መቀራረብ የታየበት የአውሮጳ ህብረትና የኩባ ግንኙነት | ዓለም | DW | 19.03.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

መቀራረብ የታየበት የአውሮጳ ህብረትና የኩባ ግንኙነት

የአውሮጳ ህብረት እአአ በ 2003 ዓም ኩባ ሰባ አምስት የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ባሰረችበት ጊዜ ከዚችው ሀገር ጋር ጀምሮት የነበረውን ውይይት ማቋረጡ ይታወሳል።

ልዊ ሚሼል

ልዊ ሚሼል

ህብረቱ ያኔ በኩባ ላይ አሳርፎት የነበረው ማዕቀብም እአአ በ 2005 ዓም በከፊል፡ በ 2008 ዓም በጠቅላላ አንስቶዋል። የአውሮጳ ህብረት የልማት ትብብር ኮሚስዮን ተጠሪ ልዊ ሚሼልም ትናንት የኩባ መዲና ሀቫናን የጎብኙበት ድርጊት፡ የዶይቸ ቬለ ባልደረባ ኤንሪኬ ሎፔስ እንደሚገምተው፡ በሁለቱ ሀገሮች መካከል አዲስ የጋራ ግንኙነት የሚጀመርበትን መንገድ ሊከፍት ይችል ይሆናል።

የኩባ መንግስትና የአውሮጳ ህብረት ኮሚስዮን የጋራ ቴክኒካዊ ትብብር ሊጀምሩ በሚችሉበት ጉዳይ ላይ የሚወያይ የሁለት ቀናት ጉባዔ በሀቫና ጠርተዋል። በውይይቱ ከአየር ንብረት ጉዳይ ጀምሮ ኩባን አምና ያጣቃውን ዓይነት ብርቱ አውሎ ነፋስን ማስወገድ እስከሚቻልበት ዘዴ ጭምር የሚመለከቱ ጉዳዮች ይነሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ፡ ህብረቱ የሚሰጠው ርዳታ ከፍ እንደሚል የአውሮጳ ህብረት የልማት ትብብር ኮሚስዮን ተጠሪ ቃል አቀባይ እንደ ጆን ክላንሲ ገልጸዋል።።

« ብርቱ አውሎ ነፋስ የሚያደርሰውን የሰብዓዊ ቀውስ ለመቀነስ የሚያስችል መካከለኛ የጊዜ ገደብ የሚኖረው፤ ተጨማሪ ርዳታ የሚሰጥበትን ጉዳይ የሚመለከት ቁልፍ ማስታወቂያ ይደረጋል። »

ይሁን እንጂ፡ የህብረቱ የልዑካን ቡድን በዚሁ ጎዞው ወቅት ስለ ገንዘብ ብቻ አይደለም የሚነጋገረው፤ የአውሮጳውያኑ የኩባ ጉዞ በሁለቱ ወገኖች መካከል ከስድስት ዓመት በፊት የተቋረጠው ውይይት እንደገና ሊነቃቃ የሚችልበትን መንገድ ከፋች ሊሆን እንደሚችልም ነው በርሊን የሚገኘው የጀርመናውያኑ የሳይንስና የፖለቲካ ተቋም ተጠባባቂ ዋና ስራ አስኪያጅ፡ ጊውንተር ማይሆልት የሚገምቱት።

« እንግዲህ አሁን ይህንን መንገስ የመተውና አዲስ የትብብር ባህል የምንጀምርበት ዕድል አግኝተናል። ይህ የአውሮጳ ህብረት ቀደም ሲልም ያቀረበውን ትብብሩ እንደገና የሚጀመርበትን ሁኔታ ያንጸባርቃል፤ እና አሁን ኩባ ይህንኑ የልማት ርዳታ ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለመሆንዋ ማጣራት ይኖርበታል። »

በዚሁ ሂደት ወቅት የሚደቀኑ እክሎችን ማስወገድ ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል። የአውሮጳ ህብረት የፊታችን ሰኔ ወር በደሴቲቱ በሰብዓዊ መብት ይዞታ ዘርፍ ያለውን ሂደት ይመረምራል። ይህ ሀያ ሰባቱ የህብረቱ አባል ሀገሮች ህብረቱ ከኩባ ጋር ውይይቱ እንደገና ይጀመር ዘንድ ያቀረቡት ቅድመ ግዴታ ነበር። ኩባውያን ይህንኑ የህብረቱን ዕቅድ አስጊ ሆኖ አላገኘውም፡ እንደ ጆን ክላንሲ ገለጻ፤

« እኛ ሁሌም በአየር ንብረት ለውጥ፡ በተፈጥሮ አካባቢ፡ ብሎም ህብረቱና ኩባ ሊያተኩሩባቸው በሚፈልጉ በተለያዩ ብዙ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ነጻና ግልጹን ውይይት እናካሂዳለን። እና በሰብዓዊ መብት ይዞታ ጉዳይም ላይ ነጻውንና ግልጹን ውይይት እንደምናካሄድም በአጽንዖት ልናገር እፈልጋለሁ። እና በዚሁ ዘርፍም መሻሻል እንዲደርግ ሁሌም እንጥራለን። »

ህብረቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት በኩባ ካቢኔ ውስጥ የተደረገው ለውጥ በጋራው ውይይት ላይ እክል ይደቅናል ብሎ አልተመለከተውም። የጀርመናውያኑ የሳይንስና የፖለቲካ ተቋም ተጠባባቂ ዋና ስራ አስኪያጅ፡ ጊውንተር ማይሆልት በህብረቱና በኩባ መካከል እንደገና የተጀመረውን ውይይት ይጠቅማሉ የሚሉትን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲህ ገልጸውታል።

« አዲሶቹ በኃላፊነት ላይ ያሉት አዲሶቹ ባለስልጣናት በፊት የየሚንስቴራቸው ተጠባባቂ ሆነው በማገልገላቸው፤ ለጉዳዩ አዲስ አይሆኑም።

ስለሆነም አዲስ ግንኙነት መፍጠር አያስፈልግም፤ ግንኙነቱን በከፊል እንዳዲስ ማዋቀርን ብቻ ስለሚጠይቅ፡እንደኔ አመለካከት፡ ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ አያሳርፍም። »

በሀቫና እና በብራስልስ መካከል አስተያየቱ እንዲህ አዎንታዊ ሆኖ መቆየት አለመቆየቱ ቢዘገይ የፊታችን ሰኔ የሚታይ ይሆናል።

ኤንሪኬ ሎፔስ/አርያም አብርሀ

ሸዋዬ ለገሰ