መፍትሔ ያልተገኘለት የቡሩንዲ ውዝግብ | አፍሪቃ | DW | 09.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

መፍትሔ ያልተገኘለት የቡሩንዲ ውዝግብ

በቡሩንዲ ሁከቱ ጨርሶ ያበቃ ይመስላል። ይሁንና፣ ውዝግቡ ከውጭ ለሚያየው ያለቀለት ቢመስልም ውስውስጡን መቀጠሉን ጠበብት አስጠንቅቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:02

ቡሩንዲ

የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ባለፈው ሚያዝያ ወር የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት ሽረዉ ለሶስተኛ ዘመነ ሥልጣን እንደሚወዳደሩ ባስታወቁበት ጊዜ በሀገሪቱ ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት እና ሁከት አሁን አብቅቶ መረጋጋት የሰፈነ እንደሚመስል የአፍሪቃ ህብረት ዲፕሎማት ካሲሚ ባምባ ገልጸዋል።

«የቡሩንዲ ሁኔታ በወቅቱ የተረጋጋ እንደሚመስል ለመናገር እፈልጋለሁ። መረጋጋት አለ ቢባልም ግን ሰዎች ይገደላሉ፣ እርግጥ ቁጥራቸው እንደበፊቱ ባይሆንም። በተለይ፣ የመንግሥቱ ተቃዋሚዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ጠንካራ ርምጃ ይወሰዳል። አንዳንድ ወጣቶች በፀጥታ ኃይላት ይታገታሉ። እድል አድርገው ካልተለቀቁ በስተቀር። አልፎ አልፎ አስከሬናቸው የሆነ ቦታ ተጥሎ ይገኛል።»

ዲፕሎማቱ ይህንን ያስታወቁት የጀርመናውያኑ የሀይንሪኽ በል የፖለቲካ ጥናት ተቋም ከዶይቸ ቤለ እና ከኔትዎርክ አፍሪካ ጋር በመተባበር ሰሞኑን በበርሊን « በቀውስ አፋፍ ላይ ለምትገኘው ቡሩንዲ ሰላማዊ መፍትሔ የማስገኘቱ ዕድል ይኖር ይሆን? » በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነበር። እንደሚታወሰው፣ በቡሩንዲ ከሚያዝያ፣ 2015 ዓመ በኋላ በቀጠሉት በርካታ ወራት በተካሄደው ደም አፋሳሽ ሁከት ቢያንስ 400 ሰዎች ተገድለዋል፣ 3,500 ታስረዋል፣ 220,000 ደግሞ ወደ ጎረቤት ሃገራት ሸሽተዋል።

ከውጭ ለሚያየው ሁኔታዎች የተረጋጉ ቢመስልም ውዝግቡ ውስውስጡን እንደቀጠለ የሚያስጠነቅቁት አንዳንድ ጠበብት፣ በሀገሪቱ በቅርቡ ሰላም የሚወርድበት ዕድል ዝቅተኛ መሆኑን ይናገራሉ። እርግጥ፣ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እውቅና ያላገኙት ፒየር ንኩሩንዚዛ የሚመሩት የቡሩንዲ መንግሥት በመላ ሀገሪቱ የሰላም ድርድር የሚመራ አንድ ኮሚቴ አቋቁሞዋል። ይሁንና፣ የኮሚቴውን ውጤታማነት፣ እንደ ጋዜጠኛ ቦብ ሩጉሪካ፣ ብዙዎችም ተጠራጥረውታል።
«ይህ ውይይት በማን እና ማን መካከል ነው የሚካሄደው? ምክንያቱም ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች በሙሉ በስደት ላይ ነው የሚገኙት። ዋነኞቹ የሲቭል ማህበረ ሰብ መሪዎች በስደት ላይ ናቸው።»

Burundi Podiumsdiskussion DW

የበርሊኑ የውይይት መድረክ

«ራድዮ ፒውብሊክ አፍሪኬን» የተባለው የግል ራድዮ ጣቢያ የቀድሞ ዋና ስራ አስኪያጅ ሩጉሪካ የመንግሥት ደህንነት ክትትልን ሸሽቶ ስደት የገባው ባለፈው ዓመት ነበር። የአፍሪቃ ህብረት ዲፕሎማት ካሲሚ ባምባም የሚደራደረው ተቀናቃኝ ወገን በሌለበት መንግሥት ብቻውን ድርድር ሊመራ አይችልም የሚለውን የሩጉሪካን አባባል ይጋሩታል። ሁሉን የሚያሳትፍ ድርድር ከቡሩንዲ ውጭ ሊካሄድ እንደሚገባ በተደጋጋሚ የቀረበውን ሀሳብ የቡሩንዲ መንግሥት ውድቅ እንዳደረገው ባምባ አስታውቀዋል።

ብዙው የቡሩንዲ ሕዝብ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላም አስከባሪ ጓድ እንዲልክ ተስፋ ቢያደርግም፣ የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ባለፈው ዓርብ አንድ የፖሊስ ኃይል ወደዚችው የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገር ለመላክ መወሰኑ ቅር እንዳሰኛቸው ሩጉሪካ አመልክተዋል። በተመድ የቡሩንዲ አምባሳደር መግለጫ መሰረት፣ የሚላኩት ፖሊሶች ቁጥር ከ20 እስከ 30 ብቻ በመሆኑ፣ ዓለም አቀፉ የፖሊስ ጓድ ለመላክ የተያዘው እቅድ ሀገሪቱን በማረጋጋቱ ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋ እንደሌላቸው ሩጉሪካ ገልጸዋል፣ ምክንያቱም ይኸው ንዑሱ የፖሊስ ጓድ የቡሩንዲን ውዝግብ ማስወገድ የሚችልበበት አቅም የለውም።

ይሁን እንጂ፣ ምንም እንኳን በበቡሩንዲ ሁከቱ አሁንም ውስጥ ለውስጥ መብላላቱን ቢቀጥልም፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሀገሪቱ በ1994 የተነሳው ዓይነት የጎሳ ጭፍጨፋ ይዳግም ይፈጠራል የሚል ስጋት የለውም፣ እንደ ጀርመናዊትዋ የበርሊን ፖሊቲክ ኡንድ ቪስንሻፍት» የተባለው የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ክላውዲያ ዚሞንስ ግምት።
«መሰረቱ፣ ሰፊው የቡሩንዲ ሕዝብ ራሱን ጎሳን መለኪያ ባደረገ መስመር ለማደራጀት ፈቃደኛ እንዳልሆነ በግልጽ እያሳየ ነው። ይህ ግን ፣በተለይ፣ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ በቡሩንዲ የርስበርስ ጦርነት ወቅት ተወያይቶ ሀቀኛ እርቀ ሰላም በመፍጠሩ ረገድ አንዳችም ስራ አለመሰራቱ ሲታሰብ፣ ጎሰኝነት በወቅቱ አንዳችም ሚና አይጫወትም ማለት አይደለም።»

እርግጥ፣ የጎሳ ጥያቄም ሀገሪቱ ለምተገኝበት ቀውስ አንዱ ምክንያት ቢሆንም፣ በጀርመን ፌዴራዊ ምክር ቤት፣ ቡንድስታግ የተወከለው የተቃዋሚው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴ ኮርዱላ ሹልስ አሸ እንዳስረዱት፣ አንድ ንዑስ የገዢው መደብ ክፍል ብቻ ከሀገሪቱ ፖለቲካ እና ኤኮኖሚ ተጠቃሚ መሆኑ ለቀውሱ መባባስ ሰፊ ድርሻ ማበርከቱ ሊረሳ አይገባም። ሹልስ አሸ እና አንዳንድ የምክር ቤት እንደራሴዎች ለውዝግቡ የራሳቸውን አስተያየት ለመያዝ በ2015 ዓም ወደዚችው ሀገር ተጉዘው ነበር።

«በዚያን ጊዜ ከቡሩንዲ የምክር ቤት አቻዎቻችን ጋር ተወያይተናል፣ እና የሚያስገርመው፣ ሁሉም ያጎሉት በወቅቱ የጎሳ ጥያቄ ውጥረት አለመፍጠሩን ነበር።»

የቡሩንዲን ውዝግብ ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማብቃትም ሁሉን ከሚያሳትፍ የሰላም ድርድር የተሻለ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ያስረዱት ሹልስ አሸ አስረድተው፣ የአውሮጳ ህብረት ከአፍሪቃ ህብረት ጋር በመተባበር በቡሩንዲ ላይ ጫና እንዲያሳርፍ አሳስበዋል። በቅርቡ ሰላም ካልወረደ በስተቀር፣ በቡሩንዲ አዲስ ግጭት እና ሁከት የሚፈነዳበት ስጋት ከፍተኛ ነው በሚለል በተሰነዘረው ሀሳብ ላይ መደቀኑን በበርሊኑ የውይይት መድረክ የተሳተፉት የፖለቲካ ተንታኞች እና ፖለቲከኞች ተስማምተውበታል፣ እንደ ክላውዲያ ዚሞንስ እንዳስጠነቀቁትም፣ ውዝግቡን በዘለቄታ ለማስወገድ ካልተቻለ ሀገሪቱ ትልቅ አደጋ ላይ የምትወድቅበት ስጋት ተደቅኖባታል።

«በቡሩንዲ በአሁኑ ጊዜ መረጋጋት ቢታይም የተረጋጋ ሁኔታ ቢታይም፣ ይህ ቀጣይ ይሆናል ማለት አይደለም። ለቡሩንዲ ቀውስ የፖለቲካ መፍትሔ እስካልተገኘለት ድረስ ሁኔታዎች በቀጣዮቹ ዓመታት ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ።»

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic