″መራሂተ መንግሥትዋ የገቡትን ቃል አልጠበቁም″ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 10.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

"መራሂተ መንግሥትዋ የገቡትን ቃል አልጠበቁም"

የጀርመኑ ገዜልሻፍት ፉዩር በድሮህተ ፎልከር «GfbV» የተሰኘዉ ለተጨቆኑ ሕዝቦች የቆመዉ ድርጅት የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፕሬዝደንት እና የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲናን ለማስፈታት ግፊት እንዲያደርጉ ጠየቀ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:44

"ሜርክል ዶክተር መረራ እንዲፈቱ ግፊት ያድርጉ"

 

የጀርመኑ ገዜልሻፍት ፉዩር በድሮህተ ፎልከር «GfbV» የተሰኘዉ ለተጨቆኑ ሕዝቦች የቆመዉ ድርጅት የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እስር ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ፕሬዝደንት እና የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲናን ለማስፈታት ግፊት እንዲያደርጉ ጠየቀ። ድርጅቱ ትናንት ባወጣዉ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚለዉ የዶክተር መረራ ጉዳና መታሰር አግባብ አይደለም። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የድርጅቱ የአፍሪቃ ክፍል ተወካይ እንደገለፁት መራሂተ መንግሥትዋ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የገቡትን ቃል አልጠበቁም ብለዋል።

ከአውሮጳ ጉዞ መልስ ሕዳር 22 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል በሚል የታሰሩትና ክሳቸዉን በመከታተል ላይ የሚገኙት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና እስከ አስር ዓመት እስር ሊፈረድባቸዉ ይችላል ሲል ስጋቱን የገለፀዉ የጀርመኑ  ለተጨቆኑ ሕዝቦች የቆመዉ ድርጅት ገዜልሻፍት ፉዩር በድሮህተ ፎልከር «GfbV»  ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የድርጅቱ የአፍሪቃ ክፍል ተወካይ ዑልሪሽ ዴሊዩስ፤  ሜርክል ከታሳሪዉ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

«መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ባለፈዉ ጥቅምት፣ 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከሲቪሉ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ዶክተር  መራራ ጉዲና ተሳታፊ ስለነበሩ መራሂተ መንግሥቷ ያውቁዋቸዋል። ሜርክል በዚያን ጊዜ የመናገር ነፃነት፤ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር  ጠይቀዋል። እና ከዚያ በኋላ አንድ የታወቀና የተቃዋሚ ተወካይ ሲታሰር ፣ አንድ ነገር ማድረግ ይገባል፣ መብትና ነፃነት እንዲከበር የሚያቀርቡት ጥያቄ እንዲያው ለይስሙላ ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ማድረግ አለባቸው። ለነዚህ በየጊዜው ይበልጡን እየተጨቆኑ ለመጡት የፖለቲካ ተቃዋሚ መሪዎችም ሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ዕጣ እንደሚቆሙ በግልጽ ማሳየት ይኖርባቸዋል። »

መራሂተ መንግስትዋ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ከተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ከሲቢል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር  መወያየታቸዉን ያወደሰዉ የድርጅቱ መግለጫ፤ የመረራ ጉዲና ድምጽ ለተጨቆኑት የኦሮሞ ማኅበረሰቦችና ለኢትዮጵያዉያን ማኅበረሰብ ወሳኝ ነዉ» ይላል። ሜርክል ከጉብኝታቸዉ በኋላ ቃል መግባታቸዉን ዴሊዮስ ያስታዉሳሉ።

« በኛ እምነት ሜርክል የገቡትን ቃል  የጠበቁ  አይመስለንም። በዝያን ጊዜ ኢትዮጵያ በተለያዪ የብዙሃን መገናኛዎች ትነሳ ስለነበር ይህን ማድረግ ግድ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለተቃዉሞ ሆነ ግጭት አንድም መረጃ እንዳይወጣ ማድረግ ስለተሳካለት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመሳሰሉ ሌሎች ችግሮች ሁሉ በቸልታ ይታለፋሉ፣ በዚህ አንጻርም ምንም አይደረግም። ይህም ነው የሚያሳስበን፣ በመሆኑም የጀርመን መንግሥት ጥሩ ንግግር ከማሰማት አልፎ ለሰብዓዊ መብት መከበር እንዲሰራ እንጠብቃለን።» 

 የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ፓርቲ አብዛኞች የአመራር አባላት መታሰራቸዉን የገለፁት ዴሊዩስ መንግሥት፤ የባለሥልጣናት ሹም ሽር አደርኩ ካለ በኋላም የነበረዉ አይነት የፖለቲካ አሰራር እንደቀጠለ ነዉ። 

« በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምንም አይነት መሰረታዊ ለዉጦች አላየንም። የመረራ ጉዲና ጉዳይን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አንድም የአሰራር ለውጥ እንደሌለ ተመልክተናል።

ዑልሪሽ ዴሊዩስ

ዑልሪሽ ዴሊዩስ

የኢትዮጵያ መንግሥት ሹም ሽር  ሲያደርግ፣ አንድ የኦሮሞ ተወላጅ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር አድርጎ ሲሾም፣ በኢትዮጵያ ሁሉ ነገር ጥሩ እንደሚሆን እና የሕዝቡን ጥያቄ ግንዛቤ ውስጥ እንደሚያስገባ ተናግሮአል። እኛ ግን ይህን ለዉጥ አለየንም፤ አሁንም በቀድሞው ፖለቲካው እንደቀጠለበት ነው ያየነው።»       

ዶክተር መረራ ከቀረቡባቸዉ ክሶች መካከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የአፈፃፀም መመርያ መተላለፍ አንዱ ነዉ። የድርጅቱ የአፍሪቃ ክፍል ተወካይ አዋጁን አስመልክተዉ ተከታዩን ብለዋል።  

« የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይራዘማል የሚል እምነት አለን፤ ሁኔታዉም ዉጥረት የተሞላበት ነዉ። ከሃገር ዉስጥ የምናገኘዉ መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ሁኔታው ከእሳተ ጎሞራ የሚመሳሰል ነው፣ እና የጊዜ ጉዳይ ነዉ እንጂ እሳተ ጎሞራዉ አንድ ቀን መፈንዳቱ አይቀርም።»

የጀርመኑ ገዜልሻፍት ፉዩር በድሮህተ ፎልከር «GfbV» የተሰኘዉ ለተጨቆኑ ሕዝቦች የቆመዉ ድርጅት ባወጣዉ መግለጫ መሠረት ከጎርጎረሳዉያኑ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ዉስጥ ተቃዉሞ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ 50 ሺህ በላይ ኦሮሞዎች ታስረዋል። 1957 ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል። 

አዜብ ታደሰ  

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic