ማሕደረ-ዜና የመን ዉጊያና ፀጥታ | ዓለም | DW | 18.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ማሕደረ-ዜና የመን ዉጊያና ፀጥታ

የዛሬ አዉነቷ ግን ሰሜን-ላይ እርስ በርስ፥ ከመሐል፥ የሽብር ፀረ፥ ሽብር፥ ከደቡብ የተገንጣይ አንድነቶች ዉጊያ የሚንጣት፥ ድሕነት ሙስና ቁልቁል የሚደፍቋት መሆኑ ነዉ።የት ያደርሳት ይሆን? ጊዜ ነዉ መላሹ

default

የመን ከጥንት ቅርሶቿ

18 01 10

ጥንት ታታሪዉ የዱር-ባሕር ሐብቷን ሸጦ ለዉጦ-ሲከብር ሲያከብራት፥ሽፍታዉ ዘራፊዎችዋ እንዳቀጨጯት፥ ብልሕ፥ አዋቂ ሠልጥኖ፥ ሥልጣኔ ሲያስረብብባት፥ጦረኛዉ እያስገበረ-ሲገባዛት፥በተረኛ እየተማረከ ሲገዛባት- ዘመነ ዘመናት አስቆጥራለች።የመን።ድሮ-ግን ቅኝ ገዢዎች በከፊል ተቆጣጥረዉ ገዙ-መዘበሯት እንጂ ሌላጋ ያደረጉትን ያህል ሕዝብ አልፈጁ አልጨርሱባትም።ኮሚንስት ካፒታሊስቶች እሁለት ገመሷት እንጂ የቬትናም፥ የኮሪያ፥ የጀርመን አይነት የእልቂጥ፥ ጥፋት ፍጥጫ ታሪክ አልታየባትም።ዛሬም ሰዎስት አይነት ጦርነት ላይ ናት።ዳራዋ መጣቀሻ፥ የሐያላንን ትኩረት የሳበዉ-፥ሳዑዲ ኢራንን ያናከሰዉ የሽብር ፀረ-ሽብር፥የሸማቂ፥የመደበኛ ጦር ዉጊያ ምክንያት እድምታ ትኩረታችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።


ባለፉት አስር አስራ-አምስት አመታት፥ የእርስ በርስ ጦርነት፥ የጎሳዎች ግጭት፥የሽፍቶች ጠለፋ፥ እገታ፥የአሸባሪዎች ጥቃት ተለይቷት አያዉቅም።የአለምን ትኩረት ያልሰባችበት ጊዜም ጥቂት ነዉ።
የመን የኖረ፥ የተማረዉ፥ እዚያዉ የመን አል-ቃኢዳን እደተቀየጠ የሚጠረጠረዉ ናይጄሪያዊ ወጣት ዑመር ፋሩቅ አብዱል ሙጠለብ ታሕሳስ ሃያ አምስት 2009 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎርሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የዩናይትድ ስቴትስን የመንገደኞች አዉሮፕላን ለማጋየት ከሞከረ ወዲሕ ደግሞ የሐያሉን አለም ልዩ ክትትል አትርፋለች።የመን።

«የመን ልክ እንደ ሶማሊያ የምናተኩርባት ብቻ ሳይትሆን ይበልጥ የምናደርግባት ሐገር ሆናለች።ይሕ የፀረ-ሽብር ትብብራችንን የምናጠናክርበት፥የሥለላዉን ጥረት ለማጠናከር አበክረን መስራት ማለት ነዉ»
የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ጎርደን ብራዉን።ጥር-ሰወስት።2010።ከብራዉን በፊት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ተመሳሳይ መልዕክት ተሰምቶ ነበር።በሳልስቱ ደግሞ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን በሌላ ቋንቋ ደገሙት።

«የመን ዉስጥ በርካታ ግጭቶች ነበሩ።ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሳታፊዎቹ ቁጥር እየጨመረ፥ ግጭቶቹም አሁን እየተባባሱ ነዉ።ለየመን መንግሥት የምንሰጠዉ ድጋፍና ርዳታ የምንጠብቀዉና የምናስቀምጠዉ መመዘኛ እንዳለ አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ለየመን ግፅ የሚያደርግበት ወቅት ነዉ።»

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ አሰለሱ።
«አሸባሪዎች መመሸጊያ እንዳያገኙ ለማረጋጋጥ ፖለቲካዊ ዉይይት እንደሚያስፈል፥ የሐሳብ ልዉዉጥ እንደሚያስፈልግ እንረዳለን።ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚያፈልግ፥ እና ወታደራዊ እርምጃ ብቻዉን መፍትሔ እንዳልሆነ እናምናለን።»
ጥር-አስራ አንድ።
ከሁለት ሺሕ ሁለት መቶ አመተ-ዓለም እስከ ስድስተኛ መቶ ክፍለ ዘመን ሳባዎች፥ አዉሳኒዎች፥ ሚኔያኖች፥ ቃጣባኒያኖች፥ሐድራሞቶች ሒምያሬቶች የተሻሙ፥ የተፈራረቁባት ሮሞች በጣሙን አጉስቶስ የከጀሏት-የዱር ቅመም፥ ሰንደል፥ ሽቷዋን፥ የከርሰ ምድር ጌጥ፥ የስልጣኔ ስጋጃ፥ የባሕር ሐብቷን ለመመዝበር ነበር።

ከስድስተኛዉ መቶ ክፍል ዘመን እስከ እስከ ሃያኛዉ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ የሙስሊም፥ የቱርክ፥የዛይዲ፥ የኦማን፥ የግብፅ ኸሊፎች፥ የብሪታንያ ቅኝ ገዢዎች እሁለት፥ እሰወስት እየገመሱ ለመግዛት የተሽቀዳደሙባት ቅሪት ስልጣኔ፥ ሐብት፥ የ

Karte Jemen Drei Bundesbürger im Jemen verschleppt deutsch

ሥልታዊ ናት

ባሕር በሯ እያጓጓቸዉ ነበር።

ዛሬ በርግጥ ያጣች የነጣች ደሐ ናት።ግን ከአለም ትልቁ የነዳጅ ዘይት የሚዛቅባቸዉ ጉርጓዶችን፥ የእስልምና ትልቁን ቅዱስ ስፍራ የያዘችዉን ስዑዲ አረቢያን ትዋሰናለች።ከፍተኛዉ የአለም የሸቀጥ የሚዘዋወርባቸዉን ቀይ ባሕርን፥ የአረቢያ ባሕርን፥ የአደን ባሕረ ሰላጤን ትጋራለች። ዛሬም ሥልታዊ ነች።ለአለም ጠቃሚ።

ጉዳትቷ ደግሞ ቻተም ሐዉስ የተሰኘዉ የብሪታንያ ጥናት ተቋም ባልደረባና ጋዜጠኛ ጂኒ ሒል እንደሚሉት የሷ ብቻ አይሆንም።
«አደጋዉ የመን ዉስጥ የከፋ አለመረጋጋት ከተፈጠረ በየመን ብቻ አይገደብም።በአረቢያ ልሳነ-ምድር ያሉ ጎረቤቶችን በሙሉ የሚነካ ነዉ-የሚሆን።ከዚሕም በተጨማሪ በአደን ባሕረ ሠላጤ የሚደረገዉን የመርከብ ጉዞ ሊያዉከዉ ይችላል።ከአደን ባሕረ ሠላጤ የባሕር ድንበር ለሚጋሩ የአፍሪቃ ሐገራትም የሚያሰጋ ነዉ።»

ከ1978 ጀምሮ መጀመሪያ የሰሜን የመን ኋላ የተዋሐደችዉ የመን፥ በቅርቡ ደግሞ በሕዝብ የተመረጡ እየተባሉ የየመንን የሚገዙት አንድ ሰዉ ናቸዉ።ፕሬዝዳት አሊ አብደላሕ ሳላሕ።

የዩናይትድ ስቴትስና የብሪታንያ የመን ዉስጥ የሸመቁ አሸባሪዎዎችን ለማስወገድ የአሊ አብደላሕ ሳላሕ መንግሥት የገጠመዉን ዉጊያ እንደሚደግፉ በግልፅ አስታዉቀዋል።በምዕራቦች ድጋፍ የተጃገ ነዉ የመን ጦር በአል-ቃኢዳ አባላት ላይ ድል መቀዳጀቱን ባለፈዉ ሳምንት ማቂያ ሲያዉጅ፥ ከአንድ መቶ ሐምሳ የሚበልጡ የሐይማኖት መሪዎች ደግሞ የዉጪ ሐይል የመመንን ከረገጠ ጂሐድ እንደሚያዉጁ አስጠንቅቀዋል።ማስጠንቀቂያዉ፥-ሂል እንደሚሉት እንደዘበት የሚታይ አይሆ

Jemen Präsident Ali Abdallah Saleh

የ32 ዓመት ገዢዋ

ንም።

«የመን ዉስጥ ጎሳዎች ጠንካሮች ናቸዉ።የሐይማኖት መሪዎችም ጠንካሮች ናቸዉ።የየመንን አቀማመጥ ብትመለከት ይሕ በጣም ወሳኝ ሚና አለዉ።የመን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በጣም ረጅም ድንበር ትጋራለች።የመን የምትገኘዉ ከትልቁ የሙስሊሞች ቅዱስ ሥፍራ መካ የተወሰነ ማይል ርቀት ላይ ነዉ።ወደ ኋላ መለስ ብለን አል-ቃዲ የተመሠረተበትን ምክንያት ብንመለከት፥ የአሜሪካ ወታደሮች በአረቢያ ልሳነ-ምድር መስፈራቸዉ ያስከተለዉ ቅሬታ ዋናዉ ነበር።የመኖች እንደ አረብ፥ እንደ ሙስሊምና እንደ አረቢያ ልሳነ ምድር ነዋሪዎች ጠንካራ መለያ አላቸዉ።እንደሚመስለኝ፥ የአሜሪካ ወታደሮች የመን ምድር እንዲሰፍሩ ከተወሰና እነዚሕ የመን ዉስጥ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ዉጥረት የሚያስከትሉ ፈተና ይሆናሉ።»

ፕሬዝዳት አሊ አብደላ ሳላሕ ያቺን ሐገር ለሰላሳ ሁለት አመት ቢገዙም የማዕከላዊ መንግሥታቸዉን መዋቅር በመላዉ ሐገሪቱ መዘርጋት አልቻሉም።ወይም አልፈለጉም።ከአራት መቶ የሚበልጡ የጎሳ መሪዎች አሉ።ሕዝቡ በየአካባቢዉ፥ በየቀበሌዉ የሚተዳደረዉ በማዕከላዊዉ መንግሥት ሳይሆን በየጎሳ ወይም በየሐይማኖት ተጠሪዎች ነዉ።
«የሕግ የበላይነት በመላዉ ሐገሪቱ አልተዘረጋም።ሕዝቡ ሕይወቱን የሚመራዉና የሚተዳደረዉ በየአካባቢዉ ባሉት በጎሳና በማሕበራዊ የፍትሕ ተቋማት አማካይነት ነዉ።አል-ቃኢዳ የመን ዉስጥ ያንሰራራዉ ግን በሁለት ሺሕ ስድስት በአሸባሪነት የሚጠረጠሩ ከሃያ-የሚበልጡ እስረኞች ከርዕሠ-ከተማይቱ እስርቤት ካመለጡ በሕዋላ ነዉ።

የጥንት ሐብት፥ ሥልጣኔዋ፥ የአሁን ሥልታዊ ጠቀሜታዋ ለሐገሬዉ ሕዝብ በትካዜ ከመቆዘሚያነት ባለፍ የተከረዉ የለም።ድሕነት፥የፍትሕ እጦት፥ የጎሳ ትምክሕት ሙስና የሚያላጋዉ ወጣት አል-ቃኢዳን በመሳሰሉ አሸባሪ ተቋማት ርዕዮት የማይማረክበት ምክንያት ማግኘት ከባድ ነዉ።ችግሩ ዉስብስብ ነዉ።መፍትሔዉም ሰፊ-ዘላቂና ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት።እንደገና ጂኒ ሂል።

«አለም አቀፉ ማሕበረሰብን የሚጠብቀዉ ፈተና አሁን ያለዉን ሁኔታ ከማባባስ ይልቅ በሚያረጋጋበት ሁኔታ የሚሳተፍበትን ሥልት መለየቱ ይመስለኛል።ማዕከላዊዉ መንግሥት የምጣኔ ሐብት ድቀት አጋጥሞታል።ይሕ የፀጥታዉን ችግር ይበልጥ እያባባሰዉ ነዉ።የመንግሥት ዋና ገቢ የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ነዉ።ነዳጁ ደግሞ እየቀነሰ ነዉ።ገንዘቡም እንዲሁ።አለም አቀፉ ማሕበረሰብ ባጭር ጊዜ በሚያስፈልገዉ ፀጥታን በማረጋጋቱ መስክ በጣም ባስቸኳይ መሳተፍ አለበት።አል-ቃዲዳ የየመን መንግሥትን ከተጋረጡበት ችግሮች አንዱ ብቻ ነዉ።

የሰሜኑ የርስ በርስ ጦርነት አለ።የደቡቡ የተገንጣዮች እንቅስቃሴ አለ።የየመን መንግሥት እነዚሕን ፈተናዎች እንዲቋቋም አለም አቀፉ ማሕበረሰብ መርዳት ከፈለገ የፀረ-ሽብር ዘመቻዉን ብቻ ላጭር ጊዜ መደገፍ በቂ አይደለም።ከዚሕ በተጨማሪ እጅግ ሰፋ ያሉ ጉዳዮችን ማለትም የምጣኔ ሐብቱን ድቀት፥ የፖለቲካዉን ችግር፥ ለማሻሻል የሚረዳ ሰፊ መርሕ መቀየስ ያለበት ይመስለኛል።»

ሐያሉ አለም የፀረ-ሽብር ዘመቻዉን የመን ለማሻገር ከመወሰኑ በፊት የሰሜን የመን የርስ በርስ ጦርነት ከየመን አልፎ ሳዑዲ አረቢያና ኢራንን አነካክቶ ነበር።ዛሬም ቀጥሏል።ሳዑዲ አረቢያ ሸማቂዎቹን መደምሰሷን በቅርቡ አስታዉቃለች። የሺዓ ሐራጥቃን በሚከተሉት የአል ሁቲ ጎሳ ሸማቂዎችና ሱኒዎች በሚበዙበት በማዕከላዊ መንግሥት ጦር መካካል ዉጊያ ከተጀመረ ግን ስድስት አመት አልፎታል።

የኢራንና የምዕራቦች የኑክሌር ዉዝግብ ባየለበት፥የኢራቁ ዉጊያ ቀዝቀዝ ባለበት በዚሕ ወቅት ለስድስት አመት ሞቅ ቀዝቀዝ የሚለዉ ጦርነት የሪያድን ክንድ የጠየቀበት፥ ከቴሕራኖች ጋር መወዛገቢያ የሆነበት ምክንያት በርግጥ ብዙ እያነጋገረ ነዉ።ጂኒ ሒል ገደምደም ያለ መልስ አላቸዉ።

«ቀደም ሲል ኢራኖች በዚሕ ግጭት ጣልቃ ገብተዋል ተብለዉ ሲወቀሱ ነበር።አሁን ግን አሳሳቢዉ ሳዑዲዎች በግጭቱ በቀጥታ መሳተፋቸዉ ነዉ።የሳዑዲዎች መሳተፍ ኢራኖች ተሳትፈዋል የሚለዉን ወቀ

Al-Qaida Al-Kaida Jemen Angriff

የአል-ቃኢዳ ተጠርጣሪ አባላት

ሳ ያኮሰምነዋል።»
------------------------------------------------------------------------------
ሮሞች አረቢያ ፌሊክስ-አስደሳቿ አረቢያ እያሉ ያደንቁ-ያሟጉሷት ነበር።ለሌሎች የገነት፥ ጀነት ተምሳሌት ነበረች።ለአረቦች የአንድ አንድ ሺሕ አንድ ሌሊት ተረት ምድር፥ የእነ አቡነዋስ ገድል አብቃይ ነበረች።ናትም።የዛሬ አዉነቷ ግን ሰሜን-ላይ እርስ በርስ፥ ከመሐል፥ የሽብር ፀረ፥ ሽብር፥ ከደቡብ የተገንጣይ አንድነቶች ዉጊያ የሚንጣት፥ ድሕነት ሙስና ቁልቁል የሚደፍቋት መሆኑ ነዉ።የት ያደርሳት ይሆን? ጊዜ ነዉ መላሹ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Dw,Interv.Ginny Hill
Negash Mohammed
Hirut Melesse

Audios and videos on the topic