ማሊ እና የጋዎ ከተማ ነዋሪዎች ሥጋት | አፍሪቃ | DW | 13.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ማሊ እና የጋዎ ከተማ ነዋሪዎች ሥጋት

በማሊ ያማፅያኑ የሙዣው ቡድን በትልቋ የሰሜን ማሊ ከተማ ጋዎ ባለፈው እሁድ ጥቃት ከሰነዘረ ወዲህ ከተማይቱ እንደገና አለመረጋጋት ሰፍኖበታል። እርግጥ፣ የማሊ እና የፈረንሣይ ጦር ኃይላት ከተማይቱን እንደተቆጣጠሩ ቢገኙም፡

የፈረንሣይ ጦር በማሊ በጀመረው ዘመቻ የጋዎን ከተማ ከፅንፈኛ ሙሥሊም ቡድኖች ባስለቀቀበት ጊዜ የታየው የፈንጠዝያ ስሜት አሁን በሥጋት ተተክቶዋል።

የሙዣው ቡድን ዓማፅያን ሰሞኑን ከማሊ ጦር ኃይል ጋ ብዙ ሰዓታት የፈጀ የተኩስ ልውውጥ እንዳካሄዱ የማሊ ጦር ኃይል ቃል አቀባይ አስታውቆዋል። ቃል አቀባዩ አክሎ እንዳስረዳው፡ የፈረንሣይ ጦር በሄሊኮፕተር ጥቃት ከሰነዘረ ካለፈው እሁድ ምሽት ወዲህ በኋላ የፈረንሣይ፡ የማሊ እና የቻድ ወታደሮች በሰሜን ማሊ የምትገኘዋን ትልቋን የጋዎ ከተማ ከሙዣው ዓማፅያን ለመከላከል እና ያማፅያኑን ግሥጋሤ ለመግታት በዚያ ተሠማርተዋል። ባንዳንድ የጋዎ ከተማ ሠፈሮች የሙዣዎ ዓማፅያን እንዳሉ ቢሰማም፡ ስለ ጋው ከተማ ጊዚያዊ ሁኔታ ለዶይቸ ቬለ ቃለ ምልልስ የሰጡት የከተማይቱ ከንቲባ ሳዱ ዲያሎ የዜናውን ትክክለኛነት ማረጋገጡ እንዳማይችሉ ገልጸዋል።
« አሸባሪዎቹ በከተማይቱ መኖራቸውን ላውቅም ሆነ ላረረጋግጥ አልችልም። ስለበርካታ አሸባሪዎች አይደለም እየተነጋገርን ያለነው። በከተማይቱ ጥቂቶች ምናልባት አንድ ወይም ሁለት የሚሆኑ ሊኖሩ ይችላሉ። ከዚያ ባለፈ ግን በከተማይቱ መደበኛው ኑሮ ቀጥሎዋል። አሸባሪዎቹን በተመለከተ ሕዝቡ መረጃ ይሰጠናል። »


ዓማፅያኑ ከሰነዘሩት ጥቃት በኋላ ትልቁ የከተማይቱ መደብር ተጨማሪ ጥቃት በመሥጋት ተዘግቶ ነበር። አንዱ የከተማይቱ ነዋሪ እንደገለጸው፡ ከፈረንሣይ ዘመቻ በኋላ ከከተማይቱ የሸሹት ፅንፈኞቹ ሙሥሊሞች እንደገና ተመልሰው ሕዝቡን እንዳያሸብሩ ሠግቶዋል።
« ፈርተናል። ፈርተናል። አድፍጠው ጥቃት እንዳይጥሉብን ሠግተናል። እነዚህ ሰዎች ምናልባት ሊመለሱ ይችሉ ይሆናል።»
የፈረንሣይ፡ የማሊ እና የቻድ ወታደሮች ወታደሮች ሕዝቡን ለማረጋጋት እና አሉ የሚባሉ አሸባሪዎችን ለማደን ጥረት መጀመራቸውን ከንቲባው ሳዱ ዲያሎ አስረድተዋል። ይሁንና፡ ዛሬ ከማሊ በወጡ ዘገባዎች መሠረት፡ የፈረንሣይ ጦር ዓማፅያኑ በከተማይቱ ማዕከል የብዙ ሰው ሕይወት ለማጥፋት በማሰብ ያጠመዱት 600 ኪሎ ፈንጂ የያዘ ቤት ውስጥ የተሰራ ቦምብ ማምከናቸውን ለፈረንሣውያኑ ዜና ወኪል አ ኤፍ ፔ ገልጸዋል። እንደሚታወሰው፡ በአንድ መቆጣጠሪያ ኬላ አንድ አጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ጥሎ አንድ ወታደር ላቆሰለበት ድርጊት ቀደም ሲል የሙዣው ቡድን ኃላፊነቱን ወስዶዋል። የቡድኑ ቃል አቀባይ አቡ ዋሊድ ዛህራዊ ለፈረንሣይ ዜና ወኪል እንዳስታወቁት፡ ፈረንሣይ ባለፈው ጥር ወር በማሊ ዘመቻ እስከጀመረችበት ጊዜ ድረስ ተቆጣጥረዋት የነበረችውን የጋዎን ከተማ መልሰው መቆጣጠር እስከሚቻል ድረስ ውጊያው ይቀጥላል።


ይህ በዚህ እንዳለ፡ በምሕፃሩ አፊስማ በሚል መጠሪያ የሚታወቀውለማሊ ተልዕኮ ድጋፍ የሚሰጠው ዓለም አቀፉ ሠራዊት ወታደሮች ዛሬም ወደዚችው ሀገር መግባታቸውን ቀጥለዋል። የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ፡ በምሕፃሩ የኤኮዋስ ሠራዊትን የወከሉት የቤኒን፡ የኮት ዲቯር እና የሴኔጋል ጦር ኃይላት ሰሞኑን ማሊ ከገቡት መካከል ተቆጥረዋል። በማሊ መከላከያ ሚንስቴር መግለጫ መሠረት፡ እስከተያዘው የየካቲት ወር ማብቂያ ከ 5000 የሚበልጡ ወታደሮች በሀገሩ ይሠማራሉ። ከ 65 እስከ 70 ከመቶ የሚሆነው አሁን በዚያ እንደሚገኝ የአፊሲማ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ያዎ አጁማኒ ገልጸዋል።
ሰሜናዊ ማሊን ተቆጣጥረው የነበሩት ፅንፈኞቹ ያማፅያን ቡድኖች ወደ መዲናይቱ ባማኮ የጀመሩትን ግሥጋሤ ለማስቆም በማሊ ፕሬዚደንት ዲያንኩንዳ ትራውሬ ጥሪ ባለፈው ጥር 11 በዚችው ሀገር የጦር ዘመቻ የጀመረችው ፈረንሣይ የፊታችን መጋቢት ወር ጦሯን ማውጣት ትፈልጋለች። በዚህም የተነሳ፡ የኤኮዋስን ጦር ኃይላት ዕዝ በተመድ ሥር ለማዋል ድርድሩ ተጀምሮዋል። ይሁን እንጂ፡ የዓለሙ መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ ያን ኤሊያሰን እንደጠቀሱት፡ የማሊ መንግሥት የተመድን ሰላም አስጠባቂ ሠራዊት ወደ ሀገሩ ለማስገባት እያመነታ ነው።
ሂደቶች ይህን በመሰሉበት ባሁኑ ጊዜ በማሊ ጦር ውስጥ የሚታየው ክፍፍል እንዲያበቃ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጥሪ አሰምተዋል። ባንድ በኩል በመፈንቅለ መንግሥት የተወገዱትን ፕሬዚደንት አማዱ ቱማኒ ቱሬን በሌላ ወገን ደግሞ የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች በሚደግፉት የጦር ቡድኖች መካከል ባለፈው ዓርብ ጥር ስምንት: 2013 በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ሁለት ወጣቶች ሲገደሉ ሌሎች በርካቶች ቆስለዋል።

አርያም ተክሌ
ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic