መያዶችን ያስጨነቀ አዲስ ሕግ በግብፅ | አፍሪቃ | DW | 11.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

መያዶችን ያስጨነቀ አዲስ ሕግ በግብፅ

በግብፅ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያዶች) ምዝገባ ቀነ-ገደብ ሰኞ ኅዳር 1 ቀን፣ 2007 ዓም ተጠናቋል። የመያዶች አዲስ ሕግ መነሻ በቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሞባረክ ወቅት እጅግ አፋኝ እንደነበረ የሚጠቀስለት ሕግ እንደሆነ ተነግሯል። በርካታ መያዶች የመወረስ አለያም የመዘጋት ዕጣ እንደተጋረጠባቸው በስጋት ተውጠው ገልጠዋል።

ጋዳ እና ራሚ (ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል ተቀይሯል)ቢቻል ዛሬውኑ አለያም በነገው ዕለት ከግብፅ ሸሽተው ቢርቁ ምርጫቸው ነው። ሁለቱም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያዶች) ውስጥ ተቀጥረው ነው የሚሰሩት። መያዶችን የሚመለከተው አዲሱ የግብፅ ሕግ አሠሪዎቻቸው ላይ ያሳደረው ስጋት ነገ ምን ሊፈጥር እንደሚችል የሚያውቁት ነገር የለም። የግብፅ የማኅበራዊ ጉዳዮች ሚንስቴር መሥሪያ ቤት መያዶች እንዲመዘገቡ የሰጠው የጊዜ ገደብ በትናንትናው ዕለት ተጠናቋል። የግብፅ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጥናት ተቋም ባልደረባ ናዲም ማንሱር እንደገለፁት ከሆነ አዲሱ የመያዶች ሕግ መያዶችን በማንኛውም ጊዙ ለእስር ለመዳረግ የሚያስችል ነው።
«እጅግ አደገኛነቱ ለሠብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ለመያዶች ብቻ ሳይሆን፤ ለአገልግሎት ሰጪ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ነው። ሌላው ቀርቶ ርዳታ ለጋሽ ድርጅቶች ሳይቀሩ እጅግ በጣም ተጨንቀዋል፤ ምክንያቱም ሕጉ በማንኛውም ጊዜ እስር ቤት የመወርወር አደጋ እንዲጋረጥባቸው አድርጓል።»
ከግብፅ የወጡት የኮንራድ አደንአወር መያድ ሠራተኞች

ከግብፅ የወጡት የኮንራድ አደንአወር መያድ ሠራተኞች

አዲሱ የመያዶች ሕግ የፈጠረው ተጽዕኖ ብዙውን ጊዜ ስለ ዲሞክራሲ እና ሠብዓዊ መብት ጉዳዮች በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን ትንታኔ ሲሰጥ ለነበረው ራሚ እጅግ አናዳጅ ሆኖበታል። ምናልባትም ትናንትና የተጠናቀቀው የመያዶች የመመዝገቢያ የጊዜ ቀነ ገደብ ለእነራሚ ብቻ ሳይሆን፤ ወደ 47,000 በሚጠጉት የግብፅ መያዶች ሠራተኞች ላይ የከፋም ነገር ሊያስከትል ይችል ይሆናል። እጎአ በ2011 የግብፅ አብዮት ከተቀጣጠለበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ መንግስቶች የመያዶች ሕግ ላይ በርካታ ለውጦችን አድርገዋል። ምንም እንኳን አጨቃጫቂ ቢሆንም መጀመሪያ ላይ የሲቪሉ ማኅበረሰብ ተወካዮች በውይይቱ ወቅት እንዲሳተፉ ይደረግ ነበር። አሁን ግን ያ አልተደረገም ይላሉ ናዲም ማንሱር።
«በአጠቃላይ ድርድሩ ወቅት አልተሳተፍንም። ልክ እንደቀድሞው ሕግ ሁሉ መሰረታዊ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና የመሥራት ነፃነት መብቶችን እጅግ ይገድባል። ደኅንነቶች የማኅበራት የየዕለት እንቅስቃሴን በቀጥታ እንዲከታተሉ መንገድ የሚከፍት ነው።»
አዲሱ ሕግ መሰረቱን ያደረገው እንደ ጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር በ2002 የሙባረክ ዘመን ይሰራበት የነበረውን የመያዶችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው ሕግ እንደሆነ ናዲም መንሱር ገልጠዋል። በሙባረክ ዘመኑ ሕግ መሰረት አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የግብፅን «ብሔራዊ አንድነት» አደጋ ላይ የሚጥል፣ የ«ኅብረተሰቡን መስተጋብር እና ሞራል» የሚጎዳ ወይንም ሙሉ በሙሉ ከፓርቲዎች አለያም ከማኅበራት ጥቅም የሚያገኝ ከሆነ በማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር እንዲታገድ ይደረጋል ይላል። በተለይ ደግሞ መያዶቹ ከውጭ ሃገራት ገንዘብ የሚያገኙ ከሆኑ ሊወረሱ፣ ሊታገዱ፣ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት ሊጣልባቸው ወይንም እስር ቤት ሊወረወሩ እንደሚችሉ ይጠቅሳል።
የግብፅ ፖሊስ መያድ ፅ/ቤት ሲገባ

የግብፅ ፖሊስ መያድ ፅ/ቤት ሲገባ

ሕጉን ተከትሎ በርካታ መያዶች እና የጀርመኑ ኮንራድ አደናወር ተቋምን ጨምሮ የፖለቲካ ተቋማት በመንግስት ተወርሰዋል። መንግስት የመያዶች ሕግን የቀየረው የሠብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች እንዲሸማቀቁ ለማድረግ ነው ሲል ራሚ ያማርራል። ጋዳ በበኩሉ «አብዮቱን እንዳላካሄድን ሁሉ ጎዳና የወጣነውን በሙሉ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ እየተበቀሉን ነው» ብሏል። የሠብዓዊ መብት ታጋዮች ባለፉት ወራት በርካታ የችቆና ተግባራትን አጋልጠዋል፣ ጠበቃዎቻቸውም ፖለቲከኞችን እና በመንግስት በደል የደረሰባቸው ሰለባዎችን ፍርድ ቤት ቆመው እንዲወክሉ አድርገዋል፣ ይኽን መሰሉ የሲቪል ማኅበረሰቡ ተግባር ለፕሬዚዳንት ኧል ሲሲ እና መንግስታቸው የማይመች ነው ሲል ራሚ አክሎ ጠቅሷል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic