መንግስት «ሕግ ማስከበር» ያለው ዘመቻና አንድምታው | ዓለም | DW | 26.05.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

መንግስት «ሕግ ማስከበር» ያለው ዘመቻና አንድምታው

ሰሞኑን ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት በዋናነት አማራ ክልል እና አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ጋዜጠኞችን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችን እና ሌሎች ከአራት ሺህ በላይ የሆኑ ሰዎችን በጅምላ በማሰሩ የመብት ተሟጋቾች እና ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪዎች ብርቱ ነቀፋ እየሰነዘሩበት ነው።

በርካቶች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ታስረዋል

ሰሞኑን ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት በዋናነት በአማራ ክልል እና አዲስ አበባ ከተማ ጋዜጠኞችን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎችን እና ሌሎች ከአራት ሺህ በላይ የሆኑ ሰዎችን በጅምላ በማሰሩ የመብት ተሟጋቾች እና ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪዎች ብርቱ ነቀፋ እየሰነዘሩበት ነው። ዛሬ በመንግስት ፀጥታ ኃይላት ስለመታሰሩ የተሰማው የፍትህ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሳይጨምር በኢትዮጵያ በቅርቡ 11 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ አውታር ባለሞያዎች ለእስር መዳረጋቸውን CPJ ትናንት ገልጾ፦ «ባለሥልጣናት ያሰሯቸውን» ጋዜጠኞች በሙሉ «ያለምንም ክስ» እንዲፈቱ ሲል ጠይቋል። መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚል የጀመረው መጠነ ሰፊ የእስር ዘመቻ ለዲፕሎማሲው ጫናዎች በር እንዳይከፍቱ ሕጋዊነትን መከተል ይገባል ሲሉ ባለሞያዎች ተናግረዋል። 

ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው (CPJ) የተሰኘው ተቋም በኢትዮጵያ በቅርቡ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ አውታር ባለሞያዎችን ጨምሮ አማራ ክልል እና አዲስ አበባ ውስጥ መንግሥት «የሕግ ማስከበር» ባለው መጠነ ሰፊ ዘመቻ ከ4,500 በላይ ሰዎች ሕገወጥ ድርጊት ላይ ተሳትፋችኋል በሚል ለእስር መዳረጋቸውን የገለጠው ከሰሞኑ ነበር። እንደ CPJ ማብራሪያ ዛሬ በመንግስት ፀጥታ ኃሎች ስለመታሰሩ የተሰማው የፍትህ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሳይጨምር በኢትዮጵያ በቅርቡ 11 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ አውታር ባለሞያዎች ለእስር መዳረጋቸውን ገልጾ፤ «ባለሥልጣናት ያሰሯቸውን» ጋዜጠኞች በሙሉ «ያለምንም ክስ» እንዲፈቱ ሲል ጠይቋል፡፡

ድንበር የለሽ ጋዜጠኞች (RSF) ቡድን በበኩሉ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አማራ ክልል ውስጥ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና መገናኛ አውታሮች እንዲፈቱ ሲል ተመሳሳይ ጥሪውን አስተጋብቷል፡፡
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መመህር የሆኖት አቶ ሰለሞን ተፈራ እንደሚሉት ግን መሰል ተቋማት የሚያቀርቡት ክስ ከፍ ያለ የዲፕሎማሲ ጫናን የሚያስከትል በመሆኑ መንግስት የሕግ ማስከበር ሂደትን ከሰዎች ነጻነት ጋር በውል በማመጣጠን ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ መከተል ይኖርበታል ብለዋል፡፡ 

ሌላው ስለጉዳዩ አሳሳብነትና በመንግስት ሊደረግ ስለሚገባው ትንቃቄ አስተያየት ያጋሩን የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ፍራኦል ታፈሰ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ ከአራት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ በፌዴራል መንግሥት እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች “በተቀናጀ መንገድ የሕግ በላይነትን ማስከበር” በሚል ባለፉት ጥቂት ቀናት መውሰድ በጀመሩት እርምጃ፣ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን አሳውቆ፤ በርካታ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ መታሰራቸውን አመልክቷል።  ኢሰመኮ መንግስት ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር ሊታቀብ ይገባልም ነው ያለው በማሳሰቢያው። 

አዲስ አበባ ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን በጋዜጠኞችና ማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ ያካሄዳል ያለው የጅምላ እስር ዘገባዎች አሜሪካን እንዳሳሰባት ገልጾ፤ የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ ኃይላት ለሕግ የበላይነት ሒደት ተገዢ እንዲሆኑ ሲል የኢሰመኮን መግለጫ አስተጋብቷል፡፡ የአምቦ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይነስ መምህሩ አቶ ሰለሞን ተፈራ መሰል ጥሪዎች ለዲፕሎማሲ ጫና ምልክት በመሆናቸው የመንግስት የህግ ማስከበሩ ሂደት ሕጋዊነት በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነው ብለዋል፡፡ 

በቅርቡ በትግራይ እና አዋሳኝ የጦርነት ቃጣናዎች የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ ድጋፍ መቀላጠፍ ሲባል ያወጀው የተኩስ አቁም እወጃ አዎንታዊ የዲፕሎማሲ ውጤት ማስገኘታቸውን የሚያነሱት ባለሞያው፤ መንግስት የቀደመ የዲፕሎማሲ ጫና ውስጥ እንዳይገባ አሁንም የጥንቃቄ እርምጃዎችን ብከተል ብለዋል፡፡ ስለወቅታዊው የአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ ስለሚፈጸመው እስራት ከቀናት በፊት ለዶቼ ቬለ ማብራሪያ የሰጡት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ መንግስት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ይሰራል ባሉት ሰሞነኛ ርምጃዎች ከሕግ ውጪ የሚፈጸም እስራት አለመኖሩንና የመለየት ሥራው እንደሚከወን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡  

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic