መከላከያ ሰራዊት የድሬዳዋ ተቃዋሚዎችን አስጠነቀቀ | ኢትዮጵያ | DW | 25.01.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

መከላከያ ሰራዊት የድሬዳዋ ተቃዋሚዎችን አስጠነቀቀ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ የድሬዳዋ ከተማ ተቃዋሚዎች "ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ ጠይቀችሁ መንገድ የዘጋችሁበትን ድንጋይ በመልቀምና በማንሳት መንገዱን ክፍት እንድታደርጉ" የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ጦሩ "ኹትና ነውጥ እንፈጥራለን" በሚሉ ላይ እርምጃ እንደሚወስድም አስጠንቅቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:54

መከላከያ ሰራዊት የድሬዳዋ ተቃዋሚዎችን አስጠነቀቀ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መንገድ በዘጉ የድሬዳዋ ከተማ ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠነቀቀ። የጦሩ የምሥራቅ ዕዝ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ተቃዋሚዎች የዘጉትን መንገድ እንዲከፍቱ አሳስቧል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ "በመልካም አስተዳደር ጉድለት ስም የህዝቡን ሠላማዊ ኑሮ እየታወከ" መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የምሥራቅ ዕዝ ችግሩ "በአመጽና በነውጥ ሳይሆን በውይይት" ሊፈታ ይገባል ብሏል።

ተቃዋሚዎች "ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ ጠይቀችሁ መንገድ የዘጋችሁበትን ድንጋይ በመልቀምና በማንሳት መንገዱን ክፍት እንድታደርጉ" የሚል ማሳሰቢያም ሰጥቷል። ጦሩ "ኹትና ነውጥ እንፈጥራለን ለሚል ፀጥታዉን ለማስከበርና ለህግ የበላይነት መከበር ሲባል አስፈላጊውን እርምጃ" እንወስዳለን የሚል ማስጠንቀቂያም ሰጥቷል።

ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ከአዲስ አበባ እና ከሐረር ወደ ከተማዋ የሚያጉዙ መንገዶችን ለሶስትኛ ቀን ዘግተው ውለዋል። የDW ዘጋቢ እንደታዘበው የከተማዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችም ግልጋሎት አይሰጡም።

ተቃዋሚዎች አደባባይ ለመውጣት ካስገደዷቸው ምክንያቶች መካከል የመልካም አስተዳደር እጦት እና የነዳጅ እጥረት እንደሚገኙበት በከተማዋ የሚገኘው የDW ዘጋቢ መሳይ ተክሉ ተናግሯል።

ወጣቶች በከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ደጃፍ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የጸጥታ አስከባሪዎች ወደ ብጥብጥ እንዳይሸጋገር ምክር ይለግሱ እንደነበር ዘጋቢያችን ተመልክቷል። ከአዲስ አበባ እና ከሐረር ወደ ድሬዳዋ የሚያመሩ መንገዶች ዛሬም ዝግ መሆናቸውን የገለጸው ዘጋቢያችን ከሰዓት በኋላ በከተማይቱ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡንም አክሏል።

በድሬዳዋ አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች በተለምዶ 40: 40: 20 ተብሎ የሚጠራው የስልጣን ክፍፍል ቀመር ሊያበቃ ይገባል የሚል ተቃውሞ አሰምተዋል። በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የስልጣን ክፍፍል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) 40 በመቶ እንዲሁም የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ) 40 በመቶ ድርሻ አላቸው። ቀሪው 20 በመቶ ለአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ለሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና ለደኢሕዴን የተተዉ ናቸው። የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የምክር ቤቱ የወንበር ክፍፍል ቀመር ጭምር በዚሁ ሥሌት ሲሰራ ቆይቷል።

ከDW የድሬዳዋ ዘጋቢ መሳይ ተክሉ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 


መሳይ ተክሉ 

አዜብ ታደሰ 
እሸቴ በቀለ 
 

Audios and videos on the topic