መብት አልባዎቹ ስደተኞች በሊቢያ  | ዓለም | DW | 24.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

መብት አልባዎቹ ስደተኞች በሊቢያ 

የሰዎች አሻጋሪዎች በሊቢያ የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ብዙም ቁጥጥር በማይደረግባቸው የሀገሪቱ ደቡባዊ ድንበሮች በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ያስገባሉ። ይህ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚታፈስበት ሥራ ሆኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:13
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:13 ደቂቃ

ስደተኞች በሊቢያ

በአሁኑ ጊዜ በሊቢያ ቁጥራቸው አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ስደተኞች አሉ ተብሎ ይገመታል። ስደተኞቹ በዚያ ቁም ስቅል እና ባርነትን ጨምሮ የተለያዩ በደሎች ይፈጸሙባቸዋል። አብዛኛዎቹ ተስፋ በመቁረጥ በደካማ ጀልባዎች ወደ አውሮጳ ለመሻገር ይሞክራሉ። ይሁን እና ኢጣልያ እና ሊቢያ በቅርቡ የተስማሙት ውል ይህን መሰሉን አደገኛ የባህር ጉዞ እያገደ ነው።  

ለአብዛኛዎቹ ሊቢያ ለሚገኙ ስደተኞች ጉዞአቸው በዚያው በተነሱበት ስፍራ አብቅቷል። ሊቢያ ርዕሰ ከተማ ትሪፖሊ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ አቧራማ አደባባይ ላይ ቁጥራቸው ወደ አንድ መቶ የሚጠጋ ወንዶች አፍሪቃውያን ተቀምጠዋል። ራሳቸውን አናት ከሚባሰው ፀሐይ ለመከላከል በእጃቸው ሸፍነዋል። ላባቸው በፊታቸው ይንቆረቆራል። ከፊት ለፊታቸው የደንብ ልብስ የለበሰ ታጣቂ እነርሱን ይጠብቃል ። ስፍራው አዳዲስ ስደተኞች የሚታጎሩበት ቦታ ነው። አልፎ አልፍ አንድ ሰው በትናንሽ ኩባያዎች ውሐ ያድላቸዋል።  «ምግብ እና ውሐ መቼ እንዳገኙም ሆነ ምን እንደተፈፀመባቸው አናውቅም» ትላለች አና። 
ሮይተርስ የዜና ወኪል ያነሳቸው ፎቶዎች በሊቢያ አሁን  ያለውን ድራማ ያሳያሉ። የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ፣በጀልባ ከሊቢያ ተነስተው ወደ አውሮጳ ለመሻገር ሙከራ ያደረጉ ሰዎችን ይዞ ወደ ተነሱበት ይመልሳል። 

   «ምንም አያጠራጥርም ኢጣልያ ለመሄድ ነበር የምንፈልገው።የተሻለ ህይወት እና ክብር ያለው ህይወት ፍለጋ። በሐገሪቱ የሚሆነው እጅግ የከፉና ጭካኔ የተሞላባት እርምጃ በመሆኑ የሚመጣውን በመጋፈጥ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ከመሞከር እና ኢጣልያ የባህር ዳርቻ ሳንደርስ እንዳንሞት ከመጸለይ በስተቀር ምንም ምርጫ የለንም። በርግጥ ይህ ነበር ግባችን»
ይላል ሱዳናዊው ስደተኛ። በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከሊቢያ በአደገኛ የባህር ጉዞ ለመሰደድ የሚዳርጋቸው በዚያ የሚደርስባቸው በደል እና ስቃይ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚያ ሲነሱም አንዳንዶቹ በሰው አሻጋሪዎች አስገዳጅነት በሰዎች በታጨቀ ጀልባ እንዲጫኑ ይደረጋሉ። ሪች የተባለው ድርጅት ለተመ የህጻናት መርጃ ድርጅት በምህጻሩ ዩኒሴፍ ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ሊቢያ ከሚገኙ አፍሪቃውያን ስደተኞች ጥቂቶች ብቻ ናቸው ገና ከሀገራቸው ሳይነሱ በጀልባ የሜዴትራንያንን ባህር የማቋረጥ እቅዳቸውን የሰረዙት። ብዙዎች በሀገራቸው የሚፈፀሙባቸውን በደሎች በመሸሽ በሌላ የአፍሪቃ ሀገር ደስተኛ ህይወት የመምራት ተስፋ ሰንቀው ነው ሊቢያ የሚሄዱት። ሊቢያ አሁንም ሀብታም ሀገር ተደርጋ ነው የምትቆጠረው። ከአፍሪቃ በነዳጅ ዘይት የበለፀገችው የሊቢያ ህዝብ ከዓመታት በፊት ከሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት ጋር ሲነጻጸር የተንደላቀቀ የሚባል ኑሮ ይኖር  ነበር። የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሞአመር ጋዳፊ  ከተገደሉ በኋላ ግን ሀገሪቱ ቀውስ ውስጥ ናት። ልዩ ልዩ ሚሊሽያዎች ሥልጣን ለመያዝ እየተዋጉ ነው። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውቅና የሰጠው የትሪፖሊ  መንግሥት ደካማ ነው። አንድ ተሰሚነት ያላቸው ጀነራል ምሥራቅ ሊቢያን እየመሩ ነው። ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው በምህጻሩ IS የተባለው ቡድንም በሀገሪቱ ይንቀሳቀሳል። ቡድኑ በተደጋጋሚ ጊዜያት ከሚሊሽያዎች ጋር ውጊያ ያካሂዳል። የሰዎች አሻጋሪዎች በሀገሪቱ የተፈጠረውን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ብዙም ቁጥጥር በማይደረግባቸው የሀገሪቱ ደቡባዊ ድንበሮች በሺህዎች የሚቆጠሩ

ስደተኞችን ያስገባሉ። ይህ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚታፈስበት ሥራ ሆኗል። ወደ ሊቢያ የሚሄዱ ሰዎች መጀመሪያ ጥቃት ነው የሚፈጸምባቸው። ሴቶች ይደፈራሉ፤ቤተሰብ ይለያያል። ህጻናት እና አዋቂዎች ለዘመናዊ ባርነት ይዳረጋሉ። 1 ሚሊዮን እንደሚሆኑ የሚገመቱ ሊቢያ ያሉ ስደተኞች ህገ ወጥ ነው የሚባሉት። እነዚህን ረዳት የሌላቸው ሰዎች የሊቢያ ወሮ በሎች ለነርሱ እንደሚያመቻቸው አድርገው ያሰቃይዋቸዋል። መንግሥት እንዲሁም ግለሰቦች የሚቆጣጠሯቸው የስደተኞች ማጎሪያዎች አሉ። ከመካከላቸው የተሻሉ የተባሉት እንኳን በሊቢያ የተመ ልዩ ልዑክ ማርቲን ኮብለር ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የሚገኙበት ሁኔታ ዘግናኝ ነው።
«ሰዎች በየተራ ነው የሚተኙት። አንዳንዶቹ በሽተኞች ናቸው። አንዳንዶቹም ይሞታሉ። በቂ ምግብ የላቸውም። በእውነት በጣም መጥፎ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት» 
ለአዳዲስ ስደተኞች ቦታ ለማስለቀቅ ቁም ስቅል ማሳየት መድፈር በዘፈቀደ መግደል እንደሚፈፀም ስደተኞች ይናገራሉ።» 
ሪች ለዩኒሴፍ ባካሄደው ጥናት ካነጋገራቸው 850 ወጣት ስደተኞች በአጠቃላይ ሊቢያ ከስደት ጉዞአቸው ሁሉ እጅግ የከፋው ቦታ መሆኑን ነው መረዳት የሚቻለው። በሊቢያ በወሮ በሎች ታግተው ከሀገራቸው ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲልኩ የሚጠየቁ፣ ያለ ምክንያት የታሰሩም ብዙዎች ናቸው። በሐገሪቱ የሰፈነው ህግ አልባነት ያስከተለው ተስፋ መቁረጥ ወጣቱ ከሊቢያው ስቃይ ለማምለጥ በአደገኛ የባህር ጉዞ ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚያነሳሳው ምክንያት ሆኗል። ይሁን እና ወደ አውሮጳ ለመሄድ ከሊቢያ የሚነሱት ስደተኞች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢጣልያ ባህር ኃይል በሚታገዙት የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ወደ ተነሱበት እየተመለሱ ነው። ዓለም አቀፉ የስደት ጉዳይ ድርጅት በምህጻሩ አይ ኦ ኤም እንደሚለው ባለፉት ሰባት ወራት በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሞከሩ 12ሺህ ስደተኞች ወደ ሊቢያ እንዲመለሱ ተደርጓል።  
አና ኦስዩስ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች