መከፋፈል የገጠመዉ የቱኒዝያ ጠንካራ ፓርቲ | አፍሪቃ | DW | 15.01.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

መከፋፈል የገጠመዉ የቱኒዝያ ጠንካራ ፓርቲ

የዛሬ ዓመቱ የቱኒዝያ ምርጫ አሸናፊ ኒዳ ቱን የተባለው ፓርቲ በመፈረካከስ ላይ ይገኛል። ፓርቲዉ አሁንም በጥምር መንግስቱ ዉስጥ ቢሆንም ያለዉ ያስተዳደር ስልጣን የተቀየረ ነዉ። ከቱኒዝያ የፀደዩ አብዮት አምስት ዓመት በኋላ ፤ ጠንካራው የፖለቲካ ፓርቲ የመከፋፈሉ ምክንያት ምን ይሆን?

ኒዳ ቱን በተሰኘዉ የቱኒዝያ የፖለቲካ ፓርቲ ዉስጥ የተለያዩ ችግሮች ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ይህ ጠንካራ ፓርቲ እስከወድያኛዉ ተፈረካክሶአል። ፓርቲዉ የመከፈል እጣ የገጠመዉ ከፓርላማና ከፕሪዚዳንታዊ ምርጫ አንድ ዓመት በኃላ ነዉ። ወይም ደግሞ የፀደዩ አብዮት በተከሰተ በአምስተኛ ዓመቱ መሆኑ ነዉ። የቀድሞዉ የቱኒዝያ አምባገነን መሪ ቤን አሊ በጎርጎረሳዉያኑ ጥር 14 2011 ዓ,ም ከስልጣን መወገዳቸዉ ይታወቃል።

ኒዳ ቱን የተባለዉ የቱኒዝያ የፖለቲካ ፓርቲ የተመሰረተዉ የቱኒዝያ አብዮት ከፈነዳ በኋላ በጎርጎርዮሳዊዉ 2012 ዓ,ም ነዉ። ይህ ወግ አጥባቂ ፓርቲ በዝያን ጊዜ አይሎ ለነበረዉ እስላማዊ ኢንሃዳ ፓርቲ ተቀናቃኝ እንዲሆን ነበር የታሰበዉ። በጎርጎርዮሳዊዉ 2014 ዓ,ም ሁለቱ ትላላቅ የቱኒዝያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃገሪቱ በተደረገዉ የምርጫ ዘመቻ በጠላትነት መተያየት ጀመሩ። ሆኖም ግን አሁንም አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጣምረው ሃገሪቱን ያስተዳድራሉ ። ኒዳ ቱን ተቀናቃኝ ፖለቲከኛና በምርጫ ዘመቻ ወቅት ቀልብ የሚስብበት የማወያያ ርዕስን አጥቶአል። የፓርቲዉን የወደፊት ርምጃ በሚመለከት በአባላቱ መካከልም ስምምንት ጠፍቶአል። የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞች፤ አዛዉንቱ የቱኒዝያ ፕሬዚዳንት ኤስቢሲ ወንድ ልጃቸዉን ተከታያቸዉ ለማድረግ የስልጣን መንበራቸዉን ማስረከብ ይፈልጋሉ ሲሉ ትችታቸዉን ይሰነዝራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ኒዳ ቱን ፓርቲ ዴሞክራሲዊ የሆኑ የፖለቲካ ምርሆች ይጎሉታል ሲሉም ይናገራሉ። ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ የፕሪዚዳንት ኤስቢሲና የልጃቸዉ ተከታዮች በዙስ ከተማ ላይ ስብሰባ አድርገዉ ነበር። ስብሰባቸዉ ለሽግግር ጊዜዉ የሚሆን መርህ ለማዘጋጀትና በመጭዉ ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ የፓርቲ ስብሰባን ለማዘጋጀት የተደረገ መሰናዶ ነበር። በዚሁ ጊዜ ከኤስቢሲና ከልጃቸዉ አፈንግጠዉ የወጡቱ የፓርቲዉ አባላት ደግሞ አንድ አዲስ ፓርቲን ለመመስረት ለመዘጋጀት በራሳቸዉ ወገን መዲና ቱኒዝ ዉስጥ ትልቅ ስብሰባን አድርገዋል። ስብሰባዉ የተመራዉ አሁን አፈንግጠዉ በወጡትና በቀድሞው የፓርቲዉ ዋና ፀሐፊ ሞዝን ማርዙክ እንዲሁም በቀድሞዉ የፓርቲ ዋና ተጠሪና የፓርላማ አባል ነበር።

«አሁን ኒዳቱን የተሰኘዉ ፓርቲ የለም። ምንም ዓይነት መዋቅርም ሆነ አካል የለውም ፤ በፓርቲው ዴሞክራሲና ምርጫ የለም። በፓርቲው ውስጥ ሰዎች የሚመረጡትም በምርጫ አይደለም »

ሲሉ አባዳ ካፊም በስብሰባዉ ላይ ንግግር አድርገዋል። አባዳ ካፊ ከ 21 ዱ የኒዳ ቱን የፓርላማ ተወካዮችአንዱ ነበሩ። የቀድሞ ፖለቲከኞ በፓርቲዉ ዉስጣዊ በሆኑ ምክንያቶች ፓርቲዉን ለቀዉ ሲወጡ የቀሩት አባላት ደግሞ ፓርቲያቸዉ ከቀድሞ የእስላማዊ ፓርቲ ኢናህዳ ጋር ጋር ጥምረት ሳይፈጥር አይቀርም ሲሉ በማሰላሰል ላይ ይገኛሉ። የ 55 ዓመቱ ሙክታር እንደሚሉት በምርጫ ወቅት ለኒዳቱን ፓርቲ ድምፅን ሰጥቻለሁ። በኒዳ ቱን ሥራ እጅግ በጣም ቅር ተሰኝቻለሁ ሲሉ ተናግረዋል። የሙክታር ምኞትና ተስፋ ኤናዳህን ሳይጨምር በቀድሞ ዋና ፀሐፊ ሞዘን ማዙክ አዲስ የሚመሰረተዉ ፓርቲ ለከፍተኛ ዲሞክራሲና ኤኮኖሚ እድገት ይታገላል የሚል ነዉ።

የቱኒዝያን ፕሬዚዳንት ኤስቢሲን የሚከተሉት የኒዳ ቱን ቡድኖች ለእስላማዊዉ ፓርቲ ምንም አላስጨነቃቸዉም። የኤህናዳ ፓርቲ ሊቀመንበር ተጠሪ ራሄድ ጋኑቺ ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ በዙስ በተካሄደዉ በዚህ ቡድን ስብሰባ ላይ በእንግድነት ተገኝተዉ ነበር። በስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግርም ከፍተኛ ጭብጨባ ተችሯቸዋል። በንግግራቸዉ ላይ በምሳሌያዊ አነጋገራቸዊ እንደጠቆሙት

«ቱኒዝያ እንደ አንድ ርግብ ትመሰላለች፤ ኢናህዳና ኒዳቱን ደግሞ ክንፎቹ ናቸው » ሲሉ ተናግረዋል።

የሕግ ጉዳይ አዋቂዉ ስሊም ላግማኒ እንደሚሉት የኒዳቱን ፓርቲ በመከፋፈሉ ምክንያት በቱኒዝያ ዉስጥ ያለዉ የፖለቲካ ምህዳር ተመጣጣኝ ለማድረግ የነበረዉ ህልም ሳይሳካ ቀርቷዋል።

በኤናዳና በኒዳ ቱን ፓርቲዎች የነበረዉ ጥያቄ ስለቱኒዝያ ማህበረሰብ ገጽታ ብቻም አልነበረም። በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የፖለቲካና የኤኮኖሚ ጥያቄዎች ፈጽሞ ተነስቶም አያዉቅም።

በቱኒዝያ ፓርላማ መንግሥት የፓርላማ አባሎችም መዉጣት የስልጣን ክፍፍሉን እንዲዘዋወር አድርጎታል። አክራሪ ሙስሊሞች በኒዳ ቱን ፓርቲ አብላጫዉን የፓርላማ መቀመጫ ይዘዉ ይገኛሉ። ስም የሌላቸዉ የአፈንጋጮቹ ቡድኖቹ በፓርላማዉ 3 ተኛዉን ቦታ ይዘዉ ነዉ የሚገኙት።

የተቀሩት የኒዳ ቱን የፓርላማ አባላት ባለፈዉ ረቡዕ ከነፃ የአገር ወዳድ ሕብረት «UPL» ፓርቲ ጋር የአራትዮሽ ፓርቲ ጥምረትን እንፈጥራለን ሲሉ አስታዉቀዋል። ኒዳቱን ፓርቲ ቢከፈልም በአስተዳደሩ በመጣመሩ በፓርላማ ዉስጥ አብላጫዉን ወንበር በማግኘት ጠንካራዉ ይሆናል።

የኢህናዳ ፓርቲ በፖለቲካዉ ከፍተኛዉን ቦታ በማግኘት መሪነቱን ይይዛል ሲሉ ስሊም ላግህማኒ ተናግረዋል። እስላማዊዉ ፓርቲ ባለፉት ምርጫዎች ብዙ ድምፅን አላገኘም መንግሥታዊ ኃላፊነትን ለመረከብም ምንም ዓይነት ፋላጎት የለዉም። የኢህናዳ ፓርቲ ይህንን የመሪነትን ዘመኑን በመጠቀም ለሚቀጥለዉ ምርጫ መዘጋጀትን ነዉ የሚፈልገዉ። በመጭዉ መጋቢት ወር ላይ የቀድሞ ኒዳ ቱን ፓርቲ አባላት በአዲስ ያቋቋሙትን ፓርቲ በይፋ ያስተዋዉቃሉ። የምርጫ የመጀመርያ ሙከራቸዉ ደግሞ በዓመቱ መጨረሻ ላይ በቱኒዚያ የአካባቢ ምርጫ ሲካሄድ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከምርጫዉ በኋላ ታድያ ከቀድሞዉ የኒዳ ቱን ፓርቲ መከፈሉ በአብላጫዉ ተጠቃሚዉ ማን እንደሆን የሚታይ ይሆናል።

አርንድ ሪክ / አዜብ ታደሰ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic