መንግሥት ጭፍጨፋውን ማስቆም ለምን ተሳነው? | ኢትዮጵያ | DW | 10.07.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

መንግሥት ጭፍጨፋውን ማስቆም ለምን ተሳነው?

በኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት እዚህም እዚያም ኼድ መለስ ይል የነበረው ብሔርን መሰረት ያደረገ ግድያ እና ጭፍጨፋ ከሰሞኑ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱ ብርቱ ቁጣ ቀስቅሷል። ባለፉት ቀናት ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ውስጥ በአብዛኛው የአማራ ብሔር ተወላጆች በተከታታይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል። ሙሉ ውይይቱ በድምፅ ከታች ይገኛል።

ዳግም ሞት፤ ዳግም ሐዘን እንዳይከሰትስ ምን ይደረግ?

በኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት እዚህም እዚያም ኼድ መለስ ይል የነበረው ብሔርን መሰረት ያደረገ ግድያ እና ጭፍጨፋ ከሰሞኑ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱ ብርቱ ቁጣ ቀስቅሷል። ባለፉት ቀናት ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ውስጥ በአብዛኛው የአማራ ብሔር ተወላጆች በተከታታይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል። ጭፍጨፋው መጠኑ ይለያይ እንጂ ውሎ አድሯል። ከበደኖ እስከ አርባጉጉ እስከ ጉራፈርዳ፤ ፤ ከቡራዩ ግድያ፣ እስከ ቤንሻንጉል እስከ ወለጋ፤ በቅርቡም ከዓመታት በፊትም ጥቃት እና ግድያው አላባራም። አስደንጋጩ ጭፍጨፋም ለአንድ ሰሞን በከንፈር መጠጣ መታለፋቸው የተለመደ መስሏል። በዚህም ኹኔታው ወዴት እያመራ ይሆን ሲሉ በርካቶች በስጋት ይጠይቃሉ።

ስጋቱ በዚሁ ሳምንት በተከናወኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባዎች ላይም በአንዳንድ ተሳታፊዎች ጎልቶ ተስተጋብቷል። «ተጠያቂነት የለም»፤ «ጥቃት ከመድረሱ በፊት የፀጥታ ኃይላት በጊዜ እንዲደርሱ ቢጠየቁም እንዳይደርሱ ይደረጋል» የሚሉ ቅሬታዎች በምክር ቤቱ አባላት ተሰምተዋል። ከተደጋጋሚ ጥያቄዎች በኋላም የአንድ ደቂቃ ጸሎት ተደርጓል። ምክር ቤቱ «በንጹሐን ዜጎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት» በማለትም አጣሪ ኮሚቴ ለማቋቋም ወስኗል። የመንግሥት አቅም ማነስ እስከምን ድረስ ነው የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ግን ተስተጋብተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፦ «ጥቃቱ የአማራ ብሄር ተወላጆችን ዒላማ ያደረገና ተጠቂዎችን ለመከላከል ሙከራ ባደረጉ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጭምር ያነጣጠረ ነው» ሲሉ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ጽፈዋል። ኅብረተሰቡ ራሱን መከላከል እንዲችልም፦ «የሚሊሻ እና የኮሙኒቲ ፖሊሲንግ ስርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል» ብለዋል። አንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የገዢው ፓርቲ አባላት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ችግር እንዳለ በግልጽ እየተናገሩ ነው። ጥቃቱ የሚደርስበት ማኅበረሰብም በመንግሥት በኩል በቂ ጥበቃ እንደማይደረግለት በተደጋጋሚ በመግለጥ ተማጽኖውን እያሰማ ነው። መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ለምን ተሳነው?  ተወያዮቹ፦ በሳምንታዊ የውይይት መድረክ አራት እንግዶች ተሳታፊ ኾነዋል።

  1. አቶ ሆነ ማንደፍሮ፤ የአማራ ማኅበረሰብ በአሜሪካ አድቮኬሲ ዳይሬክተር፤
  2. አቶ አምሓ መኮንን፤ የሕግ ባለሞያዎች ለሰብአዊ መብት ዋና ዳይሬክተር
  3. አቶ ያሬድ ኃይለማሪያም፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ማእከል ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም
  4. አቶ መስፍን አማን የፖለቲካ ተንታኝ እና ጸሐፊ ናቸው። 

ሙሉ ውይይቱን በድምፅ ማጫወቻው ማዳመጥ ይቻላል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች