መዋዕለ-ነዋይ በአፍሪቃ | ኤኮኖሚ | DW | 14.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

መዋዕለ-ነዋይ በአፍሪቃ

አፍሪቃ ያለፈውን አሠርተ-ዓመት ባልተቋረጠ የኤኮኖሚ ዕድገት በማሳለፍ ለውጭው ዓለም የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ከመቼውም ይልቅ ማራኪ እየሆነች መምጣቷ በየጊዜው የሚጠቀስ ጉዳይ ነው።

default

የምዕራቡ ዓለም የኤኮኖሚ ጠበብት ዛሬ ኩባንያዎቻቸው ዕድሉ እንዳያመልጣቸው አዘውትረው ሲቀሰቅሱ መሰማቱም የተለመደ ነገር ሆኗል። እርግጥ በሌላ በኩል በክፍለ-ዓለሚቱ ለመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች የተሟላ አስተማማኝ ሁኔታ አለመኖሩም ሌላው ሃቅ ነው። ይሁንና ውስጣዊው መዋዕለ-ነዋይ፤ ኢንተር-አፍሪቃን ኢንቨስትመንት ሳይቀር በዕድገት አቅጣጫ በማምራት ላይ ነው የሚገኘው።

በዛሬው ጊዜ በአፍሪቃ የዕድገት ዕርምጃ ለመጠቀም ሲሯሯጡ የሚታዩት እንግዲህ የአውሮፓ፣ የእሢያ ወይም የአሜሪካ መዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች ብቻ አይደሉም። አፍሪቃውያን ራሳቸው ብዙ ሳይርቅ በጓሯቸው ዕድል መኖሩን እየተገነዘቡና እየነቁ በመሄድ ላይ ናቸው። ለውጭ ካፒታል መሳብ ምክንያት የሆኑት ሂደቶች የሃብት ዕድገት፣ ቀጣይነት ያለው የኤኮኖሚ ዕርምጃና በማበብ ላይ የሚገኘው የወጣቶች ቁጥር ወዘተ- የደቡብ አፍሪቃን፣ የኬንያን፣ የናይጄሪያን ወይም የናሚቢያን መዋዕለ-ነዋይ ሳይቀር በመሳብ ላይ ናቸው።

መረጃዎችን ለመጥቀስ በጎርጎሮሳውያኑ 2003 እና 2011 መካከል በነበሩት ሰባት ዓመታት ውስጥ በአዳዲስ የውጭ ቀጥተኛ ፕሮዤዎች ላይ የዋለው ኢንተር-አፍሪቃን መዋዕለ-ነዋይ በ 23 ከመቶ ጨምሯል። አሃዙ ከ 2007 ወዲህ እንዲያውም ወደ 32,5 ከመቶ ከፍ ማለቱ ነው የሚነገረው። ይህም አፍሪቃዊ ካልሆኑ መጤ ገበዮች ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ የላቀና ከበለጸገው ዓለም ከሚቀርበው ቀጥተኛ መዋዕለ ነዋይም በአራት ዕጅ ገደማ ከፍ ያለ መሆኑ ነው።

የአፍሪቃ ድንበር አቋሯጭ መዋዕለ-ነዋይ ውስጣዊ ኩባንያዎች አዳዲስ ገበዮች ስለሚያስፈልጓቸው እያደገ መሄዱም በግልጽ የሚታይ ነገር ሆኗል። በመንግሥታት ደረጃም ሰፊ የሃብት ምንጭ ያላቸው ሃገራት ለምሳሌ የጡረታ ገንዘብን መዋዕለ-ነዋይ ማድረጋቸው እንዲሁ ጨምሯል። ለዚህ መንስዔ የሆነው ከሣሃራ በስተደቡብ ያለው በዓለም ላይ ወጣት የሆነው አካባቢ ሕዝብ የዕድሜ ይዞታ ነው። አካባቢው የጡረታ ገንዘብ ክምችትን በተመለከተ እስከ 2030 ዓ-ም ድረስ ድክመት የማይታይበት ብቸኛው የዓለም አካባቢ እንደሚሆን የዓለም ባንክ ያመለክታል።

በያዝነው ምዕተ-ዓመት አጋማሽ ገደማ በሰርቶ-አደር ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው የአፍሪቃ ሕዝብ ዛሬ ካለበት 500 ሚሊዮን ወደ 1,2 ቢሊዮን ከፍ የሚል ይሆናል። ይህም በንጽጽር በዓለምአቀፍ ደረጃ ከአራት የአንዱን ሠራተኛ ድርሻ መያዝ ማለት ነው። በሕዝብ ብዛት ግዙፍ ከሆነችው ከቻይና አንጻርም ከስምንት አንዱን!

በአፍሪቃ በስራ ላይ የሚውለው የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ-ነዋይ ወደፊትም የሚቀጥል የረጅም ጊዜ የካፒታል፣ የሙያና የቴክኖሊጂ ምንጭ ሲሆን የአፍሪቃ ውስጣዊ የአካባቢ መዋዕለ-ነዋይ ታላላቅ የውጭ ካፒታል አቅራቢዎችንም የሚያደፋፍር እንደሚሆን የብዙ የመስኩ ባለሙያዎች ዕምነት ነው። የውጭ ኩባንያዎች ገንዘባቸውን ከውስጥ ኩባንያዎች ጀርባ ሆነው በስራ ላይ ማዋሉን እንደሚመርጡ ልምዱ ያላቸው ወገኖች ይናገራሉ። በሌላ አነጋገር የውስጥ መዋዕለ-ነዋይ ለውጭ ካፒታል ማደግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለት ነው።

በኢንተር-አፍሪቃው መዋዕለ-ነዋይ ረገድ እስካሁን ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይዛ የቆየችው በመዋቅራዊ ዕድገት ረገድ በክፍለ-ዓለሚቱ ራመድ ያለችው ደቡብ አፍሪቃ ናት። ወደ ሰሜን ቀደም ብለው ከዘለቁት ኩባንያዎቿ መካከል MTN-ንና ሾፕራይትን የመሳሰሉት ይገኙበታል። ደቡብ አፍሪቃ ዛሬ በክፍለ-ዓለሚቱ መዋዕለ-ነዋይ ከሚያደርጉት ዋና ዋና አምሥት የዓለም ሃገራት መካከል አንዷ ናት።

በአፍሪቃ ምሥራቅና ምዕራብ አኳያ ደግሞ ኬንያና ናይጄሪያ ቀደምቱ ድንበር አቋረጭ መዋዕለ ነዋይ አድራጊዎች ሆነው ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል በክፍለ-ዓለሚቱ ቀደምት ባለጸጋ በአሊኮ ዳንጎት ይዞታ ስር የሚገኘው የናይጄሪያ ኩባንያ «ዳንጎት ሤሜንት» በአፍሪቃ ለመስፋፋት አምሥት ቢሊዮን ዶላር በስራ ላይ ለማዋል ተነስቷል። ኩባንያው በካሜሩን፣ ሤኔጋል፣ ኢትዮጵያ፣ ዛምቢያና ደቡብ አፍሪቃ ፋብሪካዎቹን ለመክፈት በማቀድ ላይ ነው።

የኬንያና የናይጄሪያ ባንኮችም እንዲሁ በአካባቢያቸው የመስፋፋት ዕርምጃ ወስደዋል። «ዩናይትድ ባንክ ፎር አፍሪካ» የተሰኘው የናይጄሪያ ባንክ ከአሁኑ ጋናን፣ ሞዛምቢክንና ታንዛኒያን ጨምሮ በ 18 የአፍሪቃ ሃገራት የተስፋፋ ሲሆን በመጪዎቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ግማሽ የሚሆን ገቢውን ከውጭ ለማግኘት ነው የሚጥረው። በወቅቱ የዚሁ ድርሻ ሃያ በመቶ ገደማ ይጠጋል። በአፍሪቃ ክፍል-ዓለም በሚቀጥሉት ዓመታት ሂደት በነዳጅ ዘይትና በጋዝ ዘርፎችም ትልቅ ዕድገት እንደሚኖር ነው የሚጠበቀው። የአፍሪቃው ባንክ የገንዘብ ክምችት ማደግ የአካባቢውን መዋዕለ-ነዋይ ፍሰት እንደሚያጠናክርም ጽኑ ዕምነት አለ።

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም በወቅቱ ስለ መካከለኛው የሕብረተሰብ ክፍል ማደግ፣ ስለ ከተማው የስራ ሃይል መጨመርና ስለዚሁ የጡረታ አበል አስተዋጽኦ ማደግም ብዙ ይወራል። ከሣሃራ በስተደቡብ የሚገኘው የአፍሪቃ ክፍል የካፒታል ክምችት እንደተቀረው አዳጊ ዓለም ሁሉ በሚቀጥሉት ሁለት አሠርተ-ዓመታት ውስጥ በሰፊው በመጨመር በ 2030 ዓ-ም ገደማ 23,3 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል። የዓለም ባንክ ባለፈው ግንቦት ወር አቅርቦት በነበረ ዘገባ እንዳመለከተው ይህም በ 2010 ከተመዘገበው 11 ትሪሊዮን ከእጥፍ በላይ መሆኑ ነው።

የመስኩ ተመራማሪዎች እንደሚሉት በክፍለ-ዓለሚቱ ውስጣዊ መዋዕለ-ነዋይ ረገድ የአፍሪቃ የጡረታ ተቋማት ግንባር-ቀደም ሊሆኑ ይችላሉ። ከሣሃራ በስተደቡብ አፍሪቃ የሚገኙት ስድሥቱ ታላላቅ የጡረታ ተቋማት ይዞታቸውን እስከፊታችን 2020 ዓ-ም ድረስ ወደ 622 ቢሊዮን ዶላርና እስከ 2050 ደግሞ ወደ 7,3 ትሪሊዮን ዶላር ከፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ነው የሚገመተው። በ 2010 ክምችቱ 260 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋ ነበር።

ዓለምአቀፉን መዋዕለ-ነዋይ በመሳቡ ረገድ በአፍሪቃ ሁኔታው የተለወጠው በተለይም በ 1995 እና 2005 መካከል ባለው ጊዜ ነው። ለዚሁም የክፍለ-ዓለሚቱ የኤኮኖሚ ለውጦችና ለዓለምአቀፉ ንግድ ክፍት እየሆነ መሄድ አስተዋጽኦ አድርጓል። ብሄራዊ የኤኮኖሚ ዕድገቶች ለኩባንያዎች ገቢ ማየል አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መታየቱም አልቀረም። በአፍሪቃ በምርት ፋብሪካዎችና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች በ 2002 ያከማቹት ካፒታል በንጽጽር ከኢንዶኔዚያ፣ ወይም ከቪየትናም ከነበረው ሲተያይ በሁለት ሶሥተኛ መጠን የላቀ ነበር። እንግዲህ በአፍሪቃ መዋዕለ-ነዋይ ማድረጉ በትልቁ ለማትረፍ በጅቷል ማለት ነው።

ይህ ደግሞ ዓለም ወደ 2008 የፊናንስ ቀውስ እያመራ ባለበት ወቅት ዋዜማ የታየው ሃቅ ነበር። ቀውሱን ምንም እንኳ ከአፍሪቃ በቀጥታ የሚያገናኘው ነገር ባይኖርም ክፍለ-ዓለሚቱን ሳይነካ ግን በቀላሉ አላለፈም። የነዳጅ ዘይትና ሌሎች ምርቶች ዋጋ መጨመር፣ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች በፍርሃቻ መቆጠብና የባንኮች ጠበቅ ማለት ለጊዜውም ቢሆን ከባድ ሁኔታን ፈጥረው ታይተዋል። ይሁን እንጂ አፍሪቃ ከሞላ-ጎደል በአብዛኛው ከቀውሱ ማዕበል በፍጥነት ማምለጥ ችላለች።

አፍሪቃን ምናልባትም እስካሁን የጎደላት እንደ እሢያ በአካባቢው ለዕድገት አርአያ የሚሆን አገር ነበር። አሁን ግን ከዚያ ለመድረስ ጅማሮ ላይ መሆኗ እየታየ ነው። በተፈጥሮ ጸጋ ባልታደለችው በሩዋንዳ እንኳ አሥር ከመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ መቻሉ ዛሬ በአርአያነት መ ነገር ይዟል። ከዚህ የተሻለ ሁኔታ ያላቸው ሃገራት ዕርምጃ ደግሞ እንደ እሢያ ሁሉ በጎረቤቶቻቸው ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ነው የሚታመነው።

እርግጥ አፍሪቃ የውጭ መዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶችን ትኩረት መሳቡ ተሳክቶላታል። በሌላ በኩል ግን ፍትሃዊ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እነዚሁ ከፍርሃቻና ጥርጣሬ ነጻ ሆነው ገንዘባቸውን በስራ ላይ እንዲያውሉ ማድረጓ ግድ ነው። ይህ ደግሞ ለባሕር ማዶም ሆነ ለውስጥ የአህጉሯ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች እኩል ጠቃሚና አስፈላጊ ጉዳይ ይሆናል። የአፍሪቃ የልማት ባንክ ፕሬዚደንት ዶናልድ ካቤሩካ የዚምባብዌን የምርጫ ማግሥት አስመልክተው ባለፈው ሰኞ ሲናገሩ ዓለምአቀፍ የመዋዕለ-ነዋይ ባለቤቶች አስተማማኝ ሁኔታን እንደሚሹ ነበር ያስገነዘቡት። ይህ በዕውነትም መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

ለማጠቃለል የአፍሪቃ የልማት ባንክ ክፍለ-ዓለሚቱ በዚህ ዓመት ከሣሃራ በስተደቡብ አካባቢ 5,8 ከመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት እንደምታሳይ ይገምታል። በያዝነው 2013 ዓ-ም በ 4,8 ከመቶና በተከታዩ 2014 ደግሞ በ 5,3 ከመቶ እንደምታድግ ነው የሚጠበቀው። እርግጥ በታላላቆቹ ገበዮች በቻይናና በኤውሮ ዞን በተፈጠረው የዕድገት ዝግመት የተነሣ አፍሪቃ ከነዚሁ በንግድና በተፈጥሮ ሃብት የተሳሰረች በመሆኗ ጨርሳ ከአደጋ የተሰወረችም አይደለችም። ካቤሩካ ይሁንና አፍሪቃ በመዋቅራዊ መሻሻል በኤኮኖሚ ዕድገቷ ጸንታ ልትቀጥል እንደምትችል ዕምነታቸው ነው። የአፍሪቃ የልማት ባንክም ለዚሁ ፕሮዤ 60 ቢሊዮን ዶላር መድቧል።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic