ሕፃናት ወታደሮች በአፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 13.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ሕፃናት ወታደሮች በአፍሪቃ

ህፃናት ለወታደርነት እንዳይመለመሉ ለማከላከል የተጀመረዉ ዘመቻ ዘንድሮም በዛሬዉ ዕለት ታስቦ ዉሏል። "Red Hand Day" በመባል የሚካሄደዉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ሲከበር ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ ነዉ።

 በዚህ ወቅትም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች እና ህፃናት ላይ የሚያተኩሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ልጆች በጦር መሳሪያ ግጭት እንዳይሳተፉ የሚያቀርቡትን ተቃዉሞ የዓለም ህዝብ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል። አፍሪቃ ዉስጥ ልጆች የጦርነትና የጥቃት ሰለባ መሆናቸዉ እንደቀጠለ፤ አማፂ ቡድኖችና የመንግስታት ሠራዊትም ለየራሳቸዉ ዓላማ እንደሚጠቀሙባቸዉ ተገልጿል።
ሱዳን፤ ደቡብ ሱዳን፤ ሲማሊያ፤ ቻድ፤ ልጆች በእርስ በርስ ጦርነት በግድ እንዲሳተፉ ከተደረገባቸዉ የአፍሪቃ ሀገራት ጥቂቶቹ ናቸዉ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ማሊ ለየት ያለ ስጋት አስከትላለች። ዓለም ዓቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሂዉመን ራይትስ ዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ታዳጊ ሕፃናት በፅንፈኛዉ እስላማዊዉ ቡድን ተገደዉ ለዉጊያ ሳይሰለፉ እንዳልቀሩ ያምናል። የድርጅቱ የምዕራብ አፍሪቃ ፅህፈት ቤት የበላይ ኮሪነ ዱፍካ ሰሜን ማሊ ዉስጥ ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ ወገኖች ጋ ካደረጉት ንግግር በመነሳት በአካባቢዉ ያለዉን ሁኔታ እንዲህ ይገልፃሉ፤


«አብዛኞቹ ልጆች ለዚህ ጉዳይ ገንዘብ እየተከፈላቸዉ ህፃናትን ለዚህ ተግባር በሚመለምሉ ትላልቅ ሰዎች አማካኝነት ነዉ ለታጣቂዉ ቡድን የሚወሰዱት። አክራሪ ሙስሊሞቹ ምልመላዉን ለረዥም ጊዜ በወግ አጥባቂነት በመንደሩ በታወቁ ሰዎች ላይ የጣሉት ይመስላል።»  
እሳቸዉ እንደሚሉትም ታጣቂዎቹ እነዚህን ልጆች በተኩስ ልዉዉጡ ግንባር የሚያሰልፉበት አጋጣሚ አለ። የአይን ምስክሮችም የፈረንሳይ ወታደሮች ጋኦ ከተማ በሚገኘዉ የአማፂያን ጦርሰፈር ላይ ጥቃት ከመሰንዘራቸዉ አስቀድሞ ልጆቹን እዚያ መመልከታቸዉን ይናገራሉ። የታዳጊዎቹ እጣፈንታም ምን እንደሆነ እስከአሁን የታወቀ ነገር የለም።  
«ስለዚህ ልጆቹ ከታጣቂ ሙስሊሞቹ ጋ እንዲሸሹ ተደርገዉ ይሁን፤ ወይም እንዲመለሱ ተደርጎ ይሁን ማወቅ አልቻልንም። አንዳንድ ወላጆች የሸሹት ታጣቂዎቹ ልጆቻቸዉን እንዲለቁላቸዉ ተማፅኖ አቅርበዋል። ልጆቹ ምን እንደደረሰባቸዉ እንግዲህ በቀጣይ መከታተልና ማጣራት ይኖርብናል።»   
ምንም እንኳን ልጆቹ ከዚህ ግርግር የማምለጥ እድሉ ቢኖራቸዉም ያለፉት የህይወት አጋጣሚ የሚያሳድርባቸዉ ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆን ነዉ የሚታመነዉ። በአንድ ወቅት በልጅ ወታደርነት ተሰማርተዉ የቆዩት ታዳጊዎች የስነልቡና ጉዳት ብቻ ሳይሆን በእድሜያቸዉ ሊያገኙት የሚገባዉን ትምህርትና ስልጠና ሁሉ ባለማግኘታቸዉ ይቸገራሉ። ኤሪክ ሞንጎ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ይህን አስተዉለዋል። የኮንጎ ሰሜናዊ ግዛት ኢቱሪ ክፍለ ሀገር ደም አፋሳሹን የእርስ በእርስ ጦርነት ለአስር ዓመት አስተናግዳለች። ሞንጎ የሚመሩት ህፃናትን የሚረዳዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት «አፊያ» ከጦር ግንባር የተመለሡ የልጅ ወታደሮችን ይንከባከባል። ሆኖም የሚደረገዉ በቂ አይደለም ነዉ የሚሉት፤


«ድርጅቱ የቀድሞ ጥፋተኞችን በሚያስተናግድበት ሂደት አድ ያስተዋለዉ ነገር አለ። ይኸዉም ልጆቹን እንዲቀበልና እንዲዋሃዱ እንዲረዳቸዉ ከማኅበረሰቡ ጋ በዚህ ጉዳይ ላይ በጋራ መስራት ይኖርብናል።»
እሳቸዉ የሚመሩት ድርጅት ሥራ ከጀመረ ከዛሬ ሶስት ዓመት አንስቶ እስካሁን 520 ልጆችን በአግባቡ እየተንከባከበ ይገኛል። «መብትና ሰላም» በተሰኘዉ ትስስር አካልነቱም ዓለም ዓቀፍ  የጦር ወንጀል ችሎት ለጉዳት ሰለባዎች በዘረጋዉ የገንዘብ ርዳታ ተቋም ይደገፋል። የዛሬ አስር ዓመት የተቋቋመዉ የገንዘብ ተቋም ለጦርነት ሰለባዎች የሚዉል ወደ1,2 ሚሊዮን ዮሮ የሚገመት ካሳ መድቧል። ፍርድ ቤቱ ባለፈዉ ዓመት ነሐሴ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በኮንጎ አማፂ ቡድን መሪ ቶማስ ሉባንጋ ሥር እንዲሰለፉ ለተገደዱ ልጆች ካሳ እንዲሰጥ ወስኗል። ሆኖም ገንዘቡ ለአማፂ ቡድኖች ዓላማ በጦር ግንባር እንዲዉሉ የተገደዱ ልጆችን ሁሉ ለመርዳት በቂ እንዳልሆነ ነዉ የተገለፀዉ። ዛሬም ከአስር ዓመታት በኋላ በኮንጎዋ ኢቱሪ የሚታየዉ ሁኔታም ለወጣቶቹ የጦርነት ሰለባዎች ገና ብዙ መሰራት የሚገባዉ ነገር እንዳለ ያመለክታል። 

 ፊሊፕ ዛንድነር

 ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic