መብራት በፈረቃ እና ስያሜ ለከዋክብቱ ስብስብ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 24.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

መብራት በፈረቃ እና ስያሜ ለከዋክብቱ ስብስብ

ለከዋክብት ስብስቡ ስያሜ ቀደም ሲል መሰጠቱን የሚገልጥ ጽሑፍ ከሳምንታት በፊት  ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ላይ መስፈሩን በመጥቀስ ማስተካከያ እንዲደረግ የጠየቊም ነበሩ። የኮከቧ ስያሜ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን በምሽት ጽልመት የመብራት ፈረቃ ውስጥ እንደገቡ ይፋ በተደረገበት ሰሞን መኾኑ ይበልጥ የመነጋገሪያ ርእስ ኾኗል።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:16

ለኮከቧ የዳቦ ስም ፍለጋ፥ መብራት በፈረቃ

የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም አቀፉ ሥነ-ፈለክ ኅብረት ተቋም አዲስ ተገኘች ላላት ኮከብ ኢትዮጵያውያን ስም እንዲያወጡ በይፋ መጋበዙ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል። ብዙዎች ለከዋክብቱ ስብስብ ስያሜ ያሉትን የላኩት በፍጥነት ነበር።  ለከዋክብት ስብስቡ ስያሜ ቀደም ሲል መሰጠቱን የሚገልጥ ጽሑፍ ከሳምንታት በፊት  ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ላይ መስፈሩን በመጥቀስ ማስተካከያ እንዲደረግ የጠየቊም ነበሩ። የኮከቧ ስያሜ ጉዳይ ኢትዮጵያውያን በምሽት ጽልመት የመብራት ፈረቃ ውስጥ እንደገቡ ይፋ በተደረገበት ሰሞን መኾኑ ይበልጥ የመነጋገሪያ ርእስ ኾኗል።  

ለኮከቧ የዳቦ ስም 

የጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት ግንቦት 14 ቀን፤ 2011 ዓም በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሩ ላይ ያወጣው ጽሑፍ፦ «ኢትዮጵያ አንድ አዲስ ለተገኘ ግዙፍ የህዋ አካል ስም እንድታወጣ እድሉ ተሰጣት» በሚል ይነበባል። «ስም በማውጣቱ አኩሪና ታሪካዊ ሂደት ከልባችሁ እንድትሳተፉ ይህ ሀገራዊ ጥሪ ቀርቦላችኋል» በማለት ነው ዘለግ ያለው መልእክት የሚጠናቀቀው።  

ብዙዎች በመሰላቸው መንገድ የተለያዩ ስሞችን ሲጠቊሙ፤ ጸደይ በትዊተር ጽሑፏ፦ «የተለየ ታሪካዊ እድል አይደልም። ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያውያን ስም የብዙ ከዋክብት ስም ወጥቷል። ይሄንን ታሪክ መጥቀስ ይገባቹህ ነበር...» ብላለች። ከዓውደ-ነገሥት ወፍካሬ ከዋክብት ጥንታዊ መጽሐፍ የተቀነጨበ የከዋክብትን ባሕሪ የሚያሳይ ፎቶም አያይዛለች።

ስም በማውጣቱ በኩል አብዛኛዎቹ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች የየራሳቸውን ፍላጎት እና አመለካከት ለማንጸባረቅ ሞክረዋል። ኹኔታው የገረመው «ዋን ኢትዮጵያ» በሚል የትዊተር ተጠቃሚ፦ «የጋራ የሚያደርገን ካጣን ያገኙዋት ያውጡላት» ብሏል። «አንዱ አብሲኒያ ሲል ሌላው ገዳ ካልተባለ ይላል። ሌላው ጥቁር ሰው ትባል ሲል አንዱ ደግሞ ቄሮ ትባል ይላል። አንዱ ምንሊክ ሲል ሌላው አብይ ይላል። ትጉሆች ፈልገው ባገኙዋት እንዴት በስም እንጣላሲልም ጠይቋል።

ጨርቆስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽሑፉ ባስነበበው መልእክቱ፦ ስያሜው ከሦስት ሳምንት በፊት ተሰጥቶ እንደተጠናቀቀ በመግለጥ የጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት የትዊተር መልእክቱን እንዲያስተካክል ጠይቋል። እንደመረጃም ሚያዝያ 24 ቀን፤ 2011 ዓም መኮንን ካሣ ስለኮከብ ስያሜ የጻፈውን አያይዟል።

«የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ» በመባል የሚታወቀው ተቋም የክብር አባል እንደኾኑ የገለጡት መኮንን ካሳ የከዋክብት ስብስቡ «ኢትዮጵያ» በሚል መሰየሙን የሚገልጥ የኢሜል መልእክት ከሦስት ሳምንት በፊት እንደደረሳቸው ጠቅሰዋል። በእርግጥ መኮንን ካሣ ከ«የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ» እንደተላከላቸው በመግለጥ ያያዙት የኢሜል ጽሑፍ የእንግሊዝኛ ቋንቋው የሰዋሰው ስህተት ቢኖረውም፤ የሚከተለውን በአማርኛ ጽፈዋል። «አለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ማሕበር ከአሁን በፊት አንድሮሜዳ በመባል የሚታወቀዉን የከዋክብት ስብስብ፣ ስሙ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ በመባል እንዲጠራ ወስኗል። ኢትዮጵያዉያን የሕዋ ተመራማሪዎች እንደነበሩ፣ ከዋክብቶችን ስም እንደሰጧቸዉ ይታወቃል» ይላል የመኮንን ካሣ ጽሑፍ።

መብራት በፈረቃ

ኢትዮጵያ እስከ መጪው ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ኤሌክትሪክ በፈረቃ ማከፋፈል ልትጀምር እንደኾነ መግለጧ እንደተሰማ ቊጣም ቀልድም መፈራረቅ  የጀመረው ወዲያው ነበር። የመብራት ፈረቃውን የቀልድ ምንጭ አድርገው የተጠቀሙበት በርካቶች ናቸው። ቴዲ ጆቡርግ በፌስቡክ ጽሑፉ፦ «እኔ ምለው የአምስት አመት ትራስፍርሜሽን ገለመሌ ግልገል ግቤ 1 2 3 ምናምን ተመረቀ የሚሉን ምንድ ነው የበግ ግልገል ነው የውኃ?» ሲል በቀልድ መልክ ጠይቋል።

ብሩክ አርዓያ ደግሞ እዛው ፌስቡክ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዓርማዎችን ከላይ እና ከታች በማድረግ ቀጣዩን ጽፏል። «መጪውን የአፍሪቃ ዋንጫ ሙሉውን እናስተላልፋለን» የሚለው ሐረግ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዓርማ ጎን ይታያል። ከታች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አጠገብ ደግሞ ቀጣዩ ጽሑፍ ይነበባል፦ «ሞቼ ነው ቆሜ

ከቀልዱ ባሻገር ቆፍጠን ያሉ መልእክቶችም ታይተዋል። አክት ላይክ ኢትዮጵያ በሚል ስም የትዊተር ተጠቃሚ በኢትዮጵያ ዜና እንዳታከተ በመግለጥ ቀጣዩን መልእክት አስነብቧል። «ኢትዮጵያ የአሜሪካን እና የኢራንን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለች ነው» ይላል በትምህርተ-ጥቅስ የሰፈረው ርእስ፤ አስተያየት ሰጪው ይቀጥላል፦ «አሁን እነሱን መከታተል ትታችሁ መብራት አምጡልን።»

ሚኪያስ ተስፋዬ  «ለጨጓራ በሽታ የሚያጋልጡ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች» ሲል ቀጣዩን ትዊተር ላይ ጽፏል። «1. መብራት ኃይል፤ 2. ውኃ ልማት፤ 3. ቴሌ። መብራት የለም፤ ውኃ የለም፤ ኔትወርክ የለም፤ ሲስተም የለም» ያለው ሚኪያስ «ሀይ ባይ የለም ሲልም ይጠይቃል። ኾኖም አሁንም ድረስ ተስፋ እንዳልቆረጠ፤ ይኼም እንደሚታለፍ በእንግሊዝኛ አክሎ ጽፏል። 

«የእኛ ነገር አንድ ወደፊት አምስት ወደ ኋላ» ስትል ትዊተር ላይ የጻፈችው ሐና ጫላ ደግሞ፦«እንዴ እኔ እኮ በቀን 5 ሰዓታት መብራት የሚጠፋበት መስሎኛል ለካ የሚበራበት ነው» ብላለች።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ባለፈው ሳምንት እሁድ ፌስቡክ ገጹ ላይ ያወጣው መግለጫ በእየ ስድስት ሰአቱ ልዩነት በሦስት ፈረቃ የነበረው አሠራር አመቺ ባለመኾኑ እንደተቀየረ ይገልጣል። እንዲህ ይነበባል። «ይህ ሦስት ፈረቃ ለአሠራር ምቹ ባለመሆኑ በሁለት ፈረቃ ሊደረግ ችሏል። በዚህም መሰረት በአዲስ አበባና አካባቢው የመብራት ፈረቃው ከማለዳው 11:00 እስከ ቀኑ 8:00 እና ከቀኑ 8:00 እስከ ምሽቱ 4:00 ሰዐት ሆኗል። ሁለቱ የፈረቃ ሰዐት በመቀያየር አገልግሎት ላይ የሚውሉ መሆኑንም አገልግሎቱ አስታውቋል። በሌሎች የሀገሪቱ ክልሎችም ያለውን መርሀ ግብር በክልል፤ በዲስትሪክትና አገልግሎት መስጫ /ቤቶች አማካኝነት የሚገለጽ ይሆናል ተብሏል» ይላል።

«ለአዲስ አበባ መብራት ሳይኖር፣ ውኃ ሳይኖር፣ በቂ የጤና ሽፋን ሳይኖር፣ በቂ የትራንስፖርት አገልግሎት ሳይኖር፣ የመኖሪያ ቤት እጦት እያሰቃየን...29 ቢሊዮን ብር የወንዝ ዳር ማስዋቢያ ካልሠራሁ ሞቼ እገኛለሁ ማለት የጤና አይደለም» ሲል የጻፈው ደግሞ ዳዊት ተስፋዬ ነው፤ ትዊተር ገጹ ላይ።

ግብዣ ከጠቅላይ ሚንሥትሩ ጋር

ሌላው ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎችን ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች መካከል ከጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ ጋር የአምስት ሚሊዮን ብር ገበታ ግብዣ ነበር።

የእራት ግብዣው በታላቁ ቤተ መንግሥት በአፄ ምኒልክ የግብር አዳራሽ ነበር የተዘጋጀው። በ«ገበታ ለሸገር» የእራት ሥነ ሥርዓት ላይ ከ240 በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸው እና ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገልጧል።  «ማይ ኢትዮጵያ» በሚል የትዊተር ተጠቃሚ፦ «እጅግ የሚያስደስት ተግባር ነው» ሲል አድናቆቱን አስፍሯል። 

ዳዊት በጋሻው፦ «አንድ ቀን ተፈናቃዮችን ያላሰበ አርቲስት ሁሉ ገበታ ለሸገር ወንዝ ምናምን ሲሉ ማየት ደም ያፈላል» የሚል አስተያየት ትዊተር ላይ ጽፏል።

ግዛው ለገሰ ፌስቡክ ላይ ባሰፈረው ዘለግ ያለ ጽሑፍ «ገበታ ለሸገር፤ ብር 5 ሚሊዮን የገበታው ዋጋ በሰው» የሚለውን የማስታወቂያ ጽሑፍ ተችቷል።  «ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባለሃብቱ አገልጋይ ነው» ያለው ግዛው uሑፍ «ከጠ/ሚር ዐብይ አሕመድ ጋር ገበታ ይቅረቡ ብሎ ማስቀመጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያለቅጥ ማግዘፍ» ያስመስላል ብሏል። 

ጠቅላይ ሚንሥትሩ በተገኙበት «የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የአብሮነት እና የምስጋናና የኢፍጣር» መርሐ ግብር የተከናወነው በዚሁ ሳምንት ነበር። ሙስሊሞች በአንድነት ተሰባስበው በጋራ በማፍጠራቸው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ደስታቸውን የገለጡ በርካቶች ናቸው። ሥነ-ሥርዓቱ በሚሊኒየም አዳራሽ ሲከናወን ንግግር ያሰሙት ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ፦«መንግሥት በጠየቃችሁት ሁሉ እና አቅም በፈቀደ ሁሉ ከጎናችሁ ኹኖ ለአንድነታችሁ የሚሠራ መኾኑን በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ» ብለዋል። የሙስሊሙ አንድነት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቃሚ መኾኑም ተገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic