መራዘም ያልታከተዉ የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን ውይይት | አፍሪቃ | DW | 26.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

መራዘም ያልታከተዉ የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን ውይይት

ኢትዮጵያ በምትገነባዉ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ግድብ ሰበብ ሦስቱ ሃገራት በተለያዩ ጊዜያት ዉይይት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። ከካይሮ የወጡ አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ግድቡን ለማጥናት ከተሰየሙ የዉጭ ኩባንያዎች አንዱ ከጥናቱ ራሱን ካገለለ በኋላ ግብፅ ግድቡን በተመለከተ ታሰማዉ የነበረዉ ሥጋት አይሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:59
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:59 ደቂቃ

የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን ውይይት

የኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ እንደ አውሮፓውያኑ ጥቅምት ወር መጨረሻ ወይም ኅዳር መጀመርያ` ላይ በካይሮ ለማካሄድ ድጋሚ እንደታቀደ ተጠቆመ።


እ.ኤ.አ. ጥቅምት 5 ቀን 2015 ላይ የሶስትዬዎሹ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ ለማካሄድ ቢታቀደም፣ በኢትዮጵያ በኩል በመንግሥት ምሥረታ ምክንያት ጊዜዉ እንዲራዘም ጥያቄ በመቅረቡ ለሁለት ሳምንት እንዲገፋ መደረጉን ዘገባዎች ያሳያሉ። በዚህ መሠረትም ስብሰባዉን በአውሮጳውያኑ ጥቅምት ወር መጨረሻ ወይም ኅዳር መጀመርያ ገደማ ለማካሄድ እንደታቀደ በዉሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ ዳይሬክተር የሆኑት ኢንጅነር ተሾመ ኣጥናፌ ለዶቼ ቬሌ ተናግርዋል።


ስብሰባዉን ማራዘም ያስፈለገበት ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአባይ ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ኢጋድና ሌሎችም ስብሰባ ሰለነበራቸዉ ነዉ እንጅ በኢትዮጵያ በኩል ያለ ችግር አይደለም ይላሉ አቶ ተሾመ። ስብሰባዉን ለማድረግ ሰብሳቢ ኮሚቴዎች አሁን ዉይይት እያደረጉ መሆኑን በመጥቀስም፣ በሚቀጥለዉ 15 ቀናት ዉሰጥ ስበሰባዉ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።


ኢትዮጵያ የምታካሂደዉ ታላቁ ህዳሴ በመባል የሚታወቀዉ የግድብ ግንባታ በግብፅና ሱዳን ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለማጥናት ሦስቱ አገሮች ያቋቋሙት የጋራ ኮሚቴ፣ ሁለት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ያካተተ ነዉ። ለዚህም በምሕፃሩ BRL በመባል የሚታወቀዉ የፈረንሣይ ኩባንያ እና ከኔዘርላንድ ዴልታሬስ ኩባንያ መመረጣቸዉን ዘገባዎች ይተቁማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዴልታረስ የተሰኘዉ ኩባኒያ፣ የፕሮጀክቱን ጥናት 30 በመቶ እንዲይዝ ቢታቀድም፣ ኩባንያዉ ራሱን ከጥናት ሥራው ማግለሉን በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ በድረገጹ አሳውቋል፡፡ እንደ ኢንጅነር ተሾመ ገለጻ ሊካሄድ የታቀደዉ ስብሰባ ዋና ዓላማም በሁለቱ ኩባኒያዎች መሃል የተፈጠረዉን ልዩነት ለመመልከት እና በቀጣይም ሥራዉ እንዴት መሆን እንዳለብት ለመወያየት ነዉ።


የኔዜርላንዱ ኩባንያ በድረገጹ ላይ ራሱን ከጥናቱ ማግለሉን ቢያሳዉቅም ለኢትዮጵያ ግን በጹሑፍ መቶ በመቶ መዉጣቱን እንዳልገለጸ በማመልከትም ሁለቱ ኩባንያዎች አብረዊ የሚሠሩበት አለያም ሥራዉ የምሠራበትን ሁኔታ እንደሚመቻች ኢንጅነር ተሾመ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል።


ድርድር ሁሌም ወጣገቦች እንዳሉት የገለፁት በኢትዮጵያ የሰላም እና ልማት ዓለም አቀፍ ተቋም ከፍተኛ ተመራማር የሆኑት አቶ አበበ አይንቴ፣ አለመስማማቱ መሠረታዊ ልዩነት ካላመጣ ወይም እስካልፈጠረ ድረስ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት እንደማይቻል አክለዉ አብራርተዋል። ይህ የሶስትዬሽ ድርድር ወደዬት ሊያመራ ይችላል ለሚለዉ አቶ አበበ ሲያስረዱ፣
ድርድሩ እንደሚቀጥል እምነት እንደላቸዉ በመጥቀስ፤ ክፍተት የተፈጠረዉ በአገሮቹ ሳይሆን በአማካርዮቹ ሰበብ ስለሆነ ያም ተነጋግሮ እና ተስማምቶ ስለተፈታ ሂደቱ በተያዘለት መርሃግብር እና በተያዘዉ የመወያያ ነጥብ ላይ እንደሚቀጥል አቶ አበበ አብራርተዋል።


የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴዉ ስድስት አባላት የያዘ ሲሆን፣ በግድብ ሥራ፣ በዉኃ ምንጭና በአከባብ ጥበቃ ላይ አራት የዓለም አቀፍ ባለሙያዎችንም እንዳካተተ ዘገባዎች ያሳያሉ።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች