መንግሥት ዜጎች ላይ የሚታየዉን ጭፍጨፋ እንዲያስቆም ተጠየቀ | ኢትዮጵያ | DW | 21.06.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

መንግሥት ዜጎች ላይ የሚታየዉን ጭፍጨፋ እንዲያስቆም ተጠየቀ

ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን በማንነታቸው ብቻ ተለይተው ጭፍጨፋ ለተፈፀመባቸው ሰዎች ምክንያቱ ከመንግሥት ቸልታ እና አደጋውን ለማስቆም ካለመፈለግ የመነጨ ነው ሲሉ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል ባወጧቸው መግለጫወች ገለፁ።

በሰዎች ላይ የደረሰዉ ጭፍጨፋ ከመንግሥት ቸልታና አደጋውን ለማስቆም ካለመፈለግ የመነጨ ነው

ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን በማንነታቸው ብቻ ተለይተው ጭፍጨፋ ለተፈፀመባቸው ሰዎች ምክንያቱ ከመንግሥት ቸልታ እና አደጋውን ለማስቆም ካለመፈለግ የመነጨ ነው ሲሉ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል ባወጧቸው መግለጫወች ገልፀዋል። ፓርቲዎቹ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ እና በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ አለመውሰዱ ተመሳሳይ የጅምላ ግድያዎች በየጊዜው እንዲፈፀሙ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ድርጊቱ ከፍተኛ የወንጀል ድርጊት እንደሆነና ንፁሃንን የማሸበር ተግባር መሆኑን በመጥቀስ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመ ግድያ ፣ ጭፍጨፋ እንዲሁም ፍጅት እንዳለ ጉባኤው መገንዘቡን የጉባኤው ሰብሳቢው ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለ DW ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለማስቆም መንግሥት አቅም የለውም የሚል እምነት እንደሌለው ያስታወቀው ጉባኤው አስፈላጊ ከሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ ወይም መንግሥት የሕወሓት ኃይሎችን ለመመከት እንዳደረገው የህልውና ዘመቻ ጥሪ ሊያደርግ እንደሚችልም አስታውቋል። ቀሲስ ትታጋይ ታደለ አክለውም "በንፀሃን ላይ የተፈፀመ ግድያ ፣ ጭፍጨፋ እንዲሁም ፍጅት እንዳለ ጉባኤው ተገንዝቧል። በሀገራችን የሚታየው የሃይማኖት ማንነት እና የብሔው ውግንናን መሰረት በማድረግ የሚፈፀም ጥላቻ፣ ማፈናቀል፣ ግድያና ፍጅት እየተባባሰ መሄዱን ፣ በተለይ ከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት እንደሆነ መቀጠሉ በእጅጉ የሚያሳስብ እንደሆነ ጉባኤው በአጽንዖት አንስቷል። ከፍተኛ የወንጀል ድርጊት እንደሆነና ንፁሃንን የማሸበር ተግባር መሆኑንም ጉባኤው ተምልክቷል" ብለዋል።

"አደጋው ነገ በእያንዳንዱ ቤት ላለመግባቱ ምንም ማረጋገጫ የለም" ያለው እናት ፓርቲ በበኩሉ መንግሥት መሠረታዊ ሕግ የማስከበር ሥራውን እንዲከውን ጠይቋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ( ኢዜማ ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲዎች መንግሥት ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ተጠያቂ ነው ብለዋል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ በተለይ " የኦሮሞ ሕዝብ ደም መፍሰስ እንዲቆም ተቃውሞ እንዲያሰማ" ሲል ጠይቃል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በበኩሉ "ችግሩ ለዓመታት የዘለቀ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ በመሆኑ መንግሥት እና ኢትዮጵያዊያን ጥቃቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችል መዋቅርና ሥርዓት ሰራሽ ሽግግር እንዲደረግ" ሲል ጠይቃል። 

 ሰኔ 14 ቀን፣ 2014 ዓ. ም መደበኛ ጉባኤውን ለማድረግ የተሰየመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዕለቱ አጀንዳ ላይ ከመወያየቱ በፊት አስቸኳይ አጀንዳ ስላለ ይታይልን በሚል ለዋና አፈ ጉባኤው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አብን ) ተመራጭ አባል ጥያቄ ቢያቀርቡም አፈ ጉባኤው ፈቃድ ባለመስጠታቸው በምክር ቤቱ የፓርቲው ተመራጭ ተወካዮች ጉባኤውን ረግጠው ወጥተዋል።

ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ 
ነጋሽ መሐመድ
 

Audios and videos on the topic