መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 22.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል

የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የፊታችን እሁድ በሀገራቸው በሚካሄደው አጠቃላይ ምክር ቤታዊ ምርጫ ለአራተኛ የስልጣን ዘመን በተወዳዳሪነት ቀርበዋል። ሜርክል ጥሩ የማሸነፍ እድል እንዳላቸው ይነገራል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:30
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:30 ደቂቃ

ሜርክል ካሸነፉ ከ2ኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ በመ/መንግሥትነት ለረጅም ዓመት የሚያገለግሉ ሁለተኛዋ ይሆናሉ። 

የክርስትያን ዴሞክራቶቹ ህብረት ፓርቲያቸው፣ በምህፃሩ ሴ ዴ ኡ በምርጫው ጠንካራው ፓርቲ እንደሚሆን በመጨረሻ የወጡ የሕዝብ አስተያየት መለኪያ መዘርዝሮች አሳይተዋል። ሜርክል ለዚሁ ትልቅ የፖለቲካ ስልጣን እንዴት በቁ? የእስከዛሬው አመራራቸውስ እንዴት ይታያል?  

አንጌላ ሜርክል ታሪክ የሰሩት በጎርጎሪዮሳዊው ህዳር 2005 የመራሔ መንግሥቱን ስልጣን በተረከቡበት ጊዜ ነው። ሜርክል በጀርመን ይህንኑ ከፍተኛ ስልጣን የያዙ የመጀመሪያዋ ሴት ከመሆናቸውም ሌላ ፣ እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 1990 ዓም ድረስ በሶሻሊስት አመራር ስር በነበረችው በጀርመን ዴሞክራቲክ ሬፓብሊክ ያደጉ የመጀመሪያዋ መራሒተ መንግሥትም ናቸው። ሜርክል በ2006 ዓም የጀርመን ውህደት በዓል ላይ  ንግግር ባሰሙበት ጊዜ ወደ ስልጣን ስለመጡበት ሁኔታ አስታውሰዋል።
« እኔን ለመሰለች ከቀድሞዋ የጀርመን ዴሞክራቲክ ሬፓብሊክ ለመጣች ሴት፣ የተዋኃደች ጀርመንን በመራሒተ መንግሥትነት ማገልገል መቻሌ ፣ ከአስር ወር የስልጣን ዘመን በኋላ፣ ባንድ በኩል  የተለመደ ነገር ይመስላል። በሌላ በኩል ግን፣  በተለይ ዛሬን በመሰለ ቀን ላይ ሆኜ ስመለከተው፣  በጣም ልዩ ነገር ሆኖ አገኝቼዋለሁ። »


ሜርክል ስልጣን ከያዙ ወዲህ በጀርመን ፖለቲካ ላይ ምልክታቸውን አስቀምጠዋል። ከነዚህም፣ ሀገራቸውን ቀስ በቀስ ከአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር ለማላቀቅ መወሰናቸው፣ ብሔራዊ የውትድር አገልግሎትን ማብቃታቸው፣ እንዲሁም፣  ልጆች ለማሳደግ ሲሉ  ለተወሰነ ጊዜ ስራቸውን አቋርጠው እቤት ለሚቆዩ አባቶችም ማበረታቻ ጥቅማ ጥቅም የመስጠቱን አሰራር ማስተዋወቃቸው ይጠቀሳሉ። እነዚህ ፖሊሲዎች ከተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጭምር ሳይቀር ድጋፍ አስገኝተውላቸዋል።  

ሜርክል ከጀርመን አልፎም በአውሮጳ እና በመላው ዓለም የተከበሩ መሪ ለመሆንም በቅተዋል። የአሜሪካውያኑ ዕለታዊ ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ ሜርክልን ነፃው ዓለም ተጠብቆ እንዲቀጥል ከሰሩት የመጨረሻዎቹ መሪዎች አንዷናቸው ብሏቸዋል። ይሁንና፣ የዩሮ ሸርፍን ያጋጠመው ውዝግብ በ2010 ዓም  እጅግ በከፋበት ወቅት፣  ግሪክን የመሳሰሉ ሀገራትን ከክስረት ለመከላከል ይቻል ዘንድ ሜርክል ጠንካራ የቁጠባ ርምጃዎች እንዲወሰዱ ሀሳብ ባቀረቡበት ጊዜ፣ ከአውሮጳውያኑ አቻዎቻቸው ብርቱ ወቀሳ ተፈራርቆባቸው እንደነበር አይዘነጋም። ርምጃዎቹ ድህነት እና ስራ አጥነት ከፍ እንዲል አድርገዋል በሚል ብዙዎች ተችተዋቸዋል። በ2015 ዓም ሜርክል ከሶርያ፣ አፍጋኒስታን እና ከሌሎች ሀገራት ለሸሹ 900,000 ስደተኞች   የሀገራቸውን ድንበሮች ክፍት ባደረጉበት ውሳኔዘቸው ብዙ ጀርመናውያንን እና ጎረቤት አውሮጳውያንን አስገርመዋል። 


« ጀርመን ጠንካራ ሀገር ናት። ብዙ ተግዳሮቶችን መወጣት ችለናል እና ይህንንም እናሳካዋለን። በመንገዳችን ላይ ችግሮች ካጋጠሙ ማስወገድ ይኖርብናል፣ ፌዴራዊው መንግሥትም ከፌዴራዊ ግዛቶቻችን እና ከአካባቢያዊ ምክር ቤቶች ጋር ባንድነት በመሆን የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል። »
ሜርክል የሕዝብን ቁጣ ለማስወገድ በማሰብ በጤና ጥበቃው ወይም በጡረታው ዘርፍ ላይ ተኃድሶ አላደረጉም በሚል ተቺዎቻቸው ይወቅሷቸዋል። የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት እያሉም የፖለቲካ አቋማቸውን ቶሎ ቶሎ ይቀይራሉ። ለምሳሌ፣ የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር ደጋፊ የነበሩት ሜርክል፣ በ2011 በጃፓን የፉኩሺማ የአቶም ተቋም ላይ አደጋ በደረሰበት ጊዜ ከዚሁ አውታር ቀስ በቀስ ለማላቀቅ መወሰናቸው አይዘነጋም። ከዚህ ሌላ ደግሞ ሜርክል ግልጽ አቋም መያዝን እና ይፋ ክርክርን ሆን ብለው ይሸሻሉ ሲሉ ዋነኛ ተፎካካሪያቸው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ ማርቲን ሹልስ ይወቅሷቸዋል።
« እኛ ሶሻል ዴሞክራቶች በሁሉም የምርጫ ዘመቻዎች ላይ መርሀችንን ማቅረብ፣ አቋማችንን ማሳወቅ፣ በጽንሰ ሀሳቦቻችን ላይ ግልጹን ውይይት ማካሄድ በያዝንበት በአሁኑ ጊዜ ፣ ሌላው ወገን ዝምታን መርጧል፣ አንጌላ ሜርክል አሉ። »
ሜርክል ፓርቲያቸው የክርስትያን ዴሞክራቶቹ ፓርቲ፣  በምህፃሩ ሴዴኡ በምክር ቤታዊው ምርጫ አብላጫውን ድምፅ ካሸነፈ ሜርክል ቀጣዮቹን አራት ዓመታት በሙሉ በመራሔ መንግሥትነት ለመስራት ቃል ገብተዋል። እና አሸንፈው መራሒተ መንግሥት ከሆኑ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ በዚሁ ስልጣን ለረጅም ዓመት የሚያገለግሉ ሁለተኛዋ ይሆናሉ ማለት ነው። 

ዳንየል ፔልስ/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ
 

Audios and videos on the topic