መላ ያልተገኘለት የ ቦኮ ሃራም አሸባሪነት | አፍሪቃ | DW | 08.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

መላ ያልተገኘለት የ ቦኮ ሃራም አሸባሪነት

ናይጀሪያ ውስጥ ፤ እስላማዊው አክራሪ ቡድን ቦኮ ሃራም፤ ከምንጊዜውም የበለጠ አሁን ተጠናክሮ ይገኛል። በሳምንቱ መግቢያ ላይ አገሪቱን ከካሜሩን ጋር በሚያዋስነው ድንበር፣ እንደገና አንድ መንደር ከቦ ጥቃት ማድረሱ ታውቋል።

በዚያ የወረራ ርምጃውም 300 ያህል ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ነው የሚነገረው። ከዚህ ሌላ፤ ከትምህርት ቤት ተጠልፈው የተወሰዱ 276 ልጃገረዶች፣ በዚህ አሸባሪ ድርጅት ቁጥጥር ሥር ነው የሚገኙት። ፈተናው ለሃጋሪቱ ብርቱ ራስ ምታት ሆኗል። ቦኮ ሃራም ያመጣውን ቀውስ ባፋጣኝ ማስወገድ የሚቻል አይመስልም።

በናይጀሪያ የሕዝቡ ቁጣ በመጨመር ላይ ነው። እስላማዊው አሸባሪ ድርጅት ቦኮ ሃራም፤ አንዳንዴ በአንድ ሳምንት ውስጥ ተደጋጋሚ አደጋ ነው የሚጥለው። በመዲናይቱ በአቡጃ መዳረሻ ንያንያ በተባለው ሠፈር ሁለት ቦታ ላይ ነበረ የማጥቃት ርምጃ የወሰዱት። መዲናይቱ አቡጃ ድረስ ዘልቀው በመግባት ህዝቡን ማሸብር ከጀመሩ ውሎ አድሯል። ሕዝቡም ተጨንቋል። በንያንያ የገበያ ቦታ አንድ አላፊ አግዳሚ እንዲህ ነበር ያሉት---

«ሰዎቻችሁ ወደዚህ መጥረው ሊረዱን ይገባል። ሁኔታው አስከፊ ነው። እኛ ናይጀሪያውያን በመሠቃየት ላይ ነን። በዚህ አገር ምንም የሚያስተማምን ሁኔታ የለም። ፕሬዚዳንቱ ፣ በእርግጥ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው ፣ ሆኖም፣ ሁሉንም መለወጥ አይችሉም።»

ዩናይትድ ስቴትስ በመካሉ ልዩ ቡድን ልካለች፤ ብዙዎች ናይጀሪያውያን ይህ እንዴት በቂ ሊሆን ይችላል? በማለት ይጠይቃሉ። ቦኮ ሃራም ከተደራጀ 12 ዓመት ሆነው። መሥራቹ ፣ ሙሐመድ ዩሱፍ እ ጎ አ በ 2009 ዓ ም፣ ከሞቱ ወዲህ፤ ንቅናቄው ይበልጥ አክራሪ መሆኑና አያሌ የጭካኔ ርምጃዎች መውሰዱ ይነገርለታል። በቅርቡ ከካሜሩን ጋር በምታዋስነው ጋምቡሩ እንጋላ በተባለው ሠፈር፣ ሰኞ ፤ 300 ያህል ሰዎች ናቸው የተገደሉት። «ደራስያን ለሰብአዊ መብት» የተሰኘው የናይጀሪያ ደራስያን ድርጅት ባልደረባ ኢማኑኤል ናዶዚ ኦንውቢኮ ሂደቱ አስፈሪ ነው ይላሉ--

«ሰዎቹ ጨለማን ተገን አድርገው አደጋ ከጣሉ በኋላ ነው የሚሠወሩት። ጦር መሣሪያ በገፍ ነው የታጠቁት። በሚገባ የጦር ሥልጠና ያገኙም ናቸው። ለዚህም ነው የኛ ወታደሮች ሰፋ ያለ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል የምንለው።»

ጥያቄ መቅረብ ከጀመረ ቆይቷል። በጦር ኃይሉ ውስጥ ጉዳዩን በጥሞና የሚያነሱ ወገኖች፤ ወታደሮቹ በመደበኛ የጦር ስልት የሠለጠኑ እንጂ በፍጥነት ከቦታ ቦታ የሚሽሎከለኩ አሸባሪ ደፈጣ ተዋጊዎችን ለመዋጋት የሚያስችል ዘዴን አላካተቱም። አሸባሪዎቹ ፣ አደጋ ጥለው ያላንዳች ችግር ተሽሎክልከው ካሜሩን ወይም ቻድ ይገባሉበመደበኛ ጦር አሸባሪዎችን መዋጋቱ የራሱ የሆነ ሳንክም ሆነ ገደብ እንዳለው ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በሚገባ ታይቷል። አምና ከግንቦት ወር አጋማሽ ገደማ አንስቶ በ3 የሰሜን ናይጀሪያ ፌደራል መስተዳድሮች የአስቸኳይ ሁኔታ አዋጅ እንደታወጀ ነው። ይህም አ።ሸባሪዎችን ለመውጋት የሚያስችል ነበረ። ይሁንና ያን ያህል የተሳካ ውጤት አይደለም የተመዘገበው።

አክራሪዎቹ ኃይሎች ከምን ጊዜውም በላቀ ሁኔታ ተጠናክረው ነው የተገኙት። በአቡጃ የጀርመኑ አደናዎር ድርጅት መሪ Hildegard Behrendt –Kigozi ከአሸባሪው ታጣቂ ኃይል ጋር ውይይት ማድረጉ ሊበጅ ይችላል ይሁን እንጂ የተሳካ ውጤት የሚያስገኝ መሆኑ ያጠራጥረኛል ባይ ናቸው።

«ከቦኮ ሃራም ጋር መቼ ውይይት ማካሄድ እንደሚቻል የማውቀው ነገር የለም። እንዲያው የሚቻል ከሆነ ማለት ነው። እንደሚመስለኝ ከዚሁ ድርጅት አንዳንድ አባላት ጋር መነጋገር ይቻላል። የሚጣለው አደጋ ተጠናክሮ በአገሪቱ በመላ እንዳይዛመት ተስፋ አለኝ ውይይቱ ባስቸኳይ እንደሚጀመር!»።

ባለፉት ጊዜያት፤ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን፣ ድርድር እንዳማይታሰብ አስታውቀዋል። ባለፈው እሁድ ከመገናኛ ብዙኀን ሰዎች ጋር በተደረገ ውይይትም ውይይት እንደማይቻል ገልጸዋል። ለዚህም የሰጡት ምክንያት፤ ንቅናቄው በግልጽ የሚታወቁ መሪዎችና ለውይይት የሚቀርብ ሰው የላቸውም የሚል ነው። ብዙዎች ናይጀሪያውያን፤ የሆነው ሆኖ ይህ የራስን አቋም ለማጠናከር ሲባል የተነገረ መሆኑን ነው የተገነዘቡት።

ከሰሜን ናይጀሪያ ሱራን ዳርባ የተባሉ ዜጋ በበኩላቸው ይህን ብለዋል።

«ይህ ትክክል አይደለም፤ የሚታመን ነገርም ሆኖ አላገኘሁትም። ለዚህ ድግሞ ምክንያት ይኖረዋል። እንደሚመስለኝ መንግሥት ማድረግ የሚገባውን አላከናወነም። ከበስተጀርባ ያሉ ሰዎችም ትርፍ ለማግኘት አንዱን ሲያነሱ አንዱን ሲጥሉ ቆይተዋል ። ይህ ጨዋታ ሊቆም ይገባል። የሚያስፈልገን ተጨባቹን ሁኔታ ተገንዝበን የቦኮሃራምን ምላሱe ማድመጥ ነው የሚሻለው። እንደሚመስለኝ ይህ ነው ችግሩን የሚፈታው።»

ብዙዎቹን ናይጀሪያውን የሚያሳስባቸው ከቺቦክ ተጠልፈው የተወሰዱት 276 ልጃገረዶች ይዞታ ነው። የአሸባሪው ድርጅት መሪ ኣቡበከር ሼካው፤ ልጃገረዶቹን እሸጣቸዋለሁ ነው ያለው። አስቸኳይ እርምጃ ይወሰድ ቢባል አደጋም ይኖረዋል።አሸባሪዎቹ ልጃገረዶቹን ጋሽ አድርገው ሊጠቀሙባቸው ይችላሉና። ቀሪው አማራጭ መፍትኄ ይላሉ ሂልደጋርድ ቤሬንድት -ኪጎዚ--

«የድርድር ሐሳብ ማቅረብና የቦኮ ሃራምን ታጣቂ ምርኮኛ በልጃገረዶቹ ለውጦ ማሰናበት ነው።»

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic