ሕግጋቱን ይጥሳል የተባለው የዓለም ባንክ | ኢትዮጵያ | DW | 28.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ሕግጋቱን ይጥሳል የተባለው የዓለም ባንክ

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የልማት ስራዎች በሚያደርገው ድጋፍ የራሱን ህግጋት እና መርሆዎች በተደጋጋሚ መጣሱ ተነገረ።የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ባንክ ያገኘውን የገንዘብ ድጋፍ በጋምቤላ ክልል ለሚያደርገው የግዳጅ የሰፈራ መርሐ-ግብር ሲጠቀምበት ቆይቷል የሚል ወቀሳም ይሰነዘርበታል።

የኢትዮጵያ መንግስት በጋምቤላ ክልል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2010 እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ የሰፈራ መርሐ-ግብር ሲያካሂድ መቆየቱን የዓለም ባንክ አጣሪ ቡድን ዘገባ ያትታል።በዘገባዉ መሠረት የሰፈራ መርሐ-ግብሩ 45,000 ነዋሪዎችን መሰረታዊ አገልግሎቶች በሚያገኙበት መንገድ ለማስፈር የታቀደ ነበር። በዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት (The International Consortium of Investigative Journalists) ይፋ የተደረገው እና ከባንኩ ሾልኮ ወጥቷል የተባለዉ የአጣሪ ቡድን ዘገባ የዓለም ባንክ ለጤና፤ትምህርት፤የገጠር መንገድ፤ግብርና፤የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ንጽህና አገልግሎቶችን ለማሳደግ ለኢትዮጵያ መንግስት ያደረገውን የ2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እና የሰፈራ ፕሮግራም ያላቸውን ግንኙነት የፈተሸ ነው። ‘ከመኖሪያ ቀያችን በግዳጅ ተፈናቅለናል’ በማለት የኢትዮጵያ መንግስትን በከሰሱ 26 የአኙዋክ ተወላጆች ጥያቄ የተቋቋመው አጣሪ ቡድን ያዘጋጀው ሰነድ የሰፈራ መርሐ-ግብሩ በግዳጅ መከናወኑን፤ ከዓለም ባንክ ለመሰረታዊ አገልግሎት ተብሎ የተመደበው ገንዘብም ነዋሪዎችን አስገድዶ ለማስፈር መዋሉን ይጠቁማል። ሰዎችን በማፈናቀልና ሌላ ሥፍራ በማስፈሩ ሒደት በአኝዋክ ተወላጆች ላይ ድብደባ፤አስገድዶ መድፈር እና ግድያ መፈጸሙን ዘግቧል።እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ1996-99 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሺን አሁን የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ፕሮፌሰር ናቸው።

Landverpachtung an ausländische Investoren in Äthiopien Flash-Galerie

«በኢትዮጵያ የጋምቤላ ክልል የተካሄደውና በ2013 የተጠናቀቀው የሰፈራ መርሐ-ግብር ለሰፊ የእርሻ መዋዕለ-ንዋይ የአኙዋክ ተወላጆችን ወደ ሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች ለማዘዋወር ያቀደ ነበር።በዚህም አንዳንዶቹ በግዳጅ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል የሚል ትችት ይቀርባል። ይህንን የግዳጅ ሰፈራ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችም አሉ።የዓለም ባንክ የሰፈራ ፕሮግራሙ በግዳጅ እንደሚካሄድ እያወቀ ድጋፍ ማድረጉ ነው አሁን ክርክር የፈጠረው።»

ከመኖሪያ ቀያቸው በግዳጅ ተፈናቅለዋል ከተባሉት የአኙዋክ ተወላጆች መካከል ወደ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ለመሰደድ የተገደዱ እንዳሉ የዓለም ባንክ አጣሪ ቡድን ዘገባ ይገልጻል። ቡድኑ የዓለም ባንክ በግዳጅ ሰፈራው በቀጥታ ተሳትፎ ባይኖረውም የገንዘብ ድጋፉ ለመርሕ-ግብሩ ማስፈፀሚያ መዋሉን ባንኩ መቆጣጠር አለመቻሉንና የተፈናቃዮቹን ደህንነት በቸልታ በማለፍ የራሱን ህግጋት እና መርሆዎች መቃረኑን ያትታል።የሰፈራ መርሐ-ግብሩን በበላይነት የሚያስፈጽሙ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትም ከዓለም ባንክ የገንዘብ ድጎማ ደሞዝ ይከፈላቸው እንደነበር ይኸው ዘገባ ይፋ አድርጓል።

ከመኖሪያ ቀያቸው በግዳጅ ተፈናቅለው ለስደት ለተዳረጉ 26 የአኙዋክ ተወላጆች የሚከራከረው ኢንክሉሲቭ ዴቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል (Inclusive Development International) ሃላፊ ዴቪድ ፕሬድ ስለጉዳዩ ጠይቀናቸው «የዓለም ባንክ የጋምቤላ ህዝቦችን ቀርቦ በማማከር ከፍርሃት እና ከሰቆቃ ነጻ በሆነ መንገድ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገ እና በማህበረሰቡ የሚመራ የመልሶ ማቋቋም ስራ መሰራት ይኖርበታል።» ሲሉ በኢ-ሜይል መልሰውልናል።

Flash-Galerie Äthiopien Land Grab

አምባሳደር ዴቪድ ሺን በበኩላቸው የአጣሪ ቡድኑ ዘገባ የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር በሚኖረው ቀጣይ ግንኙነት ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖ ለመኖሩ እርግጠኛ አይደሉም።

«የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ለረጅም ጊዜ የዘለቀ መልካም ግንኙነት አለው።ኢትዮጵያ የዓለም ባንክን ድጋፍ በመጠቀም ጥሩ ምሳሌ እንደሆነችም ያምናል። በኢትዮጵያ የሰፈራ መርሐ-ግብር መካሄድ ከጀመረ ብዙ ጊዜ ሆኖታል። አንዳንዶቹ በግዳጅ የተካሄዱ ነበሩ። ችግሩ አዲስ ሳይሆን የቆየ ነው። ስለዚህ ባንኩ ችግሩ አንዳች ውሳኔ ወይም እርምጃ ያስፈልገው እንደሆነ መወሰን ይኖርበታል። ለጊዜው ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ የማውቀው ነገር የለም።»

የዓለም ባንክ የስራ አስፈጻሚ የአጣሪ ቡድኑን ዘገባ ከመገምገሙ በፊት ምንም አስተያየት እንደማይሰጥ የባንኩ የአፍሪቃ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ፊል ሄይ መናገራቸውን ዓለም አቀፍ የምርመራ ጋዜጠኞች ጥምረት ዘግቧል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም. በተጠናቀቀው የሰፈራ መርሐ-ግብር 37,883 ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው ወደ ሌላ አካባቢዎች መዘዋወራቸውን የዓለም ባንክ አጣሪ ቡድን ዘገባ ያትታል። በግዳጅ ሌላ አካባቢ የተዘዋወሩት የአኙዋክ ተወላጆች ከለም የመኖሪያ አካባቢያቸው ለመልቀቅ ባይፈልጉም በፖሊሶችና ወታደሮች መገደዳቸውን በዚህም የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ዘገባው ገልጿል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic