መጠናከር የሚሻ የህክምና ዘርፍ | ጤና እና አካባቢ | DW | 05.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

መጠናከር የሚሻ የህክምና ዘርፍ

በዓለም ላይ 80 በመቶዉ የሚሆነዉ የማህፀን በር ካንሰር ተጠቂ የሚገኘዉ አዳጊ ሃገራት ዉስጥ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።

ለዚህ ዋና ምክንያቱም ችግሩ ስር ሳይሰድ ለማወቅ የሚያስችለዉ የህክምና ባለሙያዎቹ ስክሪኒንግ የሚሉት ምርመራ በወቅቱ ስለማይደረግ መሆኑን እዚህ ጀርመን ሃይሊገንሽታት በተካሄደዉ የፅንስና ማህፀን ህክምና ባለሙያዎች ጉባኤ ላይ ተገልጿል። ኢትዮጵያ ዉስጥም በርካታ ሴቶች ለዚህ መጋለጣቸዉ ነዉ የተነገረዉ።

ዶክተር አና ኪፈር በጀርመኗ ቱሪንገን ከተማ አይሽፌልክ ክሊኒክ ዉስጥ የፅንስና ማሕፀን ህክምና ከፍተኛ ባለሙያ ሲሆኑ ላለፉት ሰባት ዓመታት በተጠቀሰዉ ሃኪም ቤት የክፍሉ ኃላፊ ናቸዉ። ዶክተር አና ኪፈር እና ኢትዮጵያዊዉ የሥራ ባልደረባቸዉ ዶክተር ደብሩ ጉባ አዲሴ በጋራ በመሆን እዚህ ጀርመን የሚገኝ የዘርፉ ህክምና ባለሙያዎች ማኅበርን ያካተተ በአዳጊ ሃገራት በስነተዋልዶ ጤናዉ ዘርፍ የልማት ትብብር እንቅስቃሴ ያካሂዳሉ።

የዘርፉ ትብብር ከምርምርና የልምድ ልዉዉጥ ባሻገር፤ በሙያዉ የተሠማሩ ሃኪሞች ተጨማሪ ስልጠናና እንዲያገኙ ማድረግ አንዱ ነዉ። ዶክተር ኪፈር እንደገለፁልኝም ከዶክተር ደብሩ ጋ በመሆን ከስድስት ዓመታት በፊት በጀመሩት ኢትዮጵያዉያን የዘርፉ ሃኪሞች ቀጣይ የሙያ ማጎልበቻ መርሃ ግብር እስካሁን ከሰላሳ 30 የሚበልጡ ኢትዮጵያዉያን ወጣት የዘርፉ ባለሙያዎች የድርህረ ምረቃ ትምህርት ተሳታፊ ሆነዋል። እናም ጀርመን የሚገኙት እነዚህ የጤና ባለሙያዎች የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚነጋገር በየዓመቱ የሚያካሂዱት ጉባኤ አለ። ዘንድሮ ትኩረት ያደረገዉ በተለይ አዳጊ ሃገራት ዉስጥ በስፋት እንደሚታይ የሚነገርለት የማሕፀን በር ካንሰር ላይ ሲሆን ኢትዮጵያ ዉስጥ በተደረገ ምርምር የተደገፈ ነበር። ዶክተር ሃና ኪፈር ከጥናቱ የተገኘዉን ሲገልጹም፤

«ኢትዮጵያ ዉስጥ የማህጸን በር ካንሰርን የሚያመጣዉ ሌላ አይነት ቫይረስ ነዉ ተብሎ ይገመት ነበር። ሆኖም በርከት ያሉ ነፍሰጡር እናቶች ላይ የተደረገ ምርመራ ያመለከተዉ ይህን ካንሰር የሚያመጣዉ ቫይረስ አዉሮጳም፤ አሜሪካም፤ እስያም ካለዉ ጋ ተመሳሳይ መሆኑን አሳይቷል። እንግዲህ ይህ ከተሰሩ ምርምሮች አንዱ ማሳያ ነዉ።»

Krankensaal im Fistula Krankenhaus in Abbis Abeba

ዶክተር ኪፈር በምህጻሩ HPV የተሰኘዉ ቫይረስ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላዉ ያለም ለማህጸን በር ካንሰር መንስኤ መሆኑን ጥናቱ ማረጋገጡንም አብራርተዋል። ይህም ለወደፊቱ በሌላዉ ዓለም በተለይም በአዉሮጳ ይህን ለመከላከል የሚያስችለዉ ክትባት ኢትዮጵያ ዉስጥም ምንም እንኳን ክትባቱ እጅግ ዉድ መሆኑ ቢታወቅም ለመስጠት እንዲታሰብ መነሻ በመሆን እንደሚረዳም ተስፋቸዉ ነዉ።

በስብሰባዉ ላይ ከኢትዮጵያን ሃኪሞች በተጨማሪ ከዛምቢያና ፔሩም ለልምድ ልዉዉጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል። ከእነሱ ሌላም በተጠቀሰዉ የህክምና ዘርፍ ትምህርት ላይ የሚገኙ እና ኢትዮጵያ ዉስጥ ልምድ ለመቅሰም የተሰማሩ ጀርመናዉያን ወጣት ባለሙያዎችም ያዩትን ለማጋራት ተሳትፈዋል። ይህ የጥናት ዉጤትም የእነሱ ነዉ። ከእነሱ ሌላ በጉባኤዉ ላይ ተጋብዘዉ በቅዱስ ጳዉሎስ ሃኪም ቤት የማህጸንና ፅንስ ሃኪም እንዲሁም የድህረ ምረቃ ትምህርት ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ባልካቸዉ ንጋቱ ተሞክሮና የየዕለት የሥራ ዉሏቸዉን አጋርተዋል።

ዶክተር አና ኪፈር ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2008ዓ,ም አንስቶ በተደጋጋሚ ወደኢትዮጵያ ስለተጓዙ በቅርበት በሴቶች የስነተዋልዶ ጤና ረገድ ያለዉን ጉድለት ማስተዋላቸዉን ይናገራሉ። በተለይ የፅንስና የማሕፀን ሃኪሞች ቁጥር ማነስና የምርመራ ስልቶችና መሳሪያዎች እጥረትን ልብ ብለዋል፤ በተደጋጋሚ ወደኢትዮጵያ በመጓዝ ያስተዋሉትን ነዉ አካፍለዉናል ከድምፅ ዘገባዉ ያገኙታል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic