መጤ ባለሙያዎች በጀርመን | ኤኮኖሚ | DW | 13.02.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

መጤ ባለሙያዎች በጀርመን

ጀርመን ውስጥ የሚገኙት በትውልድ አገራቸው በሙያ የሰለጠኑ መጤዎች ኑሮ አብዛኛውን ጊዜ ቀላል አይደለም። ለዚህም ምክንያቱ በአገራቸው የተማሩት ሙያ ዕውቅና አለማግኘት ሆኖ ቆይቷል። ሜካኒኩና የቴክኒክ ባለሙያው በታክሲ ሾፌርነት፤ ሕጻናት አሳዳጊዋና ነርሷ በጽዳት ሥራ፤

እንዲሁም ኢንጂነሩ በአነስተኛ ማሕበራዊ ድጎማ የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን መግፋታቸው በጣሙን የተለመደ ነገር ነው። በጥቅሉ ጀርመን ውስጥ ብዙ መጤዎች በሰለጠኑበት ሙያ ተቀጥረው ለመሥራት አልበቁም።

ለዚህም ምክንያቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በውጭ የሙያ ትምህርቱን ያጠናቀቀ መጤ ዕውቅና ሊያገኝ የሚችልበት ምርመራ አለመኖሩ ነበር። አሁን በመጠኑም ቢሆን ተመስገን ነው ካለፈው ሚያዚያ ወር 2012 ዓ-ም ወዲህ የቀድሞው ሁኔታ ተለውጧል። ለዚህ ደግሞ በተለይ በዚህ በጀርመን ሰፍኖ የሚገኘው በሙያ የሰለጠነ የሥራ ሃይል እጥረት በአንድ በኩል እንዲሁም የሕብረተሰቡ እያረጀ መሄድ በሌላ አነሳሽ ምክንያቶች መሆናቸው አልቀረም።

ለነገሩ ዛሬ ሶሥት ሚሊዮን ሕዝብ በሥራ አጥነት በይፋ ተመዝግቦ በሚገኝባት በጀርመን ከ 850 ሺህ የሚበልጥ የሥራ ቦታ የሚይዘው አጥቶ ነው የሚገኘው። ለምሳሌ በብዙ የዕጅ ጥበብ የሙያ መስኮች የሰለጠነ የሥራ ሃይል በጣሙን ይጎላል። ታዲያ በዚህ ጉዳይ የጎደለውን ለማሟላት ለውጥ ማስፈለጉ አልቀረም። በመሆኑም የጀርመን መንግሥት አዲስ የቀጠራ ደምብ በዚህ ዓመት አጋማሽ በፊታችን ሐምሌ ወር ላይ እንደሚጸና ነው የሚጠበቀው።

የጀርመን መንግሥት ቀደም ሲል በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ምሁራን ወደ አገር እንዲገቡ ማቃለያ ዕርምጃ ሲወስድ አረንጓዴ ካርድ በሚል በጊዜ የተገደበ ፈቃድ በመስጠት ከሕንድ የኤሌክትሮኒክ ኤክስፐርቶችን ለመሳብ ቀድሞ የተደረገው ሙከራ ግን እንደታሰበው ስኬታማ ሣይሆን ቀርቷል። የአውሮፓ የኤኮኖሚ ትብብር ድርጅት OECD የሚያሳስበው ጀርመን በሁለቱም መስኮች፤ ማለትም ምሁራንንና የሰለጠኑ ሙያተኞችን በመሳቡ ረገድ እስካሁን ከታየው በበለጠ መጠን በሯን በዓለምአቀፍ ደረጃ መክፈቷ ግድ እንደሆነ ነው።

የድርጅቱ ምክትል ጠቅላይ ጸሃፊ ኢቭ ሌቴርም እንደሚሉት ጀርመን በሕብረተሰቡ የማርጀት ሂደት የተከተለውን የሙያተኛ እጥረት ለማለዘብ ይህን ዕርምጃ የግድ መውሰድ ይኖርባታል። ሆኖም ግን አገሪቱ ማሻሻያ ዕምጃዎችን መውሰዷ ባይቀርም ከአውሮፓ ሕብረት ውጭ በያመቱ የምታስገባቸው በሙያ የሰለጠኑ ሠራተኞች ቁጥር ከ 25 ሺህ አይበልጥም። ይህ ከካናዳ ወይም ከአውስትራሊያ ቢነጻጸር በአሥር ዕጅ ያነሰ ነው የሚሆነው። እናም ጀርመን በሯን በሰፊው መክፈት አለባት መባሉ ለዚህ ነው።

የሰለጠኑ ሙያተኞችን እጥረት አስመልክቶ በጀርመን የሥራ ገበያ ላይ ወሣኝ ለውጥ ካልተደረገ በ 2025 ገደማ፤ በአሥር/አሥራ ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሙያተኛው ቁጥር ከዛሬው አንጻር በስድሥት ሚሊዮን ያነሰ እንደሚሆን ነው የሚታመነው። ይህ ደግሞ እያበበ ለሚሄደው የጀርመን ኤኮኖሚ መርዝ እንደሚሆን ነው በጉዳዩ ላይ አተኩረው የሚገኙ ጠበብት የሚናገሩት። የጀርመን መንግሥት ደግሞ ይህን አላጣውም። እናም ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት ሁኔታውን ለማሻሻል ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይታወሳል።

የዚሁ ዕርምጃ አንድ አካልም በውጭ ሃገራት ትምሕርታቸውን ላጠናቀቁ መጤዎች ዕውቅና ለመስጠት ጥርጊያ የሚከፍት ሕግን ማስፈን ነበር። ይህም ሕግ ካለፈው ዓመት ወዲህ ሕያው ሲሆን የጀርመን ፌደራል የትምሕርትና የምርምር ሚኒስቴር ተቋም ባልደረባ ራልፍ ማየር እንደሚያስረዱት ትልቅ ለውጥ ነው።

«እስካሁን መጤዎች የሚታዩት ከተረጂነት አንጻር ብቻ ነበር። አሁን ግን በውጭ አገር ለጀርመን የሥራ ገበያ ጠቃሚና ተፈላጊ የሆነ ጥሩ የሙያ ስልጠና ያጠናቀቀ መቅጠር ተጀምሯል»

ጀርመን ውስጥ ከሚኖሩት ሶሥት ሚሊዮን ገደማ የሚጠጉ የሙያ ትምሕርት ያጠናቀቁ መጤዎች መካከል ሁለት ሚሊዮኑ በውጭ አገር ትምሕርታቸውን የጨረሱ ናቸው። ከነዚሁ በርካቶቹም ጀርመን ከገቡ አንስቶ በትምሕርት እንዳልታነጹ ሲቆጠሩና በአገሪቱ የሥራ ገበዮች ላይም ዕድል አጥተው ነው አሠርተ-ዓመታት ያሳለፉት። አሁን የትምሕርታቸው ደረጃ ተጠንቶ በአግባብ ማዕረግ እንዲሰጠው የማስደረግ ሕጋዊ መብት አላቸው። ይህም ጉዳዩ የሚመለከተው የጀርመን ፌደራል ምጣኔ-ሃብት ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ባልደረባ ኡልሪሽ ሽንላይትነር እንደሚሉት ለተቋማቸው ፈታኝ መሆኑ አልቀረም።

«የአንድን የውጭ ሥልጠና ደረጃ ከጀርመኑ ጋር ማነጻጸሩ በጣም ከባድ ነገር ነው። እኛ እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ያለን ሲሆን ይሄው ከንቱ ሆኖ እንዲቀር አንፈልግም። ስለዚህም የትምሕርቱ ደረጃ ምን ያህል እንደሆነ በትክክል መጣራትና ምናልባት ጉድለት ካለም በትክክል መሟላት ይኖርበታል»

በሙያው ሥልጠና ዘርፍ እስካሁን ለጀርመን ኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤት በውጭ አገር ትምሕርታቸውን ያጠናቀቁ ከሶሥት ሺህ የሚበልጡ መጤዎች ማመልከቻዎች ለዕውቅና ቀርበው ይገኛሉ። ከነዚሁ ሰባት መቶ የሚሆኑት መጤ የሰለጠኑ ሙያተኞችም ተሳክቶላቸው ተቀባይነት አግኝተዋል። የትኛው የሙያ ስልጠናና ከየት አገር የመነጨው ከጀርመኑ እንደሚመሳሰል ወይም እኩል እንደሚታይ ለማነጻጸር አስፈላጊውን መረጃ BQ-Portal ከተሰኘው የኢንተርኔት ፕሮግራም ማግኘት ይቻላል።

ይሄው የጀርመን ኤኮኖሚና ሣይንስ ዘርፎች የጋራ ፕሬዤ ሲሆን ፕሮግራሙ የሚራመደው በፌደራሉ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት በመደገፍ ነው። የፕሮዤው ሃላፊ የጀርመን የምጣኔ-ሃብት ኢንስቲቲዩት ባልደረባ ዲርክ ቨርነርም እንዲሁ ጉዳዩ ፈታኝ መሆኑን ነው የሚናገሩት። ቨርነር እንደሚሉት አንድን ከፖላንድ የመነጨን ቀቃይ በቀላሉ ደረጃው ይሄ ነው ብሎ መደልደል አያዳግትም። ግን እንበል ከኡጋንዳ የመጣውን መመዘኑ ከባድ እንደሚሆን ነው የሚነገሩት።

«የሙያ ስልጠና ስርዓታቸው ከኛ ሲነጻጸር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለ ብዙ ሃገራት አሉ። ይህን በግልጽ መናገር ያስፈልጋል። በአንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ምናልባት የስልጠና ደምቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን አሳሪነት የሌላቸው የሃሣብን ያህል ሆነው ነው የሚታዩት። እንግዲህ ደረጃና ጥራትን የሚመለከተው መስፈርት ለየት ያለ ሲሆን የምሥክር ወረቀቶቻቸው በሚቀርቡበት ጊዜ ምን ያህል ደሞዝ እንደሚገባቸው መወሰኑ ቀላል አይሆንም። እንደ አገሩና እንደ ሙያው ዓይነት የተለያዩ ምላሾች ይኖራሉ ማለት ነው»

በኢንተርኔቱ መረጃ ፕሮግራም ላይ እስካሁን የሃያ ሃገራት መለያ ዳታዎች ተሰብስበው ይገኛሉ። የዕውቅና ፈላጊዎቹ ማመልከቻዎች ግን 80 ሃገራትን የሚያዳርሱ ናቸው። ጥንቃቄ በተመላው ግምት መሠረት ዛሬ ቢያንስ 200 ሺህ በጀርመን የሚኖሩ መጤዎች የሚሰሩት ከሙያ ደረጃቸው በታች ነው። በበርሊን የአንድ የትምሕርት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ኒሃት ሶርጌች እንደሚሉት እነዚሁ ከጊዜ ጋር ሁኔታውን በመቀበል አንዳች ነገር ለመለወጥ ሃሞት የላቸውም።

«ባለፉት ዓመታት የተወሰነ የቸልተኝነት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሁሉን ነገር የመተው ስሜት የተስፋፋ ሲሆን ከባሕሉ በቀላሉ መቀላቀል አለመቻሉም በመጤው አስተሳሰብ ላይ የባዕድነት ተጽዕኖን እያጠነከ መሄዱ አልቀረም። ስለዚህም ይሄው ወገን ወደ ኋላ እያሸገሸገ ማሸለቡን ነው የመረጠው። እና እንዲነቃ መቀስቀስና ሕብረተሰቡ እንደሚቀበለው ስሜት እንዲያድርበት ማድረጉ ግድ ነው»

ሕጋዊ መብት መኖሩ ብቻውን አይበቃም። የዕውቅናው ሕግ በሁሉም ደረጃ ህያው እንዲሆን መደረግ ይኖርበታል። የትምሕርት ሚኒስቴሩ ባለሥልጣን ራልፍ ማየር እንደሚሉት እርግጥ ነገሩ ቀላል አይደለም። በተለይም ፋይሎቹን በሚመለከቱት የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች ዘንድ ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ መደረጉ አስፈላጊ የሚሆን ነው የሚመስለው።

«እነዚህ በጥቂቱም ቢሆን የጥሩ መስተንግዶ ባሕልን መማርና ሕጉንም ሕይወት መስጠት አለባቸው። ይህ ነው የወቅቱ ታላቅ ፈተና! በኢንዱስትሪና በንግድ ም/ቤቶች አኳያ ሁኔታው የተሻለ ነው። እነዚሁ ለኢንዱስትሪዎቹ የቀረቡ ሲሆኑ ፍላጎታቸውንም በሚገባ ያውቃሉ። ግን ለምሳሌ የሕክምናን ወይም የነርስነትን ሙያ በተመለከተ ምርመራውን የሚያካሂዱት የመንግሥት ጤና ጥበቃ ተቋማት ሲሆኑ እነዚህ ደግሞ የኩባንያዎቹን ያህል የሠራተኛ እጥረት ግፊት የሚሰማቸው አይደሉም»

ሌላው መሰናክል ለዕውቅናው ተግባር የሚያስፈልገው ወጪ ነው። ለአንድ ውስብስብ ለተባለ የትምሕርት ደረጃ ማጣሪያ ምርመራ በልምድ 600 ኤውሮ ገደማ የሚያስፈልግ ሲሆን ወጪው እስከ 2000 ኤውሮ ሊዘልቅም የሚችል ነው።

«በወጪው መጠን ላይ በዕጅ ያሉት ሰነዶችና ገና ተፈልገው መቅረብ የሚኖርባቸው ሰነዶች ብዛት ወሣኝነት አለው። ኦሪጂናል የምስክር ወረቀቶችን ማቅረብ ካልተቻለና ሰለ ምንጩ አገር የትምሕርት ስርዓት መረጃ ከሌለ ደግሞ ሁኔታው ይበልጥ ከባድ ይሆናል። ይህን መሰሉ ሁኔታዎች በብዛት ሲከሰቱ የዘመናቸውን ርዝመት ያህል ለምርመራ ከባድ የሚሆኑም ናቸው። በከፊል የትምሕርት ተቋማቱ ሕያው አይደሉም፤ በከፊል ከሌሎች ሃገራት ጋር ለመተባበር ፍላጎት የላቸውም ወይም ከናካቴው ፍቱን አይደሉም»

ያም ሆነ ይህ የትምሕርት ደረጃቸውን ለማስመርመር የሚፈልጉት መጤዎች ወጪውን በተመለከተ ብቻቸውን አይተዉም። እንደ ሙያው ተፈላጊነትና ክብደት በጀርመን የሥራ ቢሮ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የሚሸፈን ይሆናል። የጀርመን ሕብረተሰብ ዛሬ ከአርባ በመቶ ባላነሰ መጠን መጦሪያ ደረጃ ላይ በደረሰበትና በሰፊው ባረጀበት ወቅት በማሕበራዊ እንክብካቤና መሰል ዘርፎች የሙያተኛው እጥረት ጎልቶ ሲሄድ ነው የሚታየው። በመሆኑም መጤ ባለሙያዎችን ዕውቅና በመስጠቱም ሆነ አዳዲስ ባለሙያዎችን በማሰልጠኑ ረገድ ቢሮክራሲና ግትር የአሠራር ዘይቤ እየለዘበ መሄዱ ግድ ነው።

መጤው የሰለጠነ ሠራተኛ ዛሬ በጀርመን ጠቃሚ የኤኮኖሚ ሃይል ሊሆን መቻሉ መዘንጋት የለበትም። ስለዚህም የዕውቅናውን ሂደት ማፋጠኑ በጣሙን አስፈላጊ ይሆናል። እስካሁን ካለው ልምድ አንጻር እርግጥ ተግባሩ ገና ጊዜ መውሰዱ የማይቀር ነው የሚመስለው።

መስፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 13.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17YVp
 • ቀን 13.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17YVp