መቋጫ ያላገኘው የብሬግዚት ውል  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 09.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

መቋጫ ያላገኘው የብሬግዚት ውል 

ሜይ ተስፋ የጣሉበት ከሌበር ጋር የጀመሩት ድርድር ካልተሳካ ሁለት አማራጮች ብቻ ናቸው የሚጠብቋቸው። ያለ ሥምምነት መውጣት አለያም የረዥም ጊዜ ማራዘሚያ ጠይቆ በአውሮጳ ፓርላማ አባላት ምርጫ መሳተፍ። ብሪታንያ ያለስምምነት ህብረቱን ለቃ የምትወጣ ከሆነ ብሪታንያም ሆነች የአውሮጳ ህብረት የበኩላቸውን ዝግጅት አድርገው እየተጠባበቁ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:09

መፍትሄ ያላገኘው የብሬግዚት ውል

የብሪታንያ መንግሥት ከአውሮጳ ህብረት ለመውጣት የተስማመበት የብሬግዚት ውል እስካሁን የብሪታንያ ፓርላማ አባላትን ድጋፍ ማግኘት አልቻለም። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ግን የብሬግዚት ቀነ ገደብ እንዲገፋ ጥያቄ አቅርበዋል። የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ነገ በጥያቄው ላይ ተነጋግረው ውሳኔ ያሳልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ከአውሮጳ ህብረት ጋር የተስማሙበትን የብሬግዚት ውል የሀገሪቱ ፓርላማ ሦስት ጊዜ ውድቅ ቢያደርግባቸውም አሁንም ተስፋ የቆረጡ አይመስልም። ፓርላማቸው ውሉን እንዲቀበል ሜይ አሁንም የተለያዩ ጥረቶችን ከማድረግ አልቦዘኑም። ወይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ጀርሚ ሀንት እንዳሉት «የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም።» ከቅርብ ጊዜዎቹ ጥረቶቻቸው አንዱ ሀገራቸው ህብረቱን ለቃ የምትወጣበት ቀነ ገደብ እንደገና እንዲገፋ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ምክርቤትን በደብዳቤ መጠየቃቸዉ ነው። ሜይ በዚህ ደብዳቤ ቀነ ገደቡ እስከ ጎርጎሮሳዊው ሰኔ 30፣2019ዓም እንዲራዘም ነው የጠየቁት። ሆኖም ከሁለት ሳምንት በፊት ይህንኑ ጥያቄ አቅርበው ህብረቱ ቀነ ገደቡን ወደ ጎርጎሮሳዊው ግንቦት

22፣2019 ዝቅ አድርጎ የብሪታንያ ፓርላማ እስከ ፊታችን አርብ ድረስ አዲስ እቅድ ይዞ እንዲቀርብ አለያም ያለስምምነት ለመውጣት እንዲወስን ነው የጠየቀው። ሜይ አርብ ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ዛሬ ከጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልና ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮ ጋርም መክረዋል። የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች ነገ በጥያቄአቸው ላይ ለመወሰን ጉባኤ ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሜይ በህብረቱ ውድቅ የተደረገውን ጥያቄአቸውን መልሰው የማቅረባቸው ምክንያት የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡበት ነው። አንዳንድ ተንታኞች ሜይ ይህን የሚያደርጉት ብሪታንያ በተለይ ከህብረቱ ያለ ስምምነት የምትወጣበት ሁኔታ ከተፈጠረ ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማሸሽ ነው የሚሉ አስተያየቶች ይሰጣሉ። ይህን ከሚሉት አንዱ በአውሮጳ የፖሊሲ ጥናት ማዕከል የብሬግዚት ጉዳዮች ተንታኝ ላሪሳ ብሩነር ናቸው። 
«እንደሚመስለኝ ቴሬሳ ሜይ ምናልባት የአውሮጳ ህብረት ለርሳቸው ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ይፈልጋሉ። ምክንያቱም የአውሮጳ ህብረት በአመዛኙ ላቀረቡት ጥያቄ አይሆንም የሚል መልስ

ሊሰጣቸው እንደሚችል ያውቃሉ። ስለዚህ በመሠረቱ የአውሮጳ ህብረት ምንም ይወስን ምን ይስማማም፣አይስማማ እርሳቸው ችግሩን በህብረቱ ሊያላክኩ ይችላሉ።እናም ህብረቱ ቀነ-ገደቡን ለማራዘም ካልተስማማ እና ይህም በሚቀጥለው ሳምንት ብሪታንያ ያለ ስምምነት ከህብረቱ የምትወጣበትን ሁኔታ ካስከተለ የአውሮጳ ህብረትን ተጠያቂ ሊያደርጉ ይችላሉ።» 
ሌሎች ተንታኞች ደግሞ  ሜይ አሁን የይራዘምልኝ ጥያቄ ያቀረቡበት ምክንያት   ባለፈው ሳምንት ከተቃዋሚው ከሌበር ፓርቲ ጋር የጀመሩት ጥረት ነው ይላሉ።  እነዚህ አስተያየት ሰጭዎች   የብሬግዚት ውል የፓርላማውን ድጋፍ እንዲያገኝ ሜይ በብሪታንያ ፓርላማ ብዙ አባላት ካሉት ከተቃዋሚው ከሌበር ፓርቲ ጋር በጀመሩት ውይይት ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል የሚል ተስፋ ስላላቸው ነው ቀነ ገደቡ እንዲገፋ የጠየቁት ይላሉ። የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴም ምክንያቱ ይኽው ነው ይላል።
የሁለቱ ፓርቲዎች ዋነኛ  ልዩነት ብሪታንያ ከህብረቱ ከወጣች በኋላ በአውሮጳ ደረጃ በተዘረጋው የጋራ የቀረጥ ስምምነት ስር ትቀጥል አትቀጥል የሚለው ነው። ሜይ የሚመሩት ወግ አጥባቂ

ፓርቲ ይህ ስምምነት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ይጋፋል ሲል ይቃወማል። ሌበር ደግሞ ብሪታንያ የዚህ ስምምነት አካል ሆና እንድትቀጥል ይፈልጋል። ሜይ እስካሁን ከሌበር መሪዎች ጋር ባካሄዱት ውይይት የተጨበጠ ስምምነት ላይ አልደረሱም። ሌበር እንደሚለዉ ጠቅላይ ሚንስትሯ ወትሮ በያዙት በብሬግዚት እቅዳቸው ላይ ተጨባጭ ለውጦችን አላደረጉም። የሜይ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ደግሞ አግባቢ ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ ነኝ እያለ ነው። ይሁን እና ሁለቱ ፓርቲዎች አሁን በመጨረሻ ሰዓት ላይ የሚያካሂዱት ድርድር ውጤት ማስገኘቱን የሚጠራጠሩ አልጠፉም። ፍራሰር ካሜሩን በአውሮጳ የፖሊስ ጥናት ማዕከል ከፍተኛ አማካሪ ናቸው። የሁለቱ ፓርቲዎች ድርድር ይሳካል ብለው አያስቡም።
« ሜይ የሌበር ፓርቲን ለመቅረብ የሞከሩበት ጊዜ አሁን የተለየ ነው። ይህን ከሁለት ዓመት በፊት ሊያደርጉት ይገባ ነበር። ያን ካልኩ በኋላ (የሌበር ፓርቲ መሪ ) ኮርቢን ከወይዘሮ ሜይ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚቻኮሉ አይመስለኝም። ምክንያቱም የሌበር ፓርቲ የብሬግዚትን ቀለም እንዲይዝ ይፈልጋሉ ብዬ አለስብም። እነርሱ የብሬግዚት ውልን የወግ አጥባቂዎቹ ፓርቲ

እንዲይዘው ነው የሚፈልጉት። ከዚያ በኋላ ሌበር ወቅቱን ያላጠበቀ ምርጫ ሲጠራ በርግጠኝነት ያሸንፋል። ይህ ነው የሚስተር ኮርቢን ስልት » 
ሜይ ከሌበር ጋር የጀመሩት ድርድር ካልተሳካ ለአውሮጳ ህብረት የሚያቀርቡት አማራጭ እቅድ ምን ሊሆን እንደሚችል አሁን ለማወቅ ያዳግታል። ሆኖም የአውሮጳ ህብረት የቀነ ገደቡን መራዘም ቢቀበል እንኳን ሜይ ባሉት አጭር ማራዘሚያ የሚስማማ አይመስልም። ከዚያ ይልቅ የህብረቱ የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ሃሳብ የማቅረብ እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል። ቱስክ 27 ቱ የህብረቱ አባል ሀገራት በዚህ ሃስብ እንዲስማሙ ተማጽነዋል። ይህ ግን የሜይ ምርጫ አይደለም ።ሜይ ተስፋ የጣሉበት ከሌበር ጋር የጀመሩት ድርድር ካልተሳካ ሁለት አማራጮች ብቻ ናቸው የሚጠብቋቸው። ያለ ሥምምነት መውጣት አለያም የረዥም ጊዜ ማራዘሚያ ጠይቆ በአውሮጳ ፓርላማ አባላት ምርጫ መሳተፍ። ብሪታንያ ያለስምምነት ህብረቱን ለቃ የምትወጣ ከሆነ ብሪታንያም ሆነች የአውሮጳ ህብረት የበኩላቸውን ዝግጅት አድርገው እየተጠባበቁ ነው። 
እየተጓተተ መፍትሄ ሳያገኝ እዚህ የደረሰው የብሬግዚት ጉዳይ መቼ መቋጫ እንደሚያገኝ አሁንም ባይታወቀም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱ ግን ብዙዎችን ያስማማል።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ
 

Audios and videos on the topic