መድበለ ፓርቲ የናፈቀዉ የታንዛኒያ ፖለቲካ | አፍሪቃ | DW | 27.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

መድበለ ፓርቲ የናፈቀዉ የታንዛኒያ ፖለቲካ

ከትናንት በስተያ እሁድ አጠቃላይ ምርጫ ባካሄደችዉ ታንዛኒያ በእጩ ፕሬዝደንቶቹ መካከል የታየዉ ያልተጠበቀና ጠንካራ ፉክክር በሀገሪቱ ዉስጥ ዉጥረት መቀስቀሱ እየተነገረ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:58
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:58 ደቂቃ

የታንዛኒያ ፖለቲካ

ለረዥም ዓመታት ሐገሪቱን የመራዉ የገዢዉ ፓርቲ የቻማ ቻ ማፒንዱዚ እጩ ጆን ማጉፉሊ ዋነኛ ተፎካካሪያቸዉን የተቃዋሚ ፓርቲ ፕሬዝደንታዊ እጩ ኤድዋርድ ሎዋሳን በጠባብ ልዩነት ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ቢገመትም፤ ዉጤቱ ግን ባጭር ቀናት ዉስጥ ይፋ እንደማይሆን ተገምቷል። ያም ቢሆን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነዉ ቻዴማ ከወዲሁ ፕሬዝደንታዊዉም ሆነ አጠቃላዩ ምርጫ ተጭበርብሯል እያለ ነዉ። በራስ ገዟ የደሴት ግዛት ዛንዚባርም በተመሳሳይ የተካሄደዉ ምርጫ ከወዲሁ ዉጤቱ ማወዛገብ ጀምሯል።

ሕንድ ዉቅያኖስን ተንተርሳ የምትገኘዉ ታንዛኒያ በምርጫ ዉዝግብም ሆነ በፖለቲካ ምስቅልቅል ብዙም ስሟ የሚጠቀስ ሀገር አልነበረችም።ዋና ከተማዋን ዳር ኤሰላም፤ ወይም ባንዳሪ ሰላማ፤ ማለትም የሰላም ወደብ እንደሚሏት በኖረዉ ባህላዊ የመደማመጥ አካሄዷ ሰላሟን ጠብቃ ሀገሪቱ የተረጋጋች ሆና ቆይታለች። የዘንድሮዉ ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ የምርጫ ፉክክሩ እየተካረረ በመምጣቱ ምናልባትም የጎረቤቶቿ ትርምስ ተጋብቶባት የእሁድ ዕለቱ ምርጫ በሰላም ላይጠናቀቅ ይችላል የሚል ስጋት ነበር።

Jakaya Kikwete Tansania Präsident

ጃካያ ኪክዌቴ

ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ጃካያ ኪክዌቴ እንደመሰሎቻቸዉ አፍሪቃዉያን መሪዎች ከሥልጣን መንበራቸዉ «ሙጥኝ» ሳይሉ፤ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት በሚፈቅድላቸዉ የጊዜ ገደብ ሁለተኛዉን የሥልጣን ዘመናቸዉን አጠናቅቀዉ ከቤተመንግሥቱ ለመዉጣት ቆርጠዋል። እሳቸዉ በሰላም የሚለቁትን የስልጣን መንበር ለመረከብ የሚታየዉ ፍትጊያ 52 ሚሊየን ሕዝብ የሚኖርባትን የተረጋጋች ሀገር ከግጭት እንዳይከታት የፀጥታ ኃይሎች ተጠናክረዉ ሰላሟን እንዲያስጠብቁ አሁን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ምንም እንኳን ታንዛኒያ የተረጋጋች ሀገር ብትሆንም ገዢዉ ፓርቲ CCM ማለትም ቻማ ቻ ማፒንዱዚ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ስልጣን ይዞ በመቆየቱ መድበለ ፓርቲ እንደናፈቃት ኖራለች። በእሁዱ ምርጫ ድምፁን ለመስጠት 22 ሚሊየን ሕዝብ ነዉ የተመዘገበዉ።

የድምፅ ቆጠራዉ ለሁለተኛ ቀን እያካሄዱ ነዉ። የሀገሪቱ ብሄራዊ የምርጫ ኮሚሽን የፕሬዝደንታዊዉን የምርጫ ዉጤት ከመግለፁ አስቀድሞ በአንዳንድ ወረዳዎች የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ዉጤቶች ይፋ መደረግ መጀመራቸዉ በሰላሟ የምትታወቀዉን ታንዛኒያን ወደዉዝግብና ቀዉስ እንዳይከታት አስግቷል። የምርጫ ዉጤቱንም ኮሚሽኑ ብቻ በይፋ እንደሚገልፅ አስታዉቋል። በምርጫዉ ወቅት ገዢዉ CCM ም ሆነ ቻዴማ ፓርቲዎች የተሰጡ ድምፆችን ለየፓርቲዉ ማዕከል የሚያስተላልፉ በጎ ፈቃደኞችን አሰማርተዉ ነበር። ተቃዋሚዉ ቻዴማ ፓርቲ ምርጫዉ ከተካሄደ በኋላ ድምጽ ለመቁጠር በበጎ ፈቃደኝነት የተሰማሩ 40 ሰዎችን ፖሊስ እንዳሠረበት አመልክቷል። የበጎ ፈቃደኞቹ መጠቀሚያ የሆነ ኮምፕዩተር እና ተንቀሳቃሽ ስልክም በፖሊስ መያዙን ፓርቲዉ ገልጿል። ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መግለጫ ባይሰጥም፤ የፖሊስ ኮሚሽነር ፖል ቻጎንጂ የድምፅ ቆጠራ ሥርዓትን በመጣስ በቻዴማ የቆጠራ ማዕከል የእስራት ርምጃ መወሰዱን አረጋግጠዋል።

Tansania Wahlen Edward Lowassa

ኤድዋርድ ሎዋሳ

ገዢዉ ፓርቲ CCM በየምርጫ ጣቢያዉ የተገኙ የመነሻ ዉጤት ከምክር ቤቱ 264 መቀመጫዎች 176ቱን እንዳገኘ አመላክተዉኛል፤ ለእጩ ፕሬዝደንትነት የቀረቡት ተወዳዳሪም ማሸነፋቸዉ የታወቀ ነዉ ይላል። ተቃዋሚ ፓርቲዉ ቻዴማ ግን ይህን ያጣጥላል። ከሶስት ወራት በፊት ከCCM ተገንጥለዉ የወጡት የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤድዋርድ ሎዋሳ የገዢዉ ፓርቲ ወገኖች ከሚገኙበት አካባቢ የወጣ ቁንፅል ዉጤት ሳይሆን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ አጠቃላይ የምርጫ ዉጤቱን በቶሎ እንዲያሳዉቅ ጠይቀዋል። ያላመኑበትን ዉጤትም እንደማይቀበሉ ነዉ ግልፅ ያደረጉት።

«የምርጫ ኮሚሽኑ በሂደቱ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ተመልክቶ የመጨረሻዉን ዉጤት ይፋ ማድረግ ይኖርበታል።»

ፕሬዝደንታዊ እጩዎቹ ማጉፉሊም ሆኑ ሎዋሳ በምርጫ ቅስቀሳቸዉ ወቅት በሀገሪቱ የሚታየዉን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንደሚያስወግዱ፤ ሙስናን እንደሚያጠፉ እና አብዛኞቹ በድህነት የሚኖሩ ወገኖችን ኑሮ እንደሚያሻሽሉ ቃል በመግባት በሺዎች የሚገመቱ ደጋፊዎችን ከኋላቸዉ አሰልፈዋል። የምርጫ ኮሚሽኑ የመጨረሻ ዉጤት ይፋ ሲደረግ ድል የቀናዉ ማን እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም ከዚያ በኋላስ ታንዛኒያ ወዴት? የሚለዉ ገና አልለየለትም። ተመሳሳይ ምርጫ ባካሄደችዉ በራስ ገዟ አስተዳደር ዛንዚባርም የዋናዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ፕሬዝደንታዊ እጩ በምርጫዉ ማሸነፋቸዉን ራሳቸዉ ይፋ አድርገዋል። ማሊም ሳይፍ ሀማድ የተባበረዉ የሲቪክ ግንባር ፓርቲ እጩ የታንዛኒያ ገዢ ፓርቲ እጩ የሆኑትን አሊ መሐመድ ሻይን በ52 በመቶ ድምፅ ማሸነፋቸዉን ይፋ አድርጓል። ሃማድ በበኩላቸዉ የምርጫ ኮሚሽኑ የሕዝቡን ዉሳኔ ያክብር እያሉ ነዉ፤

Tansania Wahlen John Pombe Magufuli

ጆን ማጉፊ

«እንደገለፅኩት ኮሚሽኑ ይፋዊ ዉጤቱን እንዲገልፅ እንፈልጋለን። ሆኖም ዶክተር ሻይን ሀገሪቱ ቀዉስ ዉስጥ እንዳትገባ ጨዋ ሰዉ እንዲሆኑ እማፀናለሁ። የሕዝብ ድምፅ መከበር ይኖርበታል። ዋናዉ ነገር ይህ የፖለቲካ ዉጥረት በሀገሪቱ እንዳይኖር ማድረግ ነዉ፤ ስለዚህም ኮሚሽኑ ከሕዝቡ ዉሳኔ ተቃራኒ የሆነ ምንም ነገር ማድረግ አይኖርበትም።»

ፓርቲዉ ባወጣዉ መግለጫም ደጋፊዎቹ ማሸነፉን እንደሚያዉቁ፤ በዚህም ደስታቸዉን ለመግለፅ መዘጋጀታቸዉን አመልክቷል። በትዕግስት በመቆየታቸዉም እነሱን ለማታለል መሞከር ያልተፈለገ መዘዝ ያስከትላል ሲልም አስጠንቅቋል። ፖሊስ የተባለዉን የምርጫ ድል ለማክበር የተሰባሰቡ የሀማድ ደጋፊዎችን በአስለቃሽ ጭስ መበተኑ ተዘግቧል። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ታንዛኒያ ከነደሴት ራስ ገዝ ግዛቷ ዛንዚባር አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሰዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic