ሚኑስካ እና የቀረበበት ትችት  | አፍሪቃ | DW | 16.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሚኑስካ እና የቀረበበት ትችት 

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ በምህፃሩ ሚኑስካ ሀገሪቱን ማረጋጋት አልቻለም በሚል ትችት ቀርቦበታል። ይሁንና፣ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሲምፕሊስ ሳራንጂ የሚኑስካን አስተዋፅዖ  የሚሞገስ መሆኑን አመልክተው በሀገሪቱ እርቀ ሰላም እንዲፈጠር ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:43
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:43 ደቂቃ

«ካለ ሚኑስካ ስምሪት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እከፋ ቀውስ ውስጥ ትወድቅ ነበር።»

« የሚኑስካ ሰላም አስከባሪዎች በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እንደገና ሰላም ለማውረድ እና ሀገሪቱን ለማረጋጋት የሚቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው።»
ጠቅላይ ሚንስትር ሲምፕሊስ ሳራንጂ ለዶይቸ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ የሰላም አስከባሪው ጓድ እንዲጠናከር የሚኑስካ ኃላፊ ዦን ፒየር ላክሯ ያቀረቡት ሀሳብ የሚደገፍ መሆኑን ነው ያስታወቁት።  የሚኑስካ ኃላፊ ዦን ፒየር ላክሯ ባለፈው ሳምንት በዠኔቭ ፣ ስዊትዘርላንድ ለተመድ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ተመልካች ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ውስጥ የኃይሉ ተግባር እየተባባሰ መሄዱን እንዳመለከቱ እና የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አሁን 10,750 ወታደሮች እና 2,100 ፖሊሶች ያሉትን ሰላም አስከባሪ ጓድ ወታደሮች ቁጥር ከፍ እንዲያደርግ  መጠየቃቸውን  ጠቅላይ ሚንስትር ሳራንጂ ገልጸዋል።


ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎች መሰል ድርጅቶች ሚኑስካ የማዕከላይ አፍሪቃን ሲቭል ሕዝብ አስፈላጊውን ከለላ አልሰጠም ሲሉ ብርቱ ወቀሳ ከሰነዘሩ በኋላ ነበር የሚኑስካ ኃላፊ ላክሯ ይህን ጥያቄ ያቀረቡት። በደቡባዊ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በሚገኘው የባስ ኮቶ ግዛት በሲቭሉ ሕዝብ ላይ ጥካኔ የተመላበት ጥቃት ፣ እንዲሁም፣ በክርስትና እምነት ተከታዮችም ላይ ሆን ተብሎ የግድያ ተግባር እየተፈፀመ መሆኑን የዓይን እማኞች አመልክተዋል። በአሊንዶ ከተማም በተካሄደ ጭፍጨፋ ቢያንስ 130 ሰዎች ተገድለዋል። የብዙዎች ሕይወት  ሊጠፋ የቻለው፣ እንደ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ገለጻ፣  በሀገሪቱ የተሰማሩት የሚኑስካ ወታደሮች አንድ ወደ አካባቢው አንድ ቀን ዘግይተው ፣ ለዚያውም ጥቂት ሆነው በመምጣታቸው  እና ከመጡም በኋላ በሀኪም ቤቶች እና ተፈናቃዮች ባሉበት ጣቢያ ብቻ ርዳታ በመስጠታቸው ነው።   ጠቅላይ ሚንስትር ሲምፕሊስ ሳራንጂ ግን ይህን ዓይነቱን ወቀሳ ለማረጋገጥ አልፈለጉም።
« በሲቭሉ ሕዝብ ላይ ለሚፈጸመው የኃይል ተግባር የሚኑስካ ሰላም አስከባሪዎችን ተጠያቂ ማድረግ ትክክለኛ አይደለም። እስኪ አስቡት፣ እነሱ ባይኖሩ ኖሮ ምን ሊፈጠር እንደሚችል። ካለሚኑስካ ርዳታ ይህች ሀገር እከፋ ቀውስ ውስጥ ትወድቅ ነበር፣ እንደ ሀገርም አትኖርም ነበር። »


ታጣቂ ሚሊሺያዎች፣ በተለይም፣ የሙስሊሞች ተፅዕኖ የበዛበት ከሴሌካ ሚሊሺያ ቡድን  የተገነጠሉ ተዋጊዎች በተለይ በባሶ ኮቲ ግዛት ውስጥ የኃይል ተግባራቸውን አስፋፍተዋል። ከነዚህ ቡድኖች መካከል አንዱ ራሱን  የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ሰላም ህብረት፣ በምህፃሩ ዩፒሲ ብሎ የሚጠራው የተሰኘው ይጠቀሳል። የዩፒሲ ተዋጊዎች ሴቶችንና ወንዶችን፣ ብዙ ጊዜም ልጆቻቸው ፊት በኃይል እንደደፈሩ፣ ከዚያ ወንዶቹን ተኩሰው እንደገደሉ፣ ሕፃናትን እናቶቻቸው ፊት ደብድበው እንደገደሉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች ከጥቂት ጊዜ በፊት ተናግረዋል። የዓይን እማኞቹ ያሉትን ያረጋገጡት የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር ሳራንጂ  ከሁሉም በላይ የሚያሳስባቸው  የቀድሞው ፕሬዚደንት ፍሮንስዋ ቦዚዜ በጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓም ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ  በሀገሪቱ የተቀሰቀሰውን ሀይማኖታዊ ግጭት ለማባባስ የሚደረገው ርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።   ከዚያን ጊዜ ወዲህ ምንም እንኳን ብዙ የሰላም ውሎች ቢፈረሙም ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ አልተረጋጋችም። ሀገሪቱ የዘር  ፍጅት እንዳሰጋት የተመድ አስጠንቅቋል።  ብዙ የሀገሪቱ ዜጎች በ2016 ዓም የተመረጡት የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፎስተ አርሾንዥ ቱዋዴራ ውዝግቡን ለማብቃትም ሆነ  ሀገሪቱን ለማረጋጋት አንድም ርምጃ አልወሰዱም፣ ያስገኙት የተሳካ ውጤትም የለም  ሲሉ ይወቅሷቸዋል። በፈረንሳይ የሚኖሩ የማዕከላይ አፍሪቃ  ሬፓብሊክ ዜጎች ፕሬዚደንት ቱዋዴራ ስልጣናቸውን እንዲለቁ በመጠየቅ በየጊዜው ተቃውሞ ሰልፎችን ያካሂዳሉ። ፕሬዚደንት ቱዋዴራ በተቀናቃኞቹ ቡድኖች መካከል እርቀ ሰላም ለማውረድ ያደረጉት ጥረት እንደሌለ እና በተለያዩት ዓማፅያን ቡድኖች መካከል ውይይት ሊጀመር የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር አለመቻላቸውን ነው ተቺዎቻቸው የሚናገሩት። ጠቅላይ ሚንስትር ሲምፕሊስ ሳራጂ ግን ይህ ወቀሳ ከእውነት የራቀ መሆኑን ነው ያስታወቁት።


« ፕሬዚደንታችን እርቀ ሰላም ለማውረድ ሁሌም  እጃቸውን እንደዘረጉ ነው። ሁላችሁም በአንድ ጠረጴዛ ዙርያ ተቀመጡ እና ስለሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ተመካከሩ ብለዋል። ሰላም የማውረዱ ተግባር የርዕሰ ብሔሩ ወይም የመንግሥቱ ወይም የምክር ቤት እንደራሴዎች ኃላፊነት ብቻ አይደለም። ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች የራሳቸውን ድርሻ ማበርከት ይኖርባቸዋል። »
ቀውሱ በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የፊናንስ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የፖለቲካ ታዛቢዎች  ይናገራሉ። የአውሮጳ ህብረት ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን ለመርዳታ በብራስልስ፣ ቤልጅየም ባካሄዳቸው የተለያዩ የለጋሽ ሀገራት ጉባዔ ለዚችው ሀገር በተደጋጋሚ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለመስጠት ቃል ተገብቶዋል።

  በሀገሪቱ ቋንቋ ቤኩ ወይም ሲተረጎም ተስፋ በሚል መጠሪያ አንድ የአውሮጳ ህብረት የሚያስተዳድረው የገንዘብ ርዳታ ተዘጋጅቷል። ገንዘቡን ከሰብዓዊ ርዳታ ጎን ለመልሶ ግንባታው ፣ እንዲሁም፣ በሚቀጥሉት ዓመታት የልማት ፕሮዤዎችን ለማካሄጃ ተግባር የማዋል እቅድ አለ። የአፍሪቃ ህብረትም ቢሆን ቀውስ ያመሰቃቀላትን የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጉዳይን  ብዙ ጊዜ  ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ በማድረግ ምክክር አካሂዷል።  ህብረቱ በመጨረሻ ስለዚችው ሀገር በተወያየበት ስብሰባው ላይ ሀገሪቱን ከምትገኝበት ምስቅልቅል ሁኔታ ማላቀቅ የሚቻልበትን ዘዴ የሚያዘጋጅ አንድ ኮሚሽን እንዲቋቋም ወስኗል። ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የቀጣዩ የተመድ ጠቅላላ ጉባዔም መወያያ አጀንዳ እንደምትሆን እና የሀገሪቱ መንግሥትም አቋምም እንደሚደመጥ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሳራንጂ ገልጸዋል። ሚሆን  ተገልጿል።  
« የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ለተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ወደ ኒው ዮርክ ይሄዳሉ፣ በዚያም በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የቀጠለው ውዝግብ እንዳይባባስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረዳ ይማፀናሉ። »
 ጠቅላይ ሚንስትር ሳራንጂ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ለቀጠለው የኃይል ተግባር  ተጠያቂዎቹ በዚያው በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተፋላሚ ወገኖች በመሆናቸው፣ ይህን ሁኔታ ለመቀየር እና ሰላም ለማውረድ ጥረቱ በዚያው በሀገሪቱ መፈለግ እንደሚገባው በአፅንዖት አስታውቀዋል።
«  መፍትሔው ሰላም ለማውረድ ከልብ መፈለግ ነው። ሁሉም ሰው ሰላም ለማውረድ ከልቡ መሻት አለበት። የሚፋለሙት ወገኖችም ሰላምን እንዲመርጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራት አስፈላጊ ነው። ሁሉም ለሰላም መቆም አለባቸው። ሰዎች ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ሲያምኑ ያኔ ሀቀኛው ሰላም ይፈጠራል፣ ካላመኑ ግን ሰላም አይወርድም። »

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች