መጪው የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት የጋና ጉብኝት | ኢትዮጵያ | DW | 04.07.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

መጪው የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት የጋና ጉብኝት

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ለሁለት ቀናት ይፋ ጉብኝት በሚቀጥለው ዓርብ ወደ ጋና ይጓዛሉ። ባራክ ኦባማ የፕሬዚደንትነቱን ስልጣን ከያዙ ወዲህ ከሰሀራ በስተደቡብ ያለው የአፍሪቃ ከፊል ሲጓዙ ይህ የመጀመሪያቸው ይሆናል።

default

የጋና መዲና አክራ

በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የአሜሪካዊው ፕሬዚደንት የውጭ ፖሊሲ አጀንዳ ላይ አፍሪቃ ቀዳሚውን ቦታ አልያዘም። ኢራቅና አፍጋኒስታን፡ ኢራንና ሰሜን ኮርያ፡ ነበሩ ትልቁን የዩኤስ አሜሪካ መስተዳድር ትኩረት ያገኙት። ይሁን እንጂ፡ ፕሬዚደንት ኦባማ በምዕራባዊ ሱዳን በዳርፉርና በደቡብ ሱዳንም የቀጠለውን ውዝግብና በሰበቡም የተከተለው ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያሳስባቸው በማስታወቅ፡ በጡረታ ላይ የሚገኙትን የቀድሞ የአየር ኃይል ሜጀር ጀነራል ስኮት ግረንን ልዩ የሱዳን ልዑካቸው አድርገው ሰይመዋል። ግሬሸን ሁለቴ ወደሱዳን በመጓዝ ሁኔታዎችን ከተመለከቱ በኋላ የዩኤስ አሜሪካ መስተዳድር ከጥቂት ቀናት በፊት የሰላሳ ሁለሀት ሀገሮች እና ድርጅቶች ተወካዮች፡ እንዲሁም የኢትዮጵያና የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የተሳተፉበት አንድ የሱዳን ተመልካች ስብሰባ በዋሽንግተን መጥራታቸው የሚታወስ ነው። በቅርቡም ከሱዳን ዓማጽያን ጋር እንደሚገናኙም ተሰምቶዋል።
ፕሬዚደንት ኦባማ ከጥቂት ሳምንታት በፊትም በዋሽንግተን ከዚምባብዌ ጠቅላይ ሚንስትር ሞርገን ቻንጊራይ ጋር ተገናኝተው ይህችው ደቡባዊት አፍሪቃ ሀገር ስለምትገኝበት አሳሳቢ ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ ተወያይተዋል።
አፍሪቃውያን ፖለቲከኞች፡ እንዲሁም አፍሪቃውያኑ ሲቭል ማስበረሰብ ከፕሬዚደንት ኦባማ የጋና ጉብኝት ብዙ እንደሚጠብቁ ነው የሚሰማው። ይሁን እንጂ፡ የዶይቸ ቬለ የአፍሪቃና የመካከለኛው ምስራቅ ክፍል ኃላፊ ኡተ ሼፈር በዩኤስ አሜሪካ የአፍሪቃ ፖለቲካ ላይ በርግጥ ለውጥ ይደረግ ይሆን ወይስ ያለፈው መንግስት ፖሊሲ ይቀጥላል ስትል አጠያይቃለች።
ፕሬዚደንት ኦባማ ከሰሀራ በስተደቡብ ካሉት አፍሪቃውያት ሀገሮች መካከል ጋናን በመጀመሪያ ለመጎብኘት ሲመርጡ ምን መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልገው ነው? እአአ በ 1957 ዓም ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ በመላቀቅ በአፍሪቃ ነጻ መንግስት ያቋቋመችው ጋና በአህጉሩ የተሳካ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ያሳየች በአርአያነት የምትጠቀስ ሀገር ናት። የፕሬዚደንት ኦባማ መስተዳድር በ 2009 ዓም መጀመሪያ ላይ የስልጣን ለውጥ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተካሄደባት ሀገር ጋና አዘውትሮ መፈንቅለ መንግስት ለሚካሄድባቸውና ምርጫ መጭበርበር ለሚታይባቸው ብዙዎቹ አፍሪቃውያት ሀገሮች ሞዴል ሆና ነው የሚያያት። በዚህም የተነሳ ነው ኦባማ ጋናን የመጀመሪያዋ የጉብኝታቸው አድራሻ ያደረጉት ይላሉ ኬንያዊው የፖለቲካ ተንታኛ ማቻያያ ሙኔኔ፡ ሌሎች ምክንያቶችንም ሙኔኔ ጠቅሰዋል።
« ጋና በያዘችው ታሪካዊ ትርጓሜ የተነሳ እንደ አርአያ ትታያለች። የጸረ ቅኝ አገዛዙን ትግል ስንመለከት፡ ጋና ነበረች ነጻነትዋን የተጎናጸፈች የመጀመሪያዋ አፍሪቃዊት ሀገር። መሪዋ ክዋሜ ንኩርማህም በአፍሪቃ ብቻ ሳይሆን፡ በዩኤስ አሜሪካም በሰብዓዊ መብት ንቅናቄም ላይ የነጻነት ምልክት ሆነዋል። እና የእስካሁኑ የአፍሪቃ ፖሊሲያቸውን በተመለከተ ግልጹን አቅጣጫ ያመላከቱት ፕሬዚደንት ኦባማ ወደ ጋና ሲሄዱም ይህንኑ ይበልጡን ግልጽ ያደርጋሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። »
ዩኤስ አሜሪካ በአህጉሩ ልትደግፋቸው በምትፈልጋቸው ኤኮኖሚያዊውና ፖለቲካዊው ዕድገት፡ ግልጽነት የሚታይበት የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፡ፖለቲካዊ ኃላፊነት እና ኃላፊነት የሚታይበት ጸረ ድህነቱ ትግል፡ ትምህርትና ዕድገትን በማራመዱ ተግባር ረገድ ጋና ጥሩ ውጤት አስመዝግባለች። ጋና ከዚህ በተጨማሪም ከዩኤስ አሜሪካ ጋር ማለፊያ ግንኙነት አላት። ይህም ራሱ ሌላ ምክንያት መሆኑን የኒው ዮርክ የኮንወል ዩኒቨርሲቲፖለቲካ ተንታኝ ኒከላስ ፋን ደር ቫል ገልጸዋል።
« ጋና የተመረጠችበት ድርጊት የዩኤስ አሜሪካ መስተዳድር ባካባቢው ዴሞክራሲያዊውን ሂደት ለማበረታት ያለውን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነው። የተሳካው የኤኮኖሚ ዕድገት ላካባቢው የያዘውንም ትርጓሜ ለማጉላት ያለውን ፍላጎት ያሳያል። »
የኦባማ የመጀመሪያ የጉብኝት አድራሻ ጋናን በመሰለ ሀገር ላይ ማረፉ የኦባማ መስተዳድር የአፍሪቃ ፖለቲካ የቀድሞው ፕሬዚደንት ቡስ መስተዳድር በአህጉሩ የጀመሩትን የመቀጠል ፍልጎት መኖሩን አረጋግጦዋል። የቡሽ መስተዳድር አፍሪቃ ኤኮኖሚያዊና የጸጥታ ጥበቃ ትርጓሜ የያዘች አህጉር አድርጎ መመልከቱ ይታወሳል። የነዳጅ ዘይትና ሌላ የተፈጥሮ ሀብት፡ እንዱሁም፡ አፍሪቃ የአሸባሪዎች መናኸሪያ እንዳትሆን ለማድረግ የቅርብ የጸጥታ ጥበቃው ፖለቲካ የቅርብ ትብብር ሊኖር እንደሚገባም መጣሩ አይዘነጋም። የዩኤስ አሜሪካ መስተዳድር እነዚህ በተመለከትያለፈው የቀድሞው የሀገሩ መስንግስት የተከተለውን ፖሊሲ እንደሚቀጥልበት የታወቀ ነው። ከኬንያዊ አባት በሚወለዱት በኦባማ አመራርም ጊዜ ቢሆን አፍሪቃ ድንገት የዩኤስ አሜሪካ የውጭ ፖለቲካ ቀዳሚ ትኩረት የምታገኝ አህጉር አትሆንም። ሆኖም፡ ከመጀመሪያ ጥቁር አሜሪካዊ ፕሬዚደንት አህጉሩ ብዙ ሊጠብቅ እንደሚችል ኬንያዊው የፖለቲካ ተንታኝ ሙኔኔ አስታውቀዋል።
« ሁሉም አፍሪቃውያን ኦባማ ከአፍሪቃ ጋር ባለው ግንኙነትም ላይ ሀገራቸው የያዘችው አቋም አዎንታዊ እንዲሆን ያደርጋሉ የሚል ትጽቢት አሳድረዋል። ዩኤስ አሜሪካ እንደ አዛዥ፡፡አፍሪቃውያን ደግሞ እንደ ጥገኞች የምታይበትን አሉታዊ አመለካከት እንዲያበቃ ነው የሚጠብቁት። የእስካሁኑ አሰራር ይህን ይመስላል። እና ዩኤስ አሜሪካ ወደፊት ለአፍሪቃውያኑ የበለጠ ክብር ታሳያለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። »
አፍሪቃውያኑ ልክ የራሳቸው እንደሆኑ ያህል ከሚኮሩባቸው ከኦባማ በሀቀኛው ትብብር ላይ የተመሰረተውን ጉድኝት ነው የሚጠብቁት።
« የእኩልነትን መልዕክት ያስተላልፋሉ ብለን እንጠብቃለን። አፍሪቃውያት ሀገሮችና ህዝቦቻቸው እንዳሁኑ ሳይሆን፡ ወደፊት በእኩልነት የሚታዩበትን ፖሊሲ እንዲከተሉ እንሻለን። ይህ ፡ የሚቀርበውን ርዳታ ወይም የርዳታውንመጠን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ጉዳዩ የአሜሪካውያኑ ምርቶች በአፍሪቃ ገበያዎች ቦታ እንዳገኙት ሁሉ። የአፍሪቃውያን ምርቶችም በአሜሪካውያኑ ገበያዎች ተመሳሳዩን ቦታ ማግኘት ይኖርባቸዋል። »
ኦባማ በጋና ምክር ቤት ያሰሙታል በሚባለው ዓቢይ ዲስኩራቸው ላይ በአህጉሩ መልካም አስተዳደር የሚስፋፋበትና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት የሚተከሉበት አሰራር የያዘውን ትርጓሜ ማጉላታቸው እና የአፍሪቃ ፖሊሲያቸው ምን ሊመስል እንደሚችል ባጠቃላዩን ገጽታ መስጠታቸው እንደማይቀር ይጠበቃል። ኦባማ አፍሪቃውያን መንግስታት የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡበት እና ሙስናን የሚታገሉበት አሰራር አስፈላጊነትን በማጉላት ያጎላሉ። አፍሪቃ ኤኮኖሚያዊን ዕድገት ታዳብር ዘንድ የኦባማ መስተዳድር ለማገዝ በማሰብ የኦባማ አስተዳደር ሀገራቸው ካሁን ቀደም ያዘጋጀችውን በምህጻሩ «አጎአ» የሚሰኘውን አርባ ሀገሮች ተጠቃሚ የሆኑበትን የአፍሪቃ ዕድገት እና የአጋጣሚ ሰነድለማስፋፋት ዕቅድ አለው። ፕሬዚደንት ቡሽ በአስር የፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ ሶስት ነጥብ ስምንት ቢልዮን ዶላር በመመደብ ኤች አይቪ ኤድስንና ወባን ለመታገል ያነቃቁትን መርሀ ግብርንም እንደሚገፋበት ተገልጾዋል።

አርያም ተክሌ