ሙጋቤና ወታደራዊ ኃይላቸዉ በዚምባቡዌ ምርጫ | የጋዜጦች አምድ | DW | 23.03.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ሙጋቤና ወታደራዊ ኃይላቸዉ በዚምባቡዌ ምርጫ

ወታደራዊ የማዕረግ አርማዎችና ጌጦች ሲያደርጉ አይታዩም። ይልቁንም የዚምባቡዌዉ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ የሽምቅ ተዋጊ ካባቸዉን ወዲያዉ አዉልቀዉ ለፓለቲካዉ ያላቸዉ ንቁ አይን እንዳለ ሆኖ ሱፋቸዉን ግጥም በማድረግ ይታወቃሉ።

የፓለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት የ81 አመቱ አዛዉንት ሙጋቤ የአገሪቱን ወታደራዊ ኃይል ብቃት ከመቼዉም ጊዜ በበለጠ በማጠናከር ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲያቸዉ በድጋሚ እንዲያሸንፍ ለማድረግ እየጣሩ ነዉ።
በመጪዉ ሳምንት በሚካሄደዉ ምርጫም በድጋሚ ተመርጠዉ በስልጣን ለመቆየት የተጠናከረ ወታደራዊ ሃይል ይጠቀማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እንደነሱ እምነት እንዲህ አይነቱ ስልት ለሙጋቤ በጣም ቀላል ነዉ። በሂደቱ እጅግ የሚያምኗቸዉን ሰዎች ይቀጥራሉ። እነዚያ ሰዎችም የአገሪቱ የጦር ሃይል እና ሌሎች የደህንነት ሃይሎች በሙሉ ከሙጋቤ ጎን የመሆናቸዉን ወሬ ለሰዉ እንዲያሰራጩ ይደረጋል።
የዛሬ 45 አመት አካባቢ በዚምባቡዌ የነፃነት ትግል ስልት አቀነባባሪነትና ርቱዕ አንደበታቸዉ የፓለቲካ ብቃታቸዉን ያሳደጉት ሙጋቤ ለወታደራዊዉ ኃይል የረጅም ጊዜ አክብሮት አላቸዉ።
ከሌላዉ የአፍሪካ አገራት በተለየ የዚምባቡዌ የጦር ኃይል አገሪቱ ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ በ1972 ነፃ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ ሙጋቤን በስልጣን ለማቆየት ከፍተኛ ሚና ተጫዉቷል።
ባለፈዉ የአዉሮጳዉያኑ 2000 ዓ.ም. የተቃዉሞ ፈተና የዲሞክራሲ ለዉጥ እንቅስቃሴ በምህፃረ ቃል MDC ከተባለዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ገጠማቸዉ።
በዚህ ጊዜ ነዉ ወታደራዊዉ ኃይል ከመቼዉም ይበልጥ ተጠናክሮ በሙጋቤና በገዢዉ ፓርቲያቸዉ ዙሪያ ዘብ እንዲቆም የተደረገዉ።
በአሁኑ ምርጫም ሙጋቤ የጦር ኃይል አዛዦችን በማነቃነቅ፤ የካበተ ልምድ ያላቸዉን የጦር ሰዎችና ወጣት ብርጌዱን በምርጫ ቅስቀሳቸዉ በማሳተፍ ተቃዋሚዎችን እንቀብራለን ሲሉ በይፋ ተናገሩ።
ልምድ እንዳካበቱ የሚነገርላቸዉ የዚምባቡዌ መሪ ባለፉት ስድስት ወራት ጡረታ የወጡትንና ለረጅም ጊዜ ያገለገሉትን የሰራዊቱን ኃላፊዎች በፓርቲዉ ዉስጥ ከፍተኛ ስልጣን ሰጥተዋል።
ከዚህም ሌላ ለቀድሞ የጦሩ ኃላፊዎች የተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች በስለላ ድርጅቱ፤ በእስር ቤት፤ በፓሊስ ኃይልና በፍርድ ቤት አካባቢ ጨምሮ ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ሰጥተዋል።
ሌሎቹንም ነፃ በሚባለዉ የዚምባቡዌ ምርጫ ኮሚሽን፤ በፓርላማና በዛኑ ፒኤፍ ዉስጥ በማዕከላዊ ኮሚቴዉ ልዩ ልዩ የስልጣን እርከን ላይ አዉጥተዋል።
በዚህ ዘዴ ተጠቅመዉም የምዕራባዉያን አሻንጉሊቶች የሚሏቸዉን ተቃዋሚዎች በምርጫዉ ከጨዋታ ዉጪ የማድረግ እቅድ ነድፈዋል።
በተለይ የዚምባቡዌ ፓለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ሙጋቤ ወታደራዊ ኃይላቸዉን በፈለጉት አቅጣጫ ማንቀሳቀስ መቻላቸዉ ለተቃዋሚዎቻቸዉ ብቻ ሳይሆን ለሌላዉ አለምም የማይበገር ኃይል እንዳላቸዉ ለማሳየት አይነተኛ ስልት ነዉ።
የዛሬ ሶስት አመት የነበረዉ ምርጫ ከመድረሱ በፊት የዚምባቡዌ ወታደራዊ ኮማንደሮች የMDC መሪ ቢያሸንፉ ወታደራዊ የክብር ሰላምታ እንደማይሰጧቸዉ ገልፀዉ ነበር።
ጦሩም በበኩሉ በተምታታ ፓለቲካ ዉስጥ እንደማይሳተፍ በመግለፅ ሙጋቤ በምርጫዉ ቢሸነፉ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት እንደሚያካሂድ አስፈራርቷል።
ዛሬ በዚምባቡዌ ካለዉ የምጣኔ ሃብት ቀዉስ በተቃራኒ ከፍተኛ የጦሩ ባለስልጣናት ናቸዉ ዉድና ዘመናዊ መኪና በማሽከርከር ሙጋቤ ከነጮች የወሰዱት ለም መሬት ባለቤት የሆኑት።
በአንድ ወቅት በእርሻ ረገድ በከፍተኛ ሁኔታ አድጎ የነበዉ የዚምባቡዌ ምጣኔ ሃብት በአሁኑ ጊዜ ጉልበቱ ተሽመድምዷል።
በዚህም ሳቢያ የዋጋ ግሽበት ከመቶ አልፎ ስድስት በመቶ ጊዜ እጥፍ አሻቅቦ ከፍተኛ የምግብና የነዳጅ እጥረት በአገሪቱ አለ። የስራ አጡም ሁኔታ 70 በመቶ ደርሷል።
ባለፉት አምስት አመታትም የአገሪቱ ሰራተኛ ከሚባለዉ ኃይል ሁለት ሶስተኛዉ ወይም 3.4 ሚሊዮን የሚሆነዉ ሰዉ ከአገር ወጥቷል።
በአገሪቱም ለመጀመሪያ ጊዜ ፓለቲካዊ ሳይሆን ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ለምርጫ ቅስቀሳ አይነተኛ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል።
የሙጋቤ መንግስትም የመሬት ፓሊሲዉን ከሚቃወሙ ከአገር ዉስጥም ሆነ ከምዕራባዉያን ከሚፈፀምበት የተቀነባበረ ሻጥር ጋር እየታገለ መጠነኛ ለዉጥ ማስመዝገቡን እየገለፀ ነዉ።
በተፈጠረዉ ዉዝግብ የተደናገረዉ የዚምባቡዌ ህዝብ ግን በብዛት በምርጫዉ ላይሳተፍ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ለማንኛዉም ሁሉም ሊለይለት ምርጫዉ አንድ ሳምንት ብቻ ቀርቶታል የዚምባቡዌ እጣፈንታ ምን ይሆን?ተዛማጅ ዘገባዎች