ማሊ፦ በወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ማግስት | አፍሪቃ | DW | 22.08.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ማሊ፦ በወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ማግስት

​​​​​​​ማክሰኞ ማምሻውን የማሊ ወታደራዊ ኹንታዎች መፈንቅለ መንግሥት ካከናወኑ በኋላ በሀገሪቱ ውጥረቱ አይሏል። ይኸው ውጥረት ወደ ሣኅል ቃጣና እንዳይዛመት በርካቶች ሰግተዋል። የአካባቢው ሃገራት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መፈንቅለ-መንግሥቱን በጽኑእ አውግዘዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:07

መፈንቅለ-መንግሥት አድራጊዎቹ ጫና በርትቶባቸዋል

ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ማሊ ከወታደራዊው መፈንቅለ-መንግስት በኋላ ውጥረት ነግሶባታል። ስጋቱ ቀድሞም በቋፍ ላይ በነበረው የሣኅል ቃጣና ሃገራት ውስጥ በፍጥነት እንዳይዛመት አስግቷል። ተቺዎች የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የምጣኔ ሐብታዊ ማኅበር (ECOWAS) በሚፈለግበት ወቅት ፈጣን ምላሽ አይሰጥም በሚል በንግድ ማኅበረሰቡ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ማሊ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 ተከስቶ ከነበረው ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በተለይ ሰሜናዊ ግዛቷ የአክራሪዎች እና አሸባሪዎች መፈንጫ ኾኖ ቆይቷል። ፈጣን ምላሽ ካልተሰጠ የዛሬ ስምንት ዓመት የተከሰተው ሊደገም ይችላል የሚል ፍራቻ ነግሷል። 

ዓለም የማሊ መፈንቅለ-መንግስት እና ተከትሎት ሊመጣ የሚችለውን ጣጣ በአንክሮ እየተከታተለ ነው። መፈንቅለ መንግሥት የለመደች በምትመስለው ማሊ ጦሩ ነሸጥ ሲያደርገው ግልበጣ ማኪያኼዱ የተለመደ ይመስላል። ቤርሊን ውስጥ በሚገኘው ላይብኒትስ ማዕከል የማኅበረሰብ ሳይንስ አጥኚ የኾኑት ናይጀሪያዪው አብዱላዬ ሶናዬ ማክሰኞ ዕለት የተፈጸመው መፈንቅለ-መንግሥት የኾነ ጊዜ መኾኑ የማይቀር እንደነበር ይናገራሉ።

«ላለፉት አምስት ወይንም ስድስት ዓመታት እየኾነ ያለውን ለተመለከተ በዚህም አለ በዚያ ይኼ ሊመጣ እንደሚችል ማስተዋል ይችላል። ምናልባት መቼ ነው የሚኾነው ለሚለው የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነበር።»

ማክሰኞ፤ ነሐሴ 12 ቀን፤ 2012 ዓ.ም የማሊ ወታደራዊ ኹንታ መፈንቅለ-መንግሥት ማከናወኑ ይፋ በኾነ በጥቂት ሰዓታት ነበር የሀገሪቱ ርእሰ-ብሔር ኢብራሒም ቦባካር ኪዬታ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ያስታወቁት። ወዲያውኑም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጨምሮ ወደ እስር ቤት ተወረወሩ።

ዓለም አቀፍ ጫና ከየአቅጣጫው የበረታበት ወታደራዊ ኹንታም በበነጋታው ነበር በሀገሪቱ አዲስ ምርጫ እንደሚካኼድ ቃል የገባው። የመንግሥት ተቃዋሚ እና ተቺዎች አብዮታዊ ርምጃውን አወድሰዋል። የፕሬዚዳንቱ ከስልጣን መወገድ በሣኅል ቃጣና ብርቱ የደኅንነት ስጋት ሊፈጥር እንደሚችል ግን ተንታኞች ያስጠነቅቃሉ። የኮናርድ አዴንአወር የሣኅል ተቋም ኃላፊ ቶማስ ሺለር የተፈራው እንዳይደርስ ስጋታቸውን ገልጠዋል።

«ባማኮ ውስጥ ከወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቱ በኋላ ቀድሞ እንደነበረው አንዳንድ ነገሮች የከፉ ኾነዋል። እጅግ የሚያስፈራው ትልቊ ነጥብ የፖለቲካ አለመረጋጋቱ የመቀጠሉ ጉዳይ ነው። በዚያ ላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፈጽሞ በማይቀበለው መንገድ በሕገ መንግስቱ የተመረጠ መንግስትን ነው እንደቀልድ ያስወገዱት።»

ልል በኾነ መልኩ የተለያዩ ተቃዋሚዎችን ያቀፈው ቅንጅት በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ (M5-RFP) የተሰኘው ንቅናቄ ካለፈው ሰኔ ወር አንስቶ ጸረ መንግሥት መጠነ ሰፊ የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያደራጅ ቆይቷል። ፕሬዚዳንቱ ማክሰኞ ከስልጣናቸው ተወገዱ እንጂ ለዐርብም ሌላ ብርቱ የተቃውሞ ንቅናቄ ይጠብቃቸው ነበር። በሺህዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ተቃዋሚዎች በወታደራዊ ኹንታ የቀድሞው ፕሬዚደንት ከሥልጣን መወገዳቸውን ለመደገፍ ትናንት በመዲናዪቱ ባማኮ አደባባይ ወጥተው ነበር።

ኢብራሒም ቦባካር ኪዬታ ላለፉት ስምንት ዓመታት በሰሜን ማሊ እንዳሻቸው የሚርመሰመሱ አሸባሪዎች እና ዓማጺያንን መቆጣጠር ተስኗቸዋል በሚል የሰላ ትችት ይሰነዘርባቸው ነበር። ኢብራሒም ቦባከር፦ እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በ2018 ዓመት ለአምስት ዓመት የስልጣን ዘመን ዳግም ተመርጠው ነበር። ከአልቃይዳ እንዲሁም ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ከሚናገሩ አክራሪዎች የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ማስቆም ተስኗቸው ቆይተዋል። በእነዚህ ቡድኖች እና በአንዳንድ የሀገሪቱ ማኅበረሰብ መካከል ይከሰቱ በነበሩ ግጭቶች የተነሳ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመአከላዊ ማሊ ለኅልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።

ዓማጺያኑ እንደውም መዲናዪቱ ባማኮ ድረስ ዘልቀውም ብርቱ ጥፋት ሲፈጽሙ የማሊ መንግስት ማስቆም ተስኖት ነበር። ለአብነት ያኽል በ2019 የደረሰው ጥቃት የሚታወስ ነው። ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ የሚጠራው ቡድን ደጋፊ መኾናቸውን የገለጡ ታጣቂዎች በወቅቱ በተጎራባች ኒጀር ድንበር አቅራቢያ ኢንዴሊማኔ ውስጥ በሚገኝ ወታደራዊ የጥበቃ ኬላ ላይ ባደረሱት ጥቃት 53 ወታደሮች ተገድለው ነበር። በዛው በ2019 ዓመት የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ማሊ፤ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀር ተጉዘው ከየሃገራቱ መሪዎች ጋር በተደጋጋሚ ተነጋግረው ነበር። የአካባቢው ደኅንነት ስጋት እንደተጋረጠበትም አስረግጠው ነበር የተናገሩት።

«አሸባሪዎቹ ፈጣን ናቸው። እናም ስለዚህ እኛም እነሱን በሚገባ ማሸነፍ እንድንችል መፍጠን ይኖርብናል።»

ማሊ ውስጥ ወታደሮቻቸውን ያሰማሩ ምዕራባውያን መንግሥታት በተለይ የማሊ ጉዳይ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በእርግጥም ሳያሳስባቸው አልቀረም። ማሊ ሲናጋ፤ የሣኅል ሰፊ በረሃማ ግዛት ተናጋ ማለት ነው። ያ ደግሞ ለእልምና አክራሪ ታጣቂዎች እና አሸባሪዎች መፈንጫነት መመቸቱን ምዕራባውያን ጠንቅቀው ያውቃሉ። አሸባሪዎቹ በቃጣናው ተጠናከሩ ማለት ስጋቱ ምዕራባውያን ዘንድ ሊደርስም ይችላል በሚል እሳቤም ነው ማሊ ውስጥ ጦር አስፍረው ክትትል የሚያደርጉት። ጀርመን፣ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ጸረ ሽብር እንቅስቃሴውን ለመደገፍ በሚል ጦራቸውን በቃጣናው አስፍረው መገኘታቸውም ለዚሁ ነው።

ምዕራባውያኑም ኾኑ የሣኅል አካባቢ ሃገራት መሪዎች ጸረ ሽብር ትግሉን በማከናወን ለማሊ ቀውስ በውይይት መፍትኄ እንዲገኝም ጥረት በማድረግ ላይ ነበሩ። የሀገሪቱ መንግሥት ከመወገዱ በፊት በሙስና ተዘፍቋል፤ የተፈለገውንም ዲሞክራሲያዊ ሒደት ማከናወን ተስኖታል በሚል በተደጋጋሚ ጊዜያት በተቃውሞ ሲናጥ ከርሟል። በስተመጨረሻም የማሊ ወታደራዊ ኹንታ የሀገሪቱን መንግስት አስወግዷል።

ተቃውሞውን ሲያስተባብሩ የነበሩት የማሊ መንግሥት ተቃዋሚዎች የሀገሪቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የ75 ዓመቱ አዛውንት ኢብራሒም ቦባካር ኪዬታን እስር ቤት ለወረወሩት ወታደራዊ አዛዦች ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

የጎረቤት ኒጀር የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ካላ ንኮውራዎ ከዶይቸ ቬለ (DW) ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ወታደራዊ መፈንቅ መንግሥቱ ለወራት ሲከናወን የነበረውን ድርድር ያሰናከለ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጠዋል።

« ለእኛ የሚያስከፋ ነው። ኹለት ወራት ሙሉ ለማደራደር በመሞከር እና የማሊ ሕዝብም የኢኮዋስ መመሪያን ማለትም ዲሞክራሲያዊ መንገድ እና አስተዳደርን ያስጠብቃል ብለን ተስፋ ሰንቀን ነበር። መፈንቅለ-መንግሥቱ ድርድሩን በኃይል ያቋረጠ ድርጊት ነበር።»

የኮናርድ አዴንአወር የሣኅል ተቋም ኃላፊ ቶማስ ሺለር በሕገ-መንግሥቱ መሰረት የተመረጠን መንግሥት በወታደራዊ መንግሥት መተካት ተቀባይነት የለውም ብለዋል። መንግሥቱን በኃይል የቀየረው ወታደራዊ ኹንታ ዓለም-አቀፋዊ ውግዘት ሊደርስበት እንደሚገባም ተናግረዋል። በእርግጥም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪቃ ኅብረት እና የአውሮጳ ኅብረት ድርጊቱን መፈንቅለ-መንግሥት በማለት ኮንነውታል። የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የምጣኔ ሐብታዊ ማኅበር (ECOWAS) ማሊ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እስክትመለስ ድረስ ከአካባቢው የንግድ ማኅበረሰብ አባልነቷ አግዷታል።

በጎረቤት ኒጀር ዋና ከተማ ኒያሜ ነዋሪ ለኾኑት ለተቃዋሚ ፖለቲከኛው ማማኔ ሳኒ አዳሞው ግን ኢኮዋስ በሚፈለግበት ወቅት ፈጥኖ የማይገኝ ተቋም ነው።

Infografik Afrika Währungszone ECOWAS EN

«ኢኮዋስ ኹሌም በጣም ዘግይቶ ነው ጣልቃ የሚገባው። መንግሥቱ ሲፍረከረክ፤ ሕዝባዊ ተቋማት ሲመዘበሩ ብሎም ነፃነት ሲገደብ ኢኮዋስ አንዳች ያለው ነገር የለም። ሰዎች መንግስቱን ለመገርሰስ ወደ ጎዳናዎቹ በወጡበት ቅጽበት ግን ኢኮዋስ ከተኛበት ነቅቶ የንግድ ማኅበረሰቡን ደንብ ለመጥቀስ ይሞክራል።»

የማኅበረሰብ ሳይንስ አጥኚው አብዶላዬ ሶናዬ መፈንቅለ-መንግስት አድራጊዎቹ ያሉትን ለውጥ ማምጣታቸውን ይጠራጠራሉ።

«እንደሚመስለኝ ላለፉት 20 ዓመት ግድም ኒጀርን ከተመለከትኽ፤ ማሊን ካየኽ የተለመደ ኾኗል። በቃ ጦሩ ጣልቃ ይገባል፤ ምስቅልቅሉን ላጸዳ ነው ወይንም ለማጽዳት እየሞከርኹ ነው ይላል። በስተመጨረሻ ግን ወደ ቀውስ የሚያመራውን መዋቅር ይኽ ነው በሚባል መልኩ አይቀይሩም።»

አብዶላዬ፦ በሣኅል ቃጣና መፈንቅለ መንግስት አንዱ ሃገር ሲፈጸም ሌሎቹ ጋርም የመደጋገም ነገር ይስተዋላል ባይ ናቸው።

«እንደሚመስለኝ አንዱ ያደረገውን ሌላው የመድገም ፍላጎት ሊኖር ይችላል። በኒጀር ወይንም በቡርኪና ፋሶ ያለውን የፖለቲካዊ ኹኔታ ስትቃኝ ምናልባትም ኮትዲቯርን ጨምሮ ተመሳሳይነት ይስተዋልባቸዋል። ምናልባት ልዩነቱ ማሊ ውስጥ ነገሮች እንደተበላሹ እና እንደተባባሱ ትንሽ ረዘም ላለ ጊዜ ይዘልቃሉ። ማሊ ውስጥ ከተከሰተው ነገር የኾነ ነገር ለማድረግ የሚነሳሱ ቡድኖች እና ግለሰቦችም በእርግጥም ይኖራሉ።»

ማሊ ውስጥ ተልእኮውን በማስፈጸም ላይ ለሚገኘው የጀርመን ጦር መፈንቅለ-መንግሥቱ በአካባቢው የጸጥታ ኹናቴ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ እንደሚረው ለመናገር ጊዜው ገና ነው። ይኽንኑም አንድ የጀርመን ጦር ቃል አቀባይ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

«በእኛ ዕይታ የሣኅል ቃጣና ቀድሞውንም መረጋጋት የራቀው አካባቢ ነው። ያን አኹንም ዕያየን ነው። ወደ አውሮጳ ለሚደረግ መጠነ ሰፊ ፍልሰትም አለመረጋጋቱ ከዋነኞቹ አንዱ ሰበብ ነው። በአካባቢው በሰፈነው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፤ ቀውስ፤ የጎሣ ግጭት እንዲሁም ሲበዛ ጽንፈኛ የኾኑ ቡድኞች በመኖራቸው የተነሳ ሰዎች ይፈልሳሉ። በአኹኑ ወቅት ግን ማሊ ውስጥ ባለው ኹኔታ በዚያ ዙሪያ አንዳች ለውጥ ይኖራል ብዬ ልናገር አልችልም፤ መጠበቅ ይኖርብናል። ይኼ የተከሰተው ነገር ምን ያኽል የተረጋጋ ነው የሚለውን መመልከት ይኖርብናል።»

የዛሬ ስምንት ዓመት ማሊ ውስጥ የተፈጸመ መፈንቅለ-መንግሥት ዳፋው ለጎረቤት ሃገራትም ተርፎ ነበር። መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ የተጠናከሩ እና በሰሜን ማሊ የተንሰራፉ አክራሪዎች በጎረቤት ኒጀር እና ቡርኪና ፋሶ ላይ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን በመሰንዘር አኹንም ድረስ የሃገራቱ የደኅንነት ስጋት ኾነዋል።

በማሊ ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ማክሰኞ ዕለት ቢያንስ አራት ሰዎች ሲገደሉ 15 ሰዎች በተተኮሰ ጥይት ቆስለዋል። የሀገሪቱ የቀድሞው ፕሬዚደንትን ጨምሮ 29 ያኽል ባለስልጣናት አኹንም ድረስ በእስር ላይ ይገኛሉ።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የአካባቢው ሃገራት ባሳደሩት ጫና ወታደራዊ ኹንታው የቀድሞው ፕሬዚደንት እንዲጎበኙ አድርጓል። የቀድሞው የገንዘብ ሚንሥትር እና ሌላ ባለሥልጣን መፍታታቸውን ዐስታውቋል። ኢኮዋስ ግን ፕሬዚደንቱ ከእስር ተለቀው ወደ ቀድሞ ሥልጣናቸው እንዲመለሱ ሲል ትእዛዝ አስተላልፏል። ተወካዮቹንም ዛሬ ወደ ማሊ ለመላክ የወሰነው ትናንት ነበር። ወታደራዊ ኹንታው «ወንድሞቻችን» ያላቸውን የኢኮዋስ ተወካዮች በደስታ እንደሚቀበል ወዲያው ነበር ያስታወቀው።

ግን ኢኮዋስም ኾነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደሚሻው መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹ ሥልጣኑን ነጥቀው እስር ቤት የወረወሯቸውን የቀድሞ የሀገሪቱ ርእሰ-ብሔር ከእስር ለቀው ሥልጣኑን ይመልሱላቸው ይኾን? ወይንስ ከየአቅጣጫው የሚሰነዘርባቸውን ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን ትተው በያዙት መንገድ ይዘልቃሉ? በደኅንነት ስጋት በተዋጠው የሣኅል ቃጣና በቀጣይ የሚከሰተውን መከታተል ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic