መካከለኛዉ ምስራቅ፦ኢራን፦ እስራኤልና አሜሪካ | ዓለም | DW | 14.11.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

መካከለኛዉ ምስራቅ፦ኢራን፦ እስራኤልና አሜሪካ

የእርምጃዉ ዓይነት እስራኤልና የዩናይትድ ስቴትስ ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኞች እንደሚሉት የኢራንን የኑክሌር ተቋማትን በጦር ሐይል መደብደብ ነዉ።ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማም ኢራንን በጦር ሐይል የመደብደብ እቅዳቸዉ አሁንም «ጠረጴዛ ላይ ነዉ።» እንዳሉ ነዉ

default

የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኃይል ድርጅት ፅ/ቤት


14 11 11

የፓሪስ ጉባኤ ዉሳኔ፣ የዋሽግተን፣ እየሩሳሌም አፀፋ፣ የዓለም ትዝብት ድንጋጤ በርግጥ ታዉቆ ነበር።የኒዮርኩን ዉይይት ሒደት፣የቪየናዉን ዘገባ ምን-እንዴትነትነትን የሚያዉቅ ከነበረ የዓለምን ዉሎ-አዳር የሚበይነዉ ጥቂት ዓለም ብቻ ነበረ።በዉሳኔ-አፀፋዉ ማግስት፣ በዉይይት-ዘገባዉ ዋዜማ እየሩሳሌም የተነበበዉ ሐአሬትስ ጋዜጣ የሆነዉን እና የሚሆነዉን ባንዲት ትንሽ ካርቱን እኩል አለዉ።ጋዜጣዉ ዩኔስኮ ጉባኤ ዉሳኔ፣ የዋሽግተንና እየሩሳሌም አፀፋ፣ የፍልስጤሞች ጥያቄ፣ የኢራን ኑክሌር እያለ እብዙ ስፍራ የሆነና የሚሆነዉን መዘርዘር አላስፈለገዉም።የብዙዉን ሥፍራ ብዙ ሁነት፣ የትልቆቹን ትልቅ ምኞት ብዙም አንድምነት በትንሽ ካርቱኑ ጠቀለለዉ።እኛ ባጭሩ እንዘርዝረዉ። አብራችሁን ቆዩ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ጋዜጠኞችና ከያኒን በአሸባሪነት መወንጀል-ማሰር-መፍታቱ አብዛኛዉን ኢትዮጵያዊ ስለኑሮ ዉድነት፣ ሥለ አባይ ግድብና መዋጮዉ ከማሰብ ማሰላሰሉ አናጥቦ በሽብር ምንነት በታሳሪ-አሳሪዎች ማንነት ላይ እንዲያተኩር ማስገደዱ ብዙ አያነጋግርም።የጦር ላዘመቱት ኬንያዎች እና ለተዘመተባቸዉ ሶማሊያዎች ደቡብ ሶማሊያ ከሚደረገዉ ዉጊያ እኩል የሚያሳስባቸዉ አይኖር ይሆናል።

የቱኒዚያዎችና የላይቤሪያዎች ሰሞናዊ ትኩረት የመሪ ምርጫ፣ የየመንና የሶሪያዎች መሪን የማስወገድ ትግል፣ የአዉሮጶች የገንዘብ ቀዉስ፣የታይላንዶች ጎርፍ፣ የቱርኮች መሬት መንቀጥቀጥ ሰሞናዊ ትኩረታቸዉ አይደለም ማለት አይቻልም።ከቀድሞዉ የሊቢያ መሪ ከኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ መገደል፥ ከገዳይ አስገዳዮች የድል-ፌስታ ማግስት የዓለም ዘዋሪዎች አብዛኛዉ ዓለም በጋራ እና በትልቁ እንዲያተኩርበት የፈቀዱለት ግን ከስልሳ-ዘመን በላይ ብዙ የሚያዉቀዉን የአንድ-ምድር ብዙ ግን አንድ ጉዳይ ነዉ።

የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አባስ ኒዮርክ-ባለፈዉ መስከረም ማብቂያ።ሕዳር 1947 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) እዚያዉ ከተማ-ኒዮርክ ለዚሁ ድርጅ-ለተባበሩት መንግሥሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፥ ያንኑ ሕዝብ ፍልስጤምን ወክለዉ ተመሳሳይ ንግግር ያደረጉት ጀማል ሁሴይን፥ አባስ ያሉትን ቢሰሙ በንግግር ዘራፊነት ይከሷቸዉ ነበር።

«እዉነቱ እስራኤል ሰላም ትፈልጋለች።እዉነቱ እኔ ሰላም

Iran Atomenergie Flash-Galerie

የኢራን የኑክሌር ጣቢያ

እፈልጋለሁ።እዉነቱ በመካከለኛዉ ምሥራቅ ምንጊዜም በተለይ በዚሕ አስችጋሪ ወቅት ሰላም ከፀጥታ ጋር መቀናጀት አለበት።እዉነታዉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዉሳኔ አማካይነት ሠላም አንመሰርትም።በባለ ጉዳዮች ቀጥታ ድርድር አማካይነት እንጂ።»

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ።አሁንም መስከረም።ከስልሳ-አራት ዓመት በፊት አይሁድን ወክለዉ እነ ሁሴይንን የሞገቱት ሞሼ ሻሬትስ የአባስ-ኔታንያሁን ሙግት ቢስሙ ኖር ትዝብታቸዉ መናፈቁ አይቀርም።

የነሁሴይንን ምኞት፣ ፍላጎት፣ ክርክር-ሙግትን ቀብሮ የእስከዛሬዉን የእልቂት ፍጅት በር የበረገደዉን
ዉሳኔ-ያስረቀቁት፣ በማባባለም-በስፈራራትም በ1947 ያስፀደቁት ሐይላት መሪ ፕሬዝዳት ሐሪ ኤስ ትሩማን ነበሩ።በስልሳ አራት አመቱ ሒደት ዓለም ብዙ ተቀይራለች።ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ግን ብዙ በተለወጠችዉ ዓለም፣የድሮዉን ቃል-እምነት አላጠፉም።

የፍልስጤም መስተዳድር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያቀረበዉ የሙሉ አባልነት ጥያቄ የዩናይትድ ስቴትስን ተቃዉሞ አልፎ ይፀደቃል ብሎ ያሰበ በርግጥ የለም።የዋሽግተን ግልፅ ተቃዉሞ ለፍትሕ፣ ዲሞክራሲ፣ ለሕዝቦች ነፃነት ቆሚያለሁ የምትለዉን የዓለም ብቸኛ ልዓለ ሐይል ሐገር የቃል-ድርጊቷን ተቃርኖ ዳግም ማገለጡ ግን አላጠያየቅም።

ተንታኞች እንዳሉት በሰብአዊ፣ ፍትሐዊነት መርሕ ይሆን በጥቅም ወገንተኝነት የፍልስጤሞችን ጥያቄ ተገቢነት የሚደገፈዉ ወገን ፈጠነም ዘገየ፥ አነሰም በዛ የእየሩሳሌም-ዋሽንግተኖችን ጥቅም ማወላከፉ አይቀረም።የአሜሪካኖችን የበጎ-ቃል መጥፎ ምግባር ተቃርኖ የታዘበዉ ወገን ቅሬታ ጥቅምን ከሚያሠጋበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት ግን ሐሳቡን-አዲስ ሐሳብ ሰረቀዉ።

የኢራን ቅጥረኛ ነብሰ ገዳዮች በዋሽንግተን የስዑዲ አረቢያን አምባሳደር ሊገድሉ ሲያደቡ ተያዙ ተባለ።ከዋሽንግተን የናኘዉ ዜና የባለጉዳዮችን ትኩረት ከፍልስጤሞች የእዉቅና ጥያቄ- እና ተቃዉሞዉ አናጥቦ ሪያድን ከቴሕራን በማላተሙ ንረት ያሽከረክረዉ ያዘ።በዚሕ መሐል ነዉ-እስራኤል የተማረከ ወታደሯን ለማስለቀቅ በአሸባሪነት ከምትወጋ-ከምታወግዘዉ፥ምዕራባዉያን ሐገራት ከሚወነጅሉት ሐማስ ጋር ያደረገችዉ ድርድር ዉጤት ይፋ የሆነዉ።

የእስረኞቹ ልዉዉጥ በቴሕራን-ዋሽንግተን ሪያድ ዉዝግብ የደበበዘዉን የፍልስጤም የአባልነት ጥያቄን እዚያዉ ረመላሕ-ጋዛ ዉስጥ ማቀጨጩ የአባስ መስተዳድርን ግራ-ቀኝ ሲያላጋዉ፥ ሐማስን ጮቤ ነበር-ያስረገጠዉ።ፓሪስ-ፈረንሳይ የተሰየመዉ የተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፥የሳይንስ፥ እና የባሕል ድርጅት (UNESCO) ጉባኤ ፍልስጤምን በሙሉ አባልነት መቀበሉ የፍልስጤሟ የቱሪዝም ሚኒስትር ኾዉሉዉድ ዳይቤስ እንዳሉት ለአባስ መስተዳድር የትንሽ ድል ብልጭታ ነዉ።

«ዉሳኔዉ ለኛ ከፍተኛ የሞራል ዋጋ አለዉ።የፍልስጤም ሕዝብ ቅርስ፥ የባሕል ቅርስ እንዳለዉ እና እንዳሳየ የዓለም የባሕል ቅርስ አካል እንደሆነ ዕዉቅና የሚሰጥ ነዉ።»

ከ1921 ጀምሮ አፈላጊነቱ ሲነገር፥ሲመከር-ሲመሰከርለት የቆየዉ ማሕበር ከተባበሩት መንግሥታት ቅርንጫፍ ድርጅቶች ሁሉ አንጋፋዉ ነዉ።የዩኔስኮ አላማ፥-ትምሕርትና ሳይንስን በማስፋፋት፥የባሕላዊ መረጃዎች ልዉዉጥን በማጠናከር-ለዓለም ሠላም ፅናት፥ ለድንሕነት መወገድ አስተዋፅኦ ማበርከት ነዉ።»
ድርጅቱን የመሠረቱት፥ ለሥራ ማስኬጂያዉ ገንዘብ የሚያዋጡት መንግሥታትም ያደረጉትን የሚያደርጉት የድርጅቱን ዓላማዎች ለማሳካት ነዉ-ነበር እምነቱ።

የፓሪስ ጉባኤ የፍልስጤምን አባልነት ሲቀበል የድርጅቱ ግንባር ቀደም መሥራች፥ዩናይትድ ስቴትስ ቀድማ፥ እስራኤል ተከትላ ለዩኔስኮ የሚሰጡትን የገንዘብ መዋጮ አቋረጡ።ይሕ ነዉ የትልቁ ድርጅት መስራቾች ፖለቲካዊ ጥቅም ካልተከበረ የትልቁ ድርጅት ትልቅ-ፍትሐዊ ዓላማ-ምግባር ባፍጢሙ ይደፋ የመባሉ አሳዛኝ ሐቅ።

የዩኔስኮ ዉሳኔ፥ የዋሽንግተን እየሩሳሌም አፀፋ እርምጃ ከተነገረ አራት ቀን አለፈዉ።የተባበሩት መንግሥታት የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን (IAEA) ሥለ ኢራን ያጠናቀረዉን ዘገባ ይፋ ለማድረግ ደግሞ አራት ቀን ቀረዉ።ሐሙስ ነዉ። ሕዳር አራት።መሪዎቹ በርግጥ አላሉትም።የዚያን ቀን የተነበበዉ የእስራኤል ዕዉቅ ጋጣጤ ሐአሬትስ የለጠፋት ካርቱን-ግን ለዚያን ቀን-ያለፈዉን መጪዉንም አለችዉ።

«ኢራንን ለመደብደብ የተዘጋጁ አራት ፓይለቶች ከጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትንያሁና ከመከላከያ ሚንስትር ኤሁድ ባራክ ፊት ቆመዉ ትዕዛዝ ሲቀበሉ ካርቱኗ ታሳያለች።ከኢራን ወደ ሐገራችሁ ሥትመለሱ ይላል በኔታናያሁ የተመሠለዉ ትዕዛዝ ረመላሕ የሚገኘዉን የዩኔስኮን ፅሕፈት ቤት ትመታላችሁ።»

የሐአሬትስ ካርቱን የዩኔስኮ እና የእስራኤል ባለሥልጣናትን ሲያወዛግብ አለም አቀፉ የአዉቶሚክ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን (IAEA) ኢራን የኑክሌር ቦምብ ለመሥራት እያደባች መሆንዋን የሚጠቁም መረጃ እንዳለዉ አስታወቀ።ሕዳር ስምንት።ድርጅቱ ኢራን የኑክሌር ቦምብ ለመስራት ለማቀዷ መረጃ አለኝ ማለቱ በርግጥ ብዙዎንች አሳስቧል።ከኢራን የረጅም ጊዜ ጠላቶች ከዋሽግተንና ከየሩሳሌም የተሰማዉ የጦር ሐይል ድብደባ አፀፋ ደግሞ ከማሳሰብ በላይ ብዙ አሥጊ ነበር።

የሁለቱ መንግሥታት መሪዎች ኢራንን ለመደብደብ ምናልባት አስበዉት ይሆናል-ግን ሌሎች እንጂ እነሱ አላሉትም።የየሩሳሌሙ ነዋሪ መሪዎቹን ቀድሞ ተናገረ።

«ኢራንን የመሠለች፥ የተረበሸችና ያልተረጋጋች ሐገር ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ ለማምረት መዘጋጀትዋ በጣም አደገኛ ነዉ።አሜሪካኖችን እንዲሕ ዓይነት ጦር መሳሪያ በሌለበት ኢራቅን ለመዉጋት ያን ያሕል ርቀት ከሔዱ፥አሁን በኢራን ላይ የሐይል እርምጃ ለመዉሰድ የሚያመነቱበት ምክንያት ሊኖር አይችልም።ጠንካራ የምጣኔ ሐብት ለመጣል ይሞከር ይሆናል።ለዚሕ ግን የቀረ ጊዜ የለም።እስራኤል ከፍተኛ ዋጋ የምትከፍልበትና ለአደጋ የምትጋለጥበት ምክንያትም የለም።»

የIAEA በ«አሳማኝ መረጃዎች» ላይ የተመሠረተ ባለዉ ዘገባዉ ኢራን ፓርቺን በተባለዉ የጦር ሠፈር ለኑክሌር ቦምብ ግብአት የሚያገለግሉ ተቀጣጣይ ንጥረ ነገሮችን እያስጠናች ነዉ።በድርጅቱ የኢራን አምባሳደር ዓሊ አስጋር ሶልታኒያሕ ግን ዘገባዉ በጣሙን የዩናይትድ ስቴትስን ፍላጎት ለማንፀባረቅ የተዘጋጀ ነዉ።

«ዘገባዉ ያልተመጣጠነ፥ ሙያዊነት የጎደለዉ፥ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማስፈፀምና በተለይ በዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲካዊ ግፊት የተዘጋጀ ነዉ።ይሕ ዘገባ ከተለመደዉ አሠራር ማፈንገጡ በጣም አሳዛኝ ነዉ።»
ዩናይትድ ስቴትስ፥ እስራኤልና ተባባሪዎቻቸዉ ግን የዘገባዉን ሐቀኝነት አልተጠራጠሩም። ካዲማ የተሰኘዉ የእስራኤል ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዚፕ ሊቪኒ እንደሚሉት ደግሞ ኢራን ከዚሕ ደረጃ መድረሷ እስራኤልን ብቻ አያሰጋም።

«የእስራኤል ችግር አይደለም።የመላዉ ዓለም ችግር ነዉ።እና ኢራን ኑክሌር እንዳትታጠቅ ለማገድ ነፃዉ ዓለም መተባበር አለበት።እርምጃ ለመዉሰድ ጊዜዉ አሁን ነዉ።»

የእርምጃዉ ዓይነት እስራኤልና የዩናይትድ ስቴትስ ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኞች እንደሚሉት የኢራንን የኑክሌር ተቋማትን በጦር ሐይል መደብደብ ነዉ።ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማም ኢራንን በጦር ሐይል የመደብደብ እቅዳቸዉ አሁንም «ጠረጴዛ ላይ ነዉ።» እንዳሉ ነዉ።የጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታናያሁ ባለሥልጠናትም የጦር ሐይሉ አማራጭ እንዳለ መሆኑን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

ሊቪኒ «ነፃ» ያሉት ዓለም የሚያስተናብራቸዉ የእስራኤልና የዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጆች ግን ኢራን በጦር ሐይል ትመታ የሚለዉን ሐሳብ አይቀበሉትም።ጀርመን አንዷ ናት።

«እኔ ብዙ ጊዜ ተናግሬያለሁ።ከዚሕም በተጨማሪ ከሌሎች ብዙ አቻዎቼ ጋር በግልም ሆነ ባደባባይ ባደረጉት ዉይይት በግልፅ እንዳስታወቅሁት ወታደራዊ አማራጭ የሚለዉ ዉይይት ጥሩ ዉጤት ያመጣል ብለን አናምንም።ፖለቲካዊ ወይም የማዕቀብ እርምጃ ይወሰድ ከሆነ ይሕ ገቢራዊ ሊሆን የሚችልና ትርጉም የሚሰጥ ይሆናል።»

የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ

ኢራን የጦር ሐይል እርምጃ አይደለም ሥለ ጦር ሐይል እርምጃ ለሚሰነዘርባት ዛቻ የምትሰጠዉ አፀፋ «የማያዳግም ነዉ» እያለች ትዝታለች።በርግጥም ዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል ኢራንን ቢደበድቡ የቴሕራኖች አፀፋ የካቡል፥ የባግዳድ፥ ወይም የትሪፖሊ ዓይነት እንደማይሆን አላጡትም።በዚሕም ሰበብ ይመስላል ታዛቢዎች እንደሚሉት የሁለቱ ሐገራት አላማ ጨረቃን ለመምታት ለፀሐይ ማለም አይነት ነዉ።

UNESCO

የዩኔስኮ ጉባኤ

ጦር ሰብቆ፥-ተጨማሪ ማዕቀብ ማፀደቅ።የሩሲያዉ ፕሬዝዳት ዲሚትሪ ሜድቬደቭ እንደሚሉት ግን ኢራንን ለመደብደብ ለመቅጣት፥ ከሚዛት-ከሚፎከረዉ እኩል ለፍልስጤም እስራኤሎች የሰላም ሒደትም ሊታሰብበት ይገባል።

«የመካከለኛዉ ምሥራቅ የሠላም ሒደት ቀጥ እንዳለ ነዉ።መፈናፈን ተስኖታል።ሥለዚሕ እኔ እንደሚመስለኝ ከዛቻ ይልቅ የሚጠቅመዉ ተረጋግቶ ሥለ መካካለኛዉ ምሥራቅ ሠላም፥ ሥለ ኢራን የኑክሌር መርሐ ግብርም ሆነ ሥለ ሌሎች ችግሮች ገንቢ ድርድርና ዉይይት ማድረግ ነዉ።አለበለዚያ ዛቻዎቹ ትልቅ ጦርነት ሊያስከትሉ ይችላሉ።ይ’ሕ ደግሞ ለመካከለኛዉ ምሥራቅ ታላቅ ድቀት ነዉ።»

ፍፃሜዉ ሜድቬዴቭ እንዳሉት ይሁን-አይሆን በርግጥ አይታወቅም።የድብደባ-ማዕቀቡ ዛቻ ማስፈራራቱ፥ የአፀፋ ፉከራዉም ግን እንደቀጠለ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሽዋዬ ለገሰ