ሙዚቃን ለሰላም | ባህል | DW | 08.09.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ሙዚቃን ለሰላም

ጦርነት ሰቆቃ እንግልትና ሞት የየለት ክስተት በሆነበት በሶርያ፤ ሙዚቃ መሳርያ ከጃቸዉ ሳይለይ በሙዚቃ ሰላምን የሚያስተጋቡ ከተለያዩ የአረብ ሃገራት የተሰባሰቡ ወጣቶች መካከል፤ የተሳተፈዉ ሶርያዊዉ ባጊሃኒ ራድሃ ይገኝበታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:45

ሙዚቃን ለሰላም

«በርሊን እጅግ ዉብ ከተማ ነዉ። በርሊን ከተማን በጣም ወድጃታለሁ። »

"Berlin is so great" አልጀርያዉያኑ ወጣት የረቂቅ ሙዚቃ ቀማሪዎች በአንድ ድምፅ «በርሊን በጣም ዉብ ነዉ» ሲሉ ነዉ ነበር የገለፁት። «ሙዚቃን ለሠላም እንጫወታለን» በሚል መርህ ወጣት አልጀርያዉያኑ ራመረኸስ ኖስሁድና፤ ባጊሃኒ ራድሃ በርሊን ላይ ባቀረቡበት የሙዚቃ መድረክም ሆነ የሙዚቃ ታዳሚዉ እንዲሁም በከተማዋ ተማርከዋል። ወጣት አልጀራዉያኑ ሙዚቀኞች የጀርመን መዲና በርሊን ተስማምታቸዋለች። ከሰሜናዊ አልጀርያ የመጡት እነዙህ ሙዚቀኞች እንደሚሉት ከሆነ እኛ ሃገር እንደሚታየዉ ዓይነት ግርግር በርሊን ላይ አይታይም። ከአገራችን ጋር በርሊንን ስናስተያያት ፀጥ ያለች ሰላማዊ ከተማ ነች ባይ ናቸዉ። ሙዚቀኞቹ ራመረኸስ እና ባጊሃኒ የሚተዋወቁት በአገራቸዉ በአልጀርያ ነዉ፤ «Young Euro Classic» በተሰኝ በርሊን ላይ የተዘጋጀዉ የረቂቅ ሙዚቃ ፊስቲቫል ላይ ሙዚቃን እንዲያቀርቡ የግብዣ ወረቀት ሲደርሳቸዉ ደስታቸዉ ወደር አልነበረዉም። ለ 17ኛ ጊዜ በርሊን ላይ በተካሄደዉ የወጣት ኦርኬስትራ ቡድን የሙዚቃ ፊስቲቫል ላይ ከአረብ ሃገራት ወጣት ሙዚቀኞች ሲካፈሉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነዉ።

Gero Schließ AYPO

አልጀርያዉያኑ ራመረኸስ ኖስሁድና፤ ባጊሃኒ ራድሃ በበርሊን

ከስምንት አረብ ሃገራት የተሰባሰቡ 63 ወጣት ሙዚቀኞች በርሊን ለ 17ኛ ጊዜ በተዘጋጀዉ የረቂቅ ሙዚቃ መድረክ ላይ ሙዚቃቸዉን ለማቅረብ ከጠዋት እስከ ምሽት ድረስ ሲለማመዱ ቆይተዋል። ከአልጀርያ ለመጡት ወጣት ሙዚቀኞች ራመረኸስና ለባጊሃኒ የበርሊኑ የሙሉቀን የሙዚቃ ልምምድ ከባድ ነበር። በርሊን ከተማ መዉጫ ላይ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት አዳራሽ ዉስጥ በጀርመናዊዉ የረቂቅ ሙዚቃ አዋቂ ሃይነር ቡልማን በመመራት በመድረክ ሊያቀርቡት የተዘጋጁትን ሙዚቃ ለአንድ ሳምንት ነዉ ሲለማመዱ የከረሙት ። ወጣቶቹ ከሙሉ ቀን ልምምድ በኋላ በርግጥም እጅግ በመድከማቸዉ በርሊን ከተማን በምሽት ለማየት አቅም አልነበራቸዉም ። ምንም እንኳ የ 27 ዓመትዋ ዋሽንት መሰል የሙዚቃ መሳርያ የምትቻወተዉ እና የ 25 ዓመቱ የባዝ ሙዚቃ ተጫዋች በርሊን ከተማን በምሽት ለማየት ቢወዱም።

ከስምንት የአረብ ሃገራት የተሰባሰቡት እነዚህ ወጣት የረቂቅ ሙዚቃ ተጫዋቾች ከአንድ ሳምንቱ የጋራ ልምምድ በኋላ ለተመልካች ዝግጅታቸዉን አቅርበዋል።

የታዋቂዉ የአሚር ካፊር፤ የአሊ ኦስማን የሙዚቃ ስራዎች እንዲሁም የዮኃንስ በርሃምስ የሙዚቃ ሥራዎች በወጣቶቹ ሙዚቀኞች በመድረክ ቀርበዋል። ይህ ብዙ ድካም የፈሰሰበት ሙዚቃ በመድረክ ሲቀርብ በአድምተኛ እጅግ ተወድዋል ፤ ከፍተና ጭብጨባንም ተቸርዋል። ከአልጀርያ የመጣችዉ ሙዚቀኛ ራመስ እንደምትለዉ ሙዚቃን የምንጫወተዉ ለሰላም ነዉ።

« በእዉነቱ በጣም ጥሩ ነበር። ሙዚቃን የተጫወትነዉም ለሰላም ነዉ ። ምክንያቱም ሁሉም አረብ ሃገሮች ሙዚቀኞቻቸዉን ልከዉ በበርሊኑ የረቂቅ ሙዚቃ መድረክ ተሳትፈዋል። ሙዚቃንም ተጫዉተዉ አሳይተዋል። ሃገራቱ እንዲወክሉላቸዉ ወጣት ሙዚቀኞችን ልከዋል። የአረብ ሃገራቱም በአንድነት ሆነዉ ለዓለም ሙዚቃቸዉን አስተዋዉቀዋል። »

ግድያ ጦርነት ሽብር ብቻ ስለሚነገርለት ስለ መካከለኛዉ ምስራቅ አካባቢ በሙዚቃ ስለአካባቢዉ ሌላ ግንዛቤ ሌላ ስዕልን ማስጨበጥ ነዉ የምንፈልገዉ ስትልም ገልጻለች።

ሙዚቃኛ ሃሰን ኦባይድ የመጣዉ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከሚታይበት በርካታ የሰብዓዊ መብት ከሚጣስበት ሰዎች ይህንኑ ሰቆቃ ሸሽተዉ አገራቸዉን ጥለዉ ከተሰደዱበት ከሶርያዋ መዲና ከደማሶቆ ነዉ። የ 21 ዓመቱ ሃሰን በሶርያ የሙዚቃ ከፍተኛ ተቋም የቫዮሊን ሙዚቃ መሳርያ አጨዋወትን ተምሮአል። ቫዩሊን የሙዚቃ መሳርያዉ ከእጁ የማይለየዉ ሃሰን በሶርያ ባለዉ ጦርነት መንፈሴ ሁሌም እንደተረበሸ ነዉ ሲል ይናገራል። ቀን ተቀን ጦርነት የቦንብ ድብደባ ጩኸት ሶቆቃ ሞት በጣም አሰቃቂ ጉዞ ሲል ሃሰን የሃገሩን ወቅታዊ ሁኔታ ይገልፃል።

Hasan Obaid AYPO

ከደማስቆ የመጣዉ ሙዚቀኛ ሃሰን አብዲ

« በሙዚቃችን ልናስተላልፍ የፈለግነዉ ወይም መልክታችን ሰላም ነዉ ። ሙዚቃንም እንወዳለን ነዉ መልክታችን። »

ሙዚቃ ለሃሰን ሁሉም ነገር ነዉ። ከሙዚቃ ቡድኑ ጋር ለሰላም ሙዚቃን የተጫወተባት በርሊን ከተማም ለመዝናናት ለረፍት የሄደባት ያህል ነዉ የተሰማዉ። « ጀርመን ሕይወት ይታያል ሲል በጀርመን ቆይታዉ ስላየዉና ስለተሰማዉ አጠር አድርጎ ለመግለፅ ይሞክራል። ሃሰን ወደ ጀርመን የመጣዉ ለአንድ ሳምንት የሙዚቃ ልምምድና ከዝያም ለ17 ኛ ጊዜ በተዘጋጀዉ «ያንግ ይሮ ክላሲክ» የረቂቅ ሙዚቃ መድረክ ላይ ሙዚቃን በመድረክ በጀርመን ለሚገኙ ታዳምያን ለማሳየት ሲሆን የአገሩ ልጅና እኩያዉ ሙዚቀኛ ካይስ ደግሞ ከወንድሙ ጋር ወደ ጀርመን መጥቶ በስደተኝነት መኖር ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል። ካይስ ከአገሩ የተሰደደዉ በጦርነቱ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በሃገሩ በሶርያ የትምህርት የስልጠና ጉዳይን በተመለከተ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን ምክንያት እንደሆነ ነዉ የሚገልጸዉ።

እንደ ካይስ ይኖርበትና ይማርበት በነበረዉ በደማስቆ የሙዚቃ ከፍተኛ ተቋም የሚገኙ የዉጭ ሃገር የሙዚቃ መምህራን ሁሉ በሃገሪቱ በተከሰተዉ ጦርነት ሰበብ እየሸሹ ወደ ሃገራቸዉ ተመልሰዋል። የሙዚቃ መማርያ ተቋሙም ተዘግቶአል። በተለይ ከሩስያ የመጡት ታዋቂ የተባሉት የሙዚቃ ምሁራን ከሶርያ ወደ ሃገራቸዉ መመለሳቸዉን ካይስ ይገልፃል።

«ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የራሽያ የሙዚቃ ፕሮፊሰሮች የሙዚቃ አስተማሪዎቻችን ነበሩ። በዚህ በሁለት ዓመት ዉስጥ እነዚህ የራሽያ የሙዚቃ ምሁራን ሁሉ ሃገሪቷን ለቀዉ ወተዋል። ስለዚህም አንድም በሙዚቃ ሞያ ምሁር የለንም። የሙዚቃ እዉቀታችን በራሽያዉያኑ የሙዚቃ ምሁራን ላይ የተመሰረተ ነዉ። ለእያንዳንዱ የሙዚቃ መሳርያ ምሁራን ነበሩ። የኔ የሙዚቃ መምህር የነበረዉ የሙዚቃ ፕሮፊሰር ወደ ሃገሩ ከተመለሰ በኋላ አንድ ሶርያዊ የቫዬሊን ሙዚቃ መሳርያ ተጫዋች ያስተምረኝ ነበር፤ ግን ምን ያህል ተማርኩት የምለዉ ነገር የለም። ራሽያዉያኑ ምሁራን ቢኖሮ ጥሩ ነበር። በሶርያ ያለዉ የሙዚቃ ተቋምም ተዘግቶአል»

እንድያም ሆኖ በአንድ መድረክ ሙዚቃን ያቀረቡት የአንድ ሃገር ልጆቹ ካይስ እና ሃሰን የጀርመን አብሮ ቆይታቸዉ፤ ተደስተዋል። በእንዲህ ዓይነት መልኩና በዚህ አይነት ደረጃ ሙዚቃን ስናቀርብ ፤ የመጀመርያችን ነዉ ሲሉም የተናገሩት።

Kais Shalgin AYPO

በሰሜናዊ ጀርመን በስደተኝነት የሚኖረዉ ሶርያዊ ሙዚቀኛ ካይስ ሻልጊን

በበርሊኑ የረቂቅ ሙዚቃ መድረክ ላይ ሙዚቃን ከተጫወቱት 63 ተሳታፊዎች መካከል አብዛኞቹ የመጡት ከግብጽ ነዉ። በጎርጎረሳዉያኑ 2006 ዓ,ም የካይሮ የረቂቅ ሙዚቃ ቡድን መስራችና የካይሮ የረቂቅ ሙዚቃ ኮስርቫቶሪ ዋና ተጠሪ ፋዉዙ ኧል ሻሚ በበርሊኑ ግዙፍ የአረብ ሃገራት የረቂቅ ሙዚቃ ትርዒት ላይ ተገኝተዉ ነበር። ዋናዉ ይላሉ ስለበርሊኑ የረቂቅ ሙዚቃ ድግስ ፋዉዙ ሻሚ ፤ ዋናዉ ከተለያዩ የአረብ ሃገራት የመጣን ሙዚቀኞች ተዋዉቀን በአንድ ላይ ሙዚቃን በጋራ ማቅረብ መቻላችን ነዉ። በመድረኩ ከሶርያ ከግብፅ ከአልጀርያ ከኢራቅ እና ከክዌት የመጡና የተለያየ የአጨዋወት ባህል የያዙ ሙዚቀኞች የቀረቡበት እንደሆን ፋዉዙ ሻሚ ተናግረዋል።

«አልጀርያዉያንና ግብጻዉያን በጋራ ያሳየነዉ የአረብ ረቂቅ ሙዚቃን የአረብ ሃገር ባህልን ነዉ። በዚሁም በሙዚቃ ሰላም፤ ፍቅርን እንደምንፈልግ ለዓለም ለማሳየት ነዉ።»

ወጣት አረባዉያኑ የረቂቅ ሙዚቃ ባለሞያዎች በርሊን ላይ ለአንድ ሳምንት የሙዚቃ ትርኢት ገና ለማሳየት ዝግጅት ላይ ሳሉ የመግብያ ትኬቱ ተሸጦ ማለቁ ተነግሮለታል። ወጣቶቹም ከአንድ ሳምንት ከፍተኛ ስራ በኋላ ደስታ ኩራት ታይቶባቸዋል። ወጣት ሙዚቀኞቹ ወደመጡበት ለመመለስ በዝግጅት ላይ ናቸዉ። ከሶርያ መዲና ደማስቆ በዚሁ መድረክ ላይ ለመገኘት ወደ በርሊን የመጣዉ ሃሰን ወደ ደማስቆ ለመመለስ በዝግጅት ላይ ይገኛል። ምንም እንኳ ሃገሩ በርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ ብትሆንም ኪነ-ጥበብን ይዞ ሃገሩ ሕይወት እንድትዘራ ጥርት በማድረጉ አድናቆትን ተቸሯል። ልምድን ፤ አብሮነትን ቀስሞ ወደ ሃገሩም እንደሚመለስም ነዉ የተነገረለት።

በሰሜናዊ ጀርመን ከወንድሙጋ በጥገኝነት መኖር የጀመረዉ ሶርያዊ ሙዚቀኛ ካይስ በበኩሉ በቀጣይ በሃንቡርግ በሚገኘዉ የሙዚቃ ተቋም የቫዩሊን ሙዚቃ መሳርያ አጨዋወትን ለመማር እቅድ ይዞአል።

«አሁን የጀርመንኛ ቋንቋ እየተማርኩ ነዉ። በሃንቡርግ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተጋባዥ ተማሪም ነኝ። የመጨረሻ ሴሚስተር ትምህርት ላይ እገኛለሁ። ቢሆንም ትምህርቴን በመቀጠል በሚቀጥለዉ ዓመት ትልቁን ፈተና መፈተን እፈልጋለሁ፤ በጀርመን ይህ ፈተና ከባድ ነዉ ። እዚህ የሚገኙ ሶርያዉያን ከሌሎች የአረብ ሃገር ሙዚቃ ጋር ምንም ዓይነት ተሞክሮ የሌላቸዉ ናቸዉ ። ታድያ ይህ እንዲህ ዓይነት መድረክ ለኛ የመጀመርያችን ነዉ። ከግብፅ ከቱኒዝያ አልያም ከሌሎች አረብ ሃገራት ከመጡ ሙዚቀኞች ጋር ስንጫወት የመጀመርያች ነዉ። ተሞክሮዉ ለኛ ሌላ ዓይነት፤ ሌላ ደረጃ ያለዉ ነዉ »

ፍሪድሪ ሜርኩሪ- የክዊን የሮክ ሙዚቃ ባንድ

ክዊን በመባል የሚታወቀዉ የብሪታንያ የሮክ ሙዚቃ ባንድ አቀንቃኝ ፍሪዲ ሜርኩሪ በኤድስ ቫይረስ ምክንያት የሳንባ በሽታ ይዞት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየዉ በጎርጎረሳኣዉያኑ 1991 ዓ,ም ነዉ ። የብርታንያዉ የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ የፍሪዲ ሜርኩሪ 70ኛ የልደት በዓል በያዝነዉ ሳምንት መግብያ ሰኞ በተለይ በሮክ ሙዚቃ አፍቃሪዎችና እንዲሁም በኩዊን የሙዚቃ ባንድ አፍቃሪዎች ዘንድ ታስቦ ዉሎአል።

USA Freddie Mercury Sänger

ፍሪድሪ ሜርኩሪ

በመድረክ አነቃናቂነቱ የሚታወቀዉ የክዊን ባንድ አቀንቃኝ ፍሪዲ ሜርኩሪ በታዋቂዉ ቬምብሊ ስታድዮም የገባዉን 70 ሺህ ሕዝብ አብሮት እንዲዘፍን የሚያደርግ ልዩ ተሰጦ የነበረዉ ከያኒ እንደነበር ተዘግቦለታል። የክዊን ባንድ ሙዚቃዉን ለተመልካች አሳይቶ ሲያበቃ ፍሪዲ ሜርኩሪ የባንዱን ስያሜ የሚገልፀዉን ምልክት ማለትን አክሊልን ይደፋ እንደነበር ነዉ የተመለከተዉ። ፍሪዲ ሜርኩሪን ጨምሮ የጊታር የከበሮ እንዲሁም ለሌች የሙዚቃ መሳርያዎችን የሚጫወቱ ብሎም የሚያዜሙ ሦስት ብሪታንያዉያን ያካተተዉ ኩዊን የተሰኘዉ የብሪታንያ የሮክ የሙዚቃ ቡድን በጎርጎረሳዉያኑ 1970 ዓ,ም ነበር የተመሰረተዉ።

ዓለም በ1980 ዎቹ የሰዉነት ደም ሴል አመንማኙንና ገዳዩን የኤድስ ቫይረስን ሲተዋወቅ፤ በግብረሰዶሙ ዓለም ራሱን ደብቆ ይኖር የነበረዉ የክዊን ሙዚቃ ባንድ አቀንቃኝ ፍሪዲ ሜርኩሪ የቫይረሱ ተጠቂ ነበር፤ ምንም እንኳ ሙዚቀኛዉ ግብረ ሰደሞ መሆኑን በኤድስ መያዙን በይፋ ባይናገርም። የፍሪዲ ሜርኩሪ የጤና ሁኔታ ከቀን ወደቀን እየተበላሸ መጣ፤ እይንዳይታወቅበትም ይጥር የነበር ቀን ከለሊት ሙዚቃን ይሰራ እንደነበርም ነዉ ታሪኩ የሚያሳየዉ ። ከጎርጎረሳዉያኑ 1985 ዓ,ም ጀምሮ የጤና ሁኔታዉን መደበቅ ያልቻለዉ ፍሪዲ፤ ሰዉነቱ እየከሳ ጤና ማጣቱ በግልፅ እየታየ መምጣት ጀመረ። ጋዜጠኞች ነገሩን ይፋ ሊያደርጉ ቢሞክሩ ፍሪዲ ሜርኩሪና የሙዚቃ ባልደረቦቹ ምንም ዓይነት ቃለ ምልልስ ባለመስጠታቸዉ ነገሩን በይፋ ሊያረጋግጥ የሚችል አልተገኘም። ምንም እንኳ አጋላጭ የፎቶ ጋዜጠኞች አንድ ጊዜ ሊመረመርበት በሄደበት ቦታ ሁሉ ተከታትለዉ ገብተዉ ነገሩን በማረጋገጫ ይፋ ለማዉጣት ቢሞክሩም።

ከቀን ወደቀን የሰዉነቱ መጠን እየቀነሰ የመጣዉ ፍሪዲ1 ሜርኩሪ በ1990 ዓ,ም የሙዚቃ ባንዱ ለብሪታንያ ሙዚቃ ላባረከተዉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ «ብሪት አዋርድ» የተሰኘዉን የክብር ሽልማት ፍሪድሪክ ሜርኩሪ መድረክ ላይ ወጥቶ የተቀበለዉ እሱ ቢሆም እናመሰግናለን መልክትን የተናገረዉ ሌላ የሙዚቃ ባልደረባዉ ነበር። ፍሪዲ በእለቱ እጅግ ከስቶ መታየቱ ተዘግቦአል። እንድያም ሆኖ የሙዚቃ ባንዱ የመጨረሻ የሙዚቃ አልበሙን ለመሰራት ትንሽ በትንሽ ሙዚቃን እየሰራ «ሜድ ኢን ኢን ሄቨን » የተሰኘዉን አልበሙን በ1991 ዓ,ም ሰርቶ ጨረሰ። ይህ የሙዚቃ ገበያ ላይ የዋለዉ ግን ከአራት ዓመት በኋላ በ1995 ዓ,ም ነበር። ኤድስ ቫይረስ እንዳለበት የማይናገረዉ እዉቁ የክዊን የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ ፍሪድሪክ ሜርኩሪ በጎርጎረሳዉያኑ 1991 ዓ,ም መጨረሻ ከዚህ ዓለም ከመለየቱ አንድ ቀን በፊት ለጋዜጠኞች በይፋ አዎ ኤድስ ቫይረስ አለብኝ ሲል አመነ። ይህን በተናገረ በነጋታዉ በቫይረሱ ምክንያት ይማቅቅበት በነበረዉ በሳንባ ምች ይህችን ዓለም ተሰናበተ። በሕይወት ዘመኑ በሰራቸዉ ድንቅ ሙዚቃዎቹ ፍሪዲ ሚርኩሪ ዛሬም ህያዉ ሆኖ ይታወሳል።

ጌሮ ሽሊስ / አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic