ማለቂያ ያጣው የዓለም ንግድ የዶሃ ድርድር | ኤኮኖሚ | DW | 21.05.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ማለቂያ ያጣው የዓለም ንግድ የዶሃ ድርድር

የዓለም ንግድን ፍትሃዊ በማድረግ ለታዳጊ አገሮች የተሻለ የልማት ዕድልን ለመስጠት ተወጥኖ እ.ጎ.አ. በ 2001 ካታር ላይ የተጀመረው የዶሃ ድርድር ዙር ከአንድ ማሰሪያ ላይ ሳይደርስ ሰባት ዓመታት አለፉት።

default

ድርድሩ ብዙ ውጣ-ውረድ ሲታይበት ለእስካሁን ክሽፈቱ ዋነኞቹ ምክንያቶች በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ለገበሬዎቻቸው የሚሰጡትን የአርሻ ድጎማ ለመቀነስና ገበዮቻቸውን ለታዳጊ አገሮች በአግባብ ለመክፈት ብዙም ፈቃደኛ አለመሆናችው ነው። የዓለም ንግድ ድርጅት ከሁለት ዓመታት በፊት ከሽፎ የተቋረጠውን የዶሃ ድርድር ዙር መልሶ በማንቀሳቀስ ከአንድ ውል ለመድረስ እስከ ቅርቡ ያደረገው ሙከራም አንዳች የረባ ዕርምጃ አልታየበትም። ከትናንት በስቲያ ታቅዶ የነበረ የጀኔቫ ስብሰባው እንደገና ተሸጋሽጓል።
ለነገሩ ዛሬ የእርሻ ምርቶች እጥረትና የምግብ ዋጋ ንረት በታዳጊው ዓለም ከመቼውም ይበልጥ የሕልውና አደጋን በደቀነበት ሰዓት ድርድሩን ከግብ በማድረስ ፍትሃዊ ንግድን ማስፈኑ ታላቅ ዕርምጃ በሆነ ነበር። ሆኖም ተሥፋ ሰጭ አዝማሚያ አይታይም። እጎ.አ. በ 1996 ዓ.ም. የተቋቋመው የዓለም ንግድ ድርጅት ካታር ርዕሰ-ከተማ ዶሃ ላይ ባካሄደው አራተኛ የሚኒስትሮች ጉባዔ አዲስና ፍትሃዊ ንግድን ለማስፈን የጸነሰው ሃሣብ በጊዜው የተሥፋ ብርሃን ነበር የሆነው። የታዳጊ አገሮች ልማት ከዚያ አንስቶ በሚካሄደው የዶሃ ድርድር ዙር ቁልፍ ጥያቄ ይሆናል። በዓለምአቀፍ ደረጃ ለነጻ ገበዮችና ንግድ በሚደረገው ትግል በተለይ የድሆች አገሮች ጥቅም ግንዛቤ ሊሰጠው ይገባል ነበር የተባለው። ሃያላን መንግሥታት ለብቻቸው ከመጋረጃ በስተጀርባ በመደራደር የሁሉም ነገር ወሣኝ የሆኑበት ጊዜም ያለፈ ታሪክ ሊሆን የተቃረበ መስሎ ነበር።
ግን አልሆነም። ዶሃ ዛሬም የትናንቱ የ 2001 ዶሃ ነው። ድርድሩ አንድም ነገር ወደፊት ፈቀቅ አላለም። ድርድሩ ከሰባት ዓመታት በፊት ሀ-ብሎ ሲጀምር በመሠረቱ የታቀደው የገበያ ፉክክርን በማዛባት ለታዳጊ ሃገራት ገበሬዎች የፉክክር ብቃት ጠንቅ የሆነውን የአውሮፓ ሕብረትና የአሜሪካ የእርሻ ድጎማ ለመቀነስ፣ ታዳጊ አገሮች የእርሻ ምርቶቻቸውን በኢንዱስትሪው መንግሥታት ገበዮች ላይ በተሻለ ሁኔታ ለመሸጥ እንዲበቁ ማድረግ፤ እንዲሁም በቀረጥ ቅነሣና በኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦት ረገድ ልዩ ደምቦችን ማስፈን ነበር። ሆኖም የዶሃው ድርድር ከተጀመረ ከሁለት ዓመታት በኋላ ሜክሢኮ-ካንኩን ላይ በ 2003 በተካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ስብሰባ ፍትህ ለሰፈነባት የንግድ ዓለም የታለመው ሕልም እንደገና ቅዠት ይሆናል።

በመስከረም 2003 ካንኩን ላይ ነባር ወይም አገሬው ገበሬዎች የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄድ ብሶታቸውን እንዲህ ገለጹ። ጊዜው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶችና የአነስተኛ ገበሬዎች ማሕበራት በዓለም ንግድ ድርጅት ላይ ጠንክረው የተነሱበትም ነበር። እነዚሁ የዓለም ንግድ ድርጅት የድሆቹና የደካሞቹ ታዳጊ ሃገራት ሣይሆን የበለጸጉት መንግሥታት ጥቅም አስጠባቂ ነው ሲሉ መግለጫ ያወጣሉ። “የዓለም ንግድ ድርጅት ከእርሻ ልማት ዘርፍ ዕጁን እንዲያወጣ እንጠይቃለን። የምግብ ምርት እንደ ጤና ጥበቃና ትምሕርት ሁሉ የንግድ ውል አካል እንዳይሆን እንጠይቃለን። አለበለዚያ የኛ ኤኮኖሚና ሕልውናችን እየጠፋ፤ የነባሩ ገበሬና በቤተሰብ ደረጃ ያነጸው መዋቅር እየወደመ ተጠቃሚ የሚሆኑት ጥቂት ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ብቻ ናቸው” ሲሉም ይወቅሳሉ።

ብዙ ቀናት ከፈጀ ጠንካራ ክርክር፣ የቀን ተሌት ድርድርና ከአደባባይ ሰልፎች በኋላ የካንኩን ጉባዔ በታዳጊ አገሮች ተቃውሞ ይከሽፋል። ከሁለት ዓመታት በኋላ በ 2005 ሆንግ ኮንግ ላይ በተካሄደው ቀጣይ የሚኒስትሮች ስብሰባም ወደፊት መራመድ አይቻልም። እርግጥ ድርድሩ እንደገና ቢቀር ለይስሙላ እንዳይከሽፍ ይደረጋል። ሆኖም በጉባዔው መጨረሻ የወጣው የጋራ መግለጫ ቁልፍ ለሆኑት አከራካሪ ነጥቦች አሁንም ተገቢውን ምላሽ የሰጠ አልነበረም። ሁሉም ነገር ተድበስብሶ ያልፋል። ታዲያ ችግሩ ተሸጋሸገ እንጂ አልተወገደም።
ከዚያን ወዲህ ሁለቱን ወገን የሚያረካ ውል ለማስፈን የተደረገው ሙከራ ሁሉ መሰናክል ገጥሞት እስከዛሬ እንደቀጠለ ነው። አንዴ የሕንዱ የንግድ ሚኒስትር ካማል ናት እንዳሉት የዶሃ ድርድር ዙር ዛሬም ቢሆን በማቃሰትና በሞቶ መካከል ነው የሚገኘው። በሌላ በኩል ስምምነቱን አንቀው የያዙት ዓበይት መሰናክሎች አሁንም የጥንቶቹ ናቸው። ምንም የተለወጠ ነገር የለም። ታዳጊዎቹ አገሮች እንደ መጀመሪያ ዕርምጃ ለአውሮፓውያንና ለአሜሪካ ገበሬዎች የሚሰጠው ግዙፍ የእርሻ ድጎማ እንዲቀነስና ምርቶቻቸው በኢንዱስትሪ ልማት ወደበለጸጉት መንግሥታት ገበዮች እንዲዘልቁ ይጠይቃሉ።

ሃብታሞቹ መንግሥታትም በፊናቸው ለኢንዱስትሪና ሌሎች ምርቶቻቸው የቀረጥ ቅነሣ እንዲደረግ ይሻሉ። በአገልግሎት ሰጭው ዘርፍ ደቡቡን ዓለም የጠቀለለ የንግድ ማለዘብ ዕርምጃም መወሰድ አለበት ባዮች ናቸው። የሆነው ሆኖ ዓለም ዛሬም እንደ ትናንቱ ፍትሃዊ ሊሆን ከሚችል የንግድ ውል ብዙ የራቀ ሆኖ ነው የሚገኘው። ይህ ደግሞ የጀርመን ወንጌላውያን የልማት አገልግሎት ድርጅት የንግድ ባለሙያ ሚሻኤል ፍራይን እንደሚሉት በተለይ ጎልቶ የሚታየው ከእርሻ ውጭ በሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶች የገበያ አገባብ ድርድር ላይ ነው።

“የቀረበው መነጋገሪያ የቀረጥ ቅነሣ ሃሣብ በተለይ ከፍተኛ ቀረጦች በሰፊው እንዲቀነሱ የሚጠይቅ ነው። ከፍተኛ ቀረጥ ያላቸው ደግሞ ታዳጊ አገሮች ናቸው። በአንጻሩ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት አገሮች ቀረጥ ዝቅተኛ ነው። ስለዚህም ለውጡ ብዙም የሚጎዳቸው አይሆንም። በአንድ ታዳጊ አገር ውስጥ የሚመረት ዕቃ ለምሳሌ ጫማ ወይም ጎማ በብሄራዊው ገበያ ላይ ችግር አይገጥመውም። ይህ የሆነው ግን በወቅቱ ትናንሾቹ አምራቾች በውጭ ኩባንያዎች ላይ በቆመ የቀረጥ ግምብ በመጠበቃቸው ነው። ምክንያቱም ብዙዎች የታዳጊ አገሮች አነስተኛ አምራቾች ከታላላቅ ኩባንያዎች ጋር በዓለም ገበያ ደረጃ ለመፎካከር የሚበቁ አይደሉም”

በዚሁ የተነሣም በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ የሚገኙት በተለይ የድሃ ድሃ የሆኑት አገሮች ቀረጥ በመቀነሱ ረገድ ለውጡን ደረጃ በደረጃ እንዲያካሂዱ የሚያስችል የበለጠ አስተያየት ሊደርግላቸው ይገባል። ግን በሌላ በኩል ሃብታሞቹ አገሮች ይህን ለመፍቀድ ዝግጁ አይደሉም። ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች እንደሚሉት ጉዳዩ በእርሻው ዘርፍም የተለየ አይደለም። ዛሬም ቢሆን እነዚሁ መንግሥታት በሰፊው በሚደጎሙ የምግብ ምርቶች የታዳጊ አገሮች ገበዮችን ማጥለቅለቃቸውን እንደቀጠሉ ነው። ውጤቱ ምርትን ማሰናከልና ትናንሽ ገበሬዎችን የሕልውና መሠረት ማሳጣት ነው።

የአውሮፓ ሕብረት የንግድ ፉክክርን የሚያዛባ የእርሻ ድጎማውን እስከ 2013 ዓ.ም ለማስወገድ ቃል መግባቱ ለብዙዎች በቂ ዕርምጃ አይደለም። ለዚያውም ለውጡ ለሕብረቱ ገበሬ በአንድ ዕጅ ወስዶ በሌላው መልሶ እንደመስጠት ያህል ነው መባሉም አልቀረም። ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ ለገበሬዎቿ የምትሰጠውን ድጎማ በሚገባ በመቁረጡ በኩል ለዓመታት በያዘችው ግትር አቋም እንደቀጠለች ነው። ስለዚህም የዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የኦክስፋም የእርሻ ልማት ባለሙያ ማሪታ ቪገርትሃለ እንደሚሉት ተጠቃሚዎቹ ታላላቅ ኩባንያዎች ሆነው ይቀጥላሉ።

“የእርሻው ገበያ መከፈት በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቅመው ምግብ አምራቹን ኢንዱስትሪና በዓለምአቀፉ ንግድ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ነው። ገበዮቹ እንዲከፈቱ ብርቱ ግፊት የሚያደርጉትም ለነገሩ እነርሱው ናቸው። በአንጻሩ የሰሜኑና የደቡቡ አምራች-ገበሬዎች ሂደቱ በሕልውናቸው ላይ ጎጂ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ደጋግመው ነው የሚያስገነዝቡት። ከዚህ አንጻር ተጠቃሚው ማን፤ ተጎጂውም ማን ሊሆን እንደሚችል ከአሁኑ ለይቶለታል ለማለት ይቻላል”

ይህ አንዱ አመለካከት ሲሆን ከበለጸጉት መንግሥታት አኳያ የሚሰነዘረው አስተያየት ደግሞ ለየት ያለ ነው። የጀርመን ፌደራል የኢንዱስትሪ ማሕበር እንደሚለው ታዳጊዎቹን አገሮች ወደፊት ለማራመድ ከሃብታሞቹ በኩል በቂ ዕርምጃ ተወስዷል። ለምሳሌ የድሃ ድሃ ተብለው የተመደቡት አገሮች በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የጣሉትን ቀረጥ መቀነስ የለባቸውም። ቀረጥ ቅነሣው የሚሠራው እንበል ብራዚል፣ ሕንድ ወይም ቻይናን በመሳሰሉት ራመድ ባሉ ለሚ አገሮች ላይ ነው። የጀርመን ኢንዱስትሪ ማሕበር ይልቁንም በአንጻሩ በልዩ አስተያየት ደምቦች ብዛት የአገሩ ኤኮኖሚ እንዳይጎዳ ነው የሚሰጋው።
ሁኔታው በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት ኩባንያዎች ወደ ታዳጊዎቹ አገሮች ገበዮች መግባታቸውን ሊያከብድ ይችላል ይላል። እንግዲህ የሰሜኑና የደቡቡ ዓለም ልዩነት ባለበት እንደቀጠለ ቢሆንም በየጊዜው ዕርምጃ ሊደረግ ነው የሚል ተሥፋ መሰጠቱ አልቀረም። የዓለም ንግድ ድርጅት ባለሥልጣን ፓስካል ላሚይም የመጨረሻው ዕድል አልተነካም ማለታቸውን አላቆሙም። ግን ይህ ከድርድሩ ይልቅ ድርጅቱን ክብደት ሰጥቶ ለማቆየት የተሰላ የዲፕሎማሲ ዘዴ ነው የሚመስለው፤ ሚሻኤል ፍራይን እንደሚያምኑት።

“ከበስተጀርባ የሚካሄደው አንድ ዓይነት የፖለቲካ ብልጣ-ብልጥነት የተመላበት የራስ ድርጅትን ሕልውና የመጠበቅ የቅስቀሣ ድርጊት ነው። በዓለም ንግድ ድርጅት መቀመጫ በጀኔቫ በዓለምና በመንግሥታት ፊት በታታሪነት ድርድር እየተካሄደ እንደሆነ አስመስሎ የመቅረብ ግፊት ያለ ይመስላል። አንዱም ድርጅቱን ጠቃሚ አድርጎ ለማሣየት የተያዘው ዘዴ የዶሃው ድርድር እንደሚቀጥል አስመስሎ መቅረቡ ነው”

እንደ ዕውነቱ ከሆነ የዶሃ ድርድር ዙር ቢቀር በጅምሩ በታሰበ መልኩ መልሶ ማንሰራራቱና ለስምምነት መብቃቱ ከንቱ ተሥፋ ነው የሚመስለው። በዚህ በያዝነው ዓመት ሂደት በጀኔባ የሚኒስትሮች ስብሰባ እንደሚካሄድ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። አንዱ የመጨረሻውም ከትናንት በስቲያ ይካሄዳል የተባለው ነበር። ግን ይህም እንደበፊቱ አልሆነም። ከዚህ አንጻር ጊዜን በከንቱ ከማባከን ለፍትሃዊ ንግድ የሚያበቃ አማራጭ መንገድ መሻቱ ከሁሉም በላይ የሚመረጥ ነው።

ተዛማጅ ዘገባዎች