገርጂ ጥግ ዛሬም ሰዉ እየተገደለ፣እየቆሰለ፣ እየተፈናቀለባት ነዉ-አምስት ዓመት።

በሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ክፉኛ የተጎዳዉ የአማራ ክልልሕዝብ በጦርነት ማግስት ሌላ ጦርነት ተጭሮበት መከራ ሳይሻገር በመከራ ይዳክራል።የኦሮሞ ወንገላዊ አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት (UOEC) ባልደረባ ፕሮፌሰር አድማሱ ኢተፋ ቱቾ መንግስትን ይማፀናሉ።
    
«ሰዎች ገበያ አይሄዱም፣ወፍጮቤት እንኳ አይሄዱም።ኤሌክትሪክም የለም።በየእለቱ ብዙ ሰዎች ይገደላሉ።እኔ እንደምሳሌ የደንቢ ዶሎዉን ጠቀስኩ እንጂ ግድያዉ በሁሉም አካባቢ ነዉ።በአማራ ክልል ወፍጮ ቤት ሰዎች መሔድ አልቻሉም።ምነዉ መንግስት፣ ሥልጣን ላይ ለዘላለም አይኖርም።ዞር ብሎ መፍትሔ ቢሰጥ ምነዉ።»

በሁለት ዓመቱ ጦርነትና መዘዙ የብዙ ሺሕ ወጣቶችዋን ሕይወት የገበረችዉ ትግራይ አብዛኛ ተፈናቃዮችዋ አሁንም በየመጠለያ ጣቢያዉ እንደሰፈሩ ነዉ።ተፈናቃዮች በዕርዳታ እጦት፣ ገበሬዎች በአዝመራ መሳት ረሐብ በሽታ እየተፈራረቀባቸዉ ነዉ።የፊናርዋ ከተማ ሐኪም ታደሰ መሐሪ ምስክር ናቸዉ።
« የሚበላ የለም።ሰዎች ምግብ ለማግኘትና ህይወታቸዉን ለማዳን ከዚሕ በጣም ወደራቀ አካባቢ ጭምር እየሸሹ ነዉ።እዚሕ አካባቢ ብዙ ሰዎች እየተሰቃዩ፣ እየተራቡ፣ እየሞቱም ነዉ።»
የአዲስ አበባና የመቀሌ መሪዎች ከዓመት ከመንፈቅ ግድም በፊት የተፈራረሙት ስምምነት በተፈለገዉ ፍጥነት ገቢር ላለመሆኑ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ይወቅሳሉ። የኤርትራ ጦርና የአማራ ታጣቂዎች ከትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ አልወጡም መባሉ፣ ተፈናቃዮች ወደየቀያቸዉ አለመመለስና ርዳታ አለማግኘታቸዉ ሁለቱን ወገኖች በተደጋጋሚ እያወዛገበ ነዉ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ በቅርቡ ናይሮቢን ሲጎበኙ የሶማሊያዉ ፕሬዝደንትም ናይሮቢ ነበሩ ግን አልተገናኙም
ከፊት ከግራ ወደቀኝ የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድምስል State House of Kenya/AA/picture alliance

የህወሓት ሠራዊት ትጥቅ አልፈታም

ባለፈዉ የካቲት መጀመሪያ ላይ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸዉ ረዳ እንዳሉት ደግሞ ከፌደራሉ መንግስትና ከተባባሪዎቹ ጋር ሲዋጉ ከነበሩ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች መካከል ከ270 ሺሕ የሚበልጡት እስካሁን ትጥቅ አልፈቱም። ሕወሓት ጠንካራ ኃይሉን እንደያዘ መቀመጡ አንዳዶች እንደሚገምቱት ለአዲስ አበባም ለአስመራም  ማስጋቱ አልቀረም። ይሁንና አቶ ጌታቸዉ እንዳሉት ሠራዊቱ ትጥቅ ያለፈታዉ በህወሐት እንቢተኝነት ሳይሆን በፈደራል መንግስቱ ድክመት ነዉ።
«ከ270 ሺሕ በላይ ሠራዊት አለን።ይሕ ሰራዊት ወደ መደበኛዉ ኑሮዉ እንዲመለስ ከተፈለገ ለዚሕ የሚጠን በጀት ሊኖር ይገባል።ይሕ እስኪሆን በየካምፖች ሆኖ ስንቅ እንዲቀርብለት ፌደራል መንግስቱ ኃላፊነት አለበት።»

የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት ከቆመ ወዲሕ ኦሮሞያና አማራ ክልሎች ዉስጥ ካማፁ ኃይላት ጋር የሚዋጋዉ የፌደራል መንግስቱ የትግራይ ረሐብተኖችና ተፈናቃዮች ስቃይ ሰቆቃ፣ የታጣቂዎቹን አደገኛነትም ሆነ የመሪዎቹን ወቀሳ በቅጡ ማስተናገድ የቻለ አይመስልም።ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የአዲስ አበባና የመቀሌ መሪዎች ኃላፊነት እንደሚሰማዉ ፖለቲከኛ ትግራይ፣ አማራ ይሁን ኦሮሚያ ክልሎች የሚያልቀዉን ሰዉ ሕይወት ማደን አይደለምዉዝግባቸዉን እንኳን ራሳቸዉ ማስወገድ አቅቷቸዉ እንደሚያዉቁና እንደለመዱት የአሜሪካ-አዉሮጳና አፍሪቃን ሽምግልና እየተማጸኑ ነዉ።
የሁለቱ ወገኖች ባለስልጣናት ፕሮቶሪያ ላይ የተፈራረሙትን ሥምምነት ገቢራዊነት ለመግምገም ያሉትን ዝግ ስብሰባ የሚመራዉ የአፍሪቃ ሕብረት፣የሚታዘቡት የአሜሪካና የአዉሮጳ ዲፕሎማቶች ናቸዉ።ዉጤቱ አልታወቀም።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችዉን የመግባቢያ ስምምነት ካልሰረዘች በስተቀር ፕሬዝደንት ሐሰን ከኢትዮጵያ መሪ ጋር እንደማይገኛኑ አስታዉቀዋል
የሶማሊያዉi ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችዉን ስምምነት አጥብቀዉ ይቃወማሉምስል REUTERS

«ኢትዮጵያና ኬንያ ብዙ ችግሮች አሉባቸዉ» እንደ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አባባል።በርግጥ የኬንያ  ችግር ከኢትዮጵያ የሚስተካከል ነዉ?ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸዉ ናይሮቢን የጎበኙበት አንዱ ምክንያት ብዙ ታዛቢዎች እንደጻፉት ኢትዮጵያ በመቸገሯ ነዉ።ጉብኝቱ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መንግስት  ካለፈው ታሕሳስ ማብቂያ ወዲሕ ከሞቃዲሾ መሪዎች ጋር የገጠመዉን  ዉዝግብ ለማስወገድ የኬንያ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ እንዲሸመግሉ ለመጠየቅ ነዉ።

የታዛቢዎቹ አስተያየት አዉነትም ሆነ ሐሰት የኢትዮጵያ መንግስት ቴሌቪዥን ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የተደረገዉን አቀባበልና ግብዢያ ከናይሮቢ በሚያሰራጭበት ሰዓት ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ እዚያዉ ናይሮቢ ዉስጥ ከሶማሊያዉ ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ማሕሙድ ጋር እየተነጋገሩ ነበር።የሶማሊያዉ መሪ የኢትዮጵያዉን ጠቅላይ ሚንስትር በቀጥታ ማነጋገር ባለመፈለጋቸዉ ሁለቱ መሪዎች አልተገናኙም።

የመግባቢያ ስምምነቱ እጣ-ፈንታ

 

የሶማሊያና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት በሸምጋይነቱ ከኬንያ ጋር ጅቡቲም ተጨምራበት በሶማሊያ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ በዓሊ ባል-አድ የተመራ የሶማሊያ የልዕኩን ቡድን ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በድብቅ ተነጋግሯል።
የኢትዮጵያን የልዑካን ቡድን የመሩት የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ የፀጥታ አማካሪ ሪዲዋን አሕመድ እንደሆኑ ምንጮች ተናግረዋል።ግን አልተረጋገጠም።
ሁለት ቀን የቆየዉ ዉይይት ግን ለአዲስ አበባና ለሞቃዲሾ ገዢዎች ጠብ ምክንያት ለሆነዉ ለኢትዮጵያና  ለሶማሊላንድ ስምምነት ሁነኛ መፍትሔ አላገኘም።  ለኢትዮጵያ ወደብ፣ ለሶማሊላንድ የሐገረ-መንግስትነት እዉቅና ያሰጣል የተባለዉ የመግባቢያ ስምምነት እስካሁን ከመግባቢያ ስምምነት አላለፈም።

የኢትዮጵያ መንግስት ከአካባቢዉም ሐገራት ከኃያላኑ መንግስታም ከፍተኛ ጫና ሥለተደረገበት ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገዉን ስምምነት አፍርሶ ከሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ጋር ሌላ ስምምነት ይፈራረማል የሚሉ ወገኖችም አሉ።

ድብቅ ጉብኝት፣ ሚስጥራዊ  ዉሳኔ፤ ምስጥራዊ ስምምነት እና ዝግ ስብሰባ የሚወዱት የአዲስ አበባ መሪዎች እስካሁን በግልፅ የተናገሩት ነገር የለም።የወደብና የሐገረ መንግስት -አዉቅና የመግባቢያ ስምምነቱና ስምነቱ የገጠመዉ ፈተና ግን መመስጠር የሚያዉቁት-የሚወዱት የአዲስ አበባ መሪዎች የፖለቲካ ዲፕሎማሲ ዕዉቀት እጠት ዉጤት መሆኑ ካነጋገረ ተነጋጋሪዎቹ ሐቅ-ሕቅ የሚላቸዉ ናቸዉ።
ኢትዮጵያ በዉስጧም፣ ሶማሊያን ከመሰሉ ከጎረቤቶችዋም  ጋር ሰላም የላትም።በትንሽ ግምት 20 ሚሊዮን ሕዝቧ ተመፅዋች ነዉ።ከዚሕ ችግረኛ ህዝብ አምስት ሚሊዮን የሚሆነዉ ጦርነት፣ግጭትና ጥቃት ከቤት ንብረቱ ያፈናቀለዉ ነዉ።ጦርነቱን ለማስቆም ተዋጊዎች ፈቃደኞች አልሆኑም ቢያንስ እስካሁን።ጦርነትን ለማቆም ተስማማን ያሉትም ወገኖች ዳግም እየተወዛገቡ ዳግም አስታራቂ ሽማግሌ እየፈለጉ ነዉ።

በስምምነቱ ገቢራዊነት ላይ ሁለቱ ወገኖች አሁንም እየተወዛገቡ ነዉ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ከፕሪቶሪያዉ ስምምነት በኋላ የፌደራሉንና የትግራይ ክልል መሪዎችን ሲያነጋግሩምስል Ethiopian Broadcasting Corporation

የኢትዮጵያ ጉዞ 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ቢሮ እንዳለዉ ችግረኛዉን ኢትዮጵያዊ ለመርዳት ለዘንድሮ ብቻ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል።ኢትዮጵያ አቅም የላትም።የችግር ቁልል።መፍትሔ አለዉ ይሆን ፕሮፌሰር አድማሱ እንደ መንፈሳዊ መሪ የቀረን ፈጣሪን መማፀን ብቻ ነዉ ይላሉ።አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸዉ አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች የሚኖረዉ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ በማጣት፣ ሌላዉ በኑሮ ዉድነት፣ በመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ ንረት፣ በመዘዋወር ዋስትና እጦት ሕይወት ኑሮዉን እያማረረ ነዉ።የተከመረዉ ችግር ኢትዮጵያን ወዴት ያጉዛት ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር