ሙስናና አግባብ የለሽ የሃብት አጠቃቀም፤ የአፍሪቃ ጠንቅ | ኤኮኖሚ | DW | 13.06.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ሙስናና አግባብ የለሽ የሃብት አጠቃቀም፤ የአፍሪቃ ጠንቅ

የአፍሪቃን ዕድገት አንቀው ከያዙት ዋና ዋና ችግሮች መካከል ሙስናና አግባብ የለሽ የብሄራዊ ሃብት አጠቃቀም ይገኙበታል። በተፈጥሮ ጸጋ የታደሉት አገሮች ሃብቱን ተጠቅመው ኋላ የቀረውን ኤኮኖሚ ለማሳደግና የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል አልበቁም፤ ወይም አልፈለጉም።

ፕሬዚደንት ቡተፍሊካ

ፕሬዚደንት ቡተፍሊካ

ብዙም በተፈጥሮ ሃብት ባልታደሉት አገሮች ደግሞ በልማት ዕርዳታም ይሁን በብድር ከውጭ የሚፈሰው ገንዘብ በጥቂት ባለሥልጣናት ኪስ እየገባ መባከኑ እንግዳ ነገር አይደለም። የተፈጥሮ ጸጋ ለብዙሃኑ ዕድገት መሠረት በመሆን ፈንታ በከንቱ ሲባክን፤ ከሞቡቱ ዛኢር፤ ከዛሬይቱ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ እስከ ናይጄሪያ፤ ከሱዳን እስከ አልጄሪያ፤ በነዳጅ ዘይትና ሌላ ሃብት ላይ የተቀመጡት አገሮች የሚገባውን ያህል አላደጉም። በክፍለ-ዓለሚቱ በነዳጅ ዘይት ግዙፍ ገቢ ከሚያስገቡት አንዷም አልጄሪያ ስትሆን ግን በዚህ ሁኔታ የአገሪቱ ሰፊ ሕዝብ አልተጠቀመም። ለምን? የአልጄሪያ ፔትሮ-ዶላር ወዴት ወይም እንዴት እየፈሰሰ ነው?

አልጄሪያ በዓለም ላይ ቀደምት ከሆኑት ነዳጅ ዘይት አምራች አገሮች አንዷ ናት። የተፈጥሮ ጋዝ ሃብትም አላት። የማግሬቧ አገር ከአራተኛው የ 2003 ዓ.ም. የነዳጅ ዘይት ቀውስ ወዲህ በደራ ንግዷ በመስኩ እንደሚጠራው በፔትሮ-ዶላር መጥለቅለቋም አልቀረም። የአልጄሪያ የተቀማጭ ሃብት ክምችት በ 2004 ዓ.ም. 32 ሚሊያርድ ዶላር ደርሶ ነበር። ይሄው በሁለት ዓመታት ውስጥ፤ በ 2006 ወደ 75 ሚሊያርድ ከፍ ሲል እስከፊታችን 2010 ዓ.ም. 160 ሚሊያርድ ዶላር እንደሚደርስ ነው የሚጠበቀው። በስድሥት ዓመታት ውስጥ በአራት ዕጅ ከፍ ይላል ማለት ነው።

የአገሪቱ ካዝና በሽብር በተወጠረችበት በ 90ኛዎቹ ዓመታት የተራቆተ እንደነበር ሲታወስ የአሁኑ በገንዘብ መጥለቅለቅ ለሰሚው የተረትን ያህል ነው የሚመስለው። በጊዜው አገሪቱ በውጭ ዕዳ ከመጠን በላይ ተውጣ በዓለም ባንክ ጥብቅ የመልሶ-ግንባታ ዕቅድ እስኪጣልባት ደርሳ ነበር። ዛሬ የመንግሥቱ ካዝና ይበጥ እንጂ በአንጻሩ የድሃው ሕዝብ መጠን ሲቀንስ አይታይም። በተለይ ብሩህ ዕድል የማይታየው ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄድ ወጣት ተሥፋውን ወደ አውሮፓ በመፍለሱ ላይ ጥገኛ አድርጎ እንደቀጠለ ነው። ስለዚህም ዛሬ እያንዳንዱ አልጄሪያዊ የሚያቀርበው ጥያቄ ከነዳጅ ዘይት ንግድ የሚገኘው ገንዘብ የት እየገባ ነው? የሚል መሆኑ ብዙም አያስደንቅም።

የአልጄሪያ ርዕሰ-ከተማ አልጂርስ ዛሬ አንድ ትልቅ የግንቢያ ስፍራ ነው የምትመስለው። በየቦታው አዳዲስ የቢሮ ሕንጻዎች፣ የገበያ ማዕከላትና ድልድዮች ይኮለኮላሉ። እንደ አውሮፓ የምድር ውስጥ-ለውስጥ ማመላለሻ የባቡር መሥመር እንኳ አልቀረም። ችግሩ ከዚህ የገጽታ ለውጥ ተጠቃሚዎቹ ጥቂቶች ብቻ መሆናቸው ነው። አልጂርስ ከግንቢያው ጎን ለጎን ቁጥር ስፍር የሌለው ሴት፣ ወንድ ወይም ሕጻናት ሳይል በኔ-ቢጤ ለማኝ የተሞላች ሆናለች። እነዚህ ደግሞ የነዳጅ ዘይት ሃብት ያስከተለው ገቢ አሻራውን ካላሳረፈባቸው የገጠር አካባቢዎች ወደ ከተማይቱ የሚጎርፉ ናቸው። የአብዛኞቹ የአፍሪቃ ታላላቅ ከተሞች ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይሆንም።

ሃቁ ይህ ከሆነ ለመሆኑ ባለፉት ዓመታት የአገሪቱን ካዝና ያጥለቀለቀው የነዳጅ ዘይት ገቢ ምን እየተሠራበት ነው? የአልጄሪያ መንግሥት መላ የአገሪቱን የኤኮኖሚ ዘርፎች በሚያዳርስ ሁኔታ ልማትን ለማፋጠንና አገሪቱን ዘመናዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አንቀሳቅሷል። የአልጄሪያ ችግር ዛሬ ገንዘብ ከየት ላግኝ ሣይሆን እንደቀድሞው እንዳይባክን ወይም እንዳይዘረፍ ምን ይደረግ የሚል ነው። ገንዘብ ችግር አለመሆኑ ግልጽ፤ የኋለኛው ቀላል ላለመሆኑ ግን አንድና ሁለት የለውም። ለማንኛውም ፕሬዚደንት አብደልአዚዝ ቡተፍሊካ የዘመናዊ ተሃድሶ ዕቅዳችውን ማንም እንዲጠራጠር አይፈቅዱም። እንደዛሬ የተሻለ ጊዜ የት ነበርና ባይ ናችው።

“አልጄሪያ ውስጥ ለመሆኑ ከዚህ ቀደም 144 ሚሊያርድ ዶላር ያወጣ ፕሮዤ የታየበት ጊዜ ነበር? ከነጻነት ወዲህ የማይታወቅ ነገር ነው። አልጄሪያ እንደዛሬው በገንዘብ ደረጃ ጥሩ ሁኔታ ያየችበት ጊዜስ ነበር? ይህም ከነጻነት ወዲህ አይታወቅም። ይህን ጥሩ ዕድል አልጄሪያን ከጨለማው ዘመን ለማውጣት ተጠቅመንበታል” ፕሬዚደንት ቡተፍላኢካ!

ፕሬዚደንት ቡተፍሊካ በተሃድሶ ስኬታችው ጨርሶ አያመንቱ እንጂ በተለይ የገጠር አካባቢው ነዋሪ የሚያስበው ሌላ ነው። ብዙ ሳይርቅ ከዋና ከተማይቱ አልጂርስ ደቡብ-ምዕራብ ሁለት ሰዓት የመኪና መንገድ ፈንጠር ብላ በምትገኘው አካባቢ በአኢን-ዳፍላ ለምሳሌ ነዋሪው በድርቅ መከራውን የሚያይና በማዕከላዊው አስተዳደር የተረሣ ነው። አካባቢው በ 90 ኛዎቹ ዓመታት የእርስበርስ ጦርነት ወቅት ሽብርተኞች የሚንቀሰሱበት ነበር። በዚሁ የተነሣም ቀያቸውን እየለቀቁ ወደ ከተሞች የተሰደዱት ብዙዎች ናቸው። የቀሩትም በከፋ የኑሮ ሁኔታ ቀጥለዋል።

“ውሃ ፍለጋ ላይ ነኝ። እዚህ ውሃ አልፎ አልፎ የሚገኝ ነገር ነው። ለነገሩ እዚያ ከስተጀርባ ማመንጫ ታንጿል። ግን ውሃ አልተገኘም። በዚህ አካባቢ ውሃና የኤሌክትሪክ ሃይል በጣም ነው የሚያስፈልገው” ይህች የ 50 ዓመት ሴት ባሕታ ትባላለች። ከአካባቢው ነዋሪዎች አንዷ ናት። ስፍራው ለዕለት ከዕለት ኑሮ የሕልውና ትግል የሚደረግበት ነው ለማለት ይቻላል። ባለቤቷ ኦመርም እንዲሁ የነዳጅ ዘይት ወሬ ሲነሣ በመከፋት ነው የሚናገረው። “ነዳጅ ዘይት! ማንም ምንም አልሰጠንም። አሃዞችና ትርፍ ይጠቅሳሉ። ግን ለእኛ እስካሁን የደረሰን አንዳች ነገር የለም”

የአልጄሪያን የእርስበርስ ጦርነት የቀሰቀሰው በ 90ኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ በአሕጽሮት FIS በመባል የሚታወቀው እሥላማዊ የፈውስ ግንባር የተሰኘ ቡድን በምርጫ ያገኘው ድል በአገሪቱ ጦር ሃይል መሻሩ ነበር። ቡድኑ በአልጄሪያ የጸጥታ ሃይላትና በደጋፊዎቻቸው ላይ ያካሄደው የሽምቅ ውጊያ አገሪቱን ቅዠት ላይ ይጥላል፤ ከ 120 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች፤ በአብዛኛውም ሲቪሎች ያልቃሉ። ገና ያኔም ለ FIS የምርጫ ድል ,መብቃት ዋነኞቹ ምክንያቶች የገዢዎች ፍትህ-ዓልባነት፣ ሙስናና የነዳጅ ዘይት ገቢው በሕብረተሰቡ ውስጥ በአግባብ አለመከፋፈል ነበሩ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሕዝብ ልማት ላይ ባወጣው ባለፈ ዘገባው አልጄሪያን ከ 173 አገሮች በ 107ኛ ቦታ ነው ያስቀመጠው። የዓለም ባንክና ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶችም ዛሬ ከአልጄሪያ 33 ሚሊዮን ሕዝብ ሶሦው፤ ማለት 12 ሚሊዮኑ ድሃ መሆኑን ይናገራሉ። እርግጥ የአልጂርሱ መንግሥት ይህን መረጃ አይቀበለውም። እንዲያውም የተባበሩት መንግሥታትን የድህነት አተረጓጎም ዘይቤ መተቸትና መንቀፉን ነው የመረጠው። የገንዘብ ሚኒስትሩ ሙራድ እምዴልሢ የከፋ ድህነት በሚለው ጠበብ ያለ አመለካከት ይወሰናሉ።
“አንድ በመቶው አልጄሪያዊ ብቻ ነው በከፋ ድህነት ላይ የሚገኝ ሊባል የሚችለው። ማለት ለኖሮው በየዕለቱ የአንዲት ዶላር ገቢ ያለው” ይላሉ። ይሁንና በኦራን ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚ ፕሮፌሰር የሆኑትን ካሪም ቡሃሪንን የመሳሰሉት ጉዳዩን በሌላ ዓይን ይመለከቱታል። ካሪም እንደሚሉት “የአልጄሪያ ድህነት በአገሪቱ የኤኮኖሚ ለውጥ ከተጀመረ ወዲህ፤ በተለይም በ 90ኛዎቹ ዓመታት ሁለተኛ አጋማሽ ከፍ ብሏል። የድህነቱ መጠን ከ 2003 ወዲህ አቆልቋይ ቢሆንም በቂ ግን አይደለም። ምክንያቱም የወቅቱ የኤኮኖሚ ዕድገት ችግሩን ለመፍታት የማይችል መሆኑ ላይ ነው”

የነዳጅ ዘይት ገቢ በጨመረባት አገር አጠቃላዩ የድህነትና የተሥፋ መቁረጥ ሁኔታ በተለይ ወጣቱን ለሽሽት ነው የዳረገው። የአገሪቱ ባለሥልጣናት በሚሉትና በተጨባጩ ሃቅ መካከል ብርቱ ቅራኔ አለ። የመጀመሪያው የገጠሩን ችግር አያንጸባርቅም። በከተሞችም ቢሆን ሌላ ዕጣ የማይታየው ወጣት ትውልድ ሕልም ወደ ውጭ ሃገራት መፍለስ ነው። በአልጂርስ ወደብ የሚታየው አገር ለቆ የመውጣት ጥረት ሁኔታውን በሚገባ ያንጸባርቃል። “የአልጂርስ ወደብ! ከምሽቱ አምስት ሰዓት ነው። በግዙፍ ግምብ የተከበበው ወደብ በርከት ባሉ ጸጥታ አስከባሪዎች ይጠበቃል። ከማገጃው ግምብ በስተጀርባ “ሃራጃ” ይሏቸዋል፤ የመጣ ይምጣ፤ የፈጀውን ይፍጅ ወደ ምዕራቡ ዓለም መሻገር የሚፈልጉ ሰዎች ሾልከው መርከብ ለመሳፈር ዕድላቸውን ይሞክራሉ። የወደፊት ተሥፋ ያልሰጠቻቸውን አገር ለቆ ለመውጣት ለምንም የማይመለሱ ናቸው። ከፍተኛ ትምሕርት ያጠናቀቁ ሰዎች ሳይቀር ከሽሽት ሌላ የሚያስቡት የላቸውም”

የሽሽቱን መንስዔ የቀድሞው የአልጄሪያ የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትርና የዛሬው የአልጂርስ ዩኒቨርሲቲ መምሕር ፕሮፌሰር ሞሐመድ-ቤን-ያሣድ እንዲህ አስቀምጠውታል። “ዕውነተኛውና ተጨባጩ የነፍስ-ወከፍ ገቢ እጅግ ዝቅተኛ ነው። አጠቃላዩን የአገሪቱን ነፍስ-ወከፍ ገቢ ለተመለከተ ግን ይሄው ከ 2000 ዓ.ም. ወዲህ በፍጥነት እያደገ ነው የመጣው። ከ 1,500 ወደ 5,000 ዶላር ከፍ ብሏል። ይሁንና ይህ ከሰንጠረዥነት አልፎ የአንድን አልጄሪያዊ ዜጋ አማካይ ገቢ በትክክል የሚያንጸባርቅ አይደለም” አልጄሪያና ወጣቷ! የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ ሥራ አጥነት፣ ድህነትና ትብትብ ቢሮክራሲ፤ ዕድገቱን አንቀው የያዙት ዋና ዋና ችግሮቹ ናቸው። ሕግ ለነገሩ አልጠፋም። ግን ማሕበራዊ ፍትህ የለም።

እርግጥ የአልጄሪያ መንግሥት በገፍ የተገኘ የፔትሮ-ዶላር ገቢውን የውጭ ዕዳውን በጊዜው ለመክፈል ተጠቅሞበታል። የአገሪቱ ዕዳ በአራት ዓመታት ውስጥ ከ 23 ወደ 5 ሚሊያርድ ዶላር ማቆልቆሉ ነው የሚነገረው። የፓሪስ ክበብ እየተባለሉ ለሚጠሩት አበዳሪዎች እንኳ በአንድ ጊዜ 8 ሚሊያርድ ዶላር ነው የከፈለው። ተቺዎች ሰፊው ሕብረተሰብ ለሕልውና አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ሁሉ ጎድለውት የአልጄሪያ መንግሥት ይህን ያህል ገንዘብ በአንዴ ማውጣቱ በገፍ በተገኘው ሃብት የሚያደርገውን ማወቅ እንደተሳነው ምልክት ነው ይላሉ። የኤኮኖሚ ጠበብትም የአልጄሪያ ኤኮኖሚ በነዳጅ ዘይት ብቻ ጥገኛ ከመሆን ይልቅ ሁል-ገብ አቅጣጫ እንዲይዝ እየመከሩ ነው።

አልጄሪያ ምንም እንኳ ከዋና ዋናዎቹ ነዳጅ ዘይት አምራች አገሮች አንዷ ብትሆንም ሃብቱን ለዕድገት በመጠቀሙ ረገድ የኋለኛዋ ናት። ለዚህ ደግሞ መጥፎ አስተዳደርና ሙስና ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው። ይህ በተፈጥሮ ጸጋ የታደሉትን የአፍሪቃ አገሮች አጠቃላይ ሃቅ ያንጸባርቃል። ሁኔታው ካልተለወጠ ሕዝቡ በአስተዳዳሪዎቹ ላይ ዓመኔታ ሊኖረው፤ የኑሮ ሁኔታው ሊሻሻልና ተፈጥሮ የሰጠው ጸጋ የዕድገቱ ቡራኬ ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ዕድገቱ በከተሞች ግዙፍ ሕንጻዎችን መደርደሩን ሣይሆን ሕዝብን ሊያስቀድም ይገባዋል።