መንግስና ቤተክርስቲያን በአሜሪካ | ዓለም | DW | 21.09.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

መንግስና ቤተክርስቲያን በአሜሪካ

በአሜሪካ ህገ መንግስት መሰረት መንግስትና ቤተ ክርስቲያን ለየቅል መሆናቸዉ ይነገራል። የሚገናኙበት ነገር ቢኖር መሪዎቹ አማንያን ሲሆኑ የእነሱ አባልነት ብቻ ነዉ።

ቡሽ በኋይት ሃዉስ

ቡሽ በኋይት ሃዉስ


በያዝነዉ በዚህ ዘመናዊ ዘመን የአገሪቱ ፕሬዝደንት ሆኑዉ ኋይት ሃዉስ ከገቡት መካከል ጆርጅ ደብልዩ ቡሽ በጥቅሉ አማኝ መሆናቸዉ ተሰምቷል።በኢንዱስትሪ ከበለፀጉት ማህበረሰቦች አንጻር ሲታዩ አሜሪካዉያን ሃይማኖት አላቸዉ ማለት ይቻላል። ከአጠቃላዩ አሜሪካዊ ሁለት ሶስተኛዉ አማኝ ነዉ። በየሳምንቱ መጨረሻም አብያተ ክርስቲያናት በምዕመናን ተሞልተዉ ይታያሉ። አብዛኛዎቹ አሜሪካዉያን በየዕለቱ የሚፀልዩ ናቸዉ። ያዉም በግላጭ። ከሞት በኋላ ባለዉ ህይወትም ያምናሉ። እንዲህ ባለዉ ማህበረሰብ ዉስጥ ታዲያ በመንግስት ፖሊስ ሃይማኖት የራሱን ሚና ይጫወታል ቢባል ይገርም ይሆን? በመሰረቱ በአገሪቱ ህገ መንግስት መንግስትና ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ መሆናቸዉ ሰፍሯል። አማኝ ናቸዉ የተባሉት ፕሬዝደንት ቡሽም ይህን እንደማይጥሱ ሊነኩትም እንደማይሞክሩ የሃይማኖት ምርምር አድራጊዉ አለን ዋልፍ ይናገራሉ፣
«በአሜሪካ መንግስታ ቤተክርስቲያንን የመለየቱ ልማድ አሁንም ህያዉ ነዉ። ህያዉነቱ ለሃይማኖት ጥቅም ሲባል እንጂ ለዓለማዊዉ ህይወት አይደለም። ለግኑኘቱ ሲባል አዉሮፓ ዉስጥ በጥቅሉ የመንግስት ቤተ ክርስቲያን አለ። በአሜሪካ ግን የእምነት ነፃነት አለን። መንግስትና ቤተ ክርስቲያንም የተለያዩ ናቸዉ። ቤተ ክርስቲያንንና የመንግስት መለያየት ለማስታጎል አንዳንድ ሃይማኖታዊ ንቅናቄዎች ቢኖሩ ኖሮ ሃይማኖቱን ይገድለዉ ነበር። ይህን የሚያደርጉ ወገኖች ግን የሉም ማለት አይደለም፤ በብዛት ሲታይ ግን አብዛኛዉ መጥምቃዉያን የመንግስትንና የቤተ ክርስቲያንን መነጣጠል ደጋፊ ናቸዉ።»
በቡሽ ዘመነ መንግስት ሃይማኖት የራሱን ቅላፄ ይዞነዉ ኋይት ሃዉስ የገባዉ። እንደዉም እሳቸዉ የክፋት ዛቢያዎች ባሏቸዉ ላይ ክሩዝ ሚሳኤላቸዉን ሳያነጥሩ በፊትም ይኸዉ አካሄዳቸዉ ከመነሻዉ ታይቷል። በአከራካሪዉ የአዉሮፓዉያኑ 2000ዓ.ም የአገሪቱ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ስልጣን ላይ ሲወጡ ለእምነት የተለየ መድረክ ይዘዉለት ኋይት ሃዉስ ገቡ። መንግስታቸዉ ያለዉን ማህኣዊ ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣና አብያተ ክርስቲያናትም እንዲጠናከሩ አመቻችተዋል። የብሩኪንግ ተቋሙ ዊልያም ጋልስቶን ደግሞ ለተባሉት ለዉጦች በምክንያትነት የሚቀርበዉ የፕሬዝደንቱ ሚና ተጋኗል ባይ ናቸዉ፤
«ጠቀሜታዉን ማጋነን ይቻላል። በርካቶች ግን የሚደረገዉ ጥረት በአንጻሩ አነስተኛ ነዉ ብለዉ ያምናሉ። የእምነቱንና የሚደረገዉን ልዩነት ማወቅ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። እዉነታዉ በዩናትድ ስቴትስ በርካታ ግብረ ሰናይ ተግባር የሚከወነዉ በሃይማኖት ተቋማት አማካኝነት ነዉ። የፕሬዝደንቱ ተነሳሽነት ጥቂት ነገር ጨምሮ ሊሆን ይቻላል ማንም ግን እንዲህ ብሎ አያምንም።»
43ኛዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብልዩ ቡሽ የመጥምቃዉያን እምነት ተከታይ ናቸዉ። ቡሽ ወደእግዚአብሄር የመጡት ዘግየት ብለዉ የአልክሆል መጠጥን እርም ብለዉ በመተዉ ታታሪ ሰራተኛ ከሆኑ በኋላ ነዉ። የቡሽን ዜና መዋዕል ከሚዘግቡት አንደ ቦብ ዎድዎርድ ያሉ ጋዜጠኞች ቡሽ በሂደት ከፍተኛዉን ሃይል መቀበል የቻሉ በሚል በአፅንዖት ይገልጿቸዋል። በሌላ ወገን በርካታ ታዛቢዎች የሚሉትና የሚወስዱትን እርምጃ ሲያስተዉሉ ቡሽ የእምነት ሰዉ ናቸዉ ወይ ማለት ጀምረዋል። አለን ዎልፍ
«ሰዎች እንደሚሉት ያሉ ክርስቲያን ላይሆኑ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ። እኔ እንደምረዳዉ ያለ ክርስቲያንም አይደሉም። ክርስትና ማለት ትህትና፤ ሰላምና የእየሱስ ክርስቶስ በባህሪዉ እንዳለዉ ያለ ሰላምን የሚያስገኝ ብቃት የመሳሰሉት እኝህ ሰዉ ላይ አላይም። እኔ የጠቀስኳቸዉና የማስባቸዉን የመሳሰሉ ክርስቲያናዊ ነፀብራቆች በፕሬዝደንቱ ዉስጥ የለም። የዉጪ ፖሊሲያቸዉ በጣም አደገኛ ነዉ ብዬ አስባለሁ። አደገኛነቱ ከሃይማኖት የመጣ ሳይሆን ምናልባት ከሃይማኖት ለማገናኘት ስለታሰበ ወይም ከራሳቸዉ ከቡሽ የግል ባህሪ የተገኘ ይሆናል።»
በተጨማሪም በአሜሪካ የሚታየዉ የእምነት ነፃነት የተምታታ ቢጤነዉ ይላሉ ዊልያም ጋልቶን። ለምክንያቱም በመጪዉ የአዉሮፓዉያኑ 2008ዓ.ም ለፕሬዝደንታዊ ምርጫ ተፎካካሪ ከሚሆኑት ታዋቂ የሪፑብሊካን ፓርቲ አባላትን ይጠቅሳሉ።
«በተከታታይ የሚጠቀሱት ሶስት ስሞች ሴናተር ሜካን፤ የቀድሞዉ የኒዉዮርክ ኪንቲግ ጁሊያኒ እንዲሁም የቀድሞዉ የማቻችቴትስ ገዢ ሚግራኒ ሲሆኑ ሰዎቹ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እምነት በማጥበቅ ይነሳሉ። እነሱ ተፎካክረዉ የሚካሄደዉ ምርጫ ከእኩያን መካከል እንዱን ለመምረጥ የሚደረግ ምርጫ ያስመስለዋል።»
ምንም እንኳን ሪፑብሊካኖቹ እምነት ያላቸዉ ቢባሉም ድሮ ከነበረዉ ሃይማኖታዊ እሴት ድራሹ በመጥፋቱ ታዛቢዎጭን እያነጋገረ ነዉ። በአገሪቱ የሚታየዉ የሃይማኖት ነፃነት ያስከተለዉ ተዛጅ ቀዉስ የእምነት ሰዎችን ግራ አጋብቷል።