ማሌዢያ፥ ቦይንግ አውሮፕላን ሳይከሰከስ እንዳልቀረ ተነገረ | ዓለም | DW | 08.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ማሌዢያ፥ ቦይንግ አውሮፕላን ሳይከሰከስ እንዳልቀረ ተነገረ

239 መንገደኞችን አሳፍሮ ሲበር የነበረ ንብረትነቱ የማሌዢያ የሆነ ቦይንግ 777 የመንገደኞች አውሮፕላን ደብዛው ከጠፋ ከ20 ሠዓታት በኋላም ሊገኝ አልቻለም።

አውሮፕላኑ ከሆቺ ሚን ከተማ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘኝ ባህር ላይ ሳይወድቅ እንዳልቀረ ተነግሯል። አውሮፕላኑ ከኩዋላላምፑር ዓለም አቀፍ ዓየር ማረፊያ አኮብኩቦ ወደ ቤጂንግ ማቅናት ከጀመረ ከጥቂት ሠዓታት በኋላ ነበር ከዓየር በረራ መቆጣጠሪያ ሠራተኞች ጋር የነበረው ግንኙነት የተቋረጠው። የዓለም አቀፍ የበረራ ደኅንነት መስሪያ ቤቶች አውሮፕላኑ የሚገኝበትን ቦታ ለመጠቆም ጥረት እያደረጉ ነው። ይሁንና አውሮፕላኑ መብረር ከጀመረ ከጥቂት ሠዓታት አንስቶ ከራዳር ውጪ መሰወሩን የቻይና ዜና አገልግሎት ሺኑዋ ዘግቧል። ለፍለጋ ከተሰማሩ ጄቶች መካከል የቬትናም የጦር ጄት የመንገደኞች አውሮፕላኑ ግንኙነቱ ተቋርጧል በተባለበት አካባቢ በሁለት ቦታዎች ላይ የፈሰሰ የነዳጅ ዝቃጭ መመልከቱን አስታውቋል። ይህም 239 መንገደኞችን ጭኖ ሲበር የነበረው የማሌዢያ ቦይንግ 777 የመንገደኞች አውሮፕላን ለመከስከሱ የመጀመሪያ ፍንጭ መሆኑ ተዘግቧል። በአውሮፕላኑ ውስጥ 227 መንገደኞች እና 12 የአውሮፕላኑ ሰራተኞች እንደነበሩም ተዘግቧል። ሁለት ጨቅላዎችም ነበሩ።

ሳይከሰከስ እንዳልቀረ በተነገረለት ቦይንግ 777 የማሌዢያ የመንገደኞች ማመላለሻ አውሮፕላን የስም ዝርዝር ላይ ጣልያናዊ ቢገኝም አንድም ጣሊያናዊ በአውሮፕላኑ እንዳልተሳፈረ የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ገለፀ። የተሳፋሪዎችን የስም ዝርዝር በያዘው መዝገብ ላይ ስሙ ሉውጊ ማራልዲ የተባለ የ37 ዓመት ጣልያናዊ እንደሚገኝ ተጠቅሶ ነበር። ሆኖም ኮሪየር ዴላ ሴራ የተሰኘ ጋዜጣ የሉውጊ ማራልዲ ፓስስፖርት ባለፈው ነሐሴ ወር ታይላንድ ውስጥ ሳይሰረቅ አልቀረም ሲል ዘግቧል። በተያያዘ የአውስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በበኩሉ በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ስሙ የተጠቀሰው የአውስትሪያ ዜጋ አውስትሪያ ውስጥ በሠላም እንደሚገኝ አስታውቋል። የሰውዬው ፓስፖርት ተሰርቆ እንደነበረም ሚንስትር መስሪያ ቤቱ ገልጿል። አውሮፕላኑ ውስጥ በርካታ ቻይናውያን፣ አውሮጳውያን እና የሌላ ሃገራት መንገደኞች ተሳፍረው እንደነበር ተዘግቧል። ከእነዚሁ መንገደኞች መካከል 152 የቻይና፣ 38 የማሌዢያ፣ 7 የኢንዶኔዢያ፣ 6 የአውስትራሊያ፣ 5 የህንድ እንዲሁም 3 የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ተሳፋሪዎች መሆናቸው ተጠቅሷል። ቀሪዎች የኢንዶኔዢያ፣ ፈረንሣይ፣ ኒውዚላንድ፣ ካናዳ፣ ዩክሬይን፣ ሩስያ፣ ታይዋን እና ኔዘርላንድ ዜጎች መሆናቸው ይፋ ሆኗል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ