መጻሕፍቶቼ መደበቅያዎቼ | ባህል | DW | 16.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

መጻሕፍቶቼ መደበቅያዎቼ

ከሃገር ከወጡ በኋላ በጣም ተስማምቶኛል ለማለት ትንሽ ያስቸግራል። ለምን ቢባል በሃገር ቤት ብዙ የለመድነዉ ነገር በመኖሩ ነዉ። በሃገር ቤት ያደግንበት ግርግሩ ጨዋታዉ ባልንጀራዉ ብቻ ሁሉም ነገር በስደት ዓለም አይገኝም። ንባብን ባህል በማድረጌ ግን አገሪ እንዳለሁ ያህል ይሰማኛል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:44

መጽሐፍ በማንበቤ ብዙም ከሃገር ቤት እንዳልርቅ አድርጎኛል

« ከሃገር ከወጡ በኋላ በጣም ተስማምቶኛል ለማለት ትንሽ ያስቸግራል። ለምን ቢባል በሃገር ቤት ብዙ የለመድነዉ ነገር በመኖሩ ነዉ። በሃገር ቤት ያደግንበት ግርግሩ ጨዋታዉ ባልንጀራዉ ብቻ ሁሉም ነገር በስደት ዓለም አይገኝም። አንድ ሰዉ በስደት ዓለም አዲስ አይነት ሕይወትን ነዉ የሚለማመደዉ። እናም በዚህ ሁሉ ዉስጥ የኔ መደበቅያ መጻሕፍት ሆነዋል ማለት ነዉ። » 

 

ለመደሰት፣ ለመዝናናት፣ ለመቆዘም፣ በባዕድ ሀገር ሆኜ ሀገሬን፣ ቤተሰቤን፣ ባልንጀሮቼን ሁሉ ስናፍቅ መሸሸጊያዬ ይለዋል መጽሐፍን። የወደደዉን መጽሐፍ ደራሲዉን ጠይቆ ነዉ የሚያነበዉ፤ ፈቃድ ካገኘ። እንዴት ደግሞ መጽሐፍን ገዝቶ አልያም ከባልንጀራ አልያም አለፍ ሲል ከቤተ መጽሐፍት ተዉሶ ማንበብ ነዉ እንጂ፤ ደራሲን መጠየቅ ያስፈልጋል? ትሉ ይሆናል። አዎ መጀመርያ ፈቃድ ይጠይቃል። ወጣት ኢዮብ ዮናስ ይባላል። ወደ ጀርመን ከመጣ ወደ አራት ዓመት እንደሆነዉ ይናገራል። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይ በፌስ ቡክ እና በዩቲዮብ በመጽሐፍ ንባብ በርካታዉ ተከታዮችን ያተረፈዉ ወጣት ኢዮብ መጽሐፍ ማንበብን ባህል ማድረግ አዋቂ ያደርጋል፤ ብሎም ከብዙ አልባሌ ነገሮች ይቆጥባል ሲል ይመክራል።

ደቡባዊ ጀርመን አቅጣጫ ባቫርያ ግዛት ዉስጥ በምትገኘዉ ቩርዝቡርግ ከተማ ነዋሪ የሆነዉ ወጣት ኢዮብ ዮናስ፤ መጽሐፍ ማንበብ የጀመረዉ ከልጅነቱ ቢሆንም፤ አሁን አሁን ግን በተለይ ወደ ጀርመን ከመጣ ወዲህ በጣም ብዙ መጽሐፍትን ከማንበቡ የተነሳ ከሃገር ቤት እንዳልራቀ ሁሉ እንዲሰማ እንዳደረገዉ ይናገራል።

«ድሮም ከልጅነቴ መጻሕፎች አነባለሁ ግን አሁን ባለኝ ትርፍ ጊዜ መጽሐፎችን አነባለሁ። ጓደኞቼ መጻሕፍቶች ናቸዉ ማለት እችላለሁ። መጽሐፍ በማንበቤ ብዙም ከሃገር ቤት እንዳልርቅ አድርጎኛል። 

የአዲስ አበባ ልጅ እንደሆነ የሚናገረዉ ወጣት ኢዮብ በአሁኑ ወቅት በጀርመን ቋንቋ ይማራል። ትንሽ ሥራም ይሠራል፤ በትርፍ ጊዜዉ ደግሞ ምርጥ ያላቸዉን መጽሐፍት በመተረክ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለአድማጭ በትረካ መልክ ያቀርባል። ኢዮብ መጽሐፍን በትረካ መልክ የማንበብ ፍቅርን ያገኘዉ እዚህ ጀርመን ከመጣ ይሆን?    

«በርግጥ ታሪኩ ረጅም ነዉ። የማንበብ እና የትረካ ፍላጎቱ የነበረኝ ከልጅነቴ ቢሆንም በልጅነቴ ቤተ- ክርስትያን አካባቢ በተለይ ሰንበት ትምህርት ቤት ቅዳሜና እሁድ ፤ ኪነ-ጥበባዊ የሆኑ ነገሮች ይቀርብ ነበር።  በዝያን ጊዜ ሰዉ በቀጠሮዉ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ስምንት ሰዓት ላይ አይመጣም ነበር። የማይመጣበት ምክንያት ደግሞ በቴሌብዥን በሃያ የተባለዉ ፕሮግራም በመኖሩ ሰዉ እሱን ለመከታተል ስለሚፈልግ ወደ ቤተ ክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤት መምጣቱን ይተወዋል። ከዝያ ሰዉ ወደ ቤተ ክርስትያን እንዲመጣ ምን እናድርግ ብለን እቅድ ስናወጣ፤ ያዉ መቶ ሃያ የተባለዉን ፕሮግራም እራሳችን ወደ ቤተክርስትያን አናመጣዉም ። ለምንስ በመንፈሳዊ ዝግጅቶች እንደመቶሃያ ሁሉ ዜና ትረካ ድራማ አንሰራም ብለን ተማከርን። ከዝያም ጀመርን ። እኔም ይህን ትረካ እና ሌሎች ዝግጅቶችን በሰንበት ትምህርት ቤት ነዉ የጀመርኩት። ማንበብ ትረካ ከልጅነቴ የነበረ ፍላጎት በመሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤቱ ዝግጅት ፍላጎቴን እንዳዳብር ረድቶኛል። ኢትዮጵያ ሳለሁ መጽሐፍ እያነበብኩ ራሴን እየቀዳሁ በካሴት አስቀምጥ ነበር።

እዚህ ጀርመን ስመጣ ደግሞ የማኅበራዊ መገናኛዉን ሳየዉ ሰዎች በተለያየ ዘዴ እና ፍላጎት ነዉ የሚጠቀሙት። እኔም ታድያ ሰዎች ትረካዬን እንዲያነቡ መጽሐፍ እያነበብኩ በሶሻል ሚዲያዉ አላስተላልፍም ብዬ ራሴን ጠየኩ። እንደቀልድም ጀመርኩት። አሁን በጣም ብዙ ሰዎች ይከታተሉኛል።  ረጃጅም  መጽሐፍቶችን እተርካለሁ። ሌላዉ መንፈሳዊ መጽሐፍቶችንም አነባለሁ።» 

ኢዮብ ዩናስ እንደሚለዉ አብዛኞች ተከታታዩቹ ድምፁን እንደሚወዱለት በተለይ ድምፅህ የራድዮ ድምፅ ነዉ እንደሚሉት ይናገራል። መጽሐፉንም ሲተርክ በመጽሐፉ ዉስጥ የሚገኙትን ገፀ-ባሕርያትን ተላብሶ የድምጽ አወጣጡ ቅላፄዉ ሁሉ በትረካዉ ዉስጥ ይደመጣል። ኢዮብ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያዉ ትረካዉን ለአድማጭ ጆሮ ከማድረሱ በፌት ልምምድ ያደርግ ይሆን?  በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በመጽሐፍ ትረካዉ ከሚታወቀዉ ከኢዮብ ዮናስ ጋር የተደረገዉን ሙሉዉን ቃለ ምልልስ የድምጽ ማድመቻ ማዕቀፉን በመከጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

 

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች