ሙኒክ፤ የባየር ሙኒክ ሥራ አስኪያጅ እስራት ብይን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 13.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ሙኒክ፤ የባየር ሙኒክ ሥራ አስኪያጅ እስራት ብይን

የጀርመን ፍርድ ቤት ዛሬ ተገቢዉን ግብር ሳይከፍሉ በማጭበርበር በተከሰሱት የባየር ሙኒክ የእግር ኳስ ቡድን ሥራ አስኪያጅ ዑሊ ሆነስ ላይ የ3 ዓመት ተመንፈቅ እስራት በየነ።

የ62 ዓመቱ ሆነስ 27,2 ሚሊዮን ዩሮ በስዊዝ ባንክ ምሥጢራዊ የባንክ ሂሳብ ማኖራቸዉን አምነዋል። ከመነሻዉ አቃቤ ሕግ 3,5 ሚሊዮን ዩሮ በማጭበርበር ነበር የከሰሳቸዉ። ሆኖም ሆነስ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የተጭበረበረዉ 18,5 ሚሊዮን ዩሮ መሆኑን ራሳቸዉ በማመናቸዉ ፍርድ ቤቱን አስደምመዋል። ቆየት ብሎም የገንዘቡ መጠን ከ27 ሚሊዮን መብለጡ ተገለጸ። በዛሬዉ ዕለትም ፍርድ ቤት ቢያንስ እስከ 20ዓመት እስራት ሊበይንባቸዉ እንደሚችል ግምት ሲሰነዘር ነበር። ሆነስ ፍርድ ቤቱን ይቅርታ በመጠይቅ እንዲራራላቸዉ መማፀናቸዉ ተዘግቧል። የሙኒክ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቃል አቀባይ አንድሪያ ቲትስ ብይኑን እንዲህ ገልጸዋል፤

«የሙኒክ ፍርድ ቤት አምስተኛ ችሎት በተገቢዉን ግብር ሳይከፍሉ በማጭበርበር ወንጀል በሰባት ነጥቦች በየተከሰሱት ላይ ባጠቃላይ በሶስት ዓመት ከመንፈቅ እስራት በይኗል።»

አቃቤ ሕግ በፈቃዳቸዉ መረጃዎችን በመስጠታቸዉ ብቻ ቅጣቱ ሊቀልላቸዉ አይገባም ሲል ተከራክሯል። በጀርመን ሕግ የገቢ ቀረጥ ማጭበርበር ታላቅ ወንጀል ነዉ። ዑሊ ሆነስ በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ብቻ ሳይሆን በመላዉ አዉሮጳ የእግር ኳስ ክለቦች ዘንድ የሚደነቀዉን የባየር ሙኒክ ክለብ ለዚህ ደረጃ በማብቃት ተወዳጅነትና ዝናን አትረፈዉ ነበር። ቀደም ሲል ግብር አጭበርብሬ አላዉቅም ባሉበት አንደበት ይህን በማድረጌ ተፀፅቻለሁ ማለታቸዉ ይፋ ሲሆን አድናቂዎቻቸዉን ግራ አጋብተዋል። የፍርድ ቤት ዉሳኔዉን ከሰሙ አንድናቂዎች አንዱ፤

«ሆነስን ወህኒ አትዝጉበት! ለባየርን የእግር ኳስ ቡድን ብዙ ነገር አድርጓል። ስለዚህ በእዉነት ይህን አታድርጉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ