መፍትሔ ያላገኘው የደቡብ ሱዳን ውዝግብ | አፍሪቃ | DW | 10.08.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

መፍትሔ ያላገኘው የደቡብ ሱዳን ውዝግብ

በደቡብ ሱዳን የሚካሄደው የርስ በርስ ጦርነት የሚያበቃበትን መንገድ የሚያፈላልገው ተቋርጦ የነበረው የሰላም ድርድር ባለፈው ሰኞ አዲስ አበባ ውስጥ ቢጀምርም፣ በደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር አንፃር የሚፋለሙት

የዓማፅያን ተደራዳሪ ቡድን ተወካዮች በዚሁ ከተቀናቃኞቹ ጎን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፣ የሲቭል ማህበረሰብ፣ የአፍሪቃ ህብረት፣ የተመድ ተጠሪዎች ተሳታፊዎች ከሆኑበት ምክክር ርቀዋል። ያማፅያኑ ተደራዳሪ ቡድን በዚሁ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ኢጋድ አደራዳሪነት በሚካሄደው እና እአአ እስከ ፊታችን ነሐሴ 12፣ 2014 ዓም ይቀጥላል ከተባለው ምክክሩ ያልተሳተፈበት ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም፣ ቡድኑ የዩጋንዳ ጦር አሁንም በደቡብ ሱዳን የሚገኝበት ድርጊት አንፃር በመጀመሪያው የስብሰባ ዕለት ተቃውሞውን ማሰማቱ ተደምጦዋል።

ያማፅያኑ ከምክክሩ መራቅ ለደቡብ ሱዳን ውዝግብ በቅርቡ በድርድር ፖለቲካዊ መፍትሔ ሊገኝ የሚችልበትን ሁኔታ አጠራጣሪ አድርጎታል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቻር ባለፈው ግንቦት ወር የሰላም ውል ቢፈራረሙም፣ ስምምነቱ የተፈረመበት ቀለም ገና ሳይደርቅ ነበር ውጊያው የቀጠለው፤ ይህ ዓይነቱ ኃላፊነት የጎደለው አሰራር የሀገሪቱን የመረጋጋት ዕድል እንዳመነመነው በኒው ዮርክ የተመድ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ዦሴፍ ሙም ማሉክ አስታውቀዋል።

« በወቅቱ የሚታየው ሁኔታ እንዲህ ሲቀጥል በቸልታ መመልከት አንችልም። ስለዚህ ዓማፅያኑ አሁን ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በታማኝነት እንዲደራደሩ እንጠብቃለን። »

ይሁን እንጂ፣ ካካባቢው የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ የሰላም ውል ለመድረስ በተጀመረው ጥረት ላይ እንቅፋት የደቀኑት ከድርድሩ የራቁት ዓማፅያን ብቻ አይደሉም፣ የመንግሥቱ ጦር ኃይል አባላት እና ከነርሱ ጋ የሚተባበሩት ሚሊሺያዎችም በየጊዜው በሲቭሎች ላይ ጥቃት ከመሰንዘር አልተቆጠቡም። የዩኤስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ሰሞኑን በዋሽንግተን በተካሄደው የዩኤስ አሜሪካ እና የአፍሪቃ ጉባዔ ላይ ከተሳተፉት የሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት መሪዎች ጋ በተገናኙበት ጊዜ በደቡብ ሱዳን የቀጠለውን የኃይል ተግባር እና ውጊያ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል ነቅፈዋል። የደቡብ ሱዳን ጎረቤት ሀገራት በዚችው ሀገር ለሚካሄደው ውዝግብ መፍትሔ ለማፈላለግ የጀመሩትን ጥረት ያሞገሡት አሜሪካዊው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በሚቀጥለው ሳምንት አንድ የልዑካን ቡድን ወደዚያ እንደሚልክ እና የሰላም የማውረድ ጥረቱንም እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።

ይህ ዓይነቱ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ጉብኝት የሚደገፍ ቢሆንም በአንድ ብቻ ተወስኖ እንደማይቀር የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት « ሂውማን ራይትስ ዎች » ተስፋውን ገልጾዋል። በደቡብ ሱዳን ከ400 የሚበልጡ የግጭቱ ሰለባዎችን እና ያይን ምስክሮችን በማነጋገር በዚያ የተፈፀሙ በደሎችን የዘረዘረ ሰነድ በትናንቱ ዕለት ያወጣው የ« ሂውማን ራይትስ ዎች » ባልደረባ ስካይ ዊለር ፣ የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ የጦር መሳሪያ ዕገዳ ሊጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

« በደቡብ ሱዳን የጦር መሳሪያ እጥረት የለም። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ከጥቂት ጊዜ በፊት ከቻይና ግዙፍ አዲስ የጦር መሳሪያ መግዛቱን ሰምተናል። እና በጦር መሳሪያ ላይ የሚደረግ እገዳ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ወደዚችው ሀገር እንዳይገባ ያከላክላል፣ ይህም እስካሁን በጣም ብዙ የመብት ረገጣ በታየበት ውዝግብ ውስጥ በሲቭሉ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ በደል እንዳይፈፀም ለማድረግ ይረዳል። »

Skye Wheeler

ስካይ ዊለር

ከዚህ በመቀጠልም የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አሁን ስምንተኛ ወሩን በያዘው እና በሺዎች የሚቆጠር ሰው ሕይወት ባጠፋው የርስ በርሱ ጦርነት ላይ የጦር ወንጀል የፈፀሙትን የተቀናቃኞቹን የደቡብ ሱዳን ቡድኖች አባላትን ለፍርድ ማቅረብ እንደሚኖርበት ስካይ ዊለር አክለው አስታውቀዋል። ይህን ርምጃ ሊወሰድ የሚችለው ግን ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ባላቸው የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ እና ቋሚ ባልሆኑት አባል ሀገራት መካከል ስምምነት ሲደርሱ ብቻ መሆኑን ስካይ ዊለር ሳያመላክቱ አላለፉም።

ከጥቂት ወራት በፊት ዩኤስ አሜሪካ እና የአውሮጳ ህብረት በሦስት ከፍተኛ የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና የተቀናቃኙ ቡድን ጦር አዛዦች ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል። አደራዳሪው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን፣ ኢጋድም የሰላሙ ድርድር ውጤት ካላስገኘ ተመሳሳይ ርምጃ እንደሚወስድ ዝቶዋል። በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና በተቀናቃኛቸው የቀድሞው ምክትል ፕሬዚደንት ሪየክ ማቸር ደጋፊዎች መካከል አሁን እንደገና የቀጠለው ደም አፋሳሽ ውጊያ በዋነኝነት የሚካሄደው በሰሜን ምሥራቃዊ የሀገሪቱ አካባቢ በሚገኘው የቡኒ ከተማ እና አቅራቢያዋ ሲሆን፣ ሰሞኑን ሚሊሺያዎች ስድስት የርዳታ ሠራተኞችን ከገደሉ በኋላ የተመድ 220 የሚጠጉ የራሱን እና የርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ሰራተኞችን ከደቡብ ሱዳን አስወጥቶዋል። ድርጅቱ በላዕላይ ናይል ግዛት ውስጥ የማባኔዝ መከላከያ ኃይላት በሚባሉት ሚሊሺያዎች እና ካካባቢው በመሸሽ ላይ ባሉት ወታደሮች መካከል በሚካሄደው ውጊያ በቡኒ ስጋት የተደቀነባቸውን ተጨማሪ ሠራተኞቹን እንደሚያስወጣ የተመድ ቃል አቀባይ ፋራን ሀቅ አክለው አስታውቀዋል የርዳታ ራተኞየተገደሉበት ደቡብ ሱዳን ሚሊሺያዎ ጥቃት ያነጣጠረው ቀደም ባለ ጊዜ በተካሄደ ውጊያ ጉዳት ደረሱባቸው ከጦሩ ከዱ የኑዌር ጎሳ አባላት ላይ ነበር። የተመድ በሰብዓዊ ርዳታ አቅራቢዎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ የጦር ወንጀል መሆኑን በማስታወቅ ድርጊቱን አውግዞታል።

ባለፈው ታህሳስ ወር በሳልቫ ኪር እና በሪየክ ማኸር መካከል በሥልጣን ሽኩቻ ሰበብ የፈነዳው ውጊያ በወቅቱ በፕሬዚደንቱ የዲንካ እና በማቻር የኑዌር ጎሣዎች መካከል ተስፋፍቶ ውዝግቡ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የተመድ ዋና ጸሐፊ የሰላም ማስከበሪያ ተልዕኮ ተከታታይ ክፍል ተጠሪ ኤድመንድ ሙሌት ገልጸዋል።

Rio de Janeiro Feier 10 Jahre Minustah UN in Haiti UN-Botschafter Edmond Mulet

ኤድመንድ ሙሌት

« ከሦስት ዓመት ነፃነት በኋላ ደቡብ ሱዳን አሁን እንደገና በአስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ አፋፍ ላይ እና ሰፊ አካባቢን የሚያጣቅስ ውስጣዊ ውዝግብ ውስጥ ትገኛለች። ይህ ሰው ራሱ የፈጠረው ቀውስ ነው። »

ኤድመንድ ሙሌት አክለው እንዳስታወቁት፣ ካለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ የቀጠለው ግጭት ከአንድ ሚልዮን የሚበልጥ ሰው አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ እና በርዳታ ላይ ጥገኛ እንዲሆን አድርጎዋል። ገበሬዎች በግጭቱ የተነሳ ማሳዎቻቸውን ማረስ እና መኸር መሰብሰብ ባለመቻላቸውም አራት ሚልዮን ሕዝብም የረሀብ ስጋት ተደቅኖበታል። ወደ 100,000 የሚጠጉ ደግሞ ራሳቸውን ከተቀናቃኞቹ ወገኖች ግጭት ለመከላከል በዚያ የተሠማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ ቅጥር ግቢዎች ውስጥ በተሰሩ መጠለያዎች ከለላ አግኝተዋል። የተለያዩ የርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በሀገሪቱ ግዙፍ የሰብዓዊ ርዳታ ስራ ቢጀምሩም የችግረኞቹ ስቃይ በቀላሉ የሚያበቃ አለመሆኑን ኤድመንድ ሙሌት በማስታወቅ ደቡብ ሱዳን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፈጣን ርምጃ እንዲወስድ ተማፅኖ አሰምተዋል።

« በደቡብ ሱዳን እየቀረበ ያለው የርዳታ ተግባር መጠን እስካሁን በየትኛውም የዓለም ሀገር ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶዋል። ይሁን እንጂ፣ የርዳታውን መጠን ለማሳደግ እና የርዳታውን ተግባር ለማንቀሳቀስ እስካሁን የቀረበው ገንዘብ በወቅቱ በዚያ ከሚታየው ግዙፉ የሕዝብ ፍላጎት ጋ በፍፁም ተመጣጣኝ አይደለም። »

የጀርመናውያኑ የዓለም የምግብ ድርጅት እንዳስታወቀው፣ በደቡብ ሱዳን በሚታየው ሰብዓዊ ቀውስ አንፃር አስቸኳይ ርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር ወደ 3,7 ሚልዮን የሚጠጋ የሀገሪቱ ሕዝብ ይራባል።

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic